Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትከሕግ በላይ ሆኖ ሕግ ማስከበር ብሎ ነገር የለም

ከሕግ በላይ ሆኖ ሕግ ማስከበር ብሎ ነገር የለም

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ሕዝብ ራሱ በራሱ እያስተዳደረ ነውን? መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር ተገናኝቶልን? ሕዝብ ተወካዮቹን (ተወካዮች የሚባሉትን) ተወካዮች ደግሞ ራሳቸው አስፈጻሚውን መቆጣጠርና መግራት የቻሉበት አስተዳደር አለን? የሚሉ ጥያቄዎችን እንኳን በግልጽ መሰማት አልፈቅድ ብሎ የኖረው የኢትዮጵያ መንግሥት አፈናና ጭቆና፣ ኢዴሞክራሲያዊነትና ኢፍትሐዊነት ያኮማተራትን ቅስምና ሐሞት የሚያነቃቃ፣ የተዳፈነ ጆሮና ልቦናን መልሶ የሚከፍት ፖለቲካ ውስጥ መግባት የጀመረው ከ2010 ዓ.ም. መጋቢት የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አመራር በኋላ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት 24ኛው የፓርላማ ንግግር (የዙፋን ዲስኩር) ከገዥው ፓርቲ ውጪ የሌላውን ሕዝብ ልብ መሳብ የሚችል አቅም ይዞ ተደምጧል፡፡ የአንድ ፓርቲ አባላት የሆኑ ተወካዮች/እንደራሴዎች የሞሉት ባለ 547 ምክር ቤት የፕሬዚዳንቱን ዓመታዊ የመክፈቻ ንግግር የሰሙትም፣ ‹የመንግሥት ተጠሪ›› የሚባለው የገዥው ፓርቲ የምክር ቤት ውስጥ አዛዥ ናዛዥ በገጠመላቸው ጆሮ አይደለም፡፡

የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ (በሥራ ዘመናቸው መጀመርያና በየዓመቱ መጀመርያ) የሚያቀርበው የመክፈቻ ንግግር ተራ የቢሻን ንግግር አይደለም፡፡ እንዳፈቀደና እንዳመቸ፣ እንዳጋጠመም የሚደረግ ንግግር አይደለም፡፡ እንደ ነገሩም ቢሆን፣ ብዙም ባይታወቅም የተለያየ ደረጃ ባላቸው ደንብና መመርያ የተደነገገ ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አሠራር መመርያ መሠረት፣ ንግግሩ የመንግሥት የፖሊሲና የሕግ ጉዳዮች ዕቅድ ይፋ ማድረጊያና ማሳወቂያ ነው፡፡

- Advertisement -

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማካሪ ጉዳዮች ኮሚቴ ባወጣው መመርያ መሠረት ደግሞ፣ የፕሬዚዳንቱን የመክፈቻ ንግግር ማን እንደሚያዘጋጀው ንግግሩ የሚያካትተውንም ይዘት ይናገራል፡፡ ዓመታዊው የመክፈቻ ንግግር የመንግሥትን ፖሊሲ የሚያንፀባርቅ ስለሆነ የሚዘጋጀው በመንግሥት ነው፡፡ በይዘትም ረገድ ያለፈውን ዓመት የመንግሥት ዋና ዋና የሥራ እንቅስቃሴዎችና ውጤቶች፣ ዋና ዋና አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች፣ በበጀት ዓመቱ ሕግ ሊወጣላቸው የታሰቡ ጉዳዮችን ሊያካትት ይገባል ይላል፡፡

የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት በ2011 ዓ.ም. መስከረም የመጨረሻ ሰኞ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ . . . ያለፈውን ዓመት አፈጻጸም በአጭሩ፣ በዋናነት ግን የ2011 በጀት ዓመት የመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫ አመላካች ነጥቦችን›› አንስተዋል፡፡ ወደ ሥልጣን የመጣውን አዲሱን አመራር የወለደውን ‹‹ጥልቅ ክፍተቶቻችንንና ችግሮቻችንን›› ገልጸዋል፡፡ አገሪቱን በአሳሳቢ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንድትገኝ ያደረጋት የአገራችንን ሰላምና መረጋጋት ፈተና ውስጥ ያስገባው የመንግሥት ችግር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በመንግሥቱ የመሳሳት ወይም የማጥፋት መጠንና ልክ ላይ ላንስማማ እንችል ይሆናል እንጂ፣ በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደም ከመንግሥት አንደበት ሲነገር ያልተሰማ ብዙ ነገር ሰምተናል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት ቁልፍ የዴሞክራሲ አስተዳደር ተቋማትን በማጠናከርና የአሠራር ነፃነታቸውን ከማስጠበቅ አንፃር የተከተልነው ያልተሟላ አካሄድም ሕዝባችን አማራጭ የትግል መድረኮች እንዳይኖሩት፣ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ የሆኑ ተቋማትም ጎልተው እንዳይወጡ ትርጉም ያለው የሲቪል ማኅበረሰብ እንቅስቃሴም እንዳይኖር ምክንያት ሆነው ቆይተዋል፤›› ብለውናል፡፡

‹‹ከወሳኝ ባለድርሻ አካላት ጋር አገራዊ መግባባት ባልተፈጠረበት የፖለቲካ ምኅዳር ለብቻችን ስንዳክር ቆይተናል፤›› ብለውም ነግረውናል፡፡ ‹‹ዜጎቻችን በፍትሕና በአስተዳደር በደል ሲሰቃዩና ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሲጣሱ እያየን በዕለት ተዕለት የአጭር ጊዜ ዕይታዎች ተውጠን ችግሮችን ከምንጮቻቸው የሚያደርቁ ዘመን ተሻጋሪ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃዎችን ሳንወስድ ለረዥም ጊዜ ቆይተን ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ መሠረታዊ ለውጦች የማድረግ ጉዳይ የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸው፣ መንግሥታቸው ያቀደውን የለውጥ ቢጋር አመላክተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ስለ‹‹ገለልተኛ ዘመን ተሻጋሪ›› ተቋማት ተናግረዋል፡፡ ‹‹የምርጫ ሕግ ሥልጣን በኃይል ከሚያዝበት አዙሪት ወጥተን በሐሳብ ክርክርና ልዕልና በሕዝብ ምርጫ ሥልጣን ወደሚያዝበት ሰላማዊና የሠለጠነ ሥርዓት የሚያሸጋግር የጨዋታ ሕግ ስለሆነ፣ መንግሥት በልዩ ትኩረት ይመለከተዋል፤›› ብለዋል፡፡ ዳኛው ከእኔ ሆኖ፣ እንዲያውም ዳኛውም የእኔ ሆኖ፣ እኔ ሆኜ፣ እኔ በሰፊ ሜዳ አንተ በቀጭን ገመድ ላይ እንሽቀዳደም በሚል ዓይነት የጨዋታ ሕግ ሲመራና ሲሠራ የኖረው ኢሕአዴግ፣ በገዛ ራሱ ውስጥም ቢሆን የተሻለ ሐሳብንና የተሻለ ችሎታን በክርክር የማንጠር፣ በድምፅ የመለየት እስትንፋስ ተጠግቶት የማያውቅ ኢሕአዴግ ይህን ያህል ጥፋቴን አውቄያለሁ የሚል ወገን ከውስጡ በመውጣቱ ምክንያትም ‹‹ወፌ ቆመች›› ሊባል ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡

የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር ከተሰማ፣ በዚህም አማካይነት ምክር ቤቱ ሥራውን ከጀመረ በኋላ የመጀመርያው ተከታዩ የምክር ቤቱ አጀንዳ (ቅድሚያ የሚሹ ሌሎች ሥራዎች ከሌሉ በስተቀር) በፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ላይ ውይይት ማድረግ ነው፡፡ ባለፉት 23 ያህል የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ንግግሮች ላይ ፓርላማው ውይይት ሲያደርግ የሚያውቁ እንደሚያስታውሱት ‹‹ሞሽን››፣ ‹‹ሞሽን›› ሲባል የድጋፍ ሞሽን ሲቀርብ፣ የማሻሻያ ሞሽን ሲባል፣ በድጋፍና በማሻሻያ ሞሽን ላይ የድጋፍ ሞሽን ሲቀርብ፣ በውይይቱ መጨረሻም ላይ የመንግሥት አቋም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲገለጽና ሲብራራ፣ ከዚያም ድምፅ ተሰጥቶ ውይይቱ ሲጠቃለል እናውቃለን፣ እናስታውሳለን፡፡

በዘንድሮ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር ላይ የሚደረገው ውይይት እንደ ቀደሙት አብዛኞቹ ውይይቶች እጅ እጅ የሚሉ፣ አለዚያም ትርጉም የለሽ የሆኑ፣ ለግብር ይውጣና ለአንደበት ወግ ያህል የሚከወኑ አይሆኑም ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህንንም (በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ለሚደረገው ውይይት የሚያስፈልገው ጊዜ ሲወሰን ቢያንስ የስምንት ቀን ጊዜ ይሰጣልና) ወደፊት እናየዋለን፡፡ የውይይቱ ዓይነትና ገጽታው ከወትሮ ይለያል ብዬ ተስፋ ሳደርግ፣ ተወራርጄም ዕዳ ስገባ ምክንያቴ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ነው፡፡ አዲሱ ሁኔታና በእሱም ላይ የተመሠረተው ለውጥ በገዥው ፓርቲ በራሱ ውስጥ መለያየት ፈጥሯል፡፡ በግንባሩ አባል ድርጅቶችና በእያንዳንዱ ድርጅት መካከል ከፋም ለማም የሐሳብ ልዩነት፣ ልዩ የመሆን ‹‹ነፃነት›› ተፈጥሯል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አባል ድርጅቶችና አባላት እንደ ድሮው የድርጅቱ፣ እንዲሁም የድርጅቱ አመራር የገደል ማሚቱዎች አይደሉም፡፡ የምክር ቤቱ አባላት እንደ ድሮው መናገር፣ መደገፍና መቃወም ያለባቸውን የሚሰፍርላቸው ቢያንስ ቢያንስ አንድ ወጥ አካል የለም፡፡ በየአባል ድርጅቶች ውስጥ አነሰም በዛም ለውጥ ተቃዋሚዎች ስላሉ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ የሚካሄደው ውይይት ‹‹የሕግ የበላይነት››ን፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት›› ይከበር ማለትን፣ እንዲሁም ከትጥቅ ትግል ወደ ሰላማዊ ትግል በጥሪ የመጡትን የተለያዩ አካላት የባህርይ አረማመድን ተገኝ አድርጎ የለውጡ ተቃዋሚዎች ድምፅ ሊሰማ ይችላል፡፡ የመሆን ምናልባት ያለው አንደኛው ነገር ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ውጥረቱና ዝምታው እንደ ነገሠ የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር ያመለከተው፣ የሕግ ጉዳዮች መርሐ ግብርና የፖሊሲ ዕቅድ የ‹‹ዝምታ ሴራ›› ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል፣ ጊዜው ሲደርስ እናየዋለን፡፡

ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ የዓብይ አህመድ መንግሥት፣ ‹‹የተጀመረው የዴሞክራይዜሽን ሥራ ከማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስና ዘለቄታዊ ሰላም፣ የሕግ የበላይነት የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ›› በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቼ እሠራዋለሁ ካላቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና በመጀመርያ የተጠቀሰው፣ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተጋረጡብን ትልቅ ፈተና ነፃነትንና ሥርዓት አልበኝነትን ባለመለየት መረን የለቀቀ ሕግና ሥርዓትን የማያከብር›› እንቅስቃሴዎችና ድርጊቶች መስፋፋታቸው ላይ ነው፡፡

