Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉኢሕአዴግና ወቅታዊ ሸክሞቹ!

ኢሕአዴግና ወቅታዊ ሸክሞቹ!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) የ60ዎች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጎምቱ አንቀሳቃሾች (ቢያንስ የተማሪዎች ንቅናቄ አባላት) ጥንስስ የወለደው፣ በግራ ዘመምነት የሚታማ የፖለቲካ ኃይል ነው፡፡ ትግሉን በበረሃ ሲጀመር በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ለኳሽነት ቢሆንም፣ በኋላ ኅብረ ብሔራዊነት የተላበሰውን ኢሕዴን (የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ)፣ በሒደትም ኦሕዴድ (የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት)፣ በመቀጠልም ደኢሕዴን (የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በማዕቀፍ የአራት ድርጅቶች የጋራ ግንባር ሆኖ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ድርጅት ሆኗል፡፡ ያም ሆኖ ግንባሩ የተዋሀደና ወደ አንድ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲነት ደረጃ ያደገ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ እርግጥ በዚህ ዕድሜው ውስጥ በርካታ የድልና የውድቀት ታሪኮችን ያሳለፈ ሲሆን፣ አሁን እስካለው ሁለተኛው ትውልድ ድረስ ቀላል የማይባሉ አስቸጋሪ ፈተናዎችና ጥልቅ ተሃድሶን የሚሹ መናወጦችም አጋጥመውታል፡፡ እስካሁን ሦስት ሊቃነ መናብርት ብቻ የመሩት ኢሕአዴግ፣ ዘንድሮ 11ኛ ጉባውን በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ አካሂዶ በቅርቡ ማጠናቀቁን በመገናኛ ብዙኃን ተከታትለናል፡፡ አንዳንዶች ያልጠበቁት ቢሆንም፣ መሪዎቹንም ከለውጥ ኃይሉ መካከል ከፍተኛ መግባባትን በሚያሳይ የድምፅ ብልጫ መምረጡን ተገንዝበናል፡፡

በግንባሩ ጉባዔም ሆነ በብሔራዊ ድርጅቶቹ መድረኮች በስፋት የተነሱና በሕዝቡም ውስጥ እየተብላሉ የሚገኙ ወሳኝ ጉዳዮች ግን አዲሱ አመራር ፈተና የሚያልፍባቸው፣ አልያም የሕዝብ ጥያቄን ባለመመለስ የሚወድቅበት ቅርቃር ውስጥ ከተውታል፡፡ በተለይ ባለፉት 25 ዓመታት ያልተደፈኑ ቀዳዳዎችና በፖለቲካዊ ሒደቱ ያልተሞሉ ጉድጓዶች በዚህ የለውጥ ወቅት አንገብጋቢ ሆነው መምጣታቸውን አለመገንዘብ አዳጋች ነው፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን የለውጥ ኃይሉ የለውጥ እንቅፋቶች ብሎ የለያቸውን ተግባራት፣ አሠራሮችና አመራሮች እያንጓለለ በአዲስ የለውጥ መንፈስና ተነሳሽነት የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ ‹‹የእናቴ መቀነት. . . ›› የሚልበት ሰበብ ሊኖረው እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ከዚህ አንፃር አገሪቱን ቢያንስ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተኩል ገደማ የሚመራው የኢሕአዴግ አዲሱ አመራር፣ የጀመረውን ለውጥ በመዋቅራዊ ሽግግርና የሕግ ማዕቀፍ እያጀበ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ለለውጡ ቀጣይነትም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ተፎካካሪዎች፣ ምሁራንና ሕዝቡ፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሲቪክ ማኅበራት. . . የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ቢኖርም፣ መንግሥት በተለይም ድህረ 11ኛ ጉባዔ ኢሕአዴግ ሊያተኩርባቸው ይገባል ያልኳቸውን አንዳንድ ተግባራት በሦስት ንዑስ ርዕሶች ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡

- Advertisement -

ሕዝብን ያሳተፈ የሰላምና አገራዊ ደኅንነት ሥራን ማስቀደም!

