Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​በዓይን አውጣዎች ዘመን ስርቆትም ጀብዱ ነው!

እነሆ መንገድ ከመብራት ኃይል ወደ ጎሮ። ኑሮና ፈታው እያደናገረው የአዳም ዘር ወዲህ ወዲያ ይቃብዛል። ገሚሱ ሐሳብ ሰቅዞ ይዞት የፊቱን ትቶ በመጣበት አቅጣጫ ይመለሳል። ተመለስ ባዩና መንገድ ጠቋሚው ጭምር ሳያስበው ሲከተለው አመልካችና ተመልካች ቁልቁል ይቦናሉ። አዙሪቱ ሰው ከሰው አይመርጥም። ተራውን እየጠበቀ ሁሉም በቀኝ ግራ ጡዘት ለመተራመስ ቀን ያለው ይመስላል። ይኼው አንዱ ስንት ሰዓት ሙሉ ተሠልፎ ውሎ “የመገናኛ ታክሲ መስሎኝ እኮ ነው፤” እያለ ፀጉሩን እየነጨ ይሮጣል። ቀኑን የሚጠብቅ ቀን በሚያሳፍረው ሆዱን ይዞ ይንከተከታል። “ተው አትሳቅ ተው። ነግ በእኔ ቀረ በቃ?” ይላል አንድ ጎልማሳ። አልኩ ለማለት ለአፍ አመል የሚለውን ይላል። መልሶ ደግሞ ስቆ አላባራ ያለውን ወጣት እያየ ይስቃል። “ሳቁ እንዴት ያስቃል?” ይለናል ዞር ብሎ።

“ሰበቡ ነጠላ ለብሼ አንች ሰበበኛ…’ የሚለውን ዜማ ፉጨት አንዲት የደም ገንቦ ማፏጨት ጀመረች። “ገባ ገባ በሉ እንጂ። ምነው መቃብር የምትገቡ መሰላችሁ እኮ?” እያለ የሚያዋክበን ወያላችን ነው። “እንዴ ተናግረህ ሞተሃል፤” ስትለው ቆንጂት፣ “ኧረ በፈጠረሽ መጀመሪያ ራስሽን አርሚ እስ? ይኼን ቁመትና ይኼን ቅርፅ ይዘሽ እንደ አደገኛ ቦዘኔ የምታፏጭው አለሽ አይደል፤” ብሎ ያዛት። “ወይ ጉድ! ይኼ የፆታ እኩልነት ስብከት እንዴት ሠርቷል እናንተ? እኔ ደግሞ እንደ ወንድ አፏጨሽ የሚላት መስሎኝ ልሰድበው ተዘጋጅቼ ነበር። ለካ ፉጨት የወንድ የሴት ከሚለው ወጥቶ በክላስ ተከፋፍሏል!” ብላ ከሾፌሩ ጀርባ በትይዩ የተቀመጠችው ወይዘሮ አሸሞረች። “በክላስ ያልተከፋፈለ ምን አለ ብለሽ ነው? ያው አታይም እንዴ አገሩን የሞላው እኮ ‘ፔንሲዮን’ ነው፤” ሲል ጎልማሳው፣ “እንጀራህን አብስል የሰው እንጀራ አትዝጋ፤” እያለ ሁሉም ወረደበት። ሰው ግን ከሥራ ይልቅ ለነገር ሲደራጅ ይቸኩላል ልበል?!

ጉዟችን ተጀምሯል። “ሳብ ሳብ አድርገው እንጂ ሾፌር። በዚህ አካሄድማ አንደርስባቸውም፤” ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙ አዛውንት ናቸው። “እነማን ናቸው ሰዶ ማሳደድ ውስጥ የከተቱን?” አላቸው ከአፍ እየነጠቀ ጨዋታ የሚያቆረፍደው ወያላ። “ሌቦቹ ናቸዋ። እኔማ አንዳንዴ ማልጄ ወጥቼ ማታ ስገባ ድንቅ የሚለኝ ቤቴ ባለበት ባስቀመጥኩበት ቁጭ ብሎ ሲጠብቀኝ ብቻ ነው። ታዲያ አንድ ቀን ስሄድ አይቼው ስመለስ እንደማጣው ስለምጠረጥር ገና በራፉን እልፍ እንዳልኩ እዞርና በል ካልተገናኘን ደህና ሰንብት። መቼም ታውቃለህ አንተን እንዲህ አሽሞንሙኖ ለማቆም ያላበኝን ላብ፣ የፈጀሁት ማገዶ እንደማይሰፈር እንደማይለካ ታውቃለህ። በምንም በማንም አለውጥህም። ዳሩ አገሩ እንደምታየው ከግዑዝ እስከ ተንቀሳቃሹ ነገር የሚሰረቅበትና የሚጠፋበት ሆኗልና ሳንለያይ ከተለያየን ሁሌም እንደማስብህ፣ እንደማልረሳህ ልንገርህ። አንተም አትርሳኝ ብዬው ወደ ጉዳዬ እገሰግሳለሁ፤” ሲሉ አጠገባቸው የተሰየመ ተሳፋሪ ፈገግ ብሎ፣ “ሲመለሱስ?” አላቸው። “ስመለስማ እስከ ዛሬ አጥቼው አላውቅም፤” ሲሉት፣ “ምን ይሉታል ድሮስ ‘ዛሬም ማሩህ?’ ከማለት ሌላ፤” ብሎ ከወይዘሮዋ ጎን የተቀመጠው ጎልማሳ ደባለቀ።

ኋላ መጨረሻ ከተሰየሙት ተሳፋሪዎች ጨዋታው ድንግር ያለው አንድ ቆዳ ጃኬት ለባሽ፣ “እኔ ምለው ቤትና ስፖኪዮ እኩል ሆኑ እንዴ?” ብሎ መጠየቅ። “እንዴት?” ሲሉት አቅራቢያዎቹ፣ “እንዲህ እንደ ቀላል ነገር ተነቅሎ የሚጠፋው ስፖኪዮ እንጂ ቤት አልነበረም ብዬ ነዋ፤” አለ። “በል ከዛሬ ጀምሮ ነው ብለህ ማመን አለብህ። በዚህ የስርቆቱን መራቀቅና ዓይን አውጣነት በቅጡ ካልተዳህ፣ ነገ ኢትዮጵያ ራሷ ስትሰረቅ ሐዘኑን የመቋቋም ጉልበት አይኖርህም፤” ብለውት አረፉት። ሰው ሰውነትን ለማዳበር ጂም ይገባል እዚህ የነገን ሐዘን ለመቋቋም ሰው እንባ ይቆጥባል። እንባ ቆጣቢ ተቋም ቢቋቋምልን ግን እንዴት አሪፍ ነበር!

ጉዟችን ቀጥሏል። መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተቀመጠችው የውበት እመቤት ከጓደኛዋ ጋር በስልክ ስለወርኃዊ ወጪዋ ታወራለች። “ብታምኝም ባታምኝ ለካርድ ብቻ በወር አንድ ሺሕ ብር አወጣለሁ። እኔማ ቁጭ ብዬ ሳስበው ግራ የገባኝ ነገር ዕውን በእኔ ኃይል ነው እየኖርኩ ያለሁት በእሱ ቸርነት?” ትላታለች። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ፣ “ለምን መስመር አታደርገውም?” ይላል። “መስመር ለማድረግ የንግድ ፈቃድ ያስፈልጋታል፤” ይላል ሌላው። “መስመር ምንድነው?” ብለው አዛውንቱ መጠየቅ። የአዛውንቱን ጥያቄ ችላ ብሎ ባለቆዳ ጃኬቱ፣ “መስመር ለማድረግ የሚያስፈልገው ንግድ ፈቃድ ብቻ አይመስለኝም። ሌላ መስመር ሳይኖረው አይቀርም፤” አለ። “ኧረ የመስመር ያለህ? አስምራችሁ ጨረሳችሁን እኮ እናንተ? ምንድነው መስመር?” አዛውንቱ በስጨት አሉ። “እኛም አናውቀውም ጋሼ። መስመር ሲሉ ሰማን ተከተልናቸው፤” ብሎ አጠገባቸው የተሰየመው ወጣት መለሰላቸው።