‹‹እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች የዜጎችን ደኅንነትና የአገሪቱን ሰላም በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተኑ ይገኛሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ዜጎች ክቡር ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ለዘመናት ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ጥለው ተሰደዋል፡፡ በጥቅሉም የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በሕግ የበላይነት መርህ የማይመራ አገር ዕጣ ፈንታው ደግሞ የማኅበራዊና የፖለቲካዊ ቀውስ መስፋፋት፣ ግጭት፣ ጥፋትና መበታተን ብቻ ነው፤›› በማለት ችግሩን የገለጸው የፕሬዚዳንቱ የመክፈቻ ንግግር፣ ‹‹ስለሆነም በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የእያንዳንዱን ዜጋ ደኅንነትና ነፃነት ለማስከበር አስፈላጊውን ሁሉ ዕርምጃ እንዲወስዱ ይደረጋል፤›› ብሏል፡፡

እውነት ነው ግጭት፣ ንብረት መውደም፣ ዘግናኝ ጥቃትና ማፈናቀል አሁንም አልቆሙም፡፡ እንዲያውም እንደ ከዚህ በፊቱ እዚህም እዚያም ብልጭ ከማለትም አልፈው፣ ከለውጡ በፊት ያልታዩ የሚሊዮኖች መፈናቀሎች የአገር አጀንዳ ሆነዋል፡፡

ከለውጡ በፊት የደረሰው ግጭት፣ ጥፋትና ውድመት ዋነኛ መነሻና መገለጫ የሆኑ መተንፈሻ ያጡ፣ የተጠራቀሙ የሕዝብ ቅሬታዎች አጋጣሚ እየጠበቁና እየፈነዱ አደጋ አድርሰዋል፡፡ በብሶት ቁጣዎች ውስጥ ብልጭ ያሉ ጭፍን ጥቃቶችም ለበለጠ አደጋ ሥጋት ሆነው ኖረዋል፡፡ ለለውጥ በተካሄደው ትግልም ውስጥ ማውደምን፣ ማጥቃትን፣ ማፈናቀልን፣ መንግሥትን ለማራድ በመሣሪያነት ሲጠቀምባቸው ዓይተናል፡፡

የግጭቱ፣ የውድመቱ፣ የጥቃቱና የማፈናቀሉ የዚህ ሁሉ ጣጣ ምንጭ ግን አሁንም በግልጽና በይፋ፣ ሳይድበሰበስና ቁልጭ ብሎ ገና መነገር አልተቻለም፡፡ ችግሮቹ በራሱ በሥርዓቱ ውስጥ የነበሩና ያሉ፣ ሥርዓቱ የተሟሸበት አመለካከትና የአገዛዙ ዘይቤ ያደረሳቸው በጥላቻ፣ በመሸካከር፣ በጠባብ ዕይታዎች የመማቀቅ ውላጆችና ውጤቶች ናቸው፡፡ ማኅበራዊ ተዛምዶንና አናሳ ጉድኝትን ከልማት አቅም ሥርጭት፣ ተግባብቶ ከመተዳደርና ከማደግ ዕድል ጋር ያልተገናዘበ፣ ሕዝብና ምሁራኑ በደንብ ያልመከሩበትና በሒደትም ሊቃና የሚችል ሆኖ ያልተቃኘው አከላለል ጠንቀኛ መርዝ ተክሏል፡፡ በአገሪቱ ያለው ብሔራዊ/ክልላዊ የአስተዳደር መዋቅር ተስማምቶ ለመተዳደርና በአመቺነቱ ሳይሆን በመሬትና በተፈጥሮ ሀብት ድርሻ ማረጋገጫነት እንደሆነ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በዚህም ምክንያት የባለቤትነት ‹‹ተፈጥሯዊ›› መብትን ለማረጋገጥና የቀረ ሒሳብ ለማወራረድ፣ እንዲሁም ድንገት መገንጠል ቢመጣ እየተባለ ግዛት ቆጠራ ውስጥ መግባት ወጋችንና ታሪካችን ሆኗል፡፡  

የአንድ ወረዳ ወይም ቀበሌ በሌላ ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ መግባት ወይም ገብቷል ተብሎ ይህ መሬትን በመንጠቅ ሲተረጎም ኖሯል፡፡ የብሔር/ብሔረሰቦችን መልክዓ ምድራዊ ይዞታ ፍፁም አድርጎ ከመወሰዱ የተነሳ አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ጋር ያለው ግንኙነት የፀብና የግጭት እንዲሆን አድርጓል፡፡ የክልሎች የራሳቸው የብቻ ባለቤትነትና ጎጆኛነት፣ በየክልሉ ውስጥ ያሉ ሰብሰብ ብለው የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን የብቻ ጎጆ ወጪነትን (ክልልነት፣ ዞንነት ይታወቅልኝ) እንዲያቀነቅኑ ቀስቃሽና ሰባኪ ሆኗል፡፡ ነባርና መጤ፣ ባለቤትና ባይተዋር መባባልም ከፍ ያለ መፈናቀልና መባረር የሚባል አደጋ አምጥቷል፡፡ መፈናቀል ማለት ደግሞ ሰብዓዊ መብትን በመርገጥ ብቻ ሳይወሰን፣ በዘመናት የተገነባ ማኅበራዊ መገማመድን የሚበጣጥስ ብሎም ወደ መፋጀት የሚመራ አደጋ ነው፡፡

በተለይ በአሁኑ ጊዜ፣ በለውጡ ጊዜ ‹‹ብሔራዊ ክልልን›› ለማስፋት ወይም የክልሉን ዳር ድንበር ለማስከበር፣ ወይም የብሔር/ብሔረሰብን ታሪካዊ የእምዬ ምድር ጫና ለማቃለል፣ እንዲሁም ‹‹ባለቤቶቹ›› ያልወደዷቸውን ‹‹ባዕዳን››፣ ‹‹መጤ››ዎች ለማፅዳት በሚል ሰበብ የሚካሄድ ግጭት ለውጡን ከማጨናገፍ በቀር ለውጡን በጭራሽ አይጠቅምም፡፡ ትናንት በትግሉ ወቅት ብጥስጣሽ ብሔርተኝነትና የፌዴራል መንግሥት ድጎማን በቀጥታ የመቃረጥ ፍላጎት ግጭት አስነስቶ ማውደምና ማፈናቀል፣ ያላግባብም ቢሆን የትግል መሣሪያ መሆን እንደቻለ ‹‹ትምህርት›› ሆኗልና ዛሬ መንግሥትን አስደንግጦ ክልል ወይም ልዩ አስተዳደር ልሁን የሚል ወይም ሌላ አድብቶ የኖረን ፍላጎትና ጥያቄ ለማሳካት፣ ወይም ሥጋቴ ያለውን ማኅበረሰብ ለመመንጠር ይህ የሽግግር ወቅት ጥሩ አጋጣሚ ነው ብሎ ሊጠቀምበት እየሞከረ ያለም ‹‹ደጋፊ›› እንዳለ ሕዝብም መንግሥትም እጅግ ልብ ሊለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የአገሪቱን ሕግና ሥርዓት የማስከበር፣ ሕገወጥነትን የመግታትና ወንጀል የመከላከል የመንግሥት ሥራ ከምንጊዜውም በላይ በዕውቀትና በሙያ ብቃት ላይ የተመሠረተ (እንደ ቀድሞው ከሕጋዊ ተቃውሞ ጋር መተናነቂያ ያልሆነ) በተለይም የተጠቀሱትን አደጋዎች ከግንዛቤ ያስገባ መሆን አለበት፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ ሕገ መንግሥታዊ ቦታ በተሰጠው በዚህ ዓመታዊ ንግግራቸው ‹‹ . . የሕግ የበላይነት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ በሕግ የበላይነት መርህ የማይመራ አገር ዕጣ ፈንታው ደግሞ የማኅበራዊና የፖለቲካዊ ቀውስ መስፋፋት፣ ግጭት፣ ጥፋትና መበታተን ብቻ ነው፤›› ብለው ሊከተል የሚችለውን አደጋ ካመላከቱና ካስጠነቀቁ በኋላ፣ በዚህ ረገድ የመንግሥትን ተግባርና ዕርምጃ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የእያንዳንዱን ዜጋ ደኅንነትና ነፃነት ለማስከበር አስፈላጊውን ሁሉ ዕርምጃ እንዲወስዱ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መተማመኛና ዋስትና የተሰጣቸውን የማንኛውም ሰው (የዜጎች ብቻ አይደለም) መብቶችና ነፃነቶች የማክበርና የማስከበር የመንግሥት ሥራ፣ እንዲሁም የሕዝብ ደኅንነትና የአገር ሰላም የማስጠበቅ የመንግሥት ግዴታ ሁልጊዜም ቢኖር ያለበት የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ እንዲያውም በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የአስተዳደር ዕርከን ሕዝብን ከየትኛውም ዓይነት ጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በዝንጉነትም ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይወጣ ለሚደርሰው ጥፋት ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ሕግ የማስከበርን የመንግሥት ተግባር ሰንከላና ትርጉም የለሽ ሲያደርገው የቆየው ዋነኛው ችግር፣ የመንግሥት ‹‹የራሱ ከሕግ በላይ ሆኖ የሕግ የበላይነት››ን አስከብራለሁ የማለት ሕመሙ ነው፡፡

ዜጋም ሆነ ዜጋ ያልሆነ ወይም ዜግነት የሌለው ሰው ጭምር ከግለሰብ አድራጊ ፈጣሪነት ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥታዊ ካልሆነ አካል አድራጊ ፈጣሪነትም ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ከራሱ ፈላጭ ቆራጭነትና አድራጊ ፈጣሪነት የሚጠበቅበት፣ የመንግሥት ሕግ አስከባሪነት፣ የመንግሥት ከሳሽነት፣ የዓቃቤ ሕግ ለሕግ ተከራካሪነት ወደ ዜጎች/ሰዎች መብት ድፍጠጣ የሚንሸራተት ከሆነ የሕግ የበላይነት የውሸትና የማስመሰል ሆኖ ይቀራል፡፡ በተለይም አሁን የምንገኝበት ልዩ ሁኔታና የዓብይ አህመድ መንግሥት የሚመራው ለውጥ የደረሰበት ገና ያልጠና የዕድገት ደረጃ፣ ልዩ ጥንቃቄዎችን የሚጠይቅ ጥበብና አመራር ያስፈልገዋል፡፡ የመንግሥት የሥልጣን አካላት ሕግ አስከባሪነት ከመብትና ነፃነት አክባሪነት ጋር መጣላት የለበትም፡፡ ከሕዝብ ለመብት ቀናዒ ከመሆን ጋር የሚላተምም አይደለም፡፡