ኢትዮጵያ በስኬትና በውድቀት ታሪክ ለዘመናት የኖረች ታሪካዊት ምድር መሆኗ የታመነና ተደጋግሞ የተነገረ ሀቅ ነው፡፡ አገሪቱ ብዝኃነት (በብሔር፣ በእምነት፣ በቋንቋና በባህል ብሎም በአመለካከት) ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባት ነች፡፡ ምንም እንኳን ብሔር ተኮር በሆነው የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር መዘዝ የተዛቡ ታሪኮች መቀንቀናቸውና ባልተገባ መንገድ መጠራጠርና ቁርሾ ምድሩን መሙላቱ፣ ከአብሮነት ይልቅ መለያየትና መገፋፋትን ያነገሠ መሆኑ ባይካድም፣ የአገሪቱ ሕዝብ መቼም ቢሆን አብሮነት ያልተለየው ለነፃነቱ ቀናዔ፣ ለአገሩ ዘብ የቆመና ፈሪኃ ፈጣሪ ያለው ሆኖ ቆይቷል፡፡

በተለይ ነፃነትንና ሉዓላዊነትን በማስከበር ረገድ አገራችን ትናንትም ሆነ ዛሬ ከራሷም አልፋ፣ ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች በአርዓያነት የምትጠቀስ የኩራት ምንጭ ነች፡፡ ይሁንና የኢኮኖሚያዊ ድቀትና የፖለቲካ መውገርገር ሲፈትናት፣ ድህነትና ኋላቀርነት ክፉኛ ሲን ዘመናትን በማሳለፏ ከበጎው ገጽታዋ ይልቅ ጨለማውና የቀውስ ወሬው በርክቶ ሲታይ እንደነበር አይካድም፡፡ የጋራ አኩሪ ታሪክና ቁርሾን የሚያስቀር ፖለቲካዊ መስተጋብርም ለትውልድ ማስተላለፍ ሳይቻል ዘመናት አልፈዋል፡፡ አሁን አገር እየተረከበ ያለው ኃይል ደግሞ በአብዛኛው ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በአፍ መፍቻ ልሳን መማርና መዳኘትን፣ በአንድ የጋራ አገራዊ ልሳን ከመጠቀም በላይ አስበልጦ የሚመለከት፣ የክልል ሰንደቅን ከአገር አቀፉ ዓርማ አጉልቶ  ለማየት የሚዳዳው፣ የመንደርና የጎሳ አጀንዳና ወሰን ከብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት በበለጠ የሚያናውዘው. . . ሆኖ እንዲበቅል ብዙ ስለተሠራበት የአገራዊ ብሔርተኝነት ፀጋው ተገፎ ይስተዋላል፡፡

እንደ አገር ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ትልቁ ትኩረት ለቡድን መብት፣ ከቡድኖችም ለብሔር አልፋና ኦሜጋ ሥልጣንና ዕውቅና መሰጠቱ፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ብሎም በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ሥር ሲተዳደሩ የኖሩና የሚተዳደሩ ዜጎችን አንዳንድ ሕዝብ ከማየት ይልቅ ሕዝቦች (ይህ አጠራር ከኢትዮጵያ ውጪ የትም አገር ሥራ ላይ እንዳልዋለ የሕገ መንግሥት ምሁሩ ጋሽ መርሐ ጽድቅ መኮንን ዓባይነህ ጽፎት አንብቤያለሁ) እያለ፣ ሁሉንም በየፊናው ወደ ፊት ጎጆ ለማስወጣት ስናለማምደው መኖራችን የተካረረ ብሔርተኝነትና መንደርተኝነት የአገር ሰላምና የሕዝቦች ደኅንነት ሥጋት ሆኗል፡፡ እንግዲህ ከለውጥ ማግሥት የተጋረጠው ቀዳሚውና አንዱ ፈተና በአንድ በኩል ካለፈው ታሪክ በተወረሱ  ውዝግቦችም ይባል፣ ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ባልተሠሩ ተግባራት የተፈጠረውን ጠባብነትና የተካረረ ብሔርተኝነት፣ አለመተማመን፣ ጥላቻና ቁርሾ በማለዘብና በመተው በአንድነት፣ በመተሳሰብና በይቅር መባባል የአገርን ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቦች ደኅንነትና በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ማረጋገጥ ዕውን ማድረግ ይገባል፡፡ የገዥው ፓርቲ ቀዳሚ ተግባር መሆንም አለበት፡፡

