ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ የከተሙት አንድ ሺሕ የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ አባላት ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ባሻገር፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት የነበረውን የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታና የመንግሥትን አፈጻጸም ገምግመዋል፡፡
በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ላደረጉት ግምገማ በ10ኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መሠረት በማድረግና አፈጻጸሞቹን ከውጤቶቹ ጋር በማመሳከር የሚተነትን ሪፖርት ቀርቦላቸዋል፡፡
በአሥረኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ ኢኮኖሚውን በየዓመቱ በአማካይ 11 በመቶ ለማሳደግና በኢኮኖሚው ውስጥ መሠረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ግብ መጣሉን፣ የቀረበው ሪፖርት ያስታውሳል፡፡
በጉባዔው የተቀመጡ የማክሮ ኢኮኖሚ ግቦችን ለማሳካት ከጉባዔው ማግሥት ጀምሮ የተቀናጁና የተደራጁ የልማት ሥራዎች የተከናወኑ መሆኑን፣ በዚህም ከአቅርቦት አንፃር 9.5 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት በመሠረታዊ የዕድገት አማራጭ ይደረስበታል ከተባለው አማካይ ዕድገት በ1.5 በመቶ ዝቅ ያለ መሆኑንም ያስረዳል፡፡
ለተመዘገበው ዝቅተኛ የዕድገት መጠን ምክንያቶች ተብለው የተቀመጠትም፣ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው አስከፊ ድርቅ፣ በተለይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋነኛ ምንጭ በሆነው የግብርና ዘርፍ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ፣ በአገሪቱ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና የወጪ ንግድ ሸቀጦች ዋጋ በዓለም ገበያ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱን በዋናነት ይጠቅሳል፡፡
የቀረበው የግምገማ ሪፖርት ኢኮኖሚው በመቀዛቀዙ የዕድገት ቅናሽ ማሳየቱን በጥቅሉ ከገለጸ በኋላ፣ በየዘርፉ ዝርዝር ግምገማውንም አቅርቧል፡፡
የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲኖርና የኢኮኖሚውን ጤንነት ለማስቀጠል የዋጋ ንረት በነጠላ አኃዝ ተገድቦ እንዲቆይ ማድረግ ተገቢ መሆኑ አቅጣጫ ተቀምጦ የነበረ መሆኑን፣ በዚሁ አግባብም ሰፊ ሥራ በመከናወኑ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. በነጠላ አኃዝ ተገድቦ የቆየው የዋጋ ንረት ከ2009 ዓ.ም. የካቲት ወር ጀምሮ እያደገ መምጣቱን ይገልጻል፡፡
በ2010 የበጀት ዓመት የሰኔ ወር አጠቃላይ የዋጋ ንረት 14.7 በመቶ የደረሰ መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡
የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ በ2007 በጀት ዓመት ከነበረበት 12.7 በመቶ፣ በ2009 የበጀት ዓመት ቅናሽ በማሳየት ወደ 11.6 በመቶ መውረዱን ያመላክታል፡፡
ይህም በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የተቀመጠው ዕቅድ አለመሳካቱን ብቻ ሳይሆን፣ ለሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደ መነሻ የተወሰደውን የ12.7 በመቶ የታክስ ድርሻ እንኳን ማስቀጠል አለመቻሉን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የመንግሥት በጀት ጉድለት መጠንና አሸፋፈን ሁኔታ የፊሲካል ፖሊሲን ውጤታማነት ከሚያሳዩ አመለካከቶች መካከል አንዱ መሆኑን የሚያስረዳው ለጉባዔው የቀረበው የኢኮኖሚ ግምገማ ሪፖርት፣ በ2009 ዓ.ም. የመንግሥት አጠቃላይ የበጀት ጉድለት 60.2 ቢሊዮን ብር እንደነበርና ይህም በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ከሚፈቀደው ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ ሦስት በመቶ በታች መሆን አለበት የሚለውን መርህ በመጣስ በ2009 ዓ.ም. ጉድለቱ 3.3 በመቶ መድረሱን ይገልጻል፡፡
የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈጻጸምን በተመለከተ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ በ2008 ዓ.ም. 4.9 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 2.9 ቢሊዮን ብር እንደሆነ፣ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ 6.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተገኘው 2.91 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር፣ በ2010 ዓ.ም. 8.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማስግኘት ዕቅድ ተይዞ የተገኘው 2.83 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የግምገማ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግር የግብርና እና የኢንዱስትሪው የማምረት አቅም ዝቅተኛ መሆን እንደሆነ፣ ለታየው የወጪ ንግድ መቀዛቀዝ ዋናው ምክንያት መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም የወጪ ንግዱን ለመምራት አመራሮች ያሳዩት ቁርጠኝነት ዝቅተኛ መሆን፣ የወጪ ንግዱን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጎ አለመገንዘብ፣ በግብይት ሰንሰለት የሚታዩ ተግዳሮቶች ሳይፈቱ መቀጠላቸው፣ ኮንትሮባንድን አለመቆጣጠር፣ የሚመረተው የወጪ ንግድ የምርት ጥራት ጉድለት ለአፈጻጸሙ ጉድለት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ መወቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ታስቦ የነበረው ከኢንዱስትሪ ምርቶች የወጪ ንግድ ውስጥ፣ የማኑፋክቸሪንግ የወጪ ንግድ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት 0.6 በመቶ፣ በ2009 ዓ.ም. ወደ 0.5 መውረዱን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ የግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ ድርሻም በተመሳሳይ ጊዜ ከ3.4 በመቶ ወደ 2.7 በመቶ ዝቅ ማለቱን ይገልጻል፡፡
