Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለበርበራ ወደብ የማስፋፊያ ግንባታ የዱባይ ኩባንያዎች ስምምነት ተፈራረሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዲፒ ወርልድ በድሬዳዋ የሎጂስቲክስ ማዕከል የመገንባት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል

የዩናትድ ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ የሆነው ዲፒ ወርልድ፣ በሶማሌላንድ የበርበራ ወደብን ለማስፋፋት የሚያስችል ግንባታ ለማካሄድ ከሌላው የዱባይ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ባለፈው ዓመት በተደረገ ስምምነት መሠረት ዲፒ ወርልድ የበርበራ ወደብን የማስተዳደር ኃላፊነትን ከሶማሌላንድ መንግሥት ከተረከበ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በተደረገው የሦስትዮሽ ድርድርና ስምምነት መሠረት፣ ኢትዮጵያ የ19 በመቶ ድርሻ ከወደቡ በመግዛት፣ ዲፒ ወርልድ በበኩሉ የ51 በመቶ፣ እንዲሁም የሶማሌላንድ መንግሥት ቀሪውን 30 በመቶ ድርሻ በመያዝ ወደቡን የማስፋፋት ሥራዎች እንደሚሠሩ አስታውቀው ነበር፡፡

ይህንን ተከትሎም ተስማሚዎቹ እንደየድርሻቸው መጠን ኢንቨስት ለማድረግ በተስማሙበት መሠረት፣ የመጀመርያውን ምዕራፍ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ የ101 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅና እ.ኤ.አ. በ2020 እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀውን ግንባታ ለማካሄድ በሶማሌላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ የፊርማ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው ሐሙስ፣ ጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት የዱባዩ ሻፋ አል ናህዳ ተቋራጭ ከዲፒ ወርልድና ከሶማሌላንድ መንግሥት ጋር ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን በሶማሌላንድ መንግሥት በኩል የፈረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳዓድ ዓሊ ሺሬ (ዶ/ር)፣ የሻፋ አል ናህዳ ተቋራጭን የሚያስተዳድረው የሻህፋ ግሩፕ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አብዶሻማክ ናስር አል ሺባኒ፣ እንዲሁም የዲፒ ወርልድ የቦርድ ሰብሳቢና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሡልጣን አህመድ ቢን ሱላይም ናቸው፡፡ በስምምነታቸው መሠረት የመጀመርያው ምዕራፍ ወደብ ማስፋፋት ግንባታ የ430 ሜትር ዝርመት ያለው የወደብ ግንባታ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል፡፡ በጠቅላላው የ800 ሜትር ዝርመት ያለው ወደብ ለመገንባት የሚያስችልና ከ440 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ግንባታ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም በመጀመርያው ምዕራፍ ግንባታ የወደቡን የመርከብ ማስተናገጃ ወይም በርዝ በ250 ሺሕ ካሬ ሜትር እንደሚያሰፋው ሲገለጽ፣ በአሁኑ ወቅት ያለው የወደቡ አቅም 150 ሺሕ ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮችን የሚያስተናግድ ሲሆን፣ ወደ 450 ሺሕ ባለ 20 እና ባለ 40 ጫማ ጥምር ኮንቴይነሮች ወደ ማስተናገዱ ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት 25 ሺሕ ቶን ሸቀጥ በተለይም የምግብ ሸቀጦችን የማስተናገድ አቅሙን ወደ 40 ሺሕ ቶን እንደሚያሳድገውም ይጠበቃል፡፡

ወደቡን የማስፋፋት ፕሮጀክት ከሚያፋጥኑት ወቅታዊ ምክንያቶች መካከል የዲፒ ወርልድ ከጂቡቲ ንብረቱን ተወርሶ የመባረር ዕርምጃ አንደኛው እንደሆነ የሚያምኑት የሶማሌላንድ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ በሌላ በኩል የኤርትራና የኢትዮጵያ ሰላም ማውረድም በሶማሌላንድ በኩል ጥድፊያውን እንደሚያጠናክረው ይነገራል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው ዕቅድ መሠረት ኢትዮጵያ የወጪና የገቢ ሸቀጦቿን 30 በመቶ በበርበራ ወደብ በኩል እንደምታስተናግድ ይጠበቅ ነበር፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ከ95 በመቶ ያላነሰው የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ ሸቀጦች በጂቡቲ ወደብ በኩል እንደሚያስተናገዱ፣ በዚህም በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ለጂቡቲ እንደሚከፈል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የጂቡቲ ወደብ በየጊዜው እያደገ በመጣው የኢትዮጵያ ወጪና ገቢ ንግድ ሳቢያ የመንግሥት አማራጭ የወደብ ፍላጎት በበርበራና በፖርት ሱዳን ላይ አተኩሮ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም የጁቡቲ ወደብ በአሁኑ ወቅት ከሚያስተናግደው ከ90 በመቶ በላይ ገቢና ወጪ ንግድ ውስጥ 30 በመቶውን ወደ በርበራ፣ አሥር በመቶውን ወደ ፖርት ሱዳን ያዞራል ቢባልም፣ ያልታሰበው የኤርትራ ወደ ዕርቅ መምጣት፣ የአሰብና የምፅዋ ወደቦች የኢትዮጵያን ዕቃዎች ለማስተናገድ ዝግጅት መጀመራቸው ለሶማሌላንድ መንግሥትና የንግድ ሰዎች የሥጋት ምንጭ እንደማይሆን ቢነገርም፣ ለጂቡቲ ግን ከባድ ሥጋት መሆኑ አልቀረም፡፡