በእርግጥ ባለፉት ስድስት ወራት አገሪቱን እየመራ ያለው አዲስ የለውጥ ኃይል፣ ከዚሁ ከኢሕአዴግ ወጥቶ ብዙኃኑ ሕዝብ ለዓመታት ሲያነሳ የነበረውን የመልማትና የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጥያቄ፣ የፖለቲካ መብት መረጋገጥ፣ የዜጎች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መስፈን፣ የአብሮነትና የመቻቻል አጀንዳን ማስተጋባት መጀመሩ ቢያንስ ከአደጋ በፊት መፍትሔ ለማየት የረዳ ይመስለኛል፡፡ በመጠኑም ቢሆን በሕዝቡ ውስጥ አንድነትና መደመር የተሰኘው እሳቤ በተግባር መታየትም ጀምሯል ለማለት ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁንም በአንድ በኩል ይህን የለውጥ መንፈስ ያልተቀበሉ፣ ጥቅማቸው የተነካባቸው ወይም በመደናገር ሽግግሩን የተጠራጠሩት ወገኖች ‹‹በለውጥ ወቅት ሊያጋጥም ይችላል›› ከሚባለውም በላይ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭትና ጥፋት እያደረሱ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ቢያንስ በአገሪቱ አምስት ክልሎች ውስጥ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች (አብዛኛዎቹ ሴቶችና ሕፃናት) ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸው ብቻ አይደለም፡፡ ምንም ሌላ ስያሜ በማይሰጠው ማንነት ላይ ባተኮረ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ከፍተኛ የአገር ሀብት ውድመት ተፈጽሟል፡፡ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና መገናኛ ብዙኃንም በዘር ተኮር ግጭትና በአገር ውስጥ መፈናቀል የውድቀት ደረጃ በቅርቡ ባወጡት መረጃ፣  የዓለም ቀዳሚ አገር እስከማለት ተሳልቀውብናል፡፡ አሁንም ቢሆን የአገር ሰላምና ደኅንነት በተሟላ መረጋጋት ውስጥ ነው ሊባልም አይችልም፡፡                              

ከዚህ አንፃር ኢሕአዴግ ለዘላቂ መፍትሔው ቁርጥ አቋም ሊወስድ ግድ ይለዋል፡፡ በቀዳሚነት ከፖለቲካ የኃይል ሚዛን ሽሚያ በመውጣት፣ የራሱን የፖለቲካ አንቀሳቃሾችና ሕዝቡን አነቃንቆ አገር ሊያረጋጋና የዜጎችን የመኖር መብት ሊያስጠብቅ ይገባል፡፡ በቀጠል የፀጥታ ኃይሉንና የፍትሕ አካሉን አጠናክሮ ሕገወጥነትን ሳያቅማማ መታገል ይኖርበታል፡፡ መንግሥታዊ ሆደ ሰፊነትና ሁሉ አቀፍ መሆን ቅቡልነት ቢኖረውም፣ ሕጋዊነትንና ሕገወጥነትን እያጠቀሰ በፖለቲካ ምኅዳር መስፋት ስም መጨማለቅ የሚፈልገውን ኃይል አደብ ማስያዝ ብሎም ፍትሕን መስመር ማስያዝ ቀዳሚው የግንባሩ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ ብዙዎች እንደሚተቹት ግን ኢሕአዴግ እስካሁን ባካሄደው ግምገማ ሊታረሙ የሚችሉ አባላቱ እንዲታረሙ፣ ከደረጃቸው መውረድ ያለባቸው ዝቅ ብለው እንዲሠሩ፣ ከድርጅቱ መሰናበት ያለባቸው እንዲሰናበቱ የሚያስችሉ አስተዳደራዊና ድርጅታዊ ዕርምጃዎችን ሲወስድ፣ አኩራፊውና  ጥቅሙ የተነካበት የራሱ ጥገኛና ዘረኛ ኃይል በንፁኃን ደም ሊታጠብ እንደሚችል ቀድሞ ማሰብና መፍትሔ ማስቀመጥ ለምን ተሳነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ መልስ ማፈላለግ ያለበትም ይኼው የለውጥ ኃይል መሆን አለበት፡፡ በእርግጥ ከበፊት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በተካሄደው የኢሕአዴግ (የብሔራዊ ድርጅቶቹ) ውስጥን የማጥራት ንቅናቄ (Internal Rectification Movement) ይኼን ያህል ግዙፍ ቁጥር ባላቸውና ቱባ አባላቱና አመራሩ ላይ ዕርምጃ ሲወስድ ይህ የመጀመሪያው ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ወገኖች ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ የድርጅቱን ዓላማ በመደገፍ በአንድም በሌላም ሕዝብ ማገልገላቸው ባይታበልም፣ በአገሪቱ ላይ ተደንቅሮ ለነበረው ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ ኢፍትሐዊነት፣ ሙሰኛነት፣ ብልሹ አስተዳደርና የፍትሕ ችግር፣ የመሬት ቅርምትና ደላላነት፣ ወዘተ. ችግሮችም ተጠያቂ ናቸው፡፡