“እናንተ ዝም ብላችሁ የሰው መስመር የምትከተሉት የራሳችሁ መስመር የላችሁም እንዴ?” ሲሉ፣ “ቢኖረንስ አባት? በቀይ የተሰመረና በነጭ የተቀለመ አንድ ነው እንዴ?” አለቻቸው ሒሳብ ለማውጣት ግድንግድ ቦርሳዋን ስትከፍት በፌስታል የተቋጠረ ደረቅ እንጀራዋን ያየንባት ጠይም። “ምን እሱ ብቻ? እንዳሻችሁ ብለውን ሲያበቁ እውነት መስሎን ስንጫወት መስመሩን የፈለጉበት ቦታ ላይ አስምረው ወጥ ረገጣችሁ ይሉናል። ከመከተል ሌላ ምን አማራጭ አለን?” አለ እዚያው ካጠገቧ የተሰየመ። “እኮ ማንን ነው የምትከተሉት?” አዛውንቱ ግራ ግብት ብሏቸው ሲጠይቁ ወጣቶቹ በአንድ ድምፅ፣ “መስመሩን ነዋ!” ብለው አሽካኩ። ወይ መስመሩና አሰማመሩ!

ወያላችን በገዛ መልሳችን ችሮታ እንደሚሰጥ ልማታዊ ባለሀብት እየተቀናጣ ያድለናል። ልክ አጠገቤ ወደ ተሰየመችው ዘመናይ ደርሶ የሆነ ነገር ሊላት ሲል፣ “አቦ አምጣ ዝም ብለህ፤” ብላ ከእጁ ነጠቀችው። “እንዴ ለካርድ ብቻ በወር አንድ ሺሕ ብር ታወጫለሽና ማመናጨቅ ትችያለሽ ያለሽ ማን ነው?” አላት እሱም አያርፍም። ­­‹‹ምን አግብቶህ የማወራውን አዳመጥክ?›› ብላ አራስ ነብር ሆነች፡፡ እሱ ‹‹ጆሮ የሕዝብ፣ አፍ የመንግሥት ሆኗል፤›› ብሎ ጠቦት ፍየል ሆነ። ታክሲያችን በአራት እግሯ ቆመች። “ኧረ በገላጋይ እባካችሁ እባካችሁ! እንዴ ትልቅ ሰው አትፈሩም ቢያንስ። እኛንስ ተውን እሳቸውን አታከብሩም?” ወይዘሮዋ መለመን ያዘች። ሾፌሩ፣ “አንተ አርፈህ ሥራህን አትሠራም?” እያለ ይጮሃል። ጋቢና የተሰየሙት ሁለቱ ተሳፋሪዎች ቆንጂትን በጥንቃቄ እያዩ፣ “የእንትና እህት እኮ ናት፤” ይባባላሉ። የሚደማመጥ ጠፋ። ተረጋጊ ልላት ዘወር ስል፣ “አይገርምህም ይኼ? እኔ ማን እንደሆንኩ አሳይሃለሁ ጠብቅ። ገና ከጀርባህ ማን እንዳለ ታወጣታለህ። አዎ፣ ማን አጥናት ብሎ እንደላከህ ትለፈልፋታለህ፤” ብላ ነገሩን ስታከረው፣ “አንቺ ምን አለበት ነገር ብታበርጂ? በማስፈራራት ወንጀል ልትከሰሺ እንደምትችይ አታውቂም እንዴ?” ብሎ ጎልማሳው አስታገሳት። የሚያስታግስ አይጥፋ!

