Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክፓርላማን ፓርላማ ለማድረግ የሚቀሩ ሕግጋትና ተግባራት

ፓርላማን ፓርላማ ለማድረግ የሚቀሩ ሕግጋትና ተግባራት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ድረስ ያሉት ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የተፈጠሩበትን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ቢገመገሙ አፅም እንጂ ሥጋ አላቸው ሊባሉ የሚችሉበት ደረጃ አይደሉም፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና ካላቸው ተቋማት አንዱ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡

ዘመናዊ መንግሥት ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ ይኖሩታል፡፡ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው ተለያይቶ፣ አንዱ ሌላውን ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ሦስት የመንግሥት አካላት በተለያዩ ዕርከኖችም ላይ ይገኛሉ፡፡ አንድ ዕርከን ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ አይደሉም፡፡

 በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ከእነዚህ ከሦስት የመንግሥት ክፍሎች መካከል ስለሕግ አውጪ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ፓርላማው ዓመታዊ ሥራን ባለፈው ሰኞ ጀምሯል፡፡ ሥራውንም እንደተለመደው በሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር አኃዱ ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በሌሎች ዕርከኖች ላይ የሚገኙ ሕግ አውጪ ምክር ቤቶች የተፈጠሩበትም ተልዕኮ እየተወጡ ነው ማለት አይቻልም፡፡

ስለሆነም እነዚህ ምክር ቤቶች የእውነት ምክር ቤቶች መሆን ባይችሉ እንኳን ቀስ በቀስ እየሆኑ እንዲሄዱ በአተገባበርም በሕግም መስተካከል ያለባቸውን የተወሰኑ ነጥቦች መጠቆም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

ሚናቸው በጥቅሉ

የፓርላሜንታዊ አሠራርን በሚከተሉ አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ በኢትዮጵም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ጥቅል መርሆችን ሥራ ላይ ለማዋል የሚረዱ ሕጎችን ያፀድቃል፡፡ ፖሊሲዎችን ያወጣል፡፡ በጀት ያፀድቃል፡፡ የሕግ አስፈጻሚውም ምክር ቤቱ ባወጣቸው ሕግጋትና ፖሊሲዎች መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ስለሚጠበቅ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ እነዚህም በትክክል ስለመፈጸማቸው ክትትል ማድረግ ዓበይት ተግባራቱ ናቸው፡፡

ፕሬዚዳንት በፓርላማ መክፈቻ

ሕግ አውጪ የሚያወጣቸውን ሕግጋት ከተለያዩ አካላት ሊመነጩ ይችላሉ፡፡ መውጣት ያለባቸውን ሕግጋትም የተለያዩ አካላት ሊያሳስቧቸው ይችላሉ፡፡ ሕግ እንዲወጣ ሊያሳስቡ ከሚችሉት አንዱ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዚዳንት) ናቸው፡፡ ይህ ዓይነት የሕግ ይውጣ ማሳሰቢያ ፓርላማ ዓመታዊ ሥራውን ሲጀምር በሚደረገው የመክፈቻ ንግግር ላይ ይቀርባል፡፡

ምክር ቤቶች ሥራ ሲጀምሩ ፕሬዚዳንታዊ የመክፈቻ ንግግር ማድረግ በፓርላሜንታዊ አገሮች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ የፖለቲካና የመራቂ (Ceremonial) ሥልጣንን ፕሬዚዳንት (ንግሥት ወይም ንጉሥ) እና ጠቅላይ ሚኒስትር በሚይዙበት አገሮች ፓርላማን ሥራ ለማስጀመር የአገሪቱ መንግሥት ምን ምን ማድረግ እንዳለበት ጠቅለል ያለ አቅጣጫን ይፋ ይደረግበታል፡፡

አንድን አገር (State) የእናት አገር ከሚያሰኟት መሥፈርቶች አንዱ (የታወቀ ወሰን፣ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ውል የመፈጸም ችሎታ) መንግሥት (Government) ያለ መሆኑ ነው፡፡ አገሪቱን በጅምላነቷ የሚወክል ፕሬዚዳንቱ ይሆንና መስተዳደሩን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የአገሪቱ ወኪል እያስተዳደራት ያለ ገዥ ፓርቲ በፓርላማ ዘመን ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይገልጻል፡፡ ስለሆነም ብዙ ጊዜ መንግሥቴ ወይም መንግሥታችን እንዲህና እንዲያ ያደርጋል እያሉ መናገር የተለመደ ነው፡፡ መንግሥት ሲባል እንደሚታወቀው ሕግ አጪውም፣ አስፈጻሚም፣ ተርጓሚውንም ስለሚይዝ መልዕክቱ ለሦስቱም ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሕግ አውጪ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ማድረግ ያለበትን ያሳውቃል፡፡ ለአገሪቱ ምን ምን ሕጎች መውጣት እንዳለባቸው ያሳውቃል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም አገራችን የሉዓላዊነቷ ወኪል የሆኑት ፕሬዚዳንት (ርዕሰ ብሔር) ሕግ እንዲወጣ የሚያደርጉትን ንግግር የሚመለከት ነው፡፡

እንደ ወትሮው ሁሉ ፕሬዚዳንቱ ዓመትም መውጣት ካለባቸው አዋጆች አድርገዋል፡፡ በእርግጥ እንደሚወጡ የጠቀሷቸው አስቀድሞ ማሻሻያ እየተደረገባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አንድ መሠረታዊ ጥያቄ አለ፡፡ ይኼውም የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ንግግርን ፓርላማው ካፀደቀው በኋላ ተፈጻሚ ባይሆን የሚኖረው ውጤት ምንድን ነው? በሌላ አገላለጽ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ የተገለጹ ጉዳዮች ተፈጻሚነታቸውን በተመለከተ ምን የሕግ ማዕቀፍ አለ? የሚለው ነው፡፡

 ለነገሩ በቀድሞዎቹ ፕሬዚዳንቶች ንግግር ላይ የተካትተው ነገር ግን ሕግ ያልወጣላቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ለአብነት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ዘመን ‹‹ዓለም አቀፍ የግለሰብ ሕግ›› እና ‹‹የአስተዳደር ሕግ›› እንደሚወጣ ቢናገሩም ሕጎቹ እስካሁን አልወጡም፡፡ ባለፈው ዓመት የተናገሩት ሳይፈጸም በሚቀጥለው የመክፈቻ ንግግር ላይ በድጋሜ ስለሌለ ሕግ መውጣት መናገራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ባለፈው ዓመትም ሕግ እንዲወጣላቸው ፕሬዚዳንቱ ጥሪ ያቀረቡባቸው የምርጫ ሕግና የኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖረው ልዩ ጥቅምን የሚመለከቱ ሕጎች አልወጡም፡፡

ፕሬዚዳንቶቹም ይህንን ለመከታተል የሚችሉበትን የሕግ ማዕቀፍ የሚያወጣላቸው ይኼው ምክር ቤት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና ምክር ቤቱ ራሱ ላይ ግዴታ የሚጥል የቁጥጥርና ክትትል ሕግ እስካሁን አላወጣም፡፡ ምክር ቤቱ ባይፈልግ እንኳን ፕሬዚዳንቶቹም ረቂቅ ሕግ ማቅረብ ይገባቸው ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ እንዲወጣ ያሳሰቡትን ሕግ ፓርላማ ሳያወጣ በሚቀርበት ጊዜስ ምንድነው መፍትሔ? ፕሬዚዳንቱ ስለአስፈጻሚና ሕግ ተርጓሚ የተናገሩትን ሕግ አውጪ እየተከታተለ ሊያስፈጽም ይችላል፡፡ ሕግ አውጪው ራሱ ያልፈጸማቸውንስ ማን ይቆጣጠረው? ለመቆጣጠሪያ የሚሆን አስገዳጅ ሕግ ማውጣት የማን ሥልጣን ነው? የፓርላማ የራሱ ወይስ የፕሬዚዳንቱ?

በገቢር ሕግ የማያመነጭ ፓርላማ

ሕግ ለማውጣት የተለያዩ ሒደቶችን ማለፍ አለበት፡፡ የመጀመርያ ማመንጨት ነው፡፡ ሕግ እንዲወጣ የሚያነሳሳ ብሎም ረቂቅ የሚያቀርብ አካል ያስፈልጋል፡፡ ሕግ የማመንጨት መብት ወይም ሥልጣንን የማነው የሚለውን በምናይበት ጊዜ እንደየአገሮቹ የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡  

