ከሞራልና ከሥነ ምግባር ዝቅጠት አመላካቾች መካከል አንዱ ስርቆት ነው፡፡ ስርቆት ትልቅም ይሁን ትንሽ ወንጀል ነው፡፡ በትምህርት አካባቢ የሚፈጸም ስርቆት ደግሞ ተደራራቢ ወንጀል ነው፡፡ ለምን ቢባል ትውልድ ገዳይ በመሆኑ፡፡ ሰሞኑን ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ከተዘጋጀ ፈተና ውስጥ ኮድ 14 የተባለ የእንግሊዝኛ ፈተና ተሰርቆ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በመለጠፉ፣ ፈተናው በጠቅላላ እንዲቋረጥ ተደርጎ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል፡፡ በዚህም ምክንያት 254 ሺሕ ያህል ተፈታኞች ያለጥፋታቸው የወንጀል ሰለባ ሆነዋል፡፡ ስርቆቱን ከፈጸሙት ወንጀለኞች ባልተናነሰ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በመለጠፍ የድርጊቱ ተባባሪ የሆኑትም መወገዝ አለባቸው፡፡ ምንም ዓይነት ምክንያት ይኑራቸው ትምህርትና ከትምህርት ጋር የሚገናኙ ጉዳዮች ለጥፋት ዓላማ መዋል የለባቸውም፡፡ የስርቆቱ ተዋናዮች ግን በአስቸኳይ ድርጊታቸው ተጣርቶ ለሕግ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
በተደጋጋሚ እንደምንለው ኃላፊነትና ተጠያቂነት በሌለበት ሕግ ይጣሳል፡፡ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ይጎዳል፡፡ የአስተዳደር ብልሹነት ይሰፍናል፡፡ ሙስና ይንሰራፋል፡፡ የማኅበረሰቡ የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶች ዋጋ አልባ ይሆናሉ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች አገር ትጎዳለች፡፡ ሕዝብ ይሳቀቃል፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት በላይ አርቀው ስለማያስቡ፣ ድርጊታቸው በሙሉ ‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው› ዓይነት በሽታ ነው የሚሆነው፡፡ ከፈተና ዝግጅቱ እስከ ፍፃሜው ድረስ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ግለሰቦች በተለያዩ ምክንያቶች ትውልድ ገዳይ የሆነ ውሳኔ ላይ ሲደርሱ፣ የሚመለከተው አካል ደግሞ በአስቸኳይ ማጣራት አድርጎ ሕጋዊ ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡ ለግል ጥቅምም ይሁን ለሌላ ዓላማ የሚውል ሕገወጥ ድርጊት በእንጭጩ ካልተቀጨ፣ ነገና ተነገ ወዲያ ከዚህ የባሱ አደጋዎች ይከሰታሉ፡፡
ብሔራዊ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ለመፈተን የተዘጋጁ ወጣቶች ሊደርስባቸው የሚችለውን መሳቀቅ ማንም በሒደቱ ያለፈ በቀላሉ ይረዳዋል፡፡ ከተፈታኞችና ከቤተሰቦቻቸው ሥነ ልቦና አንፃር ችግሩን ስንመዝነው የተፈጸመው ድርጊት ወንጀል ነው፡፡ አድማሱ የጠበበ ቢሆንም ፈተና ከዚህ በፊትም ተሰርቆ ያውቃል፡፡ ነገር ግን ዘመን አመጣሹ ማኅበራዊ ሚዲያ ሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ ግን ፈተና ሲሰረቅ፣ በደቂቃዎች ውስጥ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ተሠራጭቶ የሚመለከታቸውን በሙሉ ስለሚያዳርስ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈታኞች ፈተና ተሰረዘ ቢባል ምን ይሰማቸዋል? ካሁን በኋላስ ላለመሰረቁ መተማመኛቸው ምንድነው? እንደገና ተዘጋጁ ተብሎ ሌላ ቀጠሮ ሲያዝ ነገ ምን እንደሚመጣ ስለማያውቁ በሚደርስባቸው ግራ መጋባት ማን ነው የሚጠየቀው? አሁን ለደረሰው የሞራል ስብራት ተጠያቂው ማን ነው? እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ የሚታዩት ችግሮች ጓዛቸውን ጠቅልለው ትምህርት አካባቢ ጎራ ሲሉ እንደ አገር መደንገጥ ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ግባ የማይባል ሥነ አመክኖአዊ ክርክር ማቅረብ የማይችሉ ወገኖች ለማይገባ ዓላማ ሲያውሉት፣ በሙስና የተተበተቡ ራስ ወዳዶች የግል ጥቅም ማግበስበሻ ሲያደርጉት፣ ለጉዳዩ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት አካል እንደ አደጋ ጊዜ በፍጥነት ተንቀሳቅሶ አጣሪ ቡድን አቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ማስታወቅ ሲሳነው፣ ወዘተ በጣም ግራ ያጋባል፡፡ የማኅበረሰባችን የረጅም ዘመን እሴቶች የሆኑት ሞራልና ሥነ ምግባር ወደ ጎን እየተገፉ ፈተናን የሚያህል ትልቅ ነገር ተሰረቀ ሲባል በጋራ አለመቆም ከማስገረም በላይ ያሳፍራል፡፡ እንደ አገር የኩረጃ መስፋፋት አሳፋሪ ሆኖ ‹ይህቺ ድንቅ የአርበኝነት ተምሳሌት የሆነች አገር ልጆች ኩረጃን እንዲያወግዙ› ተማፅኖ በቀረበ ማግሥት፣ ዋናው ፈተና ተሰርቆ ወጣ ሲባል ያሳቅቃል፡፡ ከማሳቀቅ በላይ ያሳፍራል፡፡
ከመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ከፍትሕ መጓደልና ከሙስና መንሰራፋት ጋር ትግል መደረግ እንዳለበትና አገሪቱ እነዚህን ችግሮች ተሸክማ መጓዝ አትችልም እየተባለ፣ የወጣቱን ትውልድ ሞራል የሚገድልና በአይረቤ ምሳሌነት የሚጠቀስ አሳፋሪ ድርጊት ተከስቷል፡፡ መንግሥት በአስቸኳይ ራሱ ጓዳ ውስጥ የተፈጸመውን ድርጊት በገለልተኛ ወገኖች ወይም በባለሙያዎች አጣርቶ ለሕግ ካላቀረበ ተጠያቂነት አለበት፡፡ ይህ ተግባራዊ እስኪደረግ ድረስ ደግሞ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ወገኖች ከኃላፊነታቸው መነሳት አለባቸው፡፡ የፈተና ስርቆት የሞራልና የሥነ ምግባር ችግርን ከማሳየቱም በላይ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ወደ ጎን እየተገፉ ማናለብኝነት መንገሡንም ያመላክታል፡፡ ተወደደም ተጠላም ለዚህ የረከሰ ተግባር ተጠያቂነት ያለባቸው ወገኖች አሉ፡፡ ሕዝብም የማወቅ መብት አለው፡፡ ከሕግ በላይ ማንም የለም፡፡ በሕግ አምላክ፡፡
ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ሲልኩ ከሚያወጡት ወጪ በተጨማሪ ለልጆቻቸው መፃኢ ጊዜ መሳካት የሚቆጥቡት ምንም ነገር የለም፡፡ ይህ የወላጆች ትልቁ ግዴታ ነው፡፡ ልጆችም በአግባቡ ትምህርታቸውን ተከታትለው ከሚያልሙት ግብ ለመድረስ ማንኛውንም ዓይነት መስዋዕትነት ይከፍላሉ፡፡ ይህም ከእነሱ የሚጠበቅ ነው፡፡ አገርን የሚረከባት የነገው ትልውድ ነውና በተቻላት አቅም ያላትን ሁሉ ታደርጋለች፡፡ ለ254 ሺሕ ፈተና ተቀማጮች በአገር ደረጃ የሚወጣው ሀብትም ከዚህ ደሃ ሕዝብ የተሰበሰበ ነው፡፡ አገሪቱ የነዳጅ ገቢ የላትም፡፡ እዚህ ግባ የሚባል የኤክስፖርት ገቢም የላትም፡፡ የአገሪቱ አርሶ አደርና ሠርቶ አደር ሕዝብ ላቡን አንጠፍጥፎ የሚያበረክተው ውስን ሀብት የአገር ፍቅር ስሜት በሌላቸው ሲባክን ያቃጥላል፡፡ ይህንን ሁሉ ታሳቢ የሚያደርግ አንድ ዜጋ በአገሩ ላይ እንዲህ ዓይነት አፀያፊ ወንጀል ሲፈጸም እንደ ቀልድ አይመለከተውም፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ከአንዳንድ ወገኖች የተላለፈው መልዕክት ግን አስደንጋጭ ከመሆኑ የተነሳ ለትዝብት የሚዳርግ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አሳዛኝ ተግባር ለማይገባ ዓላማ ከማዋል ይልቅ፣ ትውልድ የሚቀረፅበት ትምህርት አካባቢ የሚፈጠር ችግር እንዴት መወገድ አለበት የሚለው ላይ ቢተጋ ይመረጣል፡፡
የትምህርት ተቋማቶቻችን የጥራት ደረጃ መውረድ፣ በየቦታው እንደ አሸን የፈሉ የመመረቂያ ጽሑፍ አዘጋጆች ገበያ መድራት፣ በትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚታየው ብልሹ አስተዳደርና ሙስና መስፋፋት፣ የትምህርት ተቋማትን እንደ ወረርሽኝ የሚያሠጓቸው የሱስ ማስያዣዎች ሃይ የሚላቸው መጥፋት፣ ወዘተ የአገሪቱ ትልቅ ራስ ምታት ናቸው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ፈተና የሚሰርቁ ሌቦች ሲታከሉበት የችግሩን መጠን ለመጋፈጥ ሊያስፈራ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለሕግ የበላይነት ሲባል ማናቸውም ዓይነት መስዕዋትነት ተከፍሎ ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት እነዚህን ችግሮች ታቅፎ የት ድረስ እንደሚጓዝ ግር ቢልም፣ አስመዘገብኳቸው ከሚላቸው ስኬቶች በስተጀርባ የመሸጉ አደገኛ ነውሮች መሆናቸውን ማመን አለበት፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር መላሸቅ ውጤት የሆነው የፈተና ሌብነት ማንንም የማይጠቅም የአገር ጠላት ነው፡፡ በተሳሳተ እሳቤ ስርቆቱን ማወደስ የብዙዎችን ህሊና ያቆስላል፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚዎችን አጣርቶ ለሕግ አለማቅረብ ደግሞ ኃላፊነት አለመወጣት ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ለዚህ ችግር መፍትሔው የሕግ የበላይነትን አረጋግጦ፣ ይህንና መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ማስቆም ነው፡፡ በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ ወጥ አቋም ለመያዝ ደግሞ ከብሔራዊ መግባባት በላይ አማራጭ የለም፡፡ በመሆኑም የዚህን አስከፊ ድርጊት ፈጻሚዎች አጣርቶ ለሕግ ማቅረብ የግድ ይሆናል!