Saturday, September 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ውዥንብሮች ትርምስ እየፈጠሩ አገር አይታመስ!

ፈጣን፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የመረጃ ልውውጦች ባለመኖራቸው ምክንያት ግልጽነት የጎደላቸው በርካታ ድርጊቶች ይስተዋላሉ፡፡ አንድ ብሔራዊ ጉዳይ ሲያጋጥም በቀጥታ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል በፍጥነት መረጃ ስለማይሰጥ፣ አገር ምድሩ በአሉባልታና በመሠረተ ቢስ ወሬዎች ይጥለቀለቃል፡፡ በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ከመቼውም ጊዜ በላይ በበረታበት በዚህ ዘመን፣ አንዳች ጉዳይ ሲከሰት መንግሥት ትክክለኛውን መረጃ በፍጥነት ካልለቀቀ ከባድ ኪሳራ ያስከትላል፡፡ የመንግሥት የተለመደ የአዝጋሚነት ባህሪ ግን ብዙ ጉዳቶች እያደረሰ ነው፡፡ በተለያዩ ሥፍራዎች ግጭቶች ሲያጋጥሙ ወይም በሕዝብ ደኅንነት ላይ አደጋ ሲጋረጥ የመንግሥት መረጃ ዘግይቶ ስለሚወጣ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በስህተት ወይም ሆን ተብለው ለሚለቀቁ ሐሰተኛ ወሬዎች ያጋልጣል፡፡ ይህም በተለያዩ ጊዜያት ተከስቷል፡፡ ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ነው ሲባል የሕዝብ የማወቅ ፍላጎትም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህ ግንዛቤ ደግሞ መረጃ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ግልጽ ያደርጋል፡፡ መረጃ የሌለው ማኅበረሰብ የውዥንብር ሰለባ ይሆናል፡፡

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማናገር አራት ኪሎ የሚገኘው የመንግሥት መቀመጫ ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው ድንገት ተከሰቱ በተባሉ ወታደሮች ምክንያት የተፈጠረው ትርምስ አይዘነጋም፡፡ ወታደሮቹ አራት ኪሎ አካባቢ ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው በብዛት ሲታዩና ወደ አካባቢው የሚወስዱ መንገዶች ሲዘጋጉ፣ በሕዝቡ ውስጥ የተፈጠረው ሥጋትና ጭንቀት ከበድ ያለ ነበር፡፡ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ጀምሮ የነገሠው ውጥረት በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የተለያዩ ውዥንብሮች እንዲሠራጩ ምክንያት ከመሆኑም በላይ፣ በወቅቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እየተከናወነ ሳይሆን አይቀርም የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደረስ አሉታዊ ሚና ተጫውቷል፡፡ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ምን እየተከናወነ እንደሆነ የሚገልጽ መንግሥታዊ አካል በመጥፋቱም፣ ብዙዎች ሥራቸውን አቁመው ወደ ቤታቸው ለመሄድ ተገደዋል፡፡ በትክክል ምን እየተከናወነ እንደሆነ የሚናገር ስላልነበር በርካታ ወገኖችም ድንጋጤ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ይባስ ብሎ ቀትር ላይ ኢንተርኔት ሲዘጋ ደግሞ የተፈጠረው ውዥንብር ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ ይህ ክስተት ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም፡፡