ወይዘሮዋ፣ “ሌላው ቢቀር እኚያን አዛውንት አታከብሩም? ይወልዷችኋል እኮ?” እያለች አለቅ አለች። ጎልማሳው ቀበል አድርጎ፣ “ሰው እኮ በዘመኑ ያሉትን መሪዎቹን፣ አስተዳዳሪዎቹን፣ ጎረቤቶቹን፣ እናቱንና አባቱን እያየ አድጎ ነው ባህሪው የሚገነባው። እነዚህ ልጆች እኮ ‘ከላይ የሚወርደውን ሐሳብ የሚቀበል እስከሆነ ድረስ አራተኛ ክፍልም ይሁን’ እየተባለ እውቀትና አዋቂ ሲዋረድ እያዩ አድገው፣ አገርን በክብርና በነፃነት ያቆዩዋት አባቶች በጡረታ ገንዘብ የቤት ኪራይ እየከፈሉ ወረት ሸምተው እየኖሩ፣ በፖለቲካና በአስተሳሰብ ልዩነት እርስ በርስ ተናንቀው ያስተናነቁን ሰዎች ሐውልት ሲቆምላቸው እያዩ አድገው ታላቅን ማክበር ብሎ ነገር ከየት ያመጡታል?” ብሎ ታክሲዋን በድንጋጤ ፀጥ ረጭ አደረጋት። አሁን እስኪ የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በሕገ መንግሥት በፀናባት አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንዲህ ሲባል እንዲህ ክው ማለት ነውር አይደለም?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ድንገት ዩኒፎርም የለበሱ ሁለት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አስቆሙንና ገቡ። “እህ ፈተና እንዴት ነው?” አለው ጎልማሳው። “ተቋርጦ ወጣን፤” አለ ያልተጠየቀው። “እንዴ በመብራት ሆነ እንዴ ማትሪክ?” መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት አንዱ ቀለደ። ተማሪው አንገቱን ወዘወዘ። “በውኃ ነው እንዳትለኝ?” ቀጠለ ቀልዱን ያ። አሁንም ሳቅ ብሎ አንገቱን ነቀነቀ። የተሳፋሪዎች ትኩረት አሁን ሙሉ በሙሉ ተማሪዎቹ ላይ አርፏል። “ለምንድነው የተቋረጠው? አሸባሪዎች ጥቃት አደረሱ? ወይኔ ወይኔ ልጄ፤” ብላ ወይዘሮዋ ልታብድ ስትቸኩል “ኧረ ቆይ ተረጋጊ። እንዴ የምን ሳንሸበር መሸበር ነው፤” አዛውንቱ ወይዘሮዋን ተቆጥተው ተማሪዎቹን ዓይን ዓይናቸውን እያዩ ሲያበቁ፣ሰ “እናንተ አትናገሩም? ትናገራላችሁ? ለምንድነው ፈተና የተቋረጠው?” ጫን ብለው ጠየቋቸው።

“እንግሊዝኛ ፈተና ተሰረቀ አሉ፤” አንደኛው መለሰ። “ምን?” ጎልማሳው አላመነም። ማንም አላመነም። ይኼኔ ‘ይኼው እዚህ ስሙ’ ብሎ ሾፈሩ ሬዲዮኑን ድምፁን ከፍ አደረገው። “የእንግሊዝኛ ፈተና ተሰርቆ በመውጣቱና ከእነመልሱ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በመሰራጨቱ ለጊዜው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንዲቋረጥ ትምህርት ሚኒስቴር ወስኗል፤” ይላል። “አበስኩ ገበርኩ! አሁን እስኪ ፈተና መስረቅ ምን ይባላል? እኛ የመልስ እንጂ የጥያቄ ችግር የለብን። ዕድሜ ለሙሰኛና ለአስጠጊዎቻቸው፤” ስትል ወይዘሮዋ ሌላው ቀበል አድርጎ፣ “የተሰረቀ ጥያቄ ሠርቶ ትውልድ የት እንዲደርስ አስበው ይሆን ሌቦቹስ?” አለ። “ዝም አትልም? እንኳን ታዳጊው ይኼው ተሰናባቹ ሌብነት ሲያዝ እንጂ፣ እስኪያዝ ድረስ ሥራ ነው ተብሎ ተመክሮ የት ደረሰ?” አለ የገቢናው። ወያላው ‘መጨረሻ’ ሲል አዛውንቱ ያሉትን አስታውሳለሁ። ‹‹እኛው እናመጣው እኛው እናሮጠው ይኼው እዚህ ተደረሰ፤›› ሲሉ በዓይን አውጣዎች ዘመን ስርቆትም ጀብዱ ነው ማለት ያስከጅል ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት