Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየሊዝ አዋጅ እንዲሻሻል ተወሰነ

  የሊዝ አዋጅ እንዲሻሻል ተወሰነ

  ቀን:

  በአገር አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የነበረው የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ ኅዳር 2004 ዓ.ም. የፀደቀው አዋጅ ቁጥር 721፣ የተወሰኑ አንቀጾች ለአሠራር አስቸጋሪ ሆነው በመገኘታቸው በድጋሚ እንዲሻሻል ተወሰነ፡፡

  በዚህ መሠረት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አዋጁን አጥንቶ የማሻሻያ ሐሳብ የሚያቀርብ ቡድን ያቋቋመ ሲሆን፣ ቡድኑ አዲስ አበባን ጨምሮ ከክልሎች ጋር መነጋገር መጀመሩ ታውቋል፡፡

  በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህ አዋጅ ግዙፍ ኩባንያዎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመገንባት የሚያቀርቧቸውን አዲስ የመሬት ጥያቄ፣ ነባር ኩባንያዎችም የሚያቀርቧቸውን የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ ለማስተናገድ የማያስችል መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመሬት የሊዝ አከፋፈል ላይም እንዲሁ ችግር መኖሩ ሲወሳ ነበር፡፡

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት አዋጁ ከወጣ ከሁለት ዓመት በኋላ የሚቀርቡለትን የመሬት ጥያቄዎች ለማስተናገድ መቸገሩን በመግለጽ፣ አስተዳደሩ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡

  በወቅቱ እንደተብራራው፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አልሚዎች በተለያዩ ጊዜያት ለማኅበራዊ አገልግሎት በተለይም ለሆቴል፣ ለሆስፒታል፣ ለገበያ ማዕከልና ለሪል ስቴት ግንባታ መሬት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

  እነዚህ ጥያቄዎች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሚቀርቡ ሲሆን፣ የከንቲባ ጽሕፈት ቤትም መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮም፣ ለመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ሐሳብ እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ይመራሉ፡፡

  ‹‹ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች›› ማለት በሊዝ አዋጅ አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 21 እና በአገራዊ ፋይዳ መመርያ ቁጥር 15/2005 መሠረት ለኢትዮጵያ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶች፣ ወይም የትብብር መስኮች ለማስፋት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ለሚኖራት የተሻለ ግንኙነት መሠረት እንዲጥሉ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ጥያቄው ከሊዝ አዋጅ ጋር የሚጋጭ ስለሆነ ለአልሚዎች ምላሽ ለመስጠት ችግር እንደፈጠረ ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ ጽሕፈት ቤቱ እንዳብራራው በሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ 7 እና ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው የከተማ መሬት የሊዝ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 11/2004 አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 2 እንደተደነገገው፣ ከላይ የተዘረዘሩት የአገልግሎት ዘርፎች የሚስተናገዱት በልዩ ጨረታ ነው፡፡ እንዲሁም በሊዝ አፈጻጸም መመርያው አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 8 ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ እየታየ ለካቢኔ ለሚመሩ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች የሚውሉ ቦታዎችን በተመለከተ ዝርዝር መሥፈርቱና የቦታ አመዳደብ ሒደቱ ራሱን በቻለ መመርያ የሚወስን መሆኑ በተደነገገው መነሻነት፣ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ለሚባሉ ፕሮጀክቶች መመርያ ቁጥር 15/2005 ቢወጣም፣ መመርያው ከሊዝ አዋጅ ጋር ይጣረሳል በሚል ወቀሳ ሲቀርብበት ነበር፡፡

  በዚህ ምክንያት ለአገልግሎት ዘርፍ መሬት እንዲሰጣቸው ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በተቀመጠው ትርጓሜና በሊዝ አዋጅ በተደነገገው መሠረት ለማስተናገድ መቸገሩንም ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪ ነባር አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚያቀርቡት የማስፋፊያ መሬት ጥያቄም መስተናገድ አልቻለም ተብሏል፡፡ በዚህ ምክንያት በርካታ ግዙፍ ኩባንያዎች የሚያቀርቡት የመሬት ጥያቄ ተቀባይነት ያጣ ሲሆን፣ በርካታ ኢንቨስተሮች አቤቱታቸውን ለከንቲባው ድሪባ ኩማና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡

  የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አላሠራ ያሉ አንቀጾችን በመሰብሰብ ከመሬት ሥሪት ባለሙያዎች ጋር እየመከረ ሲሆን፣ በውይይቱ በጉዳዮቹ ላይ መግባባት ላይ ከተደረሰ በቅርቡ አዋጅ ቁጥር 721 በድጋሚ እንደሚሻሻል የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

  በዚህ ጉዳይ ላይ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...