በድሉ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውድቀትም ዋና ተዋናይ ወይም በአድርባይነት ተሸንጋይ፣ አልያም አገርና ሕዝብን ለመበታተን አልሞ በመሥራት የታሪኩ አካል ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ እውነት በድርጅቱም ሆነ በሕዝቡ ውስጥ እየታወቀ በሕግ አግባብ ተጠያቂ ማድረግ እንኳን ባይፈለግ፣ አደናቃፊዎች አርፈው እንዲቀመጡ በትጋት አለመሥራት ግን ያለ ጥርጥር የሚጋብዘው ውድቀትን ብቻ ሳይሆን የአገር መፍረስንም ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ሁኔታውን መገምገምም ብቻ ሳይሆን እርምት መውሰድ ግድ የሚለውም ከዚሁ እውነታ በመነሳት ነው፡፡ ስለሆነም በቅድሚያ ኢሕአዴግ ውስጡንና ዙሪያውን በመፈተሽ፣ በቀጠል የሰላም እጅ ሲዘረጋለት አሁንም ሕዝብና ሕዝብን እያበጣበጠ ሕይወቱን ለማረጋጋት የሚሻ ኃይል ካለም ሳያቅማማ በማጋለጥ አገርን ማረጋጋት፣ የሕዝብን መከራና እንግልትም መቀነስ ብቻ ሳይሆን ማስቀረት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በ11ኛው የድርጅቱ ጉባዔ የአቋም መግለጫም ሆነ በምክክሩ ወቅት ከተባለውም በላይ በተግባር ለሕዝቦች አንድነትና እኩልነት መስፈን ታጥቆ መነሳት ይኖርበታል፡፡

ሕዝቡን ያሳተፈ የምጣኔ ሀብት ለውጥን ማጠናከር!