መረጃ በመጥፋቱ ምክንያት ብቻ በርካታ አሉባልታዎችና ሐሰተኛ ወሬዎች ከተደላደሉ በኋላ፣ መንግሥት ዘግይቶ መረጃ ሲለቅ ተዓማኒነቱ የወረደ ይሆናል፡፡ የዚያን ቀን ምሽት በጣም ከዘገየ በኋላ በዕለቱ የተከሰተው ጉዳይ በድምፅና በምሥል ሲቀርብ ብዙዎች ለማመን ተቸግረዋል፡፡ አንዳንዶች የተነገረውን መረጃ እንደ ድራማ ሲቆጥሩት፣ ሌሎች ደግሞ ከዚህ ድራማ ጀርባ ሌላ የተደበቀ ክስተት እንዳለ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተፈጠረውን ሁኔታ በዝርዝር ቢያስረዱም፣ ከወታደሮቹ ጋር ከተወያዩ በኋላ አብረዋቸው ስፖርት ሲሠሩና ፎቶ ሲነሱ ቢታዩም፣ በዘገየው መረጃ ምክንያት የተለያዩ ተጓዳኝ ጉዳዮች ሲወሩ ሰንብተዋል፡፡ ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ መንግሥት ከማንም በፊት ቀድሞ ትክክለኛውን መረጃ መልቀቅ ሲገባው፣ ማኅበራዊ ሚዲያውን መውቀሱ ነው፡፡ የመንግሥት የሚመለከተው አካል በፍጥነት ወጣ ብሎ ትክክለኛው መረጃ ቢለቅ እኮ፣ የማኅበራዊው ሚዲያ እንቶ ፈንቶ ትኩረት አያገኝም ነበር፡፡ ስለዚህ ጣትን ወደ ሌላ ከመቀሰር በፊት ራስን ማስተካከል መቅደም አለበት፡፡ የራስን ኃላፊነት ሳይወጡ ሌላውን ለመውቀስ መሯሯጥ ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝቡ በከባድ ጭንቀት ውስጥ ሆኖ ሠራዊቱ ውስጥ ሥርዓተ አልበኝነት ተፈጥሮ ነው? የደኅንነት ተቋማት ውስጥ ክፍተት ወይም አሻጥር አለ? ወይስ በአገሪቱ ውስጥ ከሕዝብ የተደበቀ የማይታወቅ ሚስጥር አለ? ወዘተ. እያለ ሲወዛገብ ወጣ ተብሎ ትክክለኛውን መረጃ የማይሰጥ ከሆነ አሉባልታ ቢናፈስ ምን ይገርማል? ይህ ጉዳይ በትኩረት ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ከበፊት ጀምሮ የመንግሥት ትልቁ ድክመት ጠንካራ የቃል አቀባይ ተቋም ማጣት ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አንድ እክል ሲያጋጥም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መረጃ ፈላጊ፣ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃንና ራሱ መንግሥት ጭምር በእጅጉ ሲቸገሩ ይስተዋላሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የፓርላማ አባላትና ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ በመረጃ ዕጦት ግራ ሲጋቡ በተደጋጋሚ ያጋጥማል፡፡ በዚህ መሀል ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ የመሸጉ ኃይሎች፣ አጋጣሚውን ለሚፈልጉት ዓላማ ይጠቀሙበታል፡፡ በተደጋጋሚ ለመታዘብ እንደተቻለው ግጭት ለመቀስቀስ ወይም በተለያዩ ወገኖች ላይ ዘመቻ ለማስከፈት፣ እነዚህ ኃይሎች የመረጃ ክፍተትን በሚገባ ተጠቅመውበታል፡፡ የተጣመሙና ምልዑነት የሚጎድላቸው ሐሰተኛ መረጃዎች በመልቀቅ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት፣ ለአገር አንጡራ ሀብት ውድመትና አለመረጋጋት አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አገር የሚያስተዳድር መንግሥትን ውሎና አዳር በተመለከተ ለሕዝብ መቅረብ ያለበት መረጃ ወቅታዊና በሀቅ ላይ የተመሠረተ ካልሆነ፣ በሚፈበረኩ ሐሰተኛ መረጃዎች ምክንያት አገር ይተራመሳል፡፡ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ይቃወሳል፡፡

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ባለፉት ስድስት ወራት የመንግሥት የሥራ እንቅስቃሴዎች፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሕዝብ በግልጽ መታየት መጀመራቸው ነው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያደረጓቸው ጉዞዎችና ውይይቶች ሕዝብ ዘንድ በስፋት መድረስ ችለዋል፡፡ ነገር ግን ለሕዝብ ግልጽ ያልሆኑና ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች እንዳሉ ደግሞ መዘንጋት የለበትም፡፡ የትጥቅ ትግል አቁመው ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ከተመለሱ፣ ነገር ግን ቅድመ ሁኔታ ማቅረብ ከሚፈልጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የተደረጉ ድርድሮችና ስምምነቶች ምን እንደሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ ከኤርትራ መንግሥት ጋር የተደረሰባቸው ስምምነቶችንና ወደፊት የሚደረጉ ስምምነቶችን አስመልክቶ ግልጽ መሆን የሚገባቸው ጉዳዮች ሊታሰብባቸው ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት ግልጽነት የጎደላቸው ድርጊቶች ያስከፈሉት መስዋዕትነትና ከባድ ጥፋቶች ዳግም ማጋጠም የለባቸውም፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች ውስጥ ለትርጉምና ለውዥንብር የሚዳርጉ ነገሮች፣ በግልጽነትና በኃላፊነት መንገድ መጥራት አለባቸው፡፡ የመንግሥት አንዱና ትልቁ ኃላፊነትም አሠራሩን ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት ማረጋገጥ ነው፡፡ ውዥንብር አገር ያተራምሳል፡፡

ይህ ዘመን ለመረጃ ትልቅ ግምት በመስጠቱ ቴክኖሎጂውም በጣም የተራቀቀ ነው፡፡ ከግለሰብ አንስቶ እስከ መንግሥት ድረስ ይብዛም ይነስም የቴክኖሎጂው ትሩፋት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ቴክኖሎጂ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ በዘመነበት በዚህ ጊዜ፣ የሚተላለፉ መረጃዎች የተጣሩና አስተማማኝ ካልሆኑ የሚከተለው ቀውስ ነው፡፡ አገር ከሚያስተዳድረው መንግሥት ጀምሮ በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚስተዋለው ችግር፣ ውዥንብር ለሚፈጥሩ አሉባልታዎች በቀላሉ መጋለጥ ነው፡፡ ከአንድ ሥፍራ የተለቀቀ መረጃ ሲኖር ኅብረተሰቡ የተዓማኒነቱን ደረጃ የማረጋገጥ ኃላፊነት ሲኖርበት፣ መንግሥት ደግሞ በግልጽነት ቀልጠፍ ብሎ ትክክለኛውን መረጃ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ግርድፍ መረጃ ሲቀርብ መቼ? የት? ለምን? እንዴት? ወዘተ. በማለት መጠየቅ የተጣራ መረጃ ለማግኘት የሚረዳ ቢሆንም፣ መንግሥት ደግሞ በተለይ ለብሔራዊ ጉዳዮች ትልቅ ግምት በመስጠት ተቋማዊ ጥንካሬውን ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡ ሕዝብ ለውጡን ደግፎ አገሩ ወደ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት እንድትጓዝ ታጥቆ ሲነሳ፣ መንግሥት በበኩሉ ለውጡን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሊያደናቅፉ የሚችሉ ሐሰተኛ መረጃዎችን ቀድሞ ማምከን አለበት፡፡ ነገር ከተበላሸ በኋላ ጣት መጠቋቆም ፋይዳ የለውም፡፡ በተለይ የፀጥታ ኃይሎች ከሚጠበቅባቸው ከፍተኛ ዲሲፕሊን አፈንግጠው የዕዝ ጠገግ (Chain of Command) የሌለ ይመስል ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽሙ፣ ትክክለኛ መረጃ ከምንጩ ካልፈለቀ አደጋ ያስከትላል፡፡ ሕግና ሥርዓት እያስከበሩ ለሕዝብ መረጃ መስጠት ስለሚጠቅም፣ በውዥንብሮች ምክንያት ትርምስ እየተፈጠረ አገር አይታመስ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...