Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የባህል ሕክምና ሰጪ ካጠፋ የሚጠየቅበት የሕግ አግባብ አለን››

አቶ መሐመድ ፈቲያ አብደላ፣ የኦሮሚያ ባህል ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት

አቶ መሐመድ ፈቲያ ከ30 ዓመት በላይ የባህል ሕክምና በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከ500 በላይ አባሎች ያሉትን የኦሮሚያ ባህል ሐኪሞች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት ይመራሉ፡፡ የባህል ሕክምና ምን ደረጃ ላይ እንዳለና ስለማኅበራቸው እንቅስቃሴ ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለባህል ሕክምና ቢያብራሩልን፡-

አቶ መሐመድ፡- የባህል ሕክምና ለዛሬው ዘመናዊ ሕክምና መሠረት የሆነና አሁንም ጭምር እያገለገለ የሚገኝ ሳይንስ ነው፡፡ የባህል ሕክምና ማለት ምድር ላይ የሚገኙ ሁሉ መድኃኒት ናቸው ብሎ የሚያምንና ያንንም በመጠቀም እንደ ሕመምተኛው ዕድሜና ሕመሙ ዓይነት በተፈጥሮአዊ መንገድ ሕክምና የሚሰጥበት ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምድር ላይ ያሉ ማለት ምን ምን ናቸው?

አቶ መሐመድ፡- ምድር ላይ ያሉ ማለት ሣር ቅጠሉ፣ እንስሳት፣ የከበሩ ማኅድናት በተወሰነ ወቅት ብቻ የሚበቅሉ ዕፀዋት በጣም በርካታ ተክሎች እያንዳንዳቸው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ የባህል ሕክምና አዋቂ ነው የሚባለው እንዴት ነው? ደረጃስ አለው?

አቶ መሐመድ፡- በዓለም ላይ የባህል ሕክምና መሰጠት ከተጀመረ ብዙ ሺሕ ዓመታትን  አስቆጥሯል፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ሳይስፋፋ የባህል ሕክምና በሰፊው ይሰጥ ነበር፡፡ አሁንም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰው እየተፈወሰበት ይገኛል፡፡ በአገራችን ደረጃ ለማውጣት ማንም የተንቀሳቀሰ ባለመኖሩ ደረጃ ለማውጣት አልተቻለም፡፡ በሌላው ዓለም እስከ ዶክትሬት የደረጃ ማዕረግ ይሰጥበታል፡፡ በእኛ በኩልም የባህል ሕክምና ደረጃ እንዲወጣለት ከኦሮሚያ ጤና ቢሮና ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየሠራን እንገኛለን፡፡ እንደኛ አመለካከት የባህል ሕክምና አዋቂ የሚባለው በየጊዜው የሚያድናቸው ሰዎች እየጨመሩ ከሄዱት የሚያክመው ሕመም ዓይነት እየጨመረ ከመጣ፣ የሰው የባህል ሕክምና አዋቂ ነው ይባላል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ይህን ሥራ ሲሠሩ ከሠላሳ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ እንዴት ጀመሩት? በዚህ ጊዜ ውስጥ የተጎዳብዎት ሰው የለም? እስከዛሬ ካከሟቸው ሕመሞች ወደ ባህል ሕክምና በብዛት የሚመጡት የትኞቹ ናቸው?