አሁን ባለው የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ሕግ ማመንጨት የሚችሉት መንግሥት (የሚኒስትሮች ምክር ቤት)፣ የምክር ቤት አባላት፣ የፓርላማ ኮሚቴዎች፣ የፓርላማ ቡድኖችና በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው ሌሎች አካላትንም እንደሚጨምር የምክር ቤቱ አሠራርና ሥነ ምግባር ደንብ ላይ ተገልጿል፡፡ እንደ ሕጉ የፓርላማ አባላትም፣ ኮሚቴዎችም ረቂቅ ማቅረብ ይችላሉ፡፡

ይሁን እንጂ እስካሁን ያለንን ልምድ ላጤነ ሰው ረቀቅ ሲያቀርብ የኖረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንጂ ሌሎቹ አይደሉም፡፡ አዲስ አዋጅም ይሁን ማሻሻያ የሚያቀርበው አስፈጻሚው ነው፡፡ የሕግ አውጪ ሚና የቀረበለትን ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ማፅደቅ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ፓርላማው በትክክል ሕግ ሲያወጣ ነበር ማለት አያስደፍርም፡፡ ሕጉን አመንጭቶ፣ ተወያይቶና አብላልቶ የማፅደቅ ተግባር አላከናወነም፡፡ ሲያከናውን የነበረው የቀረበለትን ረቀቅ ማፅደቅ (ማኅተም ማድረግ እንደማለት ነው) ብቻ ነው፡፡  

ፓርላማው ሕግ የሚያወጣው በአገሪቱ ያሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በመዳሰስ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ አሠራሮችን ለመዘርጋት ነው፡፡ የሚወጡት ሕግጋትም እንደ ሁኔታ የወንጀል አለበለዚያም የፍትሐ ብሔር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ችግሮቹን ለመቅረፍ አስቀድሞ ለመከላከል፣ የኅብረተሰቡን አኗኗር ለማሻሻልና ዋስትና ለማበጀት፣ የዜጎችን መብትና ግዴታ ለማሳወቅ፣ ወዘተ ነው፡፡  እንዲህ ዓይነት ይዘት ያላቸውን ሕግጋት በማውጣት አስፈጻሚ አካል ተግባራዊ እንዲያደርጋቸው ነው፡፡ ይሁን እንጂ እየሆነ ያለው አስፈጻሚው አካል መፈጸም የሚፈልገውን ራሱ አርቅቆ ለፓርላማ በማቅረብ ያስፀድቃል፡፡ መሆን የነበረበት ፓርላማው ሕግ አስፈጻሚው ምን መፈጸም እንዳለበት በዋናነት በራሱ ተነሳሽነት ችግሮችን አጥንቶ ሕግ አዘጋጅቶ መስጠት ሲገባው በተገላቢጦሽ አስፈጻሚው በምን መንገድ መፈጸም እንዳለበት ሕግ አዘጋጅቶ ያስፀድቃል፡፡ እዚህ ላይ አስፈጻሚው አካል ሕግ ማመንጨት የለበትም ማለት ሳይሆን፣ ይህ ተግባር በዋናነት የፓርላማው ነው ለማለት ነው፡፡

በፓርላሜንታዊ ሥርዓት የተወሰኑ የአስፈጻሚው አካል የሕግ አውጪም አባል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተለይ በዕውቀትም በአመራር ብቃትም የተሻሉት የፓርላማ አባል ሆነው ሳለ ሚኒስትር፣ ኮሚሽነርና ሌሎች ባለሥልጣንም ይሆናሉ፡፡ በፓርቲ አመራርነት ዝቅ ያሉ፣ በዕውቀትና በአመራር ብቃትም እንዲሁ መለስተኛ የሆኑት ደግሞ በቋሚነት ፓርላማው ውስጥ ብቻ ይቆያሉ፡፡ የኋላ ረድፈኞች (Back Benchers) በመሆን ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሚቀሩት የኋላ ረድፈኞችን ነው ሕግ ያወጡ ዘንድ የሚጠበቀው፡፡

የአገራችን የፓርላማ ሁኔታም እነዚህ የፓርላማ ቋሚ ተሠላፊ የሆኑ የኋላ ረድፈኞችን በተለያዩ አማካሪዎች ስለማይደገፉ፣ ከላይ እንደገለጽነው በዕውቀትና ክህሎትም የተሻሉት ስላልሆነ በራሳቸው ሕግ የማመንጨት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሕግ አመንጭቶ ረቀቅ ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን የዕውቀት፣ የቴክኒክና የፋይናንስ አቅም ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሳይኖሩ ሕግ አርቅቆ ማቅረብ አዳጋች መሆኑ አይቀርም፡፡