ሥር ነቀል የምጣኔ ሀብት ለውጥ ለማምጣት የፖሊሲ ማሻሻያና ጊዜ ማስፈለጉ አይቀርም፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ቢያንስ ፍትሐዊነትን በማረጋጋትና ዘረፋውን በማስቆም ብቻ ነባሩን የምጣኔ ሀብት ዕርምጃና ዕድገት አጠናክሮ መቀጠል ሊበጅ  ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት የልማት ሥራዎችን ማፋጠን ብቻ ሳይሆን፣ የግል ባለሀብቱና ዜጋው በነፃነትና በፍትሐዊነት የሚንቀሳቀስበት የምጣኔ ሀብት ዕድገትና የገበያ መስተጋብር ካለመደነቃቀፍ ዕውን መሆን አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ‹‹የተሃድሶው ዋነኛ ዓላማ የተጀመረውን ግዙፍ አገራዊ ለውጥ በማስቀጠል አገሪቱን በልማትና በዕድገት ከፍተኛ ማማ ላይ እንድትደርስ ማድረግ ነው፤›› ከማለቱ አንፃር ደግሞ፣ ከወዲሁ አፈ ቀላጤዎችን ሳይሆን ሕዝቡን ማዳመጥና ማሳተፍ ስህተት ላይ ከመውደቅ ያድነዋል፡፡ እዚህ ላይ የፖለቲካ ተገዳዳሪዎች የሕዝብ ድምፅ አራማጆች እንደ መሆናቸው በተጀመረው መንገድ ተፎካካሪዎችን እያቀራረቡ በጋራ መተማመን የዴሞክራሲ ተቋማትን የማዋቀር፣ የምርጫ ሕግን የመሳሰሉ ወሳኝ ግብዓቶችን የማሻሻል፣ ብሎም ለትልቁ አገራዊ ሥዕል በጋራ የመሥራት ጉዳይ ከማስቀደም ባሻገር፣ ለምጣኔ ሀብትና ገበያ መረጋጋትም ቢሆን አገራዊ ድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ አለባቸው፡፡              እስካሁንም በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት ከሕዝቡ ጋር በተደረጉ ዴሞክራሲያዊ ውይይቶች በሕዝቡ የተነሱ ሰፊ ቅሬታዎችን፣ ተፈጸሙ የተባሉ በደሎችን፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦትን፣ የመሬት ቅርምትን፣ በሥልጣን ያላግባብ የመጠቀምን፣ የጠባብነትና የትምክህት አመለካከቶችንና የመሳሰሉትን ተግዳሮቶች በመታገልና በመዋጋት ረገድ ተጨማሪና ተከታታይ ተግባራት ያስፈልጋሉ፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ አስተዳደር የተወሰዱ አመርቂ ዕርምጃዎች (ያላግባብ ተይዘው ያለጥቅም አንድ ትውልድ ያሳለፉ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ የማስገባት፣ በሕገወጥ መንገድ የዘረፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ማስመለስ፣ በትርፍና በኢፍትሐዊነት የተያዙ ቤቶችን ለድሆች ማስተላለፍ፣ በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የውጭ ምንዛሪዎችንና ሕገወጥ መሣሪያዎችን የመውረስ…)      ዓይነት የተሃድሶ ቀንዲሎችን መለኮስ ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ ምንም እንኳን ዘላቂነት ባይታይበትም፣ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞችም የዚህ ዓይነት ዕርምጃዎችን ተመልክተናል፡፡ በሌላው አካባቢ ግን ወሬው እንኳን ስለመኖሩ አልሰማንም፡፡ ሕዝብን የሚያሳትፍ የሚባሉት ሌሎች ዕርምጃዎች ሊባሉ የሚችሉትም በሜጋ ፕሮጀክቶች አካባቢ (በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና በግዙፍ መሠረተ ልማቶች. . . )  የነበረውንና ያለውን ክፍተት ለይቶ ሕዝብን ወደ ማስቆጣት ሳይሄድ ማረም ይገባል፡፡ በተለይ ሜቴክ (ብረታ ብረትና ኮርፖሬሽን) በተባለው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት አማካይነት የተፈጸመው ‹‹የጤና የማይመስል›› ጥፋት ተጣርቶ ፕሮጀክት መንጠቅ ብቻ ሳይሆን፣ ለጥፋቱም በአንድ በኩል በግልጽ መጠየቅ ያለበት ማንኛውም አካል ከሕግ በላይ ስለማይሆን እንዲጠየቅ፣ በሌላ በኩል የአገርን ምጣኔ ሀብት የሚያደቅና የሕዝብን ሞራል የሚጎዳ የፕሮጀክት መቧተትን የማረም ወሳኝ ዕርምጃ በድኅረ ጉባዔው ከኢሕአዴግ የሚጠበቅ ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ ከዚሁ ተነጥሎ የማይታየው በብድርም ሆነ ባልተገባ መንገድ ጥቅም የማጋበስ አካሄድ ወደ ግለሰቦች የነጎደ የአገርና የሕዝብ ገንዘብ ተመልሶ ለአገር ጥቅም እንዲውል ሥራዎች መጀመር አለባቸው፡፡ ለዚህ ወሳኝ ጉዳይ ሕዝቡ በእኔነት ስሜት እንዲተባበር ማድረግም ለውጡን ይበልጥ ለማሳለጥ ይበጅ ይሆናል፡፡

