Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሰማያዊ ፓርቲ የለውጥ ሒደቱን በመደገፍ የበኩሉን እንደሚወጣ አስታወቀ

ሰማያዊ ፓርቲ የለውጥ ሒደቱን በመደገፍ የበኩሉን እንደሚወጣ አስታወቀ

ቀን:

አገርን ለማረጋጋትና የለውጥ ሒደቱን ለማስቀጠል በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና በግንባሩ ጉባዔዎች፣ እንዲሁም በፓርላማ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እውነተኛ የለውጥ ሰዎችና ሐሳቦች ወደፊት መምጣታቸውን መታዘቡን ሰማያዊ ፓርቲ አስታወቀ፡፡

ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ እየተካሄደ ላለው የለውጥ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አድናቆት የቸረው ሰማያዊ ፓርቲ ይህን ያስታወቀው ዓርብ ጥቅምት 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹የአገርና የሕዝብን ሰላምና መረጋጋት ከማስፈን አንፃር የፓርቲ ርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ሊገድቡን አይገባም፤›› በሚል ርዕስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

‹‹በሕዝብ መስዋዕትነት የተገኘው ድል በአስተማማኝ መሠረት ላይ ፀንቶ ይቆም ዘንድ፣ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት ግድ ይላል፡፡ ወደ ትናንቱ የከፋ አገዛዝና ጨቋኝ ሥርዓት ላለመመለስና አገርን ከመበታተን አደጋ ለመታደግ ሁላችንም እጅ ለእጅ መያያዝ ይኖርብናል፤›› በማለት፣ የተጀመረውን የለውጥ ሒደት ለመደገፍና ለማስቀጠል ሁሉም የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የአገርንና የሕዝብን ሰላም ከማረጋጋት አኳያ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ የገለጸው ፓርቲው፣ ከዚህ በተጨማሪም የፓርቲው መዋቅሮች ባሉበት የአገሪቱ ክፍሎችም እንዲሁ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ከምንጊዜውም በላይ የሰላምና የማረጋጋት ሥራ እንዲያከናውኑ እየቀሰቀሰ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

‹‹ተስፋ የሰነቅንበት የለውጥ ሒደት ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ዕርቅን፣ መደመርን፣ እንዲሁም አንድነትን በሚጠይቅበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ‹ይኼ ሠፈር የእኔ ነው›፣ ‹ይኼኛው የአንተ አይደለም› በሚል እሰጥ አገባ ማንሳቱ ተገቢ አለመሆኑንና ፓርቲያችንም በአጽንኦት የሚያወግዘውና ወቅቱን ያላገናዘበ ነው፤›› በማለት፣ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ለለውጡ መሰናክል ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ይኖራቸዋል ብሎ እንደማያምን አስታውቋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች እየታየ ያለው የዜጎች አሰቃቂ ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ከአገርና ከአኅጉር አልፎ ዓለምን እያሳሳበ የሚገኝ አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት ነው፤›› በማለት፣ ‹‹አሮጌውን ነገር በአዲስ ለመተካት በሚደረግ ትግል መፋተጉ አይቀሬ ነው፤›› ሲል ችግሮቹ በለውጡ ምክንያት የተፈጠሩ ፍትጊያዎች ውጤት ሊሆኑ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡  

‹‹በአሁኑ ጊዜ የለውጥ ኃይሎችና የለውጥ ሐሳቦች አሸናፊ ሆነው መውጣታቸውና የሽግግር ሒደቱም ሆነ ለውጡ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱ መልካም ዜና ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን ለማርገብና አገርና ሕዝብን ለማረጋጋት ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመላ አገሪቱ በየወረዳው ሕዝባዊ ውይይት ጀምሯል፤›› በማለት፣ ፓርቲው ለውጡን ለመደገፍ የበኩሉን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡

ስለሆነም በግለሰብም ሆነ በቡድን በመንቀሳቀስ ዜጎችን ከሰላማዊ ኑሯቸው የሚያፈናቅሉና ሰላምን የሚያደፈርሱ ወንጀለኞችን አጥብቆ እንደሚያወግዝ፣ መንግሥትም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ከምንጊዜም በላይ እንዲወጣና አስተማሪ የሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድና ሁሉን አቀፍ ውይይት በአስቸኳይ እንዲጀመር፣ መንግሥትም ይህንን በማመቻችት ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት እንዲመጣ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...