ሌላው የፓርላማ አባላት በራሳቸው ተነሳሽነት ረቂቅ የሚዘጋጀው ብዙ ጊዜ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ በሌለበት ፓርላማ በዚህ መንገድ ረቂቅ የሚቀርብበት አጋጣሚ ዝቅተኛ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ፓርላማችን እውነተኛ የፓርላማ ሚናውን በመወጣት ረገድ ፓርላማ ነው ሊባል የሚችል አለመሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ አስፈጻሚ የሚያቀርበው ረቀቅ ሕግ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ‹‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ›› እንዲሉ፡፡

ላለመቆጣጠሩ ተቆጣጣሪ የሌለ ፓርላማ

የሕግ አውጪው ክትትልና ቁጥጥር የሚመነጨው ያወጣቸው ሕጎች፣ ያፀደቃቸው ፖሊሲዎች በትክክል ሥራ ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ካለበት ኃላፊነት ነው፡፡ በሹመት ጊዜም ይሁንታውን የሚሰጣቸውና ቃለ መሃላ የሚያስገባቸው ባለሥልጣናት ግዴታቸውን ስለመወጣታቸው በቅርበት ለማረጋገጥ ነው፡፡

ሕግ አውጪው ባስቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ያልሠራን ሚኒስትር ወይም ሹመኛ፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ በዚሁ በኩል ዕርምጃ እንዲወሰድበት የማድረግ ሥልጣን እንዳለው ከላይ የተገለጸው ደንብ ይገልጻል፡፡ በዚህ ረገድ ዕርምጃ የተወሰደበት ባለሥልጣን ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ ባለፈው የፓርላማ ዘመን ማብቂያ ላይ እያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በ2011 የበጀት ዓመት መሥራት ያለበትን ከፓርላማው ጋር ውል እንዲዋዋል አድርገዋል፡፡ ይኼም ቢሆን የመነጨው ከሕግ አስፈጻሚው እንጂ ከፓርላማው (ከሕግ አውጪው) አይደለም፡፡ ለነገሩ በቅርቡ የሚታጠፉም፣ እንደ አዲስ የሚዋቀሩም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንደሚኖሩ ይፋ ስለተደረገ ቀሪ የሚሆኑም እንደ አዲስ የሚደረጉ ውሎችም ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ የሕግ አውጪው መውጣት የሚገባውን የቁጥጥርና ክትትል ኃላፊነት እየተወጣ ባለመሆኑ አስፈጻሚው አካል በዚህ መንገድ ተቆጣጠሩኝ በማለት ያቀረበው ጥሪ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን ወሳኝ ነው፡፡ በርካታ ፋይዳዎችም አሉት፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ላይ እንደተቀመጠው የክትትልና ቁጥጥር ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡ የመጀመርያው አስፈጻሚው አካል የሚያከናውናቸው ሥራዎች ሕግንና ሥርዓትን ተከትለው እየተፈጸሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አስቀድሞ ምክር ቤቱ ሥርዓት ማበጀት አለበት ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው የክትትልና የቁጥጥር ዓላማ ደግሞ፣ ፈጣን፣ ፍትሐዊ፣ ቀልጣፋና ዘላቂ ልማት መኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ መርሁ ይህ ቢሆንም ቅሉ በርካታ የልማት ተቋማት በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብ እየባከነ መሆኑን ለፓርላማው ለራሱ በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርቶች መቅረባቸው ይታወቃል፡፡ ይባስ ብሎም ምርት ሳይጀመሩ አገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ወለድ በመክፈል ላይ መሆኗን ፓርላማውም ጭምር ያውቃል፡፡ ፓርላማው ግን አይቆጣጠርም፡፡ በሌላ አገላለጽ ተቆጣጥሯል የሚያሰኝ ዕርምጃም አልወሰደም፡፡

 ሌላው ደግሞ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን እንዲሰፍን ማድረግ ነው፡፡ አስፈጻሚው ራሱ ያመነው በአገራችን የተከሰተው መጥፎ አስተዳደር ችግር አንዱ ነው፡፡ ለእዚህ ችግር በመፍትሔነት የተዘረጋው በአስፈጻሚው በራሱ በኩል ሲሆን፣ እሱም “በጥልቀት መታደስ” የሚል አሠራር ነው፡፡ ይህ ሲሆን ሕግ አውጪው የዘረጋው የቁጥጥርና ክትትል ዘዴና ሥርዓት ግን የለም፡፡

