Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉእንደ ትውልድ በክብር ይሰናበት

እንደ ትውልድ በክብር ይሰናበት

ቀን:

60ዎቹ ወጎች እንደ ማሳረጊያ

በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

የመደመርና የይቅርታ የዴሞክራሲያዊ ንጣፎች

- Advertisement -

የድሮ ጓደኞቼ ከዓብይ ጋር ተደምረሃል ወይ? አሉኝ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማለታችሁ ነው? መልሱ አዎንታ ሲሆን እንዲህ አልኳቸው፡፡ እኔ ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና ከሕዝቦች የለውጥ ፍላጎት ጋር ነው የምደመረው፡፡ ቲም ለማ የሚባል ሳይታወቅ ለዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ መሆን ሳልታክት የአቅሜን ስታገል ነበርኩኝ፡፡ አሁንም ለውጡ የሚያስተማምን እስኪሆን እቀጥላለሁ፡፡ የነበረው የአሕአዴግ ከፊል አምባገነን አስተዳደር በሠራቸው በጎ ተግባራት በማመሥገን እንዲለወጥ ነበር የምታገለው፡፡  ለመታገል ስወስን ነው ከሕዝቦች ፍትሐዊ ጥያቄ ጋር የተደመርኩት፡፡ ከአንድ ሰው ጋር መደመር አይቻልም፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ታግለው እያረጋገጡት ያለውን የለውጥ እንስቅስቃሴ ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው አደርጋለሁ የሚል መሪ ሲገኝ፣ አደናቃፊ ሆኖ እስካልተገኘ ከየትኛውም ብሔር ይምጣ አቅሜ እጅግ ውስን ቢሆንም የማንም ይሁንታ ሳልፈልግ መደገፍ ግዴታዬ መሆኑን ጠንቅቄ አውቃለሁ አልኳቸው፡፡ በመጀመርያው ምርጫ ቢያሳፍሩኝም በኢሕአዴግ 17ኛው ጉባዔ ወቅት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሊቀመንበር ዓብይ በመመረጣቸው፣ ለአገራችን መረጋጋት ካለው ፈይዳ አንፃር በእጅጉ ለማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በመጀመርያው ምርጫ ያን ዓይነት አቋም መያዛቸው ቢገርመኝም፡፡

መደመር፣ ይቅርታ ወዘተ. በመንግሥት ደረጃ መርሆዎች ሲሆኑ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉት መሠረታዊ ጥንካሬዎች አጉልቶ የሚያሳይና ኋላ ቀርነትን የሚደፍቅ በመሆኑ እጅግ አድርጌ አደንቀዋለሁ፡፡ ለእኔ መደመር ማለት የሁለም ኢትዮጵያዊ ሕዝቦች እሴት፣ ገንዘብ፣ ጉልበትና ጊዜ አስተባብሮ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡  በእያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ውስጥ ያሉ ትውፊቶችን በሚገባ አጥንቶ እንደ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሉንን በጎ እሴቶች፣ አመለካከትና ተግባር አንጥሮ አውጥቶ የሁሉም ማድረግ ነው፡፡ በሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ግንባታ ወቅት እንቅፋት የሆኑትን ኋላቀር አስተሳሰብና ተግባር የፈጠሩት የጥላቻና የመጠቃቃት ሁኔታ በይቅርታ አስታግሶ ተያይዞ መሄድ ነው፡፡  ይህም ሊሆን የሚችለው  በሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ ዙሪያ ነው፡፡

