አራተኛውን የወጣቶች ኦሊምፒክ አፍሪካዊቷ ሴኔጋል እንድታሰናዳ መመረጧ ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡ በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ሦስተኛ የወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ በተደረገው ምርጫ ሴኔጋል ያሸነፈችው ከናይጄሪያና ቱኒዝያ ጋር ተወዳድራ ነው፡፡
የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን እስካሁን ለማዘጋጀት ያልታደለችው አፍሪካ ‹‹ጊዜ ለአፍሪካ›› በሚል መሪ ቃል ነበር የኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ የሴኔጋልን አዘጋጅነት ያበሰሩት፡፡
ኮሚቴው በቦነስ አይረስ ባካሄደው 133ኛው ጉባዔ ላይ ከተወዳዳሪ አገሮች መካከል መመዘኛውን ማሟላትዋ ተረጋግጦ ለአዘጋጅነት ኃላፊነት የተሰጣት ሴኔጋል፣ በወቅታዊ ሁኔታዋ የተረጋጋችና የተለያዩ የስፖርት መሠረተ ልማቶች እያከናወነች ያለች፣ ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች ምቹ የስፖርት ማዕከሎች መኖራቸው ተመራጭ አድርጓታል፡፡
አፍሪካ የወጣቶች የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ማዘጋጀት መቻሏ ለሌሎችም ዝግጅቶች በር ከፋች እንደሚሆንላት እምነታቸው መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
የ2010 የዓለም ዋንጫን ማሰናዳት የቻለችውና በከፍተኛ የቱሪስት መስቦችም የምትታወቅ ደቡብ አፍሪካ ትልቅ ማሳያ እንደሆነችም ተገልጿል፡፡
የ2022 የወጣቶች ኦሊምፒክ ለማሰናዳት ሴኔጋል ከወዲሁ ዝግጅት መጀመሯንና ስታዲየሞችና የስፖርት ማዕከላትን ለመገንባትና ለማደስ ከ150 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋታል ተብሏል፡፡
በቀጣይም እንደ አልጄሪያ፣ ቱኒዝያ፣ ሞሮኮና ግብፅ ፓራሊምፒክን ለማሰናዳት ቅድመ ግምት እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