‹‹ሌላው ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ውስጥ ላለመሆኗ ዋነኛው መገለጫ፣ በዓለም ገበያ ያላት ድርሻና ተወዳዳሪነት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ ነው፤›› ሲል ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
የመንግሥት ልማት ድርጅቶችንና ፕራይቬታይዜሽንን በተመለከተ የተቀመጠው አቅጣጫ መንግሥት የማይተካ ልማታዊ ሚናውን በብቃት መወጣት እንዲችል፣ በቅድሚያ በእጁ የሚገኙትንና በግሉ ዘርፍ እንደሚካሄዱ የታመነባቸውን ተቋማት (ኢንተርፕራይዞች) ወደ ግሉ ዘርፍ ሙሉ በሙሉ ማዘዋወር እንደበር ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ለልማት የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የተጀመረውን ፈጣን ዕድገት ለማስቀጠልና ሕዝቡን በየደረጃው የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ እንዲሁም የገበያ ጉድለቶችን ለመሙላት መንግሥት በጥንቃቄና በተመረጡ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች የልማት ድርጅቶችን በማቋቋም መግባት እንዳለበት በአሥረኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ አቅጣጫ መቀመጡን ያስታውሳል፡፡
በዚህ ረገድ የተፈጸመው ተግባር የዕቅዱ ፍፁም ተቃራኒ መሆኑን የግምገማ ሪፖርቱ በከፍተኛ ችግርነት ተችቶታል፡፡
የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውጤታማ መሆን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ የገበያ ሥርዓትን በፍጥነት በመገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው፣ የልማት ድርጅቶች በኦፕሬሽንም ሆነ በፕሮጀክት አተገባበር ደካማ አፈጻጸም ሲኖራቸው ደግሞ የገበያ ሥርዓቱን በማመሰቃቀልና መንግሥት በገበያው በተመረጠ ሁኔታ ጣልቃ በመግባት፣ የኢኮኖሚ ዕድገቱን በማሳለጥ የሚኖረውን አቅም እንደሚያዳክመው ይገልጻል፡፡ ይኼንን ሁኔታ በተለይ የከፋ የሚያደርገው የውጭ ምንዛሪ ሳያመነጩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠቀሙና የውጤታማነት ችግር ያለባቸው ሲሆን፣ የምንዛሪ እጥረቱን በማባባስ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ፍጥነት የመጉዳት ውጤት እንደሚኖራቸው ይተነትናል፡፡ ከዚህም በመነሳት ‹‹በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ይኸው ነው፤›› በማለት ችግሩን ያስቀምጣል፡፡ በአማራጭ የመፍትሔ ሐሳብነትም የሚከተለውን ያመላክታል፡፡
‹‹በጠባብ ዕይታ ላይ በመመሥረት የአፈጻጸም ችግራቸውን አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ወጥቶ ስትራቴጂካዊና ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖሊሲ ሪፎርም በማካሄድ፣ በፍጥነት ወደ ግል የማዘዋወሩን ሥራ የማፋጠንና በአዲስ መልክ የሚገባባቸውን ፕሮጀክቶች በጥንቃቄ የመምራትና በበቂ ጥናት ላይ ተመሥርቶ የማፋጠን ሥራ ይጠይቃል፤›› በማለት፣ በቅርቡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን በከፊልና በሙሉ ለመሸጥ የወሰነው፣ ከዚህ በመነሳት መሆኑን የግምገማ ሪፖርቱ ያስታውቃል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ዕቅድና አፈጻጸምን በተመለተም ዕቅዱና አፈጻጸሙ የማይገናኙ መሆናቸውን፣ የግምገማ ሪፖርቱ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም በሁለኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ማገባደጃ ዓመት ማለትም በ2012 ዓ.ም. 12,208 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ለማሳካት፣ በዚህ ዕቅድ መሠረትም እስከ 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ 6,889 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ላይ መደረስ እንዳለበት ግብ የተጣለ ሲሆን፣ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ማሳካት የተቻለው የማመንጨት አቅም 4,351 ሜጋ ዋት መሆኑን የግምገማ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
ለዚህ ዕቅድ አለመሳካት በመንግሥት እንዲገነቡ የታቀዱት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ፋይናንስ መንግሥት ማግኘት ባለመቻሉ፣ ለዚህም እንደ ምክንያትነት መንግሥት ያለበት የተወዘፈ የውጭ ብድር ጫና አዲስ ብድሮችን እንዳያገኝ ወይም በሌላ አነጋገር የአገሪቱ የመበደር አቅም በተጠቀሰው ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ በመምጣቱ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