እኔም በሥልጣን በነበርኩበት (በዚያን ጊዜ ባይገባኝም) ዓይነት የራሳችሁን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ ፖለቲካው አግላይ፣ ኅብረተሰቡን ደግሞ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ፣ ጠባብ፣ አንጃ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ወዘተ. እያላችሁ የተለየ ሐሳብ ያለውን የማሳደድና ሕዝቦችን የመከፋፈል አገዛዛችሁን ለማስጠበቅና ለማርዘም የመንግሥት ሀብት፣ ጊዜና መዋቅር ተጠቅማችሁ ኅብረተሰቡ በፍርኃት እንዲኖር አድርባይነትና ተለማማጭነት እንዲነግሥ ያደረጋችሁትን ተግባራት ለማረም የግድ የሚል ውዝፍ ሥራ ነው መደመር ማለት፡፡ በራስ የደረሰ ከሁሉም ይመራልና በራሳችን የደረሰውን ከተገነዘባችሁት ላስታውሳችሁ አልኩኝ፡፡ የአገራችን የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ዕድሎች፣ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች የአቅማችንን ያህል ለማበርከት በምናደርጋቸው ሙከራዎች እንደ ጠላት በማየት፣ በወረዳዎች ሳይቀሩ እነ እከሌ ጠላቶች ናቸው አትስሟቸው እየተባለ በሚደረገው ዘመቻ ሥርዓቱ እስከ ምን ድረስ አፋኝና የተለየ ሐሳብ ለማስተናገድ ፍላጎቱም፣ ወኔውም፣ አቅሙም እንደሌለው ነበር የሚያሳየው፡፡  ይባስ ብላችሁ እኛ ስንጽፍ ትንሽም ብትሆን ምን የሚጠቅም ሐሳብ አለው? ከማለት ይልቅ ሥልጣን ፈልገው ነው፣ ቂም በቀል ስላላቸው ነው፣ ወይም የተማሩ መሆናቸውን ለዓለም ለማሳወቅ ነው ብላችሁ የራሳችሁን በሥልጣን መቆየት ዓላማችሁን በሚያጋልጥ ሁኔታ (Mirror Imaging) እኛን ማወከብ ምን ይባላል አልኳቸው (የመሰለንን ሐሳብ እንድናራምድ በግልጽ በአደባባይ ያበረታቱንን (ክቡር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) እና ክቡር አቶ ጌታቸው ረዳን አይመለከትም)፡፡ ሁሉንም አመለካከቶችና አማራጮች በማስተናገድ ሕዝቦች የመሰላቸውን እንዲወሱኑ ማድረግ ነው መደመር በማለት ጨመርኩላቸው፡፡ የለውጡ መንፈስ፣ ጥልቀት፣ ስፋትና ተቋማዊ እንዲሆን የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማድነቅና በመደገፍ በለውጥ ስም አግላይና የመንጋ ፖለቲካ እንዲቀር፣ የቀን ጅቦች፣ 27 ዓመታት ቆሻሻና ፀረ ለውጥ እያሉ ሕዝቦችን የማሸማቀቅ እንቅስቃሴ ለውጡን ለመቀልበስ የሚችሉ አስተሳሰቦች በመሆናቸው አሁንም በመታገል መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ 

መደመር፣ ይቅርታ፣ ወዘተ. የፓስተር ሰበካ ነው እኮ አለኝ በጎን የነበረው፡፡ ይጎዳል ወይ አልኩት? ፖለቲካዊ ግን አይደለም አለኝ፡፡ 99.9 በመቶ የተለያዩ ሃይማኖቶች አማኝ ባለበት ኅብረተሰብ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ከባህል ጋር ተሳስረው ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገረውን በጎና ሞራላዊ እሴት ለአገር ግንባታ፣ በሕዝቦቻችን እኩልነት ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያ አንድነት መጠቀሙ እንዴት ብሎ ሊወገዝ ይችላል? ማርክሲዝም ሆነ ሊበራሊዝም በውል ሳናውቀው በጥራዝ ነጠቅና በተበጣጠሰ እናውቃለን ብለን ጠቅላላ ሁኔታው በማይፈቅደው ኅብረተሰብ ላይ ለመጫን መፈለግ የጥፋት ጥፋት ነው፡፡ በምዕመናን ወይም በአባቶች ዘንድ የሚታየው ኋላ ቀርነት ሕዝቡ ራሱ  የሚታገለው ሆኖ፣ እንደ ባህል የሚታዩትን መደመርና ይቅርታ ማጉላት እንዴት ነው የምትቃወሙት?  ጭፍን ተቃውሞ አገር ያጠፋል አልኩኝ፡፡

የ1960ዎቹ ትውልድ የመደመር ፖለቲካ ተሸካሚ ሊሆን አይችልም

ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ ዴሞክራሲያዊ ትውልድ የፖለቲካ አመራሩን ካልነጠቀ አገራችን ወደ ከፍተኛ ቀውስና መውጫ ወደ ሌለው ጡዘት እንደምትገባ አቋሜን ሳራምድ ነበር፡፡ ከ1960ዎቹ ትውልድ ከእኔ ጋር የሚሰማሙ ጥቂት ቢኖሩም አብዛኛዎቹ እኔ ያገኘኋቸው ስድብ ይመስላቸዋል፡፡ እንደ ትውልድ ዴሞክራሲያዊ ወይም ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሚባል የለም ይላሉ፡፡ በእኔ አመለካከት የ1960ዎቹ ትውልድ እንደ ትውልድ ሲታይ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም ሲባል፣ ልክ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት መሳፍንቶች ሥርዓት ነው እንደ ማለት ነው፡፡ አካፋውን አካፋ ማለት ይኖርብናል በማለት ነበር የምሟገተው፡፡

