Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅትን የተፈታተነው ዚካ ቫይረስ

የሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅትን የተፈታተነው ዚካ ቫይረስ

ቀን:

የዚካ ቫይረስ ወረርሽኝ አምና በብራዚል ሲከሰት በአገሪቱ ከሁለት ወራት በኋላ የሚካሄደውን 31ኛውን ኦሊምፒያድ ለሚያዘጋጀው አካል፣ የቫይረሱ ሥርጭት እክል ሊሆንበት እንደሚችል ሥጋት ነበር፡፡ ይህ ሥጋት ደግሞ ዛሬ በኦሊምፒኩ በሚሳተፉ አገሮችና አትሌቶች እንዲሁም በጐብኝዎች ላይ አጥልቷል፡፡ ወደ 16 ሺሕ የሚጠጉ አትሌቶችንና ከ600 ሺሕ በላይ ጐብኚዎችን በኦሊምፒኩ ድግስ ለማስተናገድ እየተዘጋጀች ያለችው ብራዚልም፣ በአገሪቱ ከአምና ጀምሮ በተከሰተው የዚካ ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ኦሊምፒኩን እንደማትሰርዝ ገልጻለች፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የጤና ባለሙያዎችና አጥኚዎች መሰረዝ ወይም ማስተላለፍ አለባት ሲሉ ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት በበኩሉ፣ ከቫይረሱ አስተላላፊ ትንኝ ራስን ጠብቆ በዝግጅቱ መታደም ይቻላል ሲል ሰሞኑን አሳውቋል፡፡ ኦሊምፒኩ መካሄድ የለበትም የሚሉት ወገኖች ደግሞ፣ ብራዚልና ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ውድድሩን ካልሰረዙ ወይም ካላስተላለፉ መዘዙ ለዓለም ይተርፋል ሲሉ ሥጋታቸውን እየሰነዘሩ ነው፡፡

ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው አጋጣሚዎች የተዛመቱ ቫይረሶች

እ.ኤ.አ. በ2010 በቫንኮቨር ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በነበረው የክረምት ኦሊምፒክ 82 ሰዎች በኩፍኝ ወረርሽኝ ተጠቅተዋል፡፡ ይህም የሆነው አንድ ቫንኮቨር የገባ ጐብኚ በሽታውን አስተላልፎ በመላው ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በመዛመቱ ነው፡፡

ኖሮቫይረስ የተባለውና አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት የሚያስከትለው ቫይረስም፣ እ.ኤ.አ. በ2006 በጀርመን በተካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታ ተከስቷል፡፡ ቫይረሱ ከጨዋታው ቀድሞ በመከሰቱና አገሪቷም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረጓ በጨዋታው ወቅት በወረርሽኙ የተጠቁት ቁጥር 65 ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ. የ2012 የለንደን ኦሊምፒክ ያለምንም የጤና ሥጋት ያለፈ ነበር፡፡ በአገሪቱ ያለው የጤና ክትትል፣ የበሽታዎች ሥርጭት፣ መነሻና መድረሻን አስመልክቶ ከመጀመሪያው ጀምሮ ክትትል የሚደረግበት፣ የሚታወቅበትና የሚገታበት የጤና ቁጥጥር ሥርዓት ውድድሩ ያለምንም የጤና ሥጋት እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

ሪዮ ከለንደን ኦሊምፒክ ምን ትማራለች?

ብራዚል በዚካ ቫይረስ ምክንያት ኦሊምፒኩ እንዳይስተጓጐልም ሆነ ጐብኚዎችና የውድድሩ ተሳታፊዎች በቫይረሱ እንዳይጠቁ ርብርብ እያደረገች ትገኛለች፡፡ ሆኖም በዚካ ቫይረስ ከተጠቁት ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳዩ የሚቆዩ በመሆናቸው፣ የቁጥጥርና የክትትል ሥራውን ፈታኝ ያደርገዋል፡፡

የዚካ ቫይረስን የሚያስተላልፉ ትንኞች አገሪቷ ቀዝቀዝ በምትልበት በነሐሴና በመስከረም ቁጥራቸው ይቀንሳል፡፡ ሆኖም ባለፈው ዓመት ሙሉውን የሙቀቱ ሁኔታ ባለመቀነሱ ቫይረሱን አሁንም ድረስ ማስወገድ አልተቻለም፡፡ ይህም በኦሊምፒኩ ምክንያት ወደ ብራዚል ሪዮ ዲጄኔሮ የሚገቡ ጐብኚዎችን ጤና ሥጋት ላይ ይጥላል፡፡ በየአገራቸው በሚመለሱበት ጊዜም ቫይረሱን ይዘው ከገቡ ዓለም በችግር ውስጥ ትወድቃለች፡፡ በተለይ ወባማ የሆኑ አካባቢዎች የችግሩ ቀዳሚ ተጠቂ ይሆናሉ፡፡

ብራዚል ኦሊምፒኩ በሚካሄድባት ሪዮ በየጊዜው የኬሚካል ርጭት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡  ውድድሩ የሚካሄደው በአንድ ከተማ ብቻ በመሆኑ ከተማዋን ከአስተላላፊ ትንኝ አፅድቶ ውድድሩን ማከናወን ይቻላል የሚል አቋም ቢኖርም፣ ከሪዮ ውጪ ያሉ ነዋሪዎች ለውድድሩ ወደ ከተማ የሚገቡ መሆናቸው የቱንም ያህል ርጭት ቢደረግ ቫይረሱን መግታት አይቻልም የሚል ሥጋት አጭሯል፡፡ በሌላ በኩል የዚካ ቫይረስን የምታስተላልፈው የወባ ትንኝ በጠብታ ውኃ ላይ መፈልፈል መቻሏ ሌላው ችግር ነው፡፡ የብራዚል ባለሥልጣናት ግን የኬሚካል ርጭት ከማድረግ ባለፈም በዘረመል ምሕንድስና የተዳቀሉ የወባ ትንኞች የዚካ ቫይረስ የምታሠራጨውን ለመቆጣጠር እስከ መጠቀምም ደርሰዋል፡፡

የሪዮ ኦሊምፒክ መሰረዝ ወይም መተላለፍ ይገባዋልን?

በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ተመራማሪው አርት ካፕላን ብራዚል ኦሊምፒኩን መሰረዝ አለባት ብለው ይከራከራሉ፡፡ ካልተሰረዘ ደግሞ ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴና አገሪቷ ኃላፊነት የጐደላቸው መሆኑን ያሳያል፣ ይህ ሳይሆን ግን ኮሚቴው ውድድሩን ይሰርዝ የሚል አቋም አላቸው፡፡ ‹‹አገሪቷ በተመሳሳይ ወቅት የዚካ ቫይረስን መዋጋትና የኦሊምፒክ ውድድር ለማዘጋጀት መሯሯጥ የለባትም፤ ሲሉም›› አሳስበዋል፡፡

የአሜሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴም በውድድሩ የሚሳተፉ የአሜሪካ አትሌቶች የጤና እክል ይገጥመናል ብለው ካሰቡ ከውድድሩ መቅረት እንደሚችሉ አሳውቋል፡፡ አንዳንድ የአሜሪካ አትሌቶችም በብራዚል ያለው ሁኔታ ኦሊምፒኩ እስከሚቃረብ ካልተለወጠ ሊቀሩ እንደሚችሉ ከወዲሁ አሳውቀዋል፡፡

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ዶ/ር ማሪ ዊልሰን ግን ሪዮ ከያዘችው አቋም ጐን ቆመዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዊልሰን፣ ኦሊምፒኩ የሚካሄድበት ነሐሴ ወር በብራዚል ቅዝቃዜ ነው፡፡ ይህም የብራዚል የጤና ባለሥልጣናት ቫይረሱን ለመቀነስ የሚያደርጉትን ርብርብ ያግዛል፡፡ ቫይረሱንም ተቀባይነት ወዳለው መጠን ለመቀነስ ይቻላል፡፡

የጆርጅታውን ኦ ኒየል ኢንስቲትዩት ፎር ናሽናል ኤንድ ግሎባል ሔልዝ ሎው ባልደረባ፣ ዶ/ር ዳኔል ላሲ በበኩላቸው፣ ‹‹ብራዚል የራሷን ግዳጅ እየተወጣች ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደግሞ የብራዚልን ጥረት ለማጠናከር፣ ለመደገፍና ለወረርሽኙ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዕድሉ አለው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የዚካ ቫይረስን አለመቆጣጠር የወባ ሥርጭትን ካለመቆጣጠር ጋር ይያያዛል፡፡ የወባ ሥርጭትን በመቆጣጠር ዚካን መቆጣጠርና ውድድሩንም ማካሄድ ይቻላል፤›› ያሉት ደግሞ የኢንተርናሽናል ጆርናል ኦፍ ኢንፌክሺየስ ዲዝዝ ዋና አዘጋጅ ኢስኪልድ ፒተርሰን ናቸው፡፡

የኦሊምፒኩ ይሰረዝልን ጥሪና የዓለም ጤና ድርጅት ምላሽ

ባለፈው ሳምንት 150 የሕክምና ኤክስፐርቶች፣ ምሁራንና ሳይንቲስቶች  በሪዮ ከሁለት ወራት በኋላ የሚካሄደው ኦሊምፒክ እንዲሰረዝ፣ ካልሆነም ጊዜው እንዲተላለፍ የዓለም ጤና ድርጅትን ጠይቀዋል፡፡

አልጄዚራ እንደ ዘገበው፣ የባለሙያዎቹ ሥጋት በኦሊምፒኩ ለመሳተፍ ከየአገሩ በሚጓዙ ሰዎች ምክንያት ከዚካ ባለፈም በወባ ትንኝ ሊተላለፉ የሚችሉ ሌሎች በሽታዎች ሊስፋፉ ይችላሉ የሚል ነው፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ግን ጥሪውን አጣጥሎታል፡፡ ‹‹በ2016 በሪዮ ሊካሄድ የታሰበውን ኦሊምፒክ መሰረዝም ሆነ ቦታ መቀየር ወይም ማራዘም፣ ቫይረሱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ሥርጭት ላይ ጉልህ ለውጥ አያመጣም፤›› ሲል ውትወታውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

ድርጅቱ በሰጠው መግለጫም፣ በብራዚል በተሠራ ዳሰሳ ውድድሩን ሊያሰርዝ የሚችል ምንም ምክንያት የለም ብሏል፡፡

የዚካ ቫይረስ ከወባ ትንኝ በተጨማሪ በግብረ ሥጋ ግንኙነትም ይተላለፋል፡፡ ጉልህ የጤና ተፅዕኖ የሚያሳድረውም በእርግዝና ወቅት ሲሆን፣ በእርግዝና ወቅት በዚካ ቫይረስ ከተጠቃች እናት የሚወለዱ ሕፃናት የአዕምሮ ዕድገት እክል ይገጥማቸዋል፡፡

 

                                                                                                                                                     

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...