ፓርላማው መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሲባል ማቋቋም ያለበት ካለበት ተቋማት ውስጥ የዕንባ ጠባቂና  የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ተቋማት ሰብዓዊ መብትን ከማስፋፋትና ከማስጠበቅ፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረምና ለማስተካከል ሲባል የተቋቋሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ባለፉት ዓመታት የተከሰቱትን ችግሮች ከመቅረፍ ኳያ እምብዛም የጎላ ድርሻ ነበራቸው ማለት አይቻልም፡፡ ከሁለቱ ተቋማት በተጨማሪም፣ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ የሆነው የፌዴራሉ ኦዲተር ጄኔራል የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በርካታ መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ አያያዝና የግዥ ዝርክርክነት ለፓርላማው ሪፖርት ቢያቀርብም እዚህ ግባ የሚባል ዕርምጃዎች ግን ፓርላማው አልወሰደም፡፡

አራተኛው የክትትልና ቁጥጥር ዓላማ፣ የቡድንና የዜጎች መብትን ማስከበር ሲሆን፣ በደንቡ ላይ የተገለጸው የመጨረሻው ዓላማ ደግሞ በመንግሥት አካላት መካከል የተቀናጀ አሠራር ማስፈን ማስቻል ነው፡፡  በዚህ ረገድ እርስ በርስ የተቀናጀ የአሠራር ሥርዓት ከመዘርጋት ይልቅ በአስፈጻሚው የሚመራ አንድ ወጥ የመንግሥት አካል ሠፍኗል ማለት ነው የሚቀለው፡፡

ከላይ የተገለጹትን ዓላማዎች ለማሳካት ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውን ሊቆጣጠር የሚችልባቸው የተለያዩ ሥልቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የመጀመርያው ፓርቲያዊ ቁጥጥር ሲሆን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉበት ፓርላማ የገዥው ፓርቲ የሚፈጽማቸውን አስተዳደራዊ እንከኖችና ሕግን ያለማስፈጸም አድራጎቶችን የሚያጋልጡበትንና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረግበት አካሄድ ነው፡፡

ከፓርቲያዊ ቁጥጥር ውጭ ደግሞ በቋሚና ልዩ ኮሚቴዎች አማካይነት የሚደረጉ ቁጥጥሮችም መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከባለፉት ልምዶቹ መረዳት የሚቻለው ምክር ቤቱ በርካታ ተቋማት ያለባቸውን ችግር እንዲያስተካክሉ ማሳሰቢያ መስጠቱን ነው፡፡ የምክር ቤቱን ድረ ገጽ የጎበኘ ሰው ከሚያገኛቸው ዜናዎች ውስጥ በርካታዎቹ ለተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተሰጡ ማሳሰቢያዎችን ነው፡፡ ከማሳሰቢያ ያለፈ ዕርምጃ ሲወሰድ አልተስተዋለም፡፡

ሌላው የቁጥጥር ሥልት ሹመኞችን ጠርቶ በመጠየቅና ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ ነው፡፡ ሚኒስትሮቹ በምክር ቤቱ በመቅረብ ሪፖርት ሲያደርጉ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ የምክር ቤቱ አሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብም ለዚህ ሥርዓት ዘርግቷል፡፡  በመሆኑም ማንኛውም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊ በዓመት ቢያንስ አንድ ጊዜ ሪፖርት የማቅርብ ግዴታ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኮሚቴዎች ጥሪ ሪፖርት ሊቀርብ ይችላል፡፡ በዚህ መልኩም የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥርም ያመጣው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንኳን በራሳቸው ፈቃድ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ሲወስኑ ፓርላማው አንድም ጊዜ ቢሆን እንኳን የመተማመኛ ድምፅ ለመንፈግ ያደረገው ምንም ዓይነት ሙከራ አልነበረም፡፡ የመንግሥታቸውን ድክመት ተገንዝበው በራሳቸው ለመልቀቅ ሲወስኑ ፓርላማው ግን ስለመንግሥታቸው ችግር ትንፍሽ አላለም፡፡