ከአየር ኃይል ዋና አዛዥነት በጡረታ ስገለል የነበረኝን የፖለቲካ ውዥንብር ማጥራት የምችለው በትምህርት ነው በማለት በዋነኛነት ሕገ መንግሥታዊና ዓለም አቀፍ ሕግ ለመማር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ እኔም እንደ ሌላው ወጣቱን ትውልድ ልፍስፍስ፣ የአገር ፍቅር የሌለውና አንድ አንቀጽ በእንግሊዝኛ መጻፍ የማይችል አድርጌ ነበር የማየው፡፡ የትውልዱን ማንነት ያለማወቅ ድንቁርና እንዳለብኝ መገንዘብ የጀመርኩት ገና ሦስት ወር ሳይሞላ ነበር፡፡ ወጣቱ ትውልድ አስተማረኝ፡፡ ተማሪ በመሆኔ የሚበዛው የትምህርት ሰዓት በክፍልም ከዚያ ውጪም ከእነሱ ጋር ብፈልግም ባልፈልግም መዋል ነበረብኝ፡፡ በክፍል ውስጥ የሚሰጡት አስተያየት፣ በግል ሻይ ስንጠጣ ያለው ወሬ፣ በቡድን የቤት ሥራ ስንሠራ፣ ላይብረሪ ገብተን በሚያነቡት መጽሐፍ፣ በውይይት ጊዜ ልዩነት ሲያስተናግዱ ሳይ በዚህ ትውልድ ምዘና እኔና ኋላቀር እምነቴ መጋጨት ጀመሩ፡፡ በ1966 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ስለነበርኩ፣ የዚያን ጊዜ የክፍል ጓደኞቼን ከአሁኖቹ ወጣት ጓደኞቼ ጋር ማወዳደር ጀመርኩ፡፡ ለማወዳደር በጣም አስቸጋሪ ሆነብኝ፡፡ የእኔ ትውልድ እየተሸነፈ መሆኑን ለመቀበል እያስቸገረኝ እንዳይሆን መጠራጠር ጀመርኩኝ፡፡

የሆነ ትውልድ ከሌላ ትውልድ ጋር ማወዳደር አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ የተለያየ ኅብረተሰባዊ ዓላማ (Task) ያላቸውን ማወዳደር ይቻላል ወይ? የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ መልሱ አይቻልም ነው፡፡ ማለት የሚቻለው አገራችን አሁን ከተያያዘችው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ዓላማ የትኛው ትውልድ ነው የበለጠ የሚያሳካው? የየትኛው ጥንካሬ ነው ወደ መድረሻችን የሚያደርሰው? ማለት ነው፡፡ የእኛ ትውልድ አገሩን ለመቀየር ስለሚፈልግ መስዋዕትነት ለመክፈልም ዝግጁ ነበር፡፡ የጀመረውን በእልህ የሚጨርስና ድህነትን የመጥላት ባህሪው በልማት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው ችሏል፡፡ ይህችን አገር ከሙሉ ተመጽዋችነት  በዓለም በፍጥነት ከሚያድጉ አገሮች ረድፍ እንድትሠለፍ ጥረት በማድረጉ፣ የኢሕአዴግ አመራር መመሥገን አለበት እላለሁ፡፡ ኢዴሞክራሲያዊ በመሆኑ ራሱ መልሶ ቢያፍርሰውም ለ25 ዓመታት ለተጎናፀፍነው ሰላም የአመራሩ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ዓላማ ተሸክሞ ከግብ ለማድረስ ግን የሚችል አይመስለኝም፡፡ የልማት ግቦች በተወሰነ ደረጃ መሳካታቸው ለዴሞክራሲ ንጣፍ ቢሆንምና የተገኘው ሰላም ለዴሞክራሲ የተመቻቸ ሁኔታ ቢፈጥርም፣ ያለ ዴሞክራሲ የአገራችን ሁኔታ ፈራሽ ነው የሚሆነው፡፡ የእኛ ትውልድና ዴሞክራሲ ለየቅል ይመስለኛል፡፡ ለምን?

የእኛ ትውልድ የተወለደውና ያደገው ፍፁም መስፍናዊ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ ነው፡፡  መስፍንነትን በመቃወም ሥርዓቱን አፍርሶ ፍትሐዊ ሥርዓት ለመገንባት ፍላጎት ቢኖረንም፣ መስፍናዊ አስተሳሰብ እንደተጫነብን ነበር፡፡  ገዥው አስተሳሰብ ብዝኃነትን የማያስተናገድና ልዩነት የማቻቻል ባህሪ የሌለው ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ቀዝቃዛው ጦርነት በነበረበትና ማርክስ ሌኒኒስት እንደ አብዮታዊ አስተሳሰብ ፋሽን የነበረበትና ስለርዕዮት ዓለሙ የነበረው ዕውቀት ጥራዝ ነጠቅነት የተላበሰ ነበር፡፡ ላብ አደር እንደ መደብ ባልጎለበተበት “የላብ አደር አምባገነንነት” ብሎ የሚፎክር ትውልድ ነው፡፡ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ጭራቅ ነው ከተባለ በኋላ ዴሞክራሲ እንደ ሌላ ፋሽን ሲወሰድም፣ ሊበራል አስተሳሰብን ከራሱ ጋር ማጠበቅ ያልቻለ ትውልድ ነው፡፡  በነበረው የአገራችን ኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ሥርጭት ምክንያት ለዴሞክራሲ አገሮች ያለው ተጋላጭነት አነስተኛ ነበር፡፡ ሬዲዮ ገበያ ተሰብስበው በሚሰማበት አገር፣ የቴሌቪዥን መስኮት ለማየት ወደ አዲስ አበባ የሚመጣበትና ለማየት ደግሞ ስሙኒ ከፍሎ፣ በሳምንት ሁለት ሦስት ጊዜ ለተወሰነ የሚታይበት አገር የነበረ ተማሪ ነው በኋላ አመራር የሆነው፡፡ የ1960ዎቹ ትውልድ እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው የተወለደው፣ ያደገውና የታገለው፣ በኋላም በመንግሥት ሥልጣን ላይ የተቆናጠጠውና በውስጥም በውጭም የተቃዋሚዎች አመራር የሆነው፡፡ ይህ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ በሩቁ የነበረው ትውልድ ከፍተኛ ልማት በማረጋገጡ የእነዚያን ቁሳቁሶች ብርቅነት እንዲያከትም ቢያደርግም፣ በዚያው ልክ ልዩ ልዩ ሐሳቦችን የሚያስተናግዱ፣ የሐሳብ ብዝኃነትን የሚያሳዩ ማንነታችንን የሚያፈኩ ሊያደርጋቸው አልቻለም ብቻ ሳይሆን እንደ ማፈኛ መሣሪያ ተጠቅሞላቸዋል፡፡ ፈልጎ ያመጣው ባለመሆኑ መረገም የሌለበት ቢሆንም፣ ዴሞክራሲ ለመገንባት እንደማይችል ግን በግልጽ በመገንዘብ ለሥራው አመሥግኖ መሸኘት ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል አዲሱ ትውልድ ሲወለድ ወይም ከሕፃንነቱ ጀምሮ ሲያድግ በሽግግር በኋላም በዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ያለፈ በመሆኑ፣ እንደ ሰው ያሉትን  ሰብዓዊ መብቶች በትምህርት ቤትም በውጭም ማወቅና መለማመድ የጀመረ በመሆኑ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ውድድር፣ በተወሰነ ደረጃ ቢሆንም በመጠቀውና በተስፋፋው የቴክኖሎጂ ግብዓት የዴሞክራሲያዊ አገሮችን በንድፈ ሐሳብም ሆነ በተግባር መከታተል የሚችል መረጃ ያለው ነው፡፡ ኋላ ቀሩን ፖለቲካዊ ባህል ለማስቀረት በተሻለ ደረጃ የሚገኝ በመሆኑ፣ ለዴሞክራሲ ግንባታ አመራር ለመስጠት እጅግ የተሻለ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ እንደ 1960ዎቹ የአገር ፍቅር የለውም የሚለው አባባል የተሳሳተ ይመስለኛል፡፡ ለመሆኑ የአገር ፍቅር ማለት ምን ማለት ነው? በ15ኛው እና በ21ኛው ከፍለ ዘመኖች የሚኖረው የአገር ፍቅር አንድ ነው? እንደሚመስለኝ የተለያየ ነው፡፡ የአገር ፍቅርም እንደ ማንኛውም ኅብረተሰብ አስተሳስብ የሚለወጥ፣ የሚያድግና የሚሰፋ ነው፡፡ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ እንደ ዋነኛ ተግበር ይዛ የምትንቀሳቀስ አገር ዋናው መመዘኛው ከዚያ የሚመነጭ ነው፡፡

“የጀግና ወዳጅ ታስታውቃለች

ከመሀል ገበታ በለው ትላለች፤”

ማለት እንደ ጀግንነት በሚቆጥረውና ራሱን የማሳደግ ውስን ምኞት በነበረው የቀድሞ ትውልድና ራሱን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግና ሀብታም ለመሆን በሚፈልግ ትውልድ መካከል ግልጽ ልዩነት አለ፡፡ ሁለቱም ለአገራቸው ፍቅር አላቸው፡፡ በተማሪነትም በአስተማሪነትም የተገነዘብኩት የአዲሱ ትውልድና የእኔ ትውልድ ንፅፅር፣ ለዴሞክራሲ ብሎም ለዘላቂ ሰላም ያለው ሚና የላቀ መሆኑን በተግባር ያየሁትን ለመተንተን መሞከሬ ነው፡፡ የ1960ዎቹ ትውልድ በአደረጃጀቱ ሲገለጽ ደርግ ነው፡፡ የመኢሶን፣ የኢሕአፓ፣ የኦነግና የሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች፣ የኢሕአዴግና የኦጋዴን ነፃ አውጪ ድርጅት፣ ሲአን፣ ወዘተ. አመራር ማለት ነው፡፡ በቃላት በላብ አደርና በወዝ አደር፣ በአሸናፊና በአቸናፊ የሚቧቀስ ቀይ ሸብርና ነጭ ሽብር ብሎ አንድ ትውልድ ያስጨረሰ፣ በፀረ ደርግ የትጥቅ ትግል ጊዜም ቢሆን እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ብሎ ሌላውን ለማጥፋት የሞከረ የጋራ አሸናፊነት “win-win” ሳይሆን የዜሮ ድምር ውጤት “Zero-sum Game” ትውልድ ነው፡፡ ዋነኛ መገለጫውም “ወይ ከእኔ ጋር ወይ በእኔ ላይ” የሚለው ነው፡፡