አቶ መሐመድ፡- ሥራውን የጀመርኩት ባሌ ነው፡፡ በአካባቢያችን ያሉትን የባህል ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች አይቼ ሥራውን ወደድኩት፡፡ ስለ ባህል ሕክምና በዓረብኛ የተጻፉትን ማንበብም ጀመርኩ፡፡ ትንሽ ትምህርትም ጨመርኩበት፡፡ መጀመርያ አካባቢ በነጻ ነበር አገልግሎት የምሰጠው፡፡ በኋላ ችግሩም እየሰፋ፣ መድኃኒት የሚቀመምበትም ግብዓት እየተወደደ ስለመጣ ትንሽ ማስከፈል ጀመርኩ፡፡ በኋላም የምሰጠውን ሕክምና በዘመናዊ መንገድ በማደራጀትና የመንግሥት ሥራዬን በመተው ሙሉ በሙሉ በዚህ ሥራ ላይ ተሰማራሁ፡፡ ዛሬ በኬንያና በእንግሊዝ ጭምር ቢሮ በመክፈት ሕክምናውን እየሰጠሁ እገኛለሁ፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሕመሞች አሉ፡፡ በብዛት ግን በቀላሉ የሚድኑ ናቸው፡፡ እኔ ከማክማቸው ሰዎች በብዛት የሚመጡት በጨጓራ ሕመም የሚሰቃዩ ናቸው፡፡ የኩላሊት ችግርም ያላቸው ይመጣሉ፡፡ እኔ እስካሁን የገጠመኝ ችግር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ማኅበራችሁ ቢገልጹልን፡-

አቶ መሐመድ፡- ኢትዮጵያና የባህል ሕክምና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው ጥናት ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች በእጅጉ የተስፋፉ ቢሆንም አሁንም 80 በመቶ ያህሉ ወደ ባህል ሕክምናው ጎራ እንደሚል አስታውቋል፡፡ ከቆዳም ስፋት አንፃር በኦሮሚያ ብዙ የባህል ሕክምና መስጫዎችና ባለሙያዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ባለሙያዎች በማሰባሰብ ተጠያቂነት እንዲኖርና ጉዳዮችንም ለመፈጸም እንዲያመች 500 የምንሆን የባህል ሐኪሞች በኦሮሚያ ጤና ቢሮ አማካይነት ማኅበራችንን በ1989 ዓ.ም. መሥርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከማኅበራችሁ ምሥረታ ጀምሮ ያከናወናችሁት ተግባራት ምን ይመስላል?

አቶ መሐመድ፡- የማኅበራችንን አባላት በኔትወርክ አያይዘናል፡፡ ሁሉም አባል የተለያየ ችሎታ ስላለው አንዱ ያልቻለውን ወይም የሚያውቀውን ወደ አንዱ ሪፈር ያደርጋል፡፡ ማን የትኛውን ሕክምና እንደሚሰጥ፣ ሒደቱስ እንዴት ነው የሚለውን ለመከታተል ችለናል፡፡ እንደዚሁም በየዓመቱ ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት በአገራችን ስላለው የባህል ሕክምና ዕድገት፣ በጓዳ የሚሰጡ የባህል ሕክምናዎች ደረጃቸውን በጠበቁ ቦታዎች መሰጠት እንዳለባቸው በማስተማርና ድጋፍ በማድረግ አብዛኞቹን ለመለወጥ ተችሏል፡፡ በተለይ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ከፍተኛውን እገዛ እያደረገልን ይገኛል፡፡ አሁን ያለንበትንም ቢሮ በእሱ እገዛ ነው ልናገኝ የቻልነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደእናንተ የሚመጡ ታካሚዎች ልሞክረው ብለው ነው ወይስ ምርጫቸው አድርገው?

አቶ መሐመድ፡- በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ወደ እኛ ይመጣሉ፡፡ አንደኛው የባህል ሕክምና በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል ለኅብረተሰቡ በጣም ቅርብ በመሆኑ ነው፡፡ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ወደ ከተማ ሄዶ መታከም ስለሚከብዳቸው ከአቅም አንጻር የሚመጡም አሉ፡፡ ይህ ግን ያለፍላጎታቸው ማለት አይደለም፡፡ እንደሚድኑም በማመን ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ብዙ ጊዜ ዘመናዊ ሕክምና በመከታተል መፍትሔ ያጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች እስካሁን ባለኝ መረጃ መፍትሔ በማግኘት የተመለሱ ናቸው፡፡ ይህን ልናውቅ የቻልነው በፊት በሆስፒታል የነበራቸውን ቆይታ፣ ከዛ ወደ ባህል ሐኪም ከመጡ በኋላ ያላቸውን የጤና ደረጃ ቃለ መጠይቆችን በማድረግ ነው፡፡ መርጠው የሚመጡም ቀላል አይደሉም፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ሕመምተኛ ወደ እናንተ ሲመጣ መጀመርያ የምታደርጉት ምንድን ነው? የባህል ሕክምና በተለይ በከተማው ኅብረተሰብ ተመራጭ ያላደረገው ምንድነው?