ለውጡ ሰላም ይፈልጋል፡፡ ለውጡ የሚጠይቀው የፖለቲካ ሰላም በስነጋ ከተገኘ ፀጥታና ረጭታ የተለየ ነው፡፡ ለውጡ በፈጠረው አዲስ ሁኔታ ውስጥ ግርግርና ድንግዝግዝ ያለ ነገር እንዳይፈጠር ለመከላከልም የመንግሥትን ግልጽነት፣ የአገሪቱን የለውጥ ኃይሎችና አገር ወዳዶች ሁሉ በሰላም ጥያቄ ላይ አንድ ላይ መግጠምን ይጠይቃል፡፡ ፓርቲዎችና የለውጥ ኃይሎች ሁሉ ከውጭ የገቡትም ጭምር የጋራ በሆኑ ሕግና ሰላም የማስከበርና ዴሞክራሲን የመገንባት የወል አደራ ላይ መግጠማቸውና መገናኘታቸው የግድ ነው፡፡ በዚህ ላይ መስማማት ከተቻለ ለውጡና ትግሉ የሚፈልገውን ሰላም ካገኘ፣ የሁሉም የትግል ኃይሎች ልብ አንድ የሰላማዊ መንገድ ላይ ከተገናኘ፣ አፈንጋጭ ቡድን ቢኖር ቁልጭ ብሎ እንዲወጣና ሕዝብ እንዲያውቀው ያስችላል፡፡ በአጠቃላይ ሕግ የማስከበርና ለውጡ የሚያስፈልገውን ሰላም የማስፈን ተግባር ለዴሞክራሲያችን ወሳኝ የሚሆነው፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሰላም ፈተና የለውጥ ኃይሎች (በገዥው ፓርቲም ውስጥ በተቃውሞውም ውስጥ) ትንቅንቅ ከሰላማዊና ከሕጋዊ መድረክ ውጪ መሆኑ ነው፡፡

ለውጡ ድል ይቀዳጅ ዘንድ ያጋጠሙትን ጣጣዎች ለማሸነፍ ከሚበጁ ተግባራት መካከል ሕግ ማስበር አንዱና ዋናው ነው፡፡ ሕገወጥነትን የመግታት የመንግሥት ዕርምጃ የራሱንም ሕግ አክባሪነት በግድ ይጠይቃል፡፡ ሕግ የማስክበርና ሕገወጥነትን የመዋጋት ጉዳይ የሁሉም እንዲሆንና የሕዝብም ድጋፍ እንዲኖረው፣ የመንግሥት ሕግ የማስከበር ተግባር ራሱም ችግር እንዳይኖርበት ጠባቂው፣ ችግር ሲፈጠርም አጋላጭና ተፋራጁ እንዲበዛ ለማድረግ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከሽፍንፍንና ድብስብስ አሠራሮች በተጨማሪ በቅርብና ሰሞኑን እንደታየው የጨዋታው ሕግ የመንግሥት የውስጠ ሚስጥር መሆኑም በሕዝብ ውስጥ ውዥንብር ይፈጥራል፡፡ የመንግሥትንም ሕግ የማስከበር ሥራ ውሽልሽል ያደርጋል፡፡ የተለያየና ውጥንቅጥ አቋም ካላቸው ቡድኖች ጋር ውጭ አገር ድረስ ተሄዶ ተፈረመ ስለተባለው ስምምነት መኖር ሳንሰማ፣ በስምምነቱ ይዘት ላይ የሚነሳው ውዝግብ መነሻ የመንግሥት አሠራር ግልጽ አለመሆኑ ነው፡፡

በጉልበት ማሰብን እየታገልንና እያሟሸሽን ሕጋዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ሁሉም ዘንድና በሕዝብም በመንግሥትም ውስጥ እንዲጠናከር ማድረግ፣ ከሕግ በላይ ሳይሆኑ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የመንግሥት ዋነኛ ተግባርና ግዳጅ መሆን አለበት፡፡ ዓብይና የለውጥ ቡድኑ እንዲሁም ለውጡን የሚመራው መንግሥት ስህተት ሠርተውላቸው ከሕዝብ ጋር ለማቆራረጥ ከማድባትና ነገር ከመሥራት የማይመለሱ መኖራቸው የሚያደናግር እውነት መሆኑን ተረድተን፣ ከሕግ በላይ ሳይሆኑ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን እንጣር፡፡ ከሕግ በላይ ሆኖ የሕግ የበላይነት ማስከበር የለምና፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...