Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አዲስ አበባችንን እየታዘባችኋት ነው? እስቲ የዛሬ 15 ዓመት አካባቢ ወደኋላ በምናብ ሄዳችሁ አዲስ አበባን አስታውሱ፡፡ እጅግ በጣም የሚገርም ለውጥ ታያላችሁ፡፡ በከተማችን በርካታ አዳዲስ መንደሮች ተመሥርተዋል፡፡ ውብ በሆኑ የመኖሪያ ቤቶችና መንገዶች የታጀቡት እነዚህ መንደሮች ወደፊት ልክ እንደ ኒውዴልሂና ካይሮ ከተማዋን ‹‹አዲሷና አሮጌዋ›› አዲስ አበባ ማሰኘታቸው አይቀርም፡፡ በተለይ የከተማዋን ምሥራቅ፣ ሰሜናዊ ምሥራቅና ደቡባዊ አቅጣጫ በአንክሮ የተመለከተ አባባሌን በሚገባ ይረዳዋል፡፡ የከተማዋ ሰሜናዊ ምዕራብና ምዕራባዊ አቅጣጫዎች አሮጌውን ከተማ ታቅፈው ቢቀመጡም፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እዚህም ፈጣን በሆነ ሁኔታ እየተከናወኑ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከዛሬ አሥር ዓመት በፊት ከአገር የወጣ ሰው ደግሞ ይኼንን በሚገባ ይገነዘበዋል፡፡ እኛ ነዋሪዎችም ጭምር፡፡

አዲስ አበባ በአስገራሚ ፍጥነት በለውጥ ሒደት ውስጥ ብትሆንም፣ ይኼንን ለውጥ በእጅጉ የሚፈታተኑ ችግሮች ግን በስፋት እየታዩ ነው፡፡ ለሳምንቱ ገጠመኜ መነሻ የሆነኝም ይኼው ጉዳይ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ስትዘዋወሩ በአስደንጋጭ ሁኔታ የለማኝ ሠራዊት ይከባችኋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደ እሳት ከሚጋረፈው የኑሮ ውድነት ጋር እየታገሉ መከራቸውን ሲያዩ፣ የለማኝ ሠራዊት ደግሞ ከተማዋን እያተራመሳት ነው፡፡ በትራፊክ መብራቶች፣ በካፌዎችና ሬስቶራንቶች ደጃፍ፣ በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ፣ በታክሲና በአውቶቡስ መሳፈርያ ቦታዎች፣ ወዘተ. ልመና የሥራ ያህል ተበራክቷል፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ ከሚገቡት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ መተዳደሪያቸው ልመና ነው፡፡ በማደግ ላይ ያለችው አዲስ አበባ ደግሞ የለማኞች መናኸሪያ እየሆነች ነው፡፡ 

እኔ በምሠራበት ቦሌ አካባቢ ከመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ግራና ቀኝ ይዞ ጫፍ ድረስ ልመና የአካባቢውን ማኅበረሰብ እያስመረረ ነው፡፡ ሕፃናት ልጆች ከታቀፈች አራስ ጀምሮ ድክ ድክ የሚሉ ታዳጊዎች ድረስ አካባቢው በልመና ተጨናንቋል፡፡ ሕፃናቱ በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎችን እጅና ልብስ እየጎተቱ ከማስቸገራቸውም በላይ፣ ከዚህ በፊት ደህና ኑሮ የሚኖሩ የሚመስሉ ሰዎች ሳይቀሩ እጃቸውን ለልመና ይዘረጋሉ፡፡ በእዚህ አካባቢ የውጭ ዜጎች ሳይቀሩ በለማኞቹ የሚደርስባቸው ወከባ ስለሚያስመርራቸው፣ የሚራመዱት ከሩጫ ባልተናነሰ ሁኔታ በፍጥነት ነው፡፡ ብዙዎችም ከለማኞች ጋር ሲጣሉ ይታያሉ፡፡ 