አቶ መሐመድ፡-  ዓለም ስትፈጠር ዘመናዊ ሕክምና አልነበረም፡፡ ባህላዊውን ሕክምና መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ዘመናዊው እየተስፋፋ የመጣው፡፡ በቀደሙት ዓመታት በኢትዮጵያ የባህል ሕክምና ባይኖር ኖሮ የጤናው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ የባህል ሕክምና በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ባይኖረው ኖሮ እንኳን ዘመናት ሊሻገር ለአንድ ዓመትም አይቆይ ነበር፡፡ ስለዚህ ሰዎች እየዳኑበት ነው ማለት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ዘመናዊ ሕክምና እንደሚሳሳተው ሁሉ የባህል ሕክምናው ላይም ስህተት ሊኖር ይችላል፡፡ በተጠቃሚውም ላይ በብዛት ችግሮች አይተናል፡፡ በኢትዮጵያ የባህል ሕክምና ምን ይመስላል? ምን ጥቅም ሰጠ? ምን ያህል ሰው ተጎጂ ሆኗል? የሚል ብዙ ጥናት ባለመኖሩ፣ እንደዚህ ነው ብሎ ለመገመት ከባድ ነው፡፡ በግምት ግን እየጠቀመን ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በተለይ በእኛ በማኅበሮቻችን አንድ ሕመምተኛ ወደእኛ ሲመጣ፣ በመጀመሪያ የደሙንና የልቡን ሁኔታ ነው የምናየው፡፡ መሣሪያ ካለን በራሳችን፣ ከሌለን ሆስፒታል አሠርቶ እንዲመጣ እናደርጋለን፡፡ ሕክምናውን የምንጀምረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ በጣም የደከመ ደግሞ በቀጥታ ወደ ዘመናዊ ሆስፒታል እንዲሄድ እናደርጋለን፡፡   

ሪፖርተር፡- የባህል ሕክምናን ከአምልኮ ጋር የሚያያይዙ አሉ፡፡ ለሕመምተኛ የሚሰጥ የመድኃኒት መጠን መብዛት፣ ሰዎችንም ለጉዳት የሚዳርጉ መድኃኒቶች በየመንገዱ መሸጥ እንደችግር ይነሳሉ፡፡ በማኅበራችሁ በኩል ችግሮችን ለመፍታት ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ መሐመድ፡- ዋናው ማኅበሩ የተቋቋመበት ዓላማ ችግሮችን ለመቅረፍ ነው፡፡ ለዚህም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀነው መመሪያ አለ፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም ዜጋ የባህል ሕክምና ሰጪ ካጠፋ የሚጠየቅበት የሕግ አግባብ አለን፡፡ በተለይ በማኅበራችን አባሎች ጉዳት የደረሰበት ወደእኛ በመምጣት ማመልከት ይችላል፡፡ እስካሁንም ሁለት ክሶች የቀረቡልን ነበሩ፡፡ እነሱም በተጠቃሚው ስህተት መሆኑን አረጋግጠን ችግሩን ፈተናል፡፡ ችግሩ የሚመጣው አንደኛ ሁሉንም አውቃለሁ በሚል የባህል አካሚ ሲሆን፣ ሁለተኛው መድኃኒት እንዴት እንደሚሰጥ ካለማወቅና ካለማንበብ የሚፈጸም ነው፡፡ ሌላውና ኅብረተሰቡ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያውቅ የምንፈልገው የባህል ሕክምና ከማንኛውም እምነት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ነው፡፡ በተለይ ከጥንቆላ ጋር እጅግ የሚጋጭ ነው፡፡ የባህል ሕክምና የዚህ ዛፍ ስር ወይም ቅጠል ለዚህኛው ሕመም ብሎ በተጨባጭ የሚያምን ነው፡፡ በእርግጥ ከእኛም ችግር አለ፡፡ በቂ ትምህርት ለኅብረተሰቡ አንሰጥም፡፡ ልዩነቱንም ስለማንገልጽ ማኅበረሰቡ የተሳሳተ ግንዛቤ አዳብሯል፡፡ በመድኃኒት አወሳሰድና ዙሪያና የተለያየ የሕክምና ችሎታ ያላቸውን ባለሙያዎችን በመለየት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራን ነው፡፡ በየመንገዱ የሚሸጡ የባህል መድኃኒቶችን ለማስቀረት ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር እየሠራን ሲሆን፣ ዕርምጃ እየተወሰደም ነው፡፡ በጥቂት ቦታዎች የሚታዩትንም ከተግባራቸው እንዲርቁ እያደረግን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የባህል ሕክምና አገልግሎቶችን እንደ ሌሎች መድኃኒቶች በፋርማሲ የማናገኛቸው ለምንድነው?

አቶ መሐመድ፡- የባህል ሕክምናን ለማዘመንና የሚሰጠውን አገልግሎት ደረጃ ለማስጠበቅ ብዙ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል፡፡ የባህል ሐኪሞቹም ወደ አደባባይ ብቅ ያሉትና መንግሥትም ዘርፉን ማየት የጀመረው በቅርቡ ነው፡፡ ከባህል መድኃኒቶቹ 90 በመቶ ያህሉ የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ይህንን አቋቁሞና አዘጋጅቶ በፋርማሲ ደረጃ ለማቅረብ ትልቅ ጥረት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ እናንተ የት ድረስ ሄዳችኋል? መንግሥትስ የሚያግዛችሁ በምን መልኩ ነው?

አቶ መሐመድ፡- ነገሮች ሁሉ የተጀመሩት በቅርብ ነው፡፡ የሕክምና ዘርፉ ያለማደጉም ምክንያት በእኛ በኩል ያለው ችግር እንዳለ ሆኖ፣ በመንግሥት ያለው ትኩረት ማነስ ነበር፡፡ አሁን ጥሩ ጅማሬዎች አሉ፡፡ በአገር አቀፍም በክልልም እንድንደራጅ በማድረግ የባህል ሕክምናው በሚያድግበት ላይ በጋራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለባህል ሕክምና የሚውሉ መድኃኒቶችን መፈተሻ ላቦራቶሪ ስለሌለው መድኃኒቶቹን እንደችሎታችን ጥቅም ላይ ማዋል አልቻልንም እንጂ ጥሩ እንቅስቃሴ አለ፡፡ ይህ ላቦራቶሪ ከተደራጀ በጤናው መስክ ለውጥ የሚያመጡ መድኃኒቶች አገልግሎት ላይ የሚውሉበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ መሐመድ፡- አሁን የተጀመሩትን ማስቀጠል አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛ የማኅበር አባሎቻችን ቁጥር በመጨመርና ያሉት የባህል ሐኪሞች ሠርቲፋይድ እንዲሆኑ እንሠራለን፡፡ እነሱ ሠርቲፋይድ ሆኑ ማለት የሕክምናቸውም የምርምራቸውም ውጤት ከአገር አቀፍ አልፎ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ያገኛል፡፡ ይህም በጤናው ሴክተር ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ማለት ነው፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሠራተኛ ስቀጥር ካለመሠልጠናቸውም በላይ ስንት ይከፈለኛል ብለው ሲጠይቁ እደነግጥ ነበር›› ወ/ሮ ቅድስት ጌታቸው፣ የሶጋ ትሬዲንግና ፖላር ፕላስ ኤክሰለንስ ሀብ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉት የሠለጠነ የሰው ኃይልና የሥራ ፈላጊው ብቃት በብዛት አይጣጣምም፡፡ በዚህም ቀጣሪዎች ብቁ የሰው ኃይል አለማግኘታቸውን፣ ሠራተኞችም የሚፈልጉትን የሥራ ዓይነት አጥተው...

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...