የዚህን ጽሑፍ የመጀመርያ ክፍል ለመቋጨት ሕግ አውጪው ወደ ትክክለኛ ፓርላማነት ለመጓዝ በርካታ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ አንዳንዶቹን ሕግ በማውጣትና በመተግበር ቀሪዎቹን ደግሞ ኃላፊነቱን በተግባር በመወጣት፡፡

የሚያወጣቸው ሕግጋትን ብንመለከት ጥራታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ ለአጠያያቂነቱ መንግሥትም ምስክር ነው፡፡ ችግሮቹን አምኖ አንዳንዶቹ ላይ ማሻሻያም እያደረገ ነው፡፡ ሕግ አመንጭው ሕጎቹ በብቃት ሳይረቀቁና ከባለድርሻ አካላትም ጋር በቂ ምክክር ሳይደረግባቸው ለምክር ቤቱ ያቀርባል፡፡ ይባስ ብሎም በዓመቱ መጨረሻ ምክር ቤቱ ለዕረፍት ሊዘጋ ሲል በርካታ ረቂቆችን ማቅረብ ልማድ ሆኗል፡፡ የቋሚ ኮሚቴዎች ጥራት ያለው የረቂቅ ሕጎች ምርመራ የማድረግ የብቃት ማነስ ጋር ተያይዞ በምክር ቤቱ የሚፀድቁ ሕጎች በአፈጻጸም ሒደት ችግር የሚፈጥሩበትና ቶሎ ቶሎ ወደ ማሻሻያ የሚመጡበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ሲከሰት ማየት ተዘውትሯል፡፡

ከላይ ያነሳናቸው ችግሮች ብዙዎቹ ለክልል ምክር ቤቶችም ይሠራሉ፡፡ የክልል ምክር ቤቶች ከፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች የሚለየባቸው ባህርያት አሏቸው፡፡ ልዩነታቸውን በመተው ጠቅለል አድርገን በምናይበት ጊዜ የክልል ምክር ቤቶች አፈጻጸማቸው ከክልል ክልል ያለው የጥንካሬና የድክመት ደረጃ ያለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ምክር ቤቶቹ ዕቅድና በጀት መርምሮ በማፅደቅ፣ የአስፈጻሚውን ሪፖርት በመገምገምና አቅጣጫ በማስቀመጥ የተለያዩ ሕጎችን በማፅደቅና በመሳሰሉት የምክር ቤቱ አባላት የወከላቸውን የሕዝብ ፍላጎቶች በግልጽ በማንሳትና በመከራከር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ማለት ቢቻልም፣ ከአስፈጻሚው ተፅዕኖ ነፃ ሆነው በመሥራትና ተልዕኳቸውን በብቃት የሚወጡበት ሥርዓት አልዘረጉም፡፡

ምክር ቤቶቹ ደረጃውን በጠበቀ አሠራር አደረጃጀት ሥነ ምግባርና የመሳሰሉት የፓርላማ አስተዳደር ሕግጋት መርሆዎች ተግባራዊ እያደረጉ ነው ማለት አያስደፍርም፡፡ ቋሚ ኮሚቴዎች በማደራጀት የተወሰኑ አባላትን ብቻ በቋሚነት እንዲሠሩ ከማድረግ ያለፈ በቋሚነት የማይሠሩት ይበዛሉ፡፡ ቋሚ የሥራ ጊዜ የላቸውም፡፡ ብዙዎቹ የምክር ቤት አባላት የካቢኔ አባላት ስለሆኑ በምክር ቤቱና በአስፈጻሚው አካል መካከል ሊኖር የሚገባውን ልዩነትና እርስ በርስ ቁጥጥር ያላገናዘበ በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን በመወጣት በኩል አሉታዊ ውጤት ያስከትላል፡፡ በዓመት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ በመሰብሰብ አስፈጻሚው አካል ያዘጋጀላቸውን ረቂቅ ሕግጋት አፅድቆ መመለስ የተለመደ አሠራር ሆኗል፡፡

የቀበሌና የወረዳ ምክር ቤቶች ለሕዝብ ቅርብ ቢሆኑም መወጣት ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንዲችሉ ትኩረት ተሰጥቶ የአቅም ግንባታ ሥራ አልተደረገላቸውም፡፡ ሕዝቡም ትኩረት አልሰጣቸውም፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቶቻችን ምክር ቤት ለማድረግ ብዙ ሥራ ይቀራል፡፡ መደረግ ያለባቸውን ቀሪ ሥራዎች እንመለስበታለን፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...