ቀድሞውንም ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ባለድርሻ መሆኗ ብዙም ያልተዋጠላት ጂቡቲ፣ የኤርትራ መምጣት ትልቅ ሥጋት እንደሆነባት በስፋት እየተነገረ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ሌሎች ወደቦችን በመጠቀም አማራጮቿን የማስፋት ፍላጎት እንዳላት መንግሥት በተደጋጋሚ ሲያስታውቅ ከመቆየት አልፎ፣ በጎረቤት አገሮች ውስጥ ወደቦችን በባለቤትነት በጋራ የማልማትና የመጠቀም ፍላጎቱን ካሳየ ወዲህ በበርበራ ወደብ የ19 በመቶ ድርሻ በመግዛት ሲሳተፍ የመጀመርያው ነው፡፡

የማስፋፊያ ግንባታ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ሲጠበቁ የውኃ ሽታ የሆኑት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አለመገኘት የከነከናቸው ጋዜጠኞች ጥያቄ ማንሳታቸው አልቀረም፡፡ የጥያቄው መነሻ መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉ ምክንያቶችን ያዘለ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ሊገኙ ያልቻሉት አገሪቱን የሚመራው መንግሥት ፓርቲ አለቆች በስብሰባ ተጠምደው መቆየታቸው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ክስተት የማስፋፊያ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት እንዳይገኙ ያስገደዳቸው ምክንያት እንደሆነ የሶማሌላንድ ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው ገልጸዋል፡፡

ባልተጠበቀ ፍጥነት ከውጥረት ወደ መግባባት የመጣው የአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሰላም ስምምነት፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሞቃዲሾ ሶማሊያን ወደ አንድ የዕርቅ ግንባር ማምጣቱ አንደኛውና ዋናው ምክንያት ነው፡፡ ይኼውም ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ፣ በሶማሌላንድና በዲፒ ወርልድ መካከል የተደረሰው የወደብ አጠቃቀምና በጋራ የማልማት ስምምነትን በመቃወም፣ ከግዛቷ አካል ከሆነችው ሶማሌላንድ ጋር ‹‹ሕገወጥ›› ስምምነት በመወደረጉ ውድቅ መደረግ አለበት የሚል ቅሬታዋን ለዓለም በማሰማቷ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስለወደብ ስምምነቱ ከሞቃዲሾ ለቀረበባት ወቀሳ የሰጠችው ምላሽ ስምምነቱ ምንም ዓይነት ሉዓላዊነት የመጋፋት አዝማሚያ እንደሌለውና ወደብ የመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ዓላማን መሠረት ያደረገ እንደሆነ በማስተባበል ነበር፡፡

ሶማሌላንድ በበኩሏ ከሞቃዲሾ ጋር በፈቃዷ ያደረገችውን አንድ አገር የመፍጠር ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. በ1991 በፍላጎቷ ማፍረሷን፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህም ሉዓላዊት አገር መሆኗን ዓለም እንዲያውቅላት ለማድረግ እየጣረች እንደምትገኝ፣ ፕሬዚዳንት አብዲ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡ ሶማሊያም ሆነች ሶማሌላንድ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለት ሉዓላዊ ጎረቤት አገሮች ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንት አብዲ፣ በበርበራ ወደብ ፕሮጀክት ሒደት ላይ ሞቃዲሾ በምንም መልኩ ጣልቃ መግባት እንደማትችል ተናግረዋል፡፡

የኤርትራ ወደ ወደብ አገልግሎት መምጣት ለበርበራ ወደብ የፉክክር ሥጋት ስለመሆኑ ከሪፖርተር ተጠይቀው፣ ፕሬዚዳንት አብዲ በሰጡት ምላሽ፣ ኢትዮጵያ ካላት የኢኮኖሚ ትልቅነትና የሕዝብ ብዛት አኳያ ሌሎች አሥር ያህል ወደቦች ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡ በመሆኑም የኤርትራን ወደ ኢኮኖሚያዊ የመጫወቻው ሜዳ መምጣትን መንግሥታቸው በአወንታዊነት እንደሚመለከተው ተናግረዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ክስተቶች የሚስተናዱበት የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ፖለቲካዊ ገበያውንም ጭምር እያጧጧፈው እንደመጣ ይነገርለታል፡፡ ከእስያ የቻይና ፍላጎት፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች መካከልም ዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስና ኳታርን ጨምሮ ሳዑዲ ዓረቢያና ኢራን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፍላጎት አላቸው፡፡ ይህ አካባቢ የኤደን ባህረ ሰላጤን ይዞ ምሥራቅ አፍሪካን ከእስያ እስከ አውሮፓና እስከ ሩቅ ምሥራቅ እስያ ያሉትን አገሮች የሚያገናኝ፣ በርካታ የንግድ መርከቦችም የሚያዘወትሩት ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቀጣና ነው፡፡

ነገሮች በዚህ ደረጃ በሚለዋወጡበት ወቅት፣ ዲፒ ወርልድ በድሬዳዋ የሎጂስቲክስ ማዕከል የመገንባት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ የዚህ መነሻው የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መሠረት፣ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ውስጥ የግል ኩባንያዎች እንዲሳተፉ እንደሚደረግና ሌሎችም አማራጭ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ታሳቢ እንደሚደረጉ የዲፒ ወርልድ የቦርድ ሰብሳቢው ሚስተር ሱሌይም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የበርበራን ኮሪደር ጨምሮ የኢትዮጵያን ምሥራቃዊ ክፍል፣ በተለይም ውጫሌ የሚባለውን አካባቢ ከበርበራ ወደብ የሚያገናኝ መንገድ የመገንባት እንቅስቃሴም ከሚጠበቁት በሶማሌላንድና በዱባዩ ኩባንያ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች