Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገር አቀፍ የትምህርት ምዝናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ሚና የቴክኒክ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ይሆናል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከግንቦት 22 ቀን እስከ 25 ቀን ቀን 2008 ዓ.ም. ሊሰጥ ታስቦ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ከተሰረዘ በኋላ፣ በድጋሚ የሚሰጠው ፈተና ዝግጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ በግብረ ኃይል እንደሚመራ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ለሪፖርተር አስታወቀ፡፡

ፈተናው ከተሰረቀ በኋላ መሰረዙ ሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ የተገለጸ ሲሆን፣ የድጋሚው ፈተና ከሰኔ 27 እስከ 30 እንደሚሰጥ ይህም ኢድ አል ፈጥርን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መግለጻቸውም ተዘግቧል፡፡

የብሔራዊ ፈተናዎች ዝግጅትና አሰጣጥን የሚመራው የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በድጋሚ የሚሰጠውን ፈተና ዝግጅት በሚመለከት ምን እያደረገ እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ገብረ እግዚአብሔር፣ ጉዳዩ በግብረ ኃይል ደረጃ እንደተያዘና ኤጀንሲውም ትዕዛዝን ከማስፈጸምና የቴክኒክ ድጋፍ ከመስጠት ውጪ ሚና እንደሌለው በመግለጽ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋዱ ላይ መግለጫ ሲሰጡ ፈተናው የተሰረዘው የኮድ 14 የእንግሊዝኛ ፈተና መውጣቱን በመረጋገጡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የእንግሊዝኛ ብቻም ሳይሆን የሒሳብና የሌሎችም ትምህርቶች ናቸው የተባሉ ፈተናዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ተለቅቀው ነበር፡፡ አንዳንዶች ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ፈተናዎቹን ማግኘታቸውን ሲገልጹ በማኅበራዊ ድረ ገጾች የመልስ ወረቀቶችም ተለቅቀው ነበር፡፡ አቶ ሽፈራው የእንግሊዝኛ ፈተናው መሰረቅ ከተረጋገጠ በኋላ ሌሎቹን ማረጋገጥ አስፈላጊ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡

ላለፉት ረዥም ወራት ሙሉ ጊዜና ትኩረታቸውን ጥናት ላይ አድርገው ለፈተና ቀን ሲዘጋጁ ለነበሩ ተማሪዎች ሁኔታው ከባድ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል፡፡ በርካታ ወላጆችም በድርጊቱ አዝነዋል፡፡ ልጃቸው ጎበዝና የደረጃ ተማሪ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ጌቱ ዓለማየሁ በሁኔታው ልጃቸው ተረብሾ እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ፈተና ተሰርቆ እያለ የፈተና ሒደቱ ቀጥሎ ብዙ የለፉና የደከሙ ተማሪዎች እንዳይጎዱ መሰረዙ ጥሩ ዕርምጃ ቢሆንም፣ ‹‹የፈተናው መሰረቅ በራሱ ግን እንደ አገር አደገኛ ነገር ነው፡፡ ትምህርት ለአንድ አገር የሁሉ ነገር መሠረት ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና መሰረቅ ደግሞ ለዚህ ትልቅ ጉዳይ ትኩረት አለመሰጠቱንና የጥንቃቄ ጉድለት መኖሩንም ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡

በየዘርፉ አስተማማኝ ሥርዓት ተዘርግቷል እየተባለ የዚህ ዓይነቱ ድርጊት መፈጸም ከባድ እንደሆነም አቶ ጌቱ ይገልጻሉ፡፡ ከአንድ ወር በፊት አቶ ሽፈራው ለተወካዮች ምክር ቤት የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ በሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳ የወረዳው ምክትል አስተዳደር የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርን በማስገደድ ፈተና እንዲሰረቅ ማድረጉን፣ በዚህም ሁለቱም ግለሰቦች በሕግ መጠየቃቸውን ገልጸው ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥም በአንድ የትምህርት ዓይነት 200 ብር ከተከፈለ ፈተና እናወጣለን የሚሉ መኖራቸውን ጠቁመው ነበር፡፡

አሁን የተፈጠረው ችግር በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር እንደሆነ፣ ፈተናዎች በአግባቡ እንዲሰጡና ተማሪዎች የልፋታቸውን ዋጋ እንዲያገኙ መንግሥት እንደሚሠራ፣ ጉዳዩ ተጣርቶ በተጠያቂዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ለፈተናው መውጣት ኃላፊነት እንወስዳለን ያሉ አካላት በማኅበራዊ ድረ ገጾች ድምፃቸውን እያሰሙ ነው፡፡ የፈተናዎች ኤጀንሲ የተወሰኑ ሠራተኞች ላይ ምርምራ ማድረግ መጀመሩን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ መሆኑን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ አርዓያ፣ ‹‹ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጠኝነት የማውቀው ነገር ግን የለም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ዓመት ለብሔራዊ ፈተናዎች አጠቃላይ ዝግጅትና ማስፈጸሚያ የወጣው 215 ሚሊዮን ብር መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 120 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ለኅትመት፣ 95 ሚሊዮን ብር ደግሞ ለፈተና አስተዳደር እንደሚውል የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አርዓያ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ፈተናውን ለማስፈጸም ደግሞ 51 ሺሕ የትምህርት ባለሙያዎችና መምህራንንም በመላ አገሪቱ ለማሰማራት ታስቦ እንደነበርም በወቅቱ ተገልጿል፡፡ 253,424 የአሥራ ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናው ላይ ይቀመጣሉ ተብሎ ነበር፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች