Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረቡት የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው ተገለጸ

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ያቀረቡት የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው ተገለጸ

ቀን:

ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ካልተወያየን በማለት ቤተ መንግሥት የገቡት የመከላከያ ሠራዊት ኮማንዶዎች፣ በፈጸሙት ድርጊት ምክንያት የሕግ ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው ተገለጸ፡፡ ወታደሮቹ ቡራዩ አካባቢ የተሰጣቸውን ፀጥታ የማስከበር ግዳጅ ከፈጸሙ በኋላ ነበር ወደ ቤተ መንግሥት ያቀኑት፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ሪፖርተር በስልክ ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ወታደሮቹ ከግዳጃችን ከተመለስን ሁለተኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማግኘት ዕድል ስለሌለን፣ አጋጣሚውን ተጠቅመን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማግኘት አለብን በማለት ነው ተያይዘው የሄዱት፤›› ሲሉ አስረድተው፣ ‹‹አንደኛውና ትልቁ ነገር በዚህ ድርጊት ላይ ከተሳተፉት አካላት ጋር ሕገ መንግሥት እንደተጣሰ፣ አካሄዳቸው ስህተት እንደሆነና በዚህም ምክያት እንደተፀፀቱ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ ድርጊቱ ስህተት ነው፡፡ በዚህ አግባብ መሄድ ለአገርም ሆነ ለተመልካችና ለኅብረተሰቡ ተገቢ አይደለም፡፡ በዚያ መንገድ መሄድ አልነበረብንም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፡፡ ሆኖም ለወደፊት በዝርዝር እየታየ ለምንድነው እዚህ ደረጃ ላይ የተደረሰው? በወቅቱ እዚህ ደረጃ ላይ ከመደረሱ በፊት በቅርበት ያለው አመራር እንዴት አላየም? ለሌላውስ እንዴት አላሳወቀም? የሚሉት ነገሮች ደግሞ በቀጣይ ይታያሉ፤›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያና በቡራዩ አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከጦላይ፣ ከሶማሌ ክልልና ከተለያዩ ሥፍራዎች እንደመጡ የተነገረላቸው ኮማንዶዎቹ፣ ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደ ጦር ሠፈራቸው እየተመለሱ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማግኘት ወደ ቤተ መንግሥት ከማቅናታቸው በፊት፣ ከግዳጅ ሥፍራቸው ሳይንቀሳቀሱ ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ሲያነሱ እንደነበር ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ወታደሮቹ ከቤተ መንግሥት ከተሸኙ በኋላ ከሚኒስትሩና ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኰንን ጋር ለሁለት ቀናት ስብሰባ ማድረጋቸውን፣ በድርጊታቸው ተፀፅተው ይቅርታ መጠየቃቸውንና ይኼንንም የሚያመለክት የአቋም መግለጫ ማውጣታቸው ተገልጿል፡፡

‹‹የእነሱን ጥያቄዎች በዝርዝር ሰምተናል፡፡ በአብዛኛው በተቋሙ የሚታወቁ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የአቅርቦቶች በጊዜ አለመቅረብ፣ የኑሮ አለመመቸት፣ የድጎማ ማነስና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በተቋም ደረጃ መታየት ስለሚችሉ ወደዚያ መሄድ እንደሌለባቸውና ይህ ደግሞ ስህተት እንደሆነ ተማምነናል፤›› ያሉት አቶ ሞቱማ፣ ‹‹ወደ ቤተ መንግሥት የሄዱት ለጥያቄ ነው እንጂ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደተወራው መንግሥት ለመገልበጥ ወይም ለሌላ ነገር አልነበረም፡፡ ነገር ግን አካሄዳቸው ስህተት ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና ይህ ክስተት ሲፈጠር አራት ኪሎ አካባቢ የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ወታደሮቹ በሥፍራው እንደተበተኑ መንገድ መዘጋቱንና ተሽከርካሪዎች ወደ ኋላ መመለስም ሆነ ወደ ፊት መሄድ እንዳይችሉ ሆነው መቆማቸውን፣ ከወታደሮቹ መሀል የተሽከርካሪዎችን ኮፈን እየመቱ እግረኞችን ሲገፈትሩ ነበር፡፡ የዓይን እማኞች ወታደሮቹ በወቅቱ ዓላማቸው ግልጽ ስላልነበር አስደንጋጭ እንደነበር አክለዋል፡፡

