Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ሚድሮክ፣ ከአምስት ዓመት በላይ ካዛንችስ አካባቢ አጥሮ ባቆየው ግቢ ውስጥ የሚገኝ ክሬን በዝገት እየተበላሸና ለመውደቅ ቀናት የቀሩት ይመስላል ፎቶ በታምራት ጌታቸው

ትኩስ ፅሁፎች

ቆርጣችሁ ጣሉት

እውቁ ባለቅኔና ደራሲ አቤ ጉበኛ ‹‹መስኮት›› ባላት መድበሉ፣

በግእዝ ቅኔ በ‹‹ለዓለም›› ስልት ከ44 ዓመታት በፊት እንዲህ ተቀኝቶ ነበር፡-

ጉቦሂ ተራጋጭ ላም፡

የክፉ ሹሞች ጥገት፡

ወተት ፍጻሜን ትነፍጋለች፡

መላሻ ካላላሷት፡

አንዳንድ ጊዜማ ስትዘል፡

ሞወደሪያዋን ቆርጣ ድንገት፡

ፍርድ ማለቢያ  እቃን፡

ታደርገዋለች እንኩትኩት፡፡

አዲስ ተክል ፍቅር፡

ሾህ ከታየበት ድንገት፡

ሁኖ ነውና አጉል ቁጥቋጦ፡

ቶሎ ቆርጣችሁ ጣሉት፡፡

***

‹‹ሱሪህ እንዲጠፋህ አትፈልግም››

አባት – ‹‹ካልተሳሳትኩ፣ ይህ የለበስከው የእኔ ከረባት ነው አይደል?››

ወጣት ልጅ – ‹‹አዎ አባባ!››

አባት – ‹‹ሸሚዙም የእኔን ይመስላል››

ወጣት ልጅ -‹‹ትክክል! አባዬ››

አባት – ‹‹ቀበቶውም ደግሞ የእኔ ነው ልበል?!››

ወጣት ልጅ – ‹‹ትክክል! አባዬ ሱሪህ እንዲጠፋብህ አትፈልግም አይደል?››

ምስጋና አየነው ‹‹የቀልዶች ወላፈን›› (1997)

*************

ዋሻ ውስጥ ድብብቆሽ

አንድ ስኮትላንዳዊና አንድ እንግሊዛዊ በባቡር ወደ ታስማንያ እየተጓዙ ነበር፡፡ መሃላቸው አንዲት ቆንጆ ሴት ተቀምጣለች፡፡ ባቡሩ በዋሻ ውስጥ ማለፍ ስለነበረበት ወደዚያ ሲገባ ድቅድቅ ጨለማ ወረሰው፡፡ የጥንት ባቡር ስለሆነም መብራት አልነበረውም፡፡ ወዲያውኑ የመሳም ድምፅ ተሰማና ጥፊ ተከተለ፡፡ ባቡሩ ከዋሻው ሲወጣ ሴቲቱና ስኮትላንዳዊው ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ተረጋግተው ተቀምጠው ሳለ እንግሊዛዊው ግን በጥፊ የተቃጠለ ፊቱን እያሻሸ ነበር፡፡ ለርሱ የመሰለውም ስኮትላንዳዊው ሴቲቱን ስለሳማት ተቆጥታ የሰነዘረችበት ጥፊ እርሱ ላይ በስህተት ያረፈ ነው፡፡ ሴቲቱ በበኩሏ ‘እንግሊዛዊው ሊስመኝ ሲሞክር ተሳስቶ ስኮትላንዳዊውን ስለሳመው በጥፊ አቃጥሎታል’ ስትል ገምታለች፡፡ ስኮትላንዳዊው ደግሞ ‘ግሩም አጋጣሚ ነው የተፈጠረልኝ፤ ባቡሩ ከፊታችን ያለው ዋሻ ሲገባ የተለመደውን የመሳም ድምፅ አሰማና ያን ሞልፋጣ እንግሊዛዊ አጠናፍረዋለሁ’ እያለ በማሰብ ላይ ነበር፡፡

  • አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)

