Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከየም ትውፊቶች

ከየም ትውፊቶች

ቀን:

በደቡብ ክልል ከሚገኙት ልዩ ወረዳዎች አንዱ የም ነው። ወረዳው ረዥም የዝናብ ወር የሚሸፍነው ከሰኔ እስከ መስከረም ሲሆን፣ አጭሩ የዝናብ ወር (በልግ) ደግሞ በየካቲትና በሚያዝያ ነው። መፀው ወቅቱ ‹‹ማር›› ሲባል፣ ክረምቱ ‹‹መሄር›› ይባላል። ከወቅቱ ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ባህላዊ በዓላትም በብሔረሰቡ ይገኛሉ። ከእነዚህም አንዱ ሄቦ ነው። በባህልና ቱሪዝም መስክ ውስጥ የተሰማራው ሔኖክ ሥዩም ‹‹ቱባ›› በተሰኘው ኅትመቱ እንደገለጸው፣ በየም ብሔረሰብ ልዩ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ባህላዊ በዓላት አንዱ ሄቦ ነው። በጉጉት የሚጠበቅና ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎበት ከመስከረም አጋማሽ እስከ ጥቅምት መግቢያ የሚከበር ነው። በበዓሉ ከወዳጅ ዘመድ ጋር የሚደረገው መገባበዝና የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት ልውውጥ ‹‹ፍርኒ ኦቱ›› (የአበባ መለዋወጥ) ይባላል። ይህ በዓል የጥጋብ በዓል ነው። በበዓሉ ሰሞን ሰውም፣ እንስሳም አይራብም። ከበዓሉ መድረስ ሦስትና ሁለት ወራት በፊት ለእንስሳት መኖ ይዘጋጃል። ይህ ከለመለመ የመኖ ሳር ታጭዶ በበረታቸው ውስጥ ተቀምጦ ቢያንስ ከሳምንት በላይ እንዲመገቡት ይደረጋል። ሄቦ እስኪያልቅ እንሰሳት በለመለመ ሳር ይታገዳሉ። ለሄቦ በዓል ለከብቶች የተለየው ሳር በሚለመልምበት ቦታ የባለቤቱም ሆነ የሌላ ሰው ከብት እንዳይገባ የክልከላ ምልክት ይሆን ዘንድ ረዘም ያሉ እንጨቶች በግጦሽ ሳሩ መካከል ይተከላሉ። እነዚህ ምልክቶች ‹‹ዛዞ›› ይባላሉ። በዓሉ ሁሉም ነገር ፅዱና አዲስ ሆኖ የሚታይበት እንዲሆን የብሔረሰቡ አባላት ግቢያቸውን በአዲስ አጥር ያጥራሉ። ይህንን አጥር የማጠሩ ኃላፊነትም የወንዶች ነው። የሄቦ በዓል መከበር የሚጀምረው መስከረም 14 ቀን ነው። ይህ ቀን ‹‹ካማ ኬሳ›› ይባላል። ‹‹ካማ›› ማለት ማር ሲሆን፣ ‹‹ኬሳ›› ማለት ደግሞ መውጣት ማለት ነው። ወደ አዲስ ዓመት ለመግባት ቂምና ቅሬታን በማስወገድ መቀደስን የሚያመላክት ሲሆን ቅራኔና የሰነበተ ቂም በሽማግሌዎች አማካይነት ዕርቀ ሰላም ወርዶ የሚወገድበት ሥርዓት የሚፈጸምበት ቀን ነው። የሄቦ በዓል መባቻ መስከረም 17 የሄቦ በዓል የመጀመርያው ዕለት ነው። በየም ብሔረሰብ ባህል ከዚህ ቀን ጀምሮ ኢሶንሲ ፊና ወይም የመጀመርያው ፊና እየተባለ መቆጠር ይጀምራል። እንዲህ እየተባለ የሚቆጠረው እስከ መስከረም ሰላሳ ነው። ፊና ማለት ከከርቀሃ የሚዘጋጅ የብሔረሰቡ የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ሲሆን የተለያየ መጠን አለው። ቅኝቱም የተለያየ ነው። በሄቦ በዓል ወቅት ብቻ ባማረ ሁኔታ ይቀኝበታል። የሙዚቃ መሣሪያው ሁሉንም አሳታፊ ከልጅ እስከ አዋቂ ሴቶችም ጭምር የሚጫወቱበት አገረሰባዊ የሙዚቃ መሣሪያ ነው። የቦጋ ጨዋታ ሥርዓት ክብረ በዓሉ ኅብረተሰቡ በሚጫወተው ጣዕመ ዜማ የታጀበ ነው። ጨዋታው ቦጋ ይባላል። የቦጋ ጨዋታ የራሱ የሆነ ሥርዓት አለው። ማንም በዘፈቀደ አይንቀሳቀስም። ጨዋታውን በሥርዓቱ የሚመራ የቦጋ ጨዋታ መሪ ይመረጣል። ይህ መሪ በብሔረሰቡ ቋንቋ ‹‹አባሚላ›› ይባላል። አባ ሚላ በጨዋታው መካከል ግጭት እንዳይፈጠር፣ ባለማወቅ ልጆች የጨዋታውን ሥርዓት እንዳያበላሹ፣ ጨዋታው ማን ቤት እንደሚጀመር፣ ስንት ሰዓት ተጀምሮ በስንት ሰዓት መጠናቀቅ እንዳለበት በየቤቱ የሚደረገው መስተንግዶ በሥርዓት እንዲካሄድ መመርያ በመስጠት ይመራሉ። የሄቦ በዓል እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም የአካባቢው ማኅበረሰብ ተሰብስቦ በየዓመቱ በሚጫወትበት ቦታ ወይም በብሔረሰቡ ቋንቋ ካኛ (ካንቻ) በሚባልበት ቦታ ቦጊኛዎች (የቦጋ ተጫዋቾች) አስፈላጊውን ቁሳቸውን ይዘው ይሰበሰባሉ። የሚሰበሰቡት እስኪበዙ ድረስ የቱቱሩ (የቀንድ መለከት) ድምፅ ያማረ ዜማ ያሰማሉ። በየቤቱ ያለውም ይህን ድምፅ በመስማት ከየቤቱ ወጥቶ ይሰበሰብና በጋሻ በነብርና በጉሬዛ ቆዳ ያጌጡ አባቶችና ታላላቆች ጨዋታውን በሠልፍ በዚግዛግ እያሰሞሰሙ በመምራት በየዓመቱ የሚባለውን የሄቦ በዓል ጨዋታ ‹‹ያሆ ያሆ ኤ ያሆ›› እያሉ የጨዋታውን ዜማ በመቀያየር ከቱቱሩው (ከቀንደ መለከቱ) ድምፅ ጋር በማዋዛት እየጨፈሩ ወደ ቀዳሚው ቤት ያመራሉ። በቤቱ በራፍ እየተጫወቱ ልጆች ከኋላ ታላላቆች ከፊት በመሆን በአንድነት ውው፣ ውው በማለት ለአጭር ጊዜ የጩኽትና የቱቱሩ (የመለከት) ድምፅ ያሰማሉ። በሶማቸው (የቀርቀሃ ዘንግ) መታ መታ በማድረግ ቁርጥ ቁርጥ ባለ ድምፅ ውው፣ ውው እየተባባሉ የተለየ እንቅስቃሴና ትርዒት ካሳዩ በኋላ በአንድነት ቦጊኛዎች በራፍ ደጅ እየዞሩ ይጨፍራሉ። በዚህ መልኩ ከተጫወቱ በኋላ ባህላዊ መጠጡ (ቦርዴ) የማኡሻና ምግር ኮበና ይቀርባል። ከበሉ ከጠጡ በኋላ አናታቸውን እንዲቀቡ ቅቤ ይሰጣቸዋል። አናታቸው የተቀቡትን ቅቤ ጋሻቸውን ጭምር በመቀባት ‹‹ጎር ዎታውቶ፣ ዎኔትስ ይኔትስ ካታውቶ፣ ሚያስ ፉፍና ፉቱ ኮንተፋው›› ‹‹ጎር የሄቦ ጌታ ይባርክዎ፣ ዓመት ዓመት ያድርስዎ፣ ከብቶችዎ ተወልደው እንደ አሸዋ አፈር ይብዛልዎት›› ብለው ይመርቃሉ። በዚህ መልኩ የሚከናወነው ጨዋታ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይቆይና ከዚያ የጋራ ጨዋታ ወደሚደረግበት ካንቻ ይመለሳሉ። በመጀመርያው የቦጋ ጨዋታ ቀን የአገር ሽማግሌዎች ባህላዊ ቡልኮ ወይም ጋቢ ለብሰው ጦር ይዘው የጋራ ጨዋታ በሚደረግበት ቦታ (ካንቻ) ቦጊኛዎች (የቦጋ ተጫዋቾች) ከቤት ለቤት ጨዋታ እስኪመለሱ ይጠባበቃሉ። ከደረሱም በኋላ በጋራ ይጮሁና የተወሰነ ‹‹የያሆ›› ጨዋታ ከተጫወቱ በኋላ ‹‹የኮምሱ›› ሥርዓት በሚደረግበት ቦታ ፊኖአቸውን (የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያ) ይዘው ከአገር ሽምግሌዎች ጋር እያዜሙ ይሄዳሉ። በሄቦ በዓል የሚነፋው ‹‹ፊኖ›› በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ካንቻ (የጭፈራው ቦታ) ይቀመጣል። ጨዋታውን አቋርጦ ለመሄድ የሚፈልግ ሰው ቢኖር እንኳን ፊኖውን በሚቀመጥበት የዛፍ ሥር አስቀምጦ ይሄዳል። የሄቦ በዓል ጨዋታ የተጠናቀቀ ዕለት የፊኖውን ደኅንነት ጠብቆ በማስቀመጥ በዓመቱ እንደገና የሚያመጣ ሰው ይመረጣል። ይህ ሁሉ ተጠብቆ የሄቦ በዓል ልዩ ግምት ተሰጥቶት በመስከረም 17 ከሚከበረው የመስቀል በዓል ጋር በመደቀ ሁኔታ ተከብሮ እስከ ጥቅምት መግቢያ ይዘልቃል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...