መንግሥትም ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከሆነ የማስተካከያ ዕርምጃ ለመውሰድ አፋጣኝ ጥንቃቄ ማድረጉን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ቢሮና የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ጥብቅ ጥበቃ እንዲደረግላቸው መደረጉን ምንጮች አክለዋል፡፡

ምንም እንኳን የትኞቹ ሥፍራዎች የጥንቃቄ ትኩረት እንደነበሩ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ ባይገልጹም፣ ‹‹የታጠቀ ኃይል በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲገባ አስፈላጊው ክትትል ሲደረግ ነበር፡፡ ችግር እንኳን ቢፈጠር ቶሎ ማስቀረት በሚቻልበት ደረጃ ዝግጅቶች በየቦታው ሲደረጉ ነበር፡፡ ይህም የማስተካከያ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የተደረገ ነው፡፡ ሁልጊዜ ዝግጁነት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎቹ ጥያቄ ነው ያቀረቡት፡፡ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ካልተኬደና የሚፈልጉት ነገር ካልተገኘ ምንድነው የሚከተለው የሚለውን ማሰብ አስፈላጊ ነበር የሚሆነው፤›› ሲሉ የተደረገውን ጥንቃቄ አረጋግጠዋል፡፡

የሠራዊቱ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኰንን፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸው አይዘነጋም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ ወታደሮቹ ዓላማቸው ከእሳቸው ጋር መገናኘት ብቻ እንደነበርና አግኝተው ማወያየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የፌስቡክ ገጻቸው ላይ፣ የሠራዊቱ አባላት እንደ ማንኛውም ዜጋ የመደመጥ መብት እንዳላቸው በመጠቆም ጥያቄያቸውን ማዳመጣቸውን አስፍረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ክስተት በመከላከያ ሠራዊት የዕዝ ሰንሰለት መላላቱን ወይም መበጠሱን የሚያመላክት ላለመሆኑ ምንም ማስተማመኛ አለ ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ ቀድሞ አለመታወቁና ወዲያው ደግሞ አስፈላጊው ዕርምጃ አለመወሰዱ የደኅንነት ሥጋት ይፈጥራል ሲሉም የሚተቹ አሉ፡፡

አቶ ሞቱማ ይኼንን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹እኛ ዘንድ ከዚያ በፊት የታወቀ ነገር አልነበረም፡፡ በዚያ ደረጃ ወደዚያ ይሄዳሉ በማለት የቅርብ አመራሮችም በያሉበት የተገነዘቡበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይህ የሚገመገም ነው፡፡ ለምን እስከዚያ ድረስ ተሄደ? ለምን ቀድሞ ባለበት ማረም አልተቻለም? ለሚለው ጉዳይ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ የቅርብ አዛዦችም ከወታደሮቹ ጋር አብረው እንደነበሩ አክለዋል፡፡

ወታደሮቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሲገቡ ‹የምንወደውን ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ለማናገር ስለመጣን ትጥቅ መፍታት የለብንም› በማለት ትጥቅ ላለመፍታት አንገራግረው እንደነበረ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አቶ ዘይኑ ጀማል በዕለቱ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር፡፡ ይሁንና የቤተ መንግሥቱ አሠራር በመሆኑ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ መግባባት ላይ መደረሱንና ከዚያም ወደ ውይይት መገባቱን አስታውቀዋል፡፡

ወታደሮቹ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር ከነበራቸው ቆይታ በኋላ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ‹ፑሽ አፕ› መሥራታቸው በምሥል ተደግፎ ተዘግቧል፡፡ የእራት ግብዣ ተደርጎላቸው መሸኘታቸውም መገለጹ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...