ከዚህ ሁሉ የተሻለ የሠሩት እንደ ኢሕአዴግና እንደ ኦነግ የመሳሰሉ ኃይሎች ናቸው፡፡ የኢትዩጵያ ሕዝቦችን በመምራት ደርግን ታግለው አሸንፈው የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ችለዋል፡፡ ዋናው አሸናፊ ኃይል ኢሕአዴግ ሌሎችም በሽግግር በመንግሥት እንዲሳተፍ ማድረጉ የሚደነቅ ነበር፡፡ እንደ ኦነግ ያሉትም መሳተፋቸው ተስፋ ሰጪ ነበር፡፡ ነገር ግን በኢሕአዴግ ከእኔ በላይ ላሳር በሚል አመለካከትና ኦነግም ከእኔ በላይ ለኦሮሞ ሕዝብ ሌላ የለም በሚል እብሪት የነበረው ተስፋ ላይ ውኃ ደፉበት፡፡ የኦነግ መውጣት ያሳደረው ጠባሳ እንዳለ ሆኖ፣ በ1987 ዓ.ም. የተዋጣለት የሚባል ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት ፀድቆ አገራችን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ተያያዘች፡፡ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የመንግሥት አወቃቀር ተቋቁሞ የግለሰብ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና የቡድን መብቶችን ያካተተ የመድበለ ፓርታ ሥርዓት ለመዘርጋት ተሞከረ፡፡

ተስፋ ተጭሮ ኢትዮጵያችን የሰላምና የልማት አገር እንድትሆን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀንና ሌሊት ሠርተው 25 የብልፅግና ዓመታት ካሳለፍን በኋላ፣ ከ2008 ዓ.ም. በኋላ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገባን፡፡ ገዥው ግንባር ኢሕአዴግ የ1960ዎቹ ትውልድ ባህሪው በሆነው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት መጠለፉ አልቀረም፡፡ ገና ከመጀመርያው ሲንፀባረቅ የነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር እየገነነ ሄዶ፣ አምባገነን የሆነበት ሁኔታ በመፈጠሩ ሕዝቦች አምፀው ገዥውን ግንባር አንበረከኩት፡፡ ራሱ እንዲፀድቅ ያደረገውን ሕገ መንግሥት አለ ወይ? እንባል የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የሕዝቦችን ሰብዓዊ መብቶች በዴሞክራሲያዊና በሕግ የበላይነት ከማረጋገጥ ይልቅ፣  ጥያቄያቸውን በጠመንጃ ለመፍታት ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ መንግሥት ካመፀ ሕዝቦች የማመፅ ተፈጥሯዊ መብት ስላላቸው፣ ተገዶ ለውጥ ማምጣት ጀምሯል፡፡

ኢሕአዴግ ከ11ኛው ጉባዔ በፊት

አሕአዴግ ራሱ እንደ ገመገመው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ በኔትወርክ ሙስና መዘፈቅና ፍትሕ ማጣት የሥርዓቱ መገለጫ ሆነዋል፡፡  በአንዳንዶቹ መሪዎች አገላለጽ መበስበስ ነው፡፡ የወንጀል ወንጀል ነው የተሠራው፡፡ ታድሰን ብለው ሁሉን ነገር ዘከዘኩት፡፡ ነገር ግን ከላይ እስከ ታች ራሱ ፓርቲው ገምግሞ ወሰነ፡፡ የፓርቲ የበላይነት እንጂ የሕግ የበላይነት ስላልተረጋገጠ ከላይኞቹ በሕግ የተጠየቀ የለም፡፡ ተሞዳሙደው አለፉት፡፡ የተበደሉት ሕዝቦች ሳይሆኑ ገዥው ግንባር እንደሆነ በሚያስመስል ሁኔታ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሳይኖር ታፍኖ ቀረ፡፡ ጥፋቱ የሥርዓቱ ሆኖ እያለና ዋናው ተጠያቂው አሕአዴግ ሆኖ እያለ፣ ወደ አንድ ድርጅት ሕወሓት መሪዎች ብቻ የተነጣጠረ መሆኑም እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡  ኢትዮጵያ የሕግ ያለህ እያለች አሁንም ታለቅሳለች፡፡

በ1993 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ታድሻለሁ ቢልም፣ የባሰ ፀረ ዴሞክራሲያዊና የሕገ መንግሥት ጥሰት በተለያየ መንገድ የሚገለጽበት ሆነ፡፡ በ1997 ዓ.ም. ሕዝቦች ተቃውሟቸውን በምርጫ በመግለጽ አዲስ አበባ ሙሉ በሙሉ፣ በሌሎች ክልሎች ትርጉም ያለው መቀመጫ ለተቃዋሚዎች በመስጠቱ ኢሕአዴግ ተርበተበተ፡፡ በአምባገነናዊ አካሄድ ቀውስን ለመፍታት ሞከረ፡፡ ግን ቅንጅቶችም ቢሆኑ ሕዝብ የሰጧቸውን ድምፅ ተረክበው ለዴሞክራሲያዊ ግንባታ ራሳቸውን ከማዘጋጀት ይልቅ፣ ያላገኙትን የሕዝብ ድምፅ ለመስረቅና የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ለመያዝ ያደረጉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ ትግል ተስፋውን አጨለመው፡፡ ኢሕአዴግ እየተቀየረ ነው፡፡  ዴሞክራሲያዊ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል፡፡ እስከ 2010 ዓ.ም. አጋማሽ የነበረው ኢሕአዴግ ግን ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ እንደተባለው ሕገ መንግሥቱ የሦስት ትውልድ መብቶችን ዕውቅና የሰጠ ነው፡፡ ሒደቱን ግን በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ “Democratic Conditionality” የሚባል ጽንሰ ሐሳብ አለ፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ካለቀ በኋላ አሽናፊዎቹ ምዕራባውያን በተለይ ከአሜሪካ ዕውቅናና ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ዕርዳታ ለመስጠት፣ ዴሞክራቲክ ሕገ መንግሥት እንደ ግዴታ የሚወሰድበት ጊዜ ነበር፡፡ በሕዝባቸው ላይ ሙሉ ቁጥጥር የሌላቸው መንግሥታት በተግባር የሚሆነውን በይደር ትተው ዴሞክራሲን መምሰል የግድ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡

ኢሕአዴግ ወደ ድል እስኪቃረብ ድረስ ማርክሳዊ ሌኒኒስት ድርጅት ነበር፡፡ ርዕዮተ ዓለሙ በሚገባ ይታወቅና ይታመንበት ነበር የሚለው ሌላ ነገር ሆኖ ግን በዓለም ደረጃ በዴሞክራቲክ አገሮች ልዕልናና በሶቭየት ኅብረት መፈራረስ ማግሥት፣ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ድርጅቱ እርግፍ አድርጎ ትቶ ማለትም የላብ አደር አምባገነናዊ አሰተሳሰቡን አሽቀንጥሮ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እቀበላለሁ ብሎ አክበሮባት ሠርቶ  ተቀየረ፡፡ መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ሳያረጋግጥ ነው የተገለባበጠው፡፡ የላብ አደሩን አምባገነንነት በመከተል  እስካሁን ድረስ “ያለ ኢሕአዴግ መንገድ ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው”፣ “ዴሞክራሲያዊ ጥርናፈ” እና “መሪ ፓርቲ” (Vanguard Party) አስተሳሰብ ከማርክሲስት ሌኒኒስት የሚፈልገውን በመውሰድ፣ ከመሳፍንታዊ የኋላ መሠረት ጋር አደባልቆ ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን አጠናከረው፡፡ የላብ አደሩ አምባገነንነት  የሚነሳው ከሶሻሊዝም ግንባታ ወቅት የቡርዣው መንገድ የጥፋት መንገድ ብቻ ሳይሆን፣ ሒደቱን ለማደናቀፍ  ከዓለም አቀፍ  ኢምፔሪያሊዝም ጋር ተሳስሮ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል የሚል እምነት ስላለው ሙሉ በሙሉ የሚጨቁንበት (Suppress) ነው፡፡  ይህ አስተሳሰብ ኅብረት ሲጨመርበት ሕዝብና ድርጅት አንድ ነው ይላል፡፡ በቃል ባለሀብቱ የሥርዓቱ ሞተር ነው እያለ በተግባር ግን ቁም ስቅል ያደርገዋል፡፡

ዴሞክራቲክ ጥርነፍ በሌኒናዊ አስተሳሰብ በቁልፍ የአደረጃጀት ጉዳይ የሚመነጨው ከላይ የተገለጸውን ተግባር ለመፈጸም የላብ አደሩ አጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አቅም ለመፍጠር ነው፡፡ በሌኒናዊ አስተሳሰብ ጥርነፋው ብቻ ሳይሆን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በፅኑ የሚታመንበት ነበረ፡፡ በኢሕአዴግ ግን እኔም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እያለሁ ሐሳብ በነፃነት የመግለጽ መብት እየከሰመ ነበር፡፡ የኢሕአዴግ አስተሳሰብ በሁለት ምክንያቶች የተሳሳተ ነው፡፡ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ጠንካራ ፖርቲዎች/ግንባሮች እንጂ መሪ ሊኖር አይችልም፡፡ መሪ ፓርቲ ሶሻሊዝም በኮሙዩኒዝም ሲከስም አብሮ የሚጠፋ እንጂ፣ በየጊዜው በምርጫ ተሸንፎ ተቃዋሚ የሚሆንበትን ሁኔታ ታሳቢ አያደርግም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መሪ ፓርቲ እንጂ መሪ ግንባር ሊኖር አይችልም፡፡