እዚሁ ላይ ከላይ ያነሳነውና ለምጣኔ ሀብታዊው ለውጥም በእጅጉ የሚያስፈልገው ብሎም ሕዝቡን ያሳተፈ እርምት የሚያሻው፣ ቢያንስ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጠውን በነፃነት የመንቀሳቀስንም ሆነ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ በሕጋዊ መንገድ ሠርቶ የመኖር መብትን የማስከበሩ ወሳኝ ሥራ ነው፡፡ በተለይ የለውጥ አብዮት ይበልጥ ተቀስቅሶባቸው በነበሩት ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የግል ባለሀብቶች (የውጭ ዜጎችም ጭምር) በተለይም ባለትልልቅ ኩባንያዎች ችግር ውስጥ መውደቃቸው ሊሸሸግ አይችልም፣ አይገባም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ለብሔራዊ ደኅንነት ዋስትና የሆነውን ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቅርና የተፈጠሩ ዕድሎችም ሲመክኑ ታይተዋል፡፡ በተለይ የማዕድን ምርት፣ የእርሻ ኢንቨስትመንትና መሰል ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ደግሞ የከፋ ክስረት ላይ ናቸው፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉም ተንገጫሰግጮ ፍሬን እንደያዘ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በብዙዎቹ የአገሪቱ ክልሎች ከሌላ አካባቢ መጥተው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎችም፣ እንኳንስ ተረጋግተው ሥራቸውን ሊቀጥሉ ይቅርና የመኖር ዋስትና እየተቸገሩ ሀብታቸውንም የሚያደርጉበት እያጡ በመባዘን ላይ ናቸው፡፡ አቅም ያለውም ወደ አዲስ አበባና ወደ ትውልድ ቀዬው መፍለስን ብቸኛ አማራጭ እያደረገ መሆኑ ቁርጠኛ መፍትሔን ይሻል፡፡ ከዚህ አንፃር የሕዝብ መሳቀቅና ሥጋት እንዲወገድ የአገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ለውጥና ተሃድሶ ያመጣው ሕዝብ ከመንግሥትና ከዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር ተሠልፎ ችግሮችን እንዲያስተካክል መደረግ አለበት፡፡ አሠላለፉ በአንድ በኩል በየትኛውም የፖለቲካ እምነትና አቋም ውስጥ ቢሆን የአገር አንድነትና አብሮነትን ሳይሸረሽር፣ ከዚህ ብኋላ (በነፍጥ ለመብት የሚታገለው ሁሉ ወደ ሰላማዊ ትግል ገብቶ እያለ) ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለውን የመብት ትግል ብቻ አማራጭ በማድረግ፣ አሁን ያለውን መንግሥትና የፀጥታ ኃይል በማክበርና በእኔነት ስሜት በማገዝ ለውጡን አስተማማኝ ማድረግ አለባቸው፡፡ ኢሕአዴግም በአስቸኳይ ይህንኑ ተግባር ወደ መሬት የማውረድ ጉዳይ ላይ ማነጣጠር አለበት፡፡

 ሕዝብን ያሳተፉ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችን ማውጠንጠን!

በየትኛውም የሠለጠነ አገር ቢሆን አንድ ጊዜ የተጻፈ ሕገ መንግሥት የሚባል ነገር የለም፡፡ አገርና ትውልድ ብሎም ውጫዊ ሁኔታው በሚያስገድደው ልክ የሕገ መንግሥት ማሻሻያን ማድረግ ያለና የተለመደ ነው፡፡ በእኛም አገር ይነስም ይብዛም 24 ዓመታት የተመራንበትን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ወደ ሌላ ትውልድ እናስቀጥለው ከተባለ ያለ ጥርጥር ማሻሻያዎችን ማድረግ ግድ ነው፡፡ ሕገ መንግሥትን ለማሻሻል                                                                                                                                                                                                                                                                                                                         ኢሕአዴግ ባለፈው ተሃድሶው ጉዳዩን ለማየት ፍላጎት ማሳየቱና ራሱ ሕገ መንግሥቱ ለመሻሻል ያለው አመቺነት አጋዥ ሆነው ይገኛሉ፡፡ መዘንጋት የሌለበት ግን በምን ያህል ፍጥነትና የሕዝብ ተሳትፎ መጠን (በዚህ ውስጥ የምሁራኑና የፖለቲከኛው ተሳትፎ አለ) ማሻሻያው ይጀመር የሚለው ነው፡፡ እዚህ ላይ እስካሁን የፖለቲካ ተፎካካሪው ሁሉ ወደ አገር እየገባ በደመነፍስ ፌስቲቫልና ጫጉላ ሸርሽር ላይ መጠመዱ እንጂ፣ ከመንግሥት ጋር ስለማሻሻያ ሕግጋትና መዋቅሮች ምክክር አለመጀመሩም በድክመት ይነሳል፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ወገኖች የምርጫ ሕጉ ተስተካክሎ በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቋቋምና አዲስ ሕገ መንግሥት ሲመሠረት የሚደርስ ተግባር እንደሆነ የሚናገሩ አሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በፍጥነት እንዲሻሻል የሽግግር መንግሥት መመሥረት ነበረበት እስከማለት የሚደርሱም አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ነገሩን አሁን ካለው ኢሕአዴግ መራሹ ውስጥ ኃይል ለውጥና የማሻሻያ ዕርምጃ አንፃር መመልከት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ በዚህ ጸሐፊ እምነትም ሆነ ብዙዎች እንደሚናገሩት፣ የአናቅጽቱ ቅደም ተከተል እንደተጠበቀ ሆኖ በርከት ያሉ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ግን ሕዝብን ያሳተፈና የዜጋውን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብትን ሳይሸራርፉ ለመተግበር የሚረዱ ሕግጋትን የማካተት (ለምርጫ ሕጉ መሻሻል መሠረት ይመጣል) ተግባር ነው፡፡

