‹‹የግዕዝ ዕውቀት ለኢትዮጵያውያን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጠቀሜታው በመንግሥትና በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ እያንዳንዱን የግዕዝ ዕውቀት ጠቀሜታ ቢዘረዝሩት መጽሐፍ ስለሚወጣው በደምሳሳው የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሥነ ምግባር፣ ሕግ፣ ነገረ ሥራይ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ፈለክ፣ ቅኔ፣ ዜማ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብና ኪነ ጥበብ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ አመለካከትና ሥነ ልቦና የተላለፈለው በግዕዝ ቋንቋ መሆኑን ማስታወስ ግን ተገቢ ነው፡፡››
በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በግዕዝ ምሁራን ‹‹ተቅዋመ ማኅቶት›› በሚል ስያሜ የተቋቋመውና በምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም ሕንፃ ውስጥ የሚገኘው የግዕዝ ትምህርት ቤት በቅርቡ በሰጠው መግለጫው ላይ ያንፀባረቀው ሐሳብ ነው፡፡ መደበኛውም ሆነ ኢመደበኛው የግዕዝ ትምህርት ከፍተኛ ልምድ ባላቸው የዩኒቨርሲቲ መምህራን በቀን፣ በማታና በበዓላትም የሚሰጥ ነው፡፡
እንደ ተቋሙ መግለጫ፣ ተግባራዊ የግዕዝ ትምህርት መርሐ ግብርና ግዕዝ ቋንቋን በዘመናዊ ዘዴ የማስተማር መርሐ ግብር ተብለው ተለይተዋል፡፡ ከመደበኛ የግዕዝ ትምህርት መርሐ ግብር የሚጀምሩት ምንም ዐይነት የግዕዝ ቋንቋ ዕውቀት የሌላቸው ሲሆኑ ትምህርቱ በድምሩ በዘጠኝ ወራት የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ ከመደበኛ የግዕዝ ትምህርት የዘለቀ ተማሪ የግዕዝ መጻሕፍትን አንብቦ የመረዳት፣ ግዕዙን ወደ አማርኛ የመተርጐምና ፣ አማርኛውንም ወደ ግዕዝ የመተርጐም ክሂሎት ይኖረዋል፡፡
ይኸው የግዕዝ ትምህርት በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለዘመናት ሲያስተምሩት በቋንቋው ውስጥ ያሉትን ቁም ነገሮች ሲመረምሩትና ግኝቶቻቸውን ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅና ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ኮሌጅ ከምሥረታቸው ጀምሮ ግዕዝን እያስተማሩ ሲሆን ወደ ዩኒቨርሲቲ እየተሸጋገረ ያለው ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ በዲፕሎማ ተወስኖ የነበረውን የግዕዝ ትምህርት ከዘንድሮ የመጀመርያ ወሰነ ትምህርት ጀምሮ ወደ መጀመርያ ዲግሪ ከፍ አድርጎታል፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት ለዘመናት በኮመን ኮርስ ደረጃ ሲሰጥ ከነበረው የግዕዝ ትምህርት ባሻገር ከአሥር ዓመት በፊት ጀምሮ በግዕዝ ሥነ ድርሳን (ፊሎሎጂ) በድኅረ ምረቃ ደረጃ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ከሦስት ዓመት ወዲህም የአክሱም፣ የባህር ዳር፣ የጎንደር፣ የመቐለ፣ የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲዎችም በግዕዝ ቋንቋ ላይ ጥናትና ምርምር ከማድረግ ባሻገር እንደ የትኩረታቸው በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ ለማስተማር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓምና በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ያጸደቀውና ወደተግባር የገባበት የግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የድኅረ ምረቃ ትምህርት በልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፎች የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙና መሠረታዊ የግዕዝ ዕውቀት ያላቸውን በመምረጥ እስተማረ ይገኛል፡፡
ባለፈው ግንቦት ወር የባህር ዳር የዩኒቨርሲቲው የሥነ ሰብ ትምህርት ክፍል ኃላፊው ዳዊት አሞኘ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ‹‹የትምህርት ክፍሉ ዋነኛ ዓላማ በጥንታዊና በመካከለኛው የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ዘመን የነበሩ ብዙም የማይታወቁ የሕክምና፣ የትምህርት፣ የፍልስፍና፣ የባህል፣ የሥነ ልቦና፣ የእምነት እንዲህም የአስተዳደር ዕውቀቶችን መዳሰስና ለጥናት በር መክፈት ነው፡፡
ሰሞኑን የወሎ ዩኒቨርሲቲም ከዘንድሮ ጀምሮ ግዕዝን በመጀመርያ ዲግሪ ለማስተማር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ትምህርቱን ለመጀመር በቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ ከምሁራንና ባለድርሻ አካላት ጋር መወያየቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዩኒቨርሲቲው እንዳስታወቀው የሥነ ከዋክብት ቀመርና የቀን አቆጣጠር፣ የባህልና የሕግ ሥርዓቶች፣ እንዲሁም አገር በቀል ሕክምናና መድኃኒት የተካተቱበት ትምህርቱን ለማስጀመር አራት መምህራን የተቀጠሩ ሲሆን፣ እስከ 18 ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት አድርጓል፡፡
ትምህርቱ በግዕዝ ቋንቋው የተጻፉ ሥራዎችን ወደ ሌሎች አገርኛ ቋንቋዎች በመተርጐም ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
ግዕዝና ሥነጽሑፍ
ግዕዝ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ በቀደምትነት ከተረጐመባቸው የዓለም ቋንቋዎች አንዱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚመረመርባቸው ቀደምት ቋንቋዎቹ አንዱ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስም በተጨማሪ መጻሕፍተ ሊቃውንት፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ሀብቶች የሆኑት ገድላት፣ ድርሳናት፣ መልካ መልኮች… እና እጅግ በርካታ የሥነ ጽሑፍ መጻሕፍት የተተረጐሙትና የተጻፉት በግዕዝ ቋንቋ ነው፡፡
እንደ ተቅዋመ ማኅቶት መግለጫ፣ ለዚህም ነው በምሁራኑ ዓለም የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ሲባል ከሁለት ሺሕ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የግዕዝ ሥነ ጽሑፍ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ አጽንኦት ተሰጥቶ የሚነገረው፡፡ ምክንያቱም አማርኛን ጨምሮ የሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በመሆኑ ነው፡፡
ስለዚህም ከላይ ከፍ ሲል በተጠቀሱት የትምህርት መስኮች ማለትም በጥንታዊ ኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ሥነ ምግባር፣ ሕግ፣ ነገረ ሥራይ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ፈለክ፣ ቅኔ፣ ዜማ፣ ሙዚቃ፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥነ ጥበብ፣ ኪነ ጥበብ በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ አመለካከትና ሥነ ልቡና ለማጥናት ለሚሻ ሁሉ የግዕዝ ቋንቋ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡ ዓድዋ አባ ገሪማ ገዳም የሚገኘውና በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጻፈ የሚታመነው የገሪማ ወንጌል በዓለም ከቀዳሚዎቹ የብራና ጽሑፎች አንዱ እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታመነ ነው፡፡
ግዕዝ ቋንቋ ከአማርኛና ትግርኛ፣ እንዲሁም ከሌሎች የኢትዮጵያ ሴማዊና ኩሽአዊ ቋንቋዎች ጋር ቃላዊና ሰዋስዋዊ ዝምድና አለው፡፡ ስለዚህ በተለይም እነዚህን ሴማዊ ቋንቋዎችን በአግባቡ ማጥናት የሚሻ ሁሉ ከግዕዝ ቋንቋ ቃላዊና ሰዋስዋዊ ዝምድና ጋር እያገናዘበ ማጥናቱ ትምህርቱ በመሠረቱ ብስለትና ጥልቀት እንዲኖረው ያስችላል ተብሎ ይታመናል፡፡
ጥንታዊት ኢትዮጵያ ከጥንታዊው ዓለም ጋር ታሪካዊና ሥነ ጽሑፋዊ ትስስር ነበራት፡፡ ለምሳሌ ከአፍሪካ ግብፅ፣ ኑብያ፣ ሱማሌ፣ ከእስያ (ሳባ፣ እስራኤል፣ ሱርስት፣ ህንድ . . .) እና ከአውሮፓ (ፅርዕ፣ ሮማይስጥ፣ እስፔይን፣ ፖርቱጋል፣ ጣሊያን፣ . . .) ጋር ታሪካዊና ሥነ ጽሑፋዊ ግንኙነት ነበራት፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች ሁሉ የተደረጉት በግዕዝ ቋንቋ አማካይነት እንደነበር ተቅዋመ ማኅቶት ያስረዳል፡፡
እነዚህንና መሰል ቁም ነገሮችን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና ለአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ጥናት የግዕዝ ቋንቋ አስፈላጊነት በመረዳት በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ላይ በሚገኙ 22 ዩኒቨርሲቲዎች የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ከጥንታዊው ግዕዝ ሥርዓተ ትምህርት ሊወስዳቸው የሚገቡ ብዙ እሴቶች እንዳሉ ያወሳው ተቋሙ፣ አማርኛ በስያሜና በትርጉም ምክንያት በውስጡ ብዙ የግዕዝ ቃላትን (ለምሳሌ ፍኖተ ካርታ፣ ርዕዮተ ዓለም አብዮት ሕገ መንግሥት፣ ኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ፣ ሥነ ሰብዕ፣…) እጅግ ብዙ አምቆ ስለያዘና ብዙዎቹ የግዕዝ ቃላት በመገናኛ ብዙኃን ተዛብተውና ተሳስተው ሲነገሩ ስለሚታይ፣ ለአጠቃላይ የቋንቋ ጥራት ሲባል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የግዕዝ ቋንቋ ዕውቀት ሊኖራቸው ይገባል ሲል ማሳሰቢያውን አቅርቧል፡፡
‹‹በመሠረቱ የመገናኛ ብዙኃን የተስተካከለ፣ ጥራትና ብቃት ያለው ቋንቋ መናገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን የተስተካከለ ቋንቋ ሲናገሩ ኅብረተሰቡም የተስተካከለ ቋንቋ ይናገራል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን የተሳሳተና የጐለደፈ ቋንቋ ከተናገሩ ኅብረተሰቡም የተሳሳተና የጐለደፈ ቋንቋ ይናገራል፤›› ሲልም አስገንዝቧል፡፡