በ1985 ዓ.ም. የኢሕአዴግ ታጋዮች ማርክሳዊ ድርጅቱ የት አለ? ፈርሷል ወይ? ከፈረሰስ ለምን? የሚል ሞጋች ጥያቄዎች አንስተው ነበር፡፡ ያለ በቂ ማብራሪያና በሥርዓት ከፍተኛ ውይይት ሳይደረግበት ተድበስብሶ ዝም ተብሎ፣ በአሁኑ ጊዜ አይቻልም የሚል መልስ ብቻ ነው የተሰጠው፡፡ አስተሳሰቡ ግን ተደብቆ ቆይቶ በኢሕአዴግ ውስጥ በተለይ በሕወሓትና በብአዴን ሌላ አክሮባት ተሠራ፡፡ በ1993 ዓ.ም. በነበረው ውስጠ ድርጅት ቀውስ ማርክሲስት አስተሳሰብ ሌኒንነት እንደገና እንደ ጓዳ ቋንቋ አንሰራርቶ፣ ችግሮቻችንንና መፍትሔዎችን በዚያ መነጽር ለማየት ተሞክሯል፡፡ ሕወሓት ውስጥ የተደራጀ ጽሑፍ ካቀረቡት አምስት አመራሮች ሁለቱ የአሸናፊው አንጃ አባላት “ነጭ ካፒታሊዝም”ን እና “አብዮታዊ ዴሞክራሲ”ን ደባልቀው አረፉት፡፡ ከተሸናፊው አንጃ ሁለቱ ግለ ሂስ አድርገው “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ጭራቅ አደረጉት፡፡ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም እንደ ርዕዮተ ዓለም ትክክል ነው ስህተት ነው ለማለት ሳይሆን፣ በሚገባ የማይታወቅና ለሁኔታው ለማይመጥን ለመስፍናዊ አስተሳሰብና ተግባር ማድመቂያ ሆነ ለማለት ነው፡፡

የተቃዋሚዎች አመራሮች በተለይ ዳያስፖራው

በደርግ ሆነ በኢሕአዴግ ዘመን ከአገራቸው የተሰደዱ የዚያ ትውልድ አባላት አንዳንዶቹ የተወሰነ ትምህርት ቢማሩና በዴሞክራሲያዊ አገር ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ  ቅንጣት ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ ሳያዝመዝግቡ ኢሕአዴግን  ለመተቸት ሲሉ ብቻ  ዴሞክራሲና ሰብዓዊነት የሚዘላብዱ፣ በዋናው አምባገነን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዘንድ ተጠልለው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንታገላለን ሲሉ የነበሩና  አሁን በገፍ የገቡ ናቸው፡፡

አብዛኛውን ድምፅ አልባ ዳያስፖራ በማገት በማድረግ ስለኢትዮጵያ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እንዳያውቅና ወደ አገሩ እንዳይመጣ፣ በተለያዩ መንገዶች ሲከለክሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግን ያዳከሙ እየመሰለቸው ኢትዮጵያ ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አትብረሩ ሲሉም ነበር፡፡ አገራቸው ተመልስው ሲገቡ አፍረው ይሆን? ይቅርታስ መጠየቅ የለባቸውም?  አንዳንዶች በድፍረትና በጭፍን አማራ የሚባል ብሔር የለም በማለት፣ ጎሳ እንጂ ብሔር ብሔረሰቦች የሉም ሲሉም የሚደነፉ ናቸው፡፡ የትግራይ ሕዝብ የተለየ የተጠቀመው ነገር በሌለበትና እያወቁ ለፖለቲካ ፍጆታቸው የትግራይ የበላይነት አለ በማለት የትግራይ ሕዝብን በሌላው እንዲጠላ ያደረጉም ጭምር ናቸው፡፡ የሕወሓት የበላይነት ሌላ የትግራይ የበላይነት ሌላ መሆኑን ዘንግተውት አይደለም፡፡   የ1960ዎቹ ትውልድ “Formative Age” የያዛቸውን መስፍናዊ፣ ቁንጽል ሌኒናዊና አብዛኛው በትጥቅ ትግል ያለፈ በመሆኑ ወታደራዊ አስተሳሰብን የራሱ ያደረገ ስለሆነ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ በ27 ዓመታት ውስጥ የሕግ በላይነት፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት ቀስ በቀስ  እያደገ ከመሄድ ይልቅ ማሽቀልቆል፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ “ማኅተም መቺ” እና ልፍስፍስ የሆኑበት፣ መንግሥትና ፓርቲ አንድ የሆኑበት የኅብረተሰቡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተገፈፉ የሄዱበት ጉዞ ነበር፡፡

መተካካቱ ላይመለስ ዕውን ሆኗል

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለያዩ አደረጃጀቶች በዋናነት ግን በኢሕአዴግ መሪነት የደርግን ሥርዓት አስወግደው የመጀመርያውን ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ከጀመሩ ከ27 ዓመታት በላይ ሆኗል፡፡ ሸግግሩ በተጀመረው ፍጥነት መሄድ አቅቶት በመቸከሉና ወደ ኋላ የመሄድ አዝማሚያ በማሳየቱ ማለትም አምባገነናዊ አካሄድ እየጎለበተ በመምጣቱ ሌላ ሁለተኛ ሸግግር አስፈልጓል፡፡ የዳበረ ዴሞክራሲ (Consolidated Democracy) ላይ እስክንደርስ የግድ በኃይል መሆን ባይኖርበትም፣ ሌሎች ሽግግሮች መኖራቸውን ታሳቢ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

የ1960ዎቹ ትውልድ እስካሁን ሲንገዳገድ ቆይቶ ስላልቻለና በሕዝቦች ትግል ተገዶ ቢሆንም፣ ከንቁና ከሙሉ ፖለቲካዊ አመራር ወደ አማካሪነት ወይም ወደ ዕረፍት በወሳኝነት እየተሸጋገረ ይገኛል፡፡ በገዥው ግንባር እህት ድርጅቶች መተካካት የሚባል ዕቅድ ቀደም ብሎ ተይዞ ሲሠራበት ቢቆይም፣ የእውነት የትውልድ መተካካት መሆኑ ቀርቶ የማይፈለግ ሰው የማግለል አሠራር ዓይነት ሆኖ ነበር፡፡ አርከበ ዕቁባይን (ዶ/ር) በመተካካት ከግንባሩ ፖለቲካዊ መሪነት አስወግዶ እንደነ አቶ ዓባይ ወልዱ ዓይነት ሰዎች መተካት ነበር የሆነው፡፡ በሁሉም ድርጅቶች በዚያ ተጉዘው ነበር፡፡

በ2007 ዓ.ም. የትግራይ ሕዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ሕወሓትን ታድሻለሁ እንዲልና አዲስ አመራር ብቅ እንዲል ቢያስገድድም፣ የፈለገውን ያህል ሊሳካ አልቻለም፡፡ የኦሮሚያ አመፅን ተከተሎ በ2009 ዓ.ም. ‹ቲም ለማ› ከየት መጣ ሳይባል የኦሕዴድ/ኦዴፓ በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ እንደ አብነት ሆኖ ሁኔታውም የሚጠይቅ በመሆኑ ግለት ጠብቆ በመሄዱ ምክንያት 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ ሲከናወን ሁሉም እህት ድርጅቶች በዋናነት ወጣቶችን፣ የተወሰነ ቢሆንም ሴቶችን ያካተቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል፡፡

ኦዴፓና ደኢሕዴን አዲሱን ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚመስልና የሚያንፀባርቅ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመምረጥ መተካካቱ ጫፍ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ የመጀመርያውን ፈተናም አልፈዋል፡፡ በአጠቃላይ በኢሕአዴግ የትውልድ መዋቅራዊ (Stractural) ለውጥ መጥቷል፡፡ አዲሱ፣ ወጣቱና ጎልማሳው ትውልድ መሪነቱን ተቆጣጥረዋል፡፡ ከእንግዲህ የ1960ዎቹን ትውልድ እያማረሩ መኖር አብቅቶለታል፡፡ አዲሱ ትውልድ የ1960ዎቹን “ኦሮማይ” ብሎ ስላሰናበተ ኃላፊነቱን መሸከም ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም ስለትናንት ገድልና ፍፃሜ የሚያወራው ተሰናብቶ ስለነገ ተስፋና ፈተና የሚጨነቅ ትውልድ ቦታውን ይዟል ማለት ነው፡፡

መዋቅራዊ ለውጥ መጥቷል ማለት የዴሞክራሲያዊ ትውልድ ዋናው ኃይል ወደ ሥልጣን መጥቷል ማለት አይደለም፡፡ ሒደቱ በከፍተኛ ደረጃ በማይመለስ ደረጃ ተጀምሯል ማለት እንጂ፣ አሁን የተረከበው አመራር ከእነ ግሳንግሱ በመሆኑና ብቃት የሌላቸውና ጽንፈኞች የተቀላቀሉበት ስለሆነ ለጊዜው መደናበርና እዚህም እዚያም ስህተት መፈጸሙ አይቀርም፡፡ ይህ መሰሉ ግሳንግስ መቀላቀሉ በጉሽ ጠላ ላይ እንደሚንሳፈፍ ገለፈት በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተተፋ የሚሄድ ይሆናል፡፡ ስህተት እየፈጸመና ከስህተቱ የመማር “መብት” ተሰጥቶት የማይመጥኑትን በራሱ ሒደት እያስወገደ ነው ያለውን ዕውቀት፣ ክህሎትና ወኔ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያችን ተስፋ ለምልሞ በሰላም ልማትና ዴሞክራሲ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ የምንችለው፡፡

ኢሕአዴግ የ1960ዎቹ ትውልድና የእነሱ ፍጡሩን በየአዳራሹ በክብር መሸኘት አለበት፡፡ ተቀዋሚዎችም ለወደፊቱ ፋይዳ የሚኖራቸው ከሆነ ለአዲሱ ትውልድ ያስረክቡ፡፡ ስለዛሬና ስለነገ አብዝቶ በሚጨነቀውና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ሊራመድ በሚችለው ተኩሶም ሆነ ተተኩሶበት፣ አስሮም ሆነ ታስሮ፣ ገሎም ሆነ አስገድሎ በማያወቀው አዲስ ትውልድ እንተካው ማለታችን ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አዲሱን ትውልድ ወክለው የ1960ዎቹን ትውልድ በክብር እንዲሸኙና አዲሱ ትውልድ ኃላፊነቱ በይፋ እንዲረከብ ቢያደርጉ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ነባር የኢሕአዴግ ታጋይና የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...