በሌላ በኩል አሁን በርከት ያሉት ክልሎች በወሰንና የማንነት ጉዳይ እየተብላሉበት ያለውን አጀንዳ አለዝቦ፣ በፌደራል ሥርዓቱም ውስጥ ሆነን ጠንከር ያለ አገራዊ አንድነትና አገራዊ ብሔርተኝነትን ለመገንባት የሚያስችሉ ሕገ መንግሥታዊ ምሰሶዎች መተከል ይኖርባቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ለብሔረሰቦች መብት መከበር ዋስትና ናቸው በሚል ተካተው ለዘመናት ሕዝቡ ቅሬታ የሚሰነዝርባቸውን (አንቀጽ 39 ልብ ይሏል) ድንጋጌዎችን ማጤንና በሕዝብ ማስወሰንም ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አሁን በአገራችን እየናሩ መጥተው የግጭቶች መነሻ የሆኑት የክልሎች ወሰን፣ የማንነት ጉዳይና በአንዳንድ አካባቢዎችም ከጎረቤት አገሮች ጋር በምንዋሰንባቸው ድንበሮች ላይ የሚታዩ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች አንገብጋቢ የፖለቲካ ትኩሳቶቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ፈለጉም አልፈለጉም፣ በአንድ አገር ውስጥ እንደሚኖር ሕዝብ በጥናት ላይ የተመሠረተ ጥቅምና ጉዳታቸው እየቀረበ፣ በሕግና በሥርዓት በተለይም ሕዝቡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየወሰኑ (በሕዝበ ውሳኔም ጭምር) መፍትሔ እንዲያገኙ ካልተደረገ መጭው ጊዜ ከቀውስ የምንወጣበት ላለመሆኑ ዋስትና አይኖርም፡፡ በተለይ አንዱ ወገን ጠያቂ ሌላው ከልካይ መምሰሉ በሕገ መንግሥታዊነት ካልታረመ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ አንድ አብነትን መዘን የአዲስ አበባን ጉዳይ እንጥቀስ፡፡ ከተማዋን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የወል መዲና ናት ከማለት አልፈን፣ የአፍሪካ ዋና ከተማና የዓለም ዲፕሎማቶች መቀመጫ ስንል ከርመን፣ አሁን እየመጣ ያለው የፖለቲካ ውዝግብ ግን ‹‹የእኔ ነች አንተን አያገባህም›› ዓይነት ባለቤትነት ዓይነት ንትርክና ግጭት መጠፋፋት ውስጥ የሚከት መሆኑ በገሃድ ታይቷል፡፡ ተመሳሳይ ቀውስ አስነሺ ውዝግቦች እንደ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ሐረርና ሌሎች ከተሞችን መነካካቱም አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ወሳኝ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢና አፋጣኝ ዕርምጃ የሚሻ ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ አገራዊ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ብቻ ሳይሆን፣ አረረም መረረም ያለፈበትን የትግል ታሪክ የሚመጥንና ለአፍሪካም በአርዓያነት የሚጠቀስበትን ተግባር ለመፈጸም ያለው የመጨረሻ ዕድል አሁን የምንገኝበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይኼንን ዕድልም በተለይ በ11ኛው ጉባዔው የለውጥ ፈላጊነቱንና የተሃድሶው አመራር አጋርነቱን አሳይቷል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ውሳኔው ሁሉ ግን በተግባርም ‹‹አፍ ከልብ ሆኖ›› ቁርጠኝነትና ሕዝብ አሳታፊነትን ጨምሮ አገር የማዳን፣ ብሎም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ለትውልድ የማስተላለፍ አደራውን ሊወጣ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...