- Advertisement -

   በእዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ምሬት የሚሰማት ጓደኛዬ፣ ‹‹መንግሥት ይኼንን ጉድ እያየ ለምን ዝም ይላል?›› በማለት ሁሌም በብስጭት ትናገራለች፡፡ በአካባቢው ካሉ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማና የሚመለከታቸው መሥርያ ቤቶች ጀምሮ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ያሉ ተቋማት የአገር ገጽታ በጎዳና ላይ ልመና ሲበላሽ እንዴት ዝም ይላሉ በማለትም ትጠይቃለች፡፡ በልመና የተሰማሩት ዜጎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች መጥተው ጎዳና ላይ ፈሰው፣ የተላላፊን ሰላም ሲያደፈርሱ የሚመለከተው አካል ለምን አይንቀሳቀስም? በልመና ላይ የተሰማሩ ዜጎችን በማሰባሰብ ጉልበት ያላቸውን ወደ ሥራ፣ ሕፃናቱን ወደ ትምህርት፣ ታማሚዎችን ወደ ሕክምና ለመውሰድ ለምን መላ አይመታም? ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን፣ ባለሀብቶችን፣ ዜጎችንና የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ተቋማትን በማስተባበር አንድ ጠንካራ ፋውንዴሽን መመሥረት ለምን ያቅታል? ልመና ገጽታን እያበላሸ ስለአገር ክብር ማውራት ከንቱ ነው፡፡

በእዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ መነሻ ከአሁን በፊት በልመና የተሰማሩ ወገኖችን በዘለቄታዊነት አቋቁማለሁ ብሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮችን ሲሰበስብ ስለነበር አንድ ድርጅት ጉዳይ፣ እኔና ጓደኛዬ ያውቃሉ የሚባሉ ሰዎችን ብንጠይቅ የት እንዳለ እንደማያውቁ ነገሩን፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጅት በግለሰቦች ተመሥርቶ በመንግሥት ድጋፍ ከፍተኛ ገንዘብ በማሰባሰብ ልመናን መቀነስ ካልቻለ፣ የመቋቋሙ ፋይዳ ምን ይሆን? ግለሰቦች ተሰባስበው ይህን ያህል ገንዘብ በተረጂዎች ስም መሰብሰብ ከቻሉ፣ መንግሥታዊ ተቋማት በተለይ የሚመለከታቸው ምን እየሠሩ ነው? ልመና ከዜጎች አልፎ የውጭ እንግዶችን ሳይቀር እንዲህ ምርር ሲያደርግ ቁጭ ብሎ ማየት ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው?

በልመና ስም ገንዘብ በማሰባሰብ ሚሊዮኖችን ሲያፍስ የነበረው ድርጅት የት እንዳለ ባናውቅም አንድ ነገር ግን ተገንዝበናል፡፡ ለዚህ ድርጅት ቅርበት የነበራት አንዲት የምናውቃት ሴት እንደነገረችን፣ ድርጅቱ በዘላቂነት አቋቁማለሁ ብሎ በልመና የተሰማሩ ወገኖችን በአውቶቡስ አጓጉዞ ወደ ቀዬአቸው ከመለሳቸው በኋላ ምንም መቋቋሚያ ስለማያገኙ በቶሎ ይመለሳሉ፡፡ ችግሩ የእነሱ መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ በልመናቸው ወቅት የቋጠሩትን ገንዘብ ያዩ ሌሎች አርሶ አደር ወንዶችና ሴቶች ጎጆአቸውን ዘግተው ከእነ ልጆቻቸው ይፈልሳሉ ስትለን ደነገጥን፡፡ ‹‹ወደ አንድ አነስተኛ መንደር አሥር ለማኞች ሲሸኙ፣ ቢያንስ አሥር እጥፍ የሚሆኑ ከዚያ አካባቢ ነቅለው ይመጣሉ፤›› ስትለን ዘገነነን፡፡ ጓደኛዬ ተናዳ ልጅቷን፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ነው እንዴ በዘላቂነት ማቋቋም የሚባለው?›› ስትላት፣ ያችኛዋም፣ ‹‹ውስጡን የሚያውቁት የሚሉት ሌላ ነው፤›› አለች፡፡ ‹‹ምን ይላሉ?›› ስትላት፣ ‹‹ልመናን እንደ አሜባ ማራባት፤›› ብላ ስትመልስ ሁላችንም አንገታችንን ደፍተን ለደቂቃዎች ተከዝን፡፡ ‹‹የማያፍሩ ሌሎችን ያሳፍራሉ›› ማለት ይኼ አይደል?

(ዘውድነሽ አስፋው፣ ከገርጂ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...