 

***

የቱርኩን ፕሬዚዳንት የተሳደበችው ሞዴል ተቀጣች

ባዮስጎራክ የተባለችውና እ.ኤ.አ. 2006 ላይ ወይዘሪቱ ቱርክ ተብላ የነበረችው የ27 ዓመቷ ወጣት በማኅበራዊ ድረ ገጽ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንን በመስደቧ ከአንድ ዓመት በላይ የሆነ ገደብ እንደተጣለባት የዘ ኢንዲፔንደንት ዘገባ ያመለክታል፡፡ በዚህ የገደብ ጊዜ ውስጥ ሞዴሏ ጥፋት መባል የሚችሉ ነገሮችን አድርጋ ብትገኝ ማረሚያ ቤት ትገባለች፡፡ ሞዴሏ ፕሬዚዳንቱን ሰድባለች የተባለው እ.ኤ.አ. 2014 ላይ በኢንስታግራም የስላቅ ግጥም በመለጠፏ ነበር፡፡ ግጥሙ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኤርዶጋንን የሚተች ሲሆን፣ ግጥሙ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ስንኞችንም እንደመሠረት ተጠቅሟል፡፡ ጉዳዩ አደባባይ ወጥቶ ተጠያቂ እንደሆነች በጊዜው ሞዴሏ ‹‹አስቂኝ ሆኖ ስላገኘሁት ለጠፍኩት እንጂ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንን የመስደብ ምንም ፍላጎት ኖሮኝ አይደለም›› ብላ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ጀመሮ ሚስተር ኤርዶጋን የስም ማጥፋት ተደርጎብኛል በማለት 2000 የሚሆኑ ክሶችን ማቅረባቸውም በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

*****************

ቀባሪዎች የሬሳ ሳጥን ሰባበሩ

ባለፈው ሳምንት በዩጋንዳ የአንድ ፖለቲከኛ የቀብር ሥነ ሥርዓት ድራማ ሆነ ብሎ ዴይሊሞኒተር የዘገበው ነው፡፡ በዩጋንዳ ቡምቦ የተባለ ግዛት በሥልጣን ላይ ያለው ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት (ኤንአርኤም) ፓርቲ ሊቀ መንበር የነበሩት ጁሊየስ ዋኮባ ሥርዓተ ቀብር ሊፈጸም ሲል ለቀስተኛው የሬሳ ሳጥኑን መሰባበር ጀመረ፡፡ ከዚያም አስከሬኑን በማውጣት ሳጥኑን መስበራቸውን ቀጠሉ፡፡ ሟች የሚመሩት ፓርቲ ምልክት ያለበትንና ፓርቲው የተገዛውን ሬሳ ሳጥን ለቀስተኞቹ የሰባበሩት ደረጃውን ያልጠበቀና የማይረባ ነው በማለት ነበር፡፡ ለቀስተኞቹ ሟች ጁሊየስ ዋኮባ ፓርቲያቸውን ለረዥም ጊዜ ከማገልገላቸው አንጻር በፓርቲው የተገዛውና የዩጋንዳ 40 ሺሕ ሽልንግ ብቻ የሚያወጣው የሬሳ ሳጥን ለክብራቸው የሚመጥን አይደለም ብለዋል፡፡ ለቀስተኞቹ ሳጥኑን መስበር ሲጀምሩ ለማስቆምና ለማረጋጋት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም የተላከውን ዓይነት ርካሽ ሳጥን ስላልጠበቁ ማስቆም እንዳልተቻለ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዴይሊ ሞኒተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፓርቲው ደረጃውን የጠበቀ ሳጥን እንደሚልክ የቀብር ሥነ ሥርዓቱን በሚገባ ለማስፈጸም የሚያስችል በጀትም እንደሚመድብ ጠብቀን ነበር፡፡ ነገር ግን የማይረባና ርካሽ ሳጥን መላኩ በጣም አስረገመን›› በማለት ሞሰስ ናንጐሻ የተባሉት እኚህ ሰው ይናገራሉ፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች