Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልግብርና የዘመነባቸው ዘጋቢ ፊልሞች

ግብርና የዘመነባቸው ዘጋቢ ፊልሞች

ቀን:

ባዮኢኮኖሚ አፍሪካ የተራድኦ ድርጅት፣ በተቀናጀ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴ (ኢንተግሬትድ ባዮኢኮኖሚ ሲስተም ወይም አይቢኤስ) ላይ ያተኮሩ ሁለት ዘጋቢ ፊልሞችን አስመረቀ፡፡ ‹‹ፍኖተ ለውጥ›› እና ‹‹ዊንድ ኦፍ ቼንጅ›› የተሰኙት ፊልሞች በተቀናጀ የግብርና ዘዴ በመጠቀም ምርታቸውን ያሳደጉ አርሶ አደሮች ተሞክሮና ባዮኢኮኖሚ አፍሪካ በተለያዩ ክልል ከተሞች የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ያሳያሉ፡፡

ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል የተመረቁት ዘጋቢ ፊልሞች፣ በዘመናዊ መንገድ ዶሮ በማርባት፣ ንብ በማነብና በተፈጥሮ ማዳበሪያ የበለፀገ ሰብልና የጓሮ አትክልት በማልማት ድርጅቱ ያሠለጠናቸው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን ሕይወት ያስቃኛሉ፡፡ ፊልሞቹ አገር በቀል ችግኞች ለአካባቢ ጥበቃ ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲሁም ተረፈ ምርትን መልሶ በመጠቀም ረገድ፣ ድርጅቱ እየሠራ ያለውን ያሳያሉ፡፡ በፊልሙ ላይ ከተካተቱት አርሶ አደሮች መካከል የከብቶችን ሽንትና እዳሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የሚጠቀሙ ይገኙበታል፡፡ የተቀናጀ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴ (አይቢኤስ) አንድ የግብርና ዘዴን ከሌላው ዓይነት ጋር ተመጋጋቢ በማድረግ የአርሶ አደሮችን ምርት እንደሚጨምር በፊልሙ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የግብርና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

አይቢኤስ በተለያዩ ክልል ከተሞች በሚተገበርበት ወቅት የየአካባቢውን የአየር ሁኔታ ከግምት በማስገባትና ሙሉ በሙሉ የተፈጥሮ ሀብትን በመመርኮዝ እንደሆነ የባዮኢኮኖሚ አፍሪካ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ትኩበት በፊልሙ ላይ ተናግረዋል፡፡

ፊልሙ በተመረቀበት ዕለት የአይቢኤስን ሥልጠና የወሰዱ ከአማራ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልል የተውጣጡ አርሶ አደሮች ተገኝተው ነበር፡፡ በፊልሙ ዙሪያ በተደረገው ውይይት የአይቢኤስን ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በየአካባቢያቸው ላሉ ሌሎች አርሶ አደሮችም ሥልጠና እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡ ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ድርጅቱ ባለፉት አሥር ዓመታት ከ50,000 በላይ አርሶ አደሮች አሠልጥኗል፡፡  

ዶ/ር ጌታቸው እንደተናገሩት፣ ፊልሙ በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የግብርና ባለሙያዎች ለረጅም ዓመታት ያደረጉትን ጥረት ያሳያል፡፡ ተፈጥሯዊ ግብአትን በመጠቀምና የተለያዩ የግብርና ዘዴዎችን በማጣመር ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል እንደሚያሳይም አክለዋል፡፡ ስለፊልሙ አስተማሪነት ሲናገሩ ‹‹በግብርናው ዘርፍ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ሐሳቡን መንግሥትና አርሶ አደሮችም አምነው ሲቀበሉት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰላማዊት አሰፋ፣ የተቀናጀ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴ ሁሉንም ዕድሜና ጾታ ያማከለ መሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ በፊልሞቹ አርሶ አደሮችን፣ በግብርና ዘርፍ ያሉ ተመራማሪዎችንና ፖሊሲ አውጪዎችን ለመድረስ እንደታቀደ አስረድተዋል፡፡

የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚኒስቴር የኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት የሆነው ግብርና አሁን ካለው በበለጠ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ቢችልም የእውቀት ክፍተት አለ፡፡ ‹‹ከመሬቱ ምርታማነትና ጊዜው ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አንፃር ከዚህ የበለጠ መጠቀም እንችል ነበር፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ምርታማነት ካልጨመረበት ምክንያት አንዱ የእውቀት ማነስ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ዘጋቢ ፊልሙ አርሶ አደሮች በእጃቸው ያሉ አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት የሚያራምደው ግብርና መር ፖሊሲ ስኬታማ እንዲሆን፣ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተጨማሪ እንደ ባዮኢኮኖሚ አፍሪካ ያሉ የተራድኦ ድርጅቶች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጠቃሚ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ድርጅቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአይቮሪኮስት፣ ኮንጎ፣ ዑጋንዳ፣ ኬንያና ሞዛምቢክ የሚሠራ ሲሆን፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የልምድና የእውቀት ልውውጥ ያደርጋል፡፡ ድርጅቱ ወንዞች እየደረቁ፣ ዛፎች እየተጨፈጨፉ፣ የአየር ንብረት እየተዛባና አርሶ አደሩ ራሱን መመገብ እየተቸገረ መምጣቱን ከግምት በማስገባት፣ ተፈጥሯዊ ሀብትን በጥንቃቄ መጠቀም ላይ ያተኮረ ሥራ ይሠራል፡፡ ተፈጥሮን ባገናዘበ መንገድ ባህላዊና ዘመናዊ ዘዬን በማጣመር፣ በትንሽ ወጪ ምርታማነትን ማስፋት የተቀናጀ የተፈጥሮ ግብርና ዘዴ ያተኮረበት ጉዳይ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...