ይኼንን የፋይናንስ ጫና ለማቃለል የግል ባለሀብቶች ኃይል በማመንጨት ለመንግሥት በሽያጭ እንዲያቀርቡ የመፍትሔ አማራጫ ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም፣ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ከመንግሥት ዋስትና የሚፈልጉ በመሆኑና ይህም በዋናነት የኃይል መሸጫ ታሪፉ ዝቅተኛ መሆን ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት ያላቸውን ፍላጎት እንደቀነሰው ያስረዳል፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት ያለው የኃይል አቅርቦት ከፍላጎት ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋነኛ ማነቆ መሆኑን፣ ከአቅርቦትና ከፍላጎት አለመጣጣም በተጨማሪ የመነጨውን ኃይል ያለ እክል ማሰራጨት አለመቻሉ ሌላው ችግር መሆኑን ያመለክታል፡፡
የማዕድን ዘርፉ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን በማፋጠን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆን፣ በተጨማሪም ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ማዕድናት እንዲመሩት በማድረግ ከውጭ በግዥ የሚገባውን ለመተካት ዕቅድ ተይዞ እንደነበር ያስረዳል፡፡ በዕቅዱ መሠረት ከማዕድን ዘርፍ በ2009 ዓ.ም. 700.8 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማሳካት የተቻለው ግን 214.2 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 27.43 በመቶ ብቻ እንደነበርና ይኼ አፈጻጸም በ2008 ዓ.ም. ከተገኘው 310.6 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ31 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱንም ይገልጻለ፡፡ ለዚህ ዝቅተኛ አፈጻጸም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ መሆን፣ የሎጂስቲክስ አለመሟላት፣ በክልሎች የኮንትሮባንድ መስፋፋትና የመንግሥት መዋቅሮች አለመናበብን በምክንያትነት ያነሳል፡፡
ጉባዔው ያሳለፋቸው የወደፊት አቅጣጫዎች
የኢሕአዴግ 11ኛ ጉባዔ የአገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም በስፋት ከገመገመ በኋላ በአብዛኛው ቀደም ብሎ በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ሙሉ በሙሉ ማሳካት ባይቻል እንኳን፣ የተሻለ አፈጻጸም ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት እንዲንቀሳቀስ በዋነኛነት ወስኗል፡፡
ኢኮኖሚው መሠረታዊ የዕድገት አማራጭ ተብሎ የተቀመጠው 11 በመቶ ዕድገት ላይ ሙሉ በሙሉ መድረስ ባይቻል እንኳን ባለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚገባ፣ መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት እንቅስቃሴው ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራና ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልግ ሀብት በአገር ውስጥ ቁጠባ እንዲገኝ፣ የተጀመረው የአገር ውስጥ ቁጠባን የማጠናከር ሥራ በቀጣይ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ወስኗል፡፡
የዋጋ ንረት ወደ ነጠላ አኃዝ እንዲመለስ በማድረግ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር እንደሚገባም እንዲሁ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ከፊሲካል ፖሊሲ አንፃር የመንግሥት ወጪ አመዳደብ በካፒታል ኢንቨስትመንትና በድህነት ቅነሳ ላይ አሁንም ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ከዚህ አንፃር የአገሪቱን ገቢ ማሳደግ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው የወሰነው የኢሕአዴግ ጉባዔ በተለይ ትልቁ የአገሪቱ የገቢ ምንጭ የሆነው የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) የንግዱ ማኅበረሰብ ላለመክፈል የኪሳራ ሪፖርት የማቅረብ ባህርይ እያሳየ በመሆኑ፣ ገቢው ባለፉት ጊዜያት መቀነሱን ጠቅሶ በዚህ ላይ ጠንካራ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት በመግለጽ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ እንዲቀመጥ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም በተሳሳቱ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሽፋኖች በሚያጭበረብሩ ላይና በኮንትሮባንዲስቶች ላይ ጠንካራ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ ለዚህም ከፍተኛ አመራሩ የቅርብ ክትትልና ቅኝት ውስጥ ሆኖ ተግባራዊ እንዲደረግ ወስኗል፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የውጭ ምርት ላኪ ባለሀብቶችን መረጃ በመያዝ፣ ወደ ውጭ ለመላክ የሚያነሳሱ ተግባራዊ ልዩ ድጋፎችን መከወን፣ የሚደረግላቸው ድጋፍም ካስገኙት የውጭ ምንዛሪ መጠን ጋር እንዲያያዝ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
ምርቶቻቸውን ለመላክ ጫፍ ላይ የደረሱ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይኼንን ማድረግ ያልቻሉ ባለሀብቶች ዝርዝር መረጃ ተይዞ ድጋፍ ማድረግና አፈጻጸምን መከታተል፣ በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የገቡና ወደፊትም የሚገቡ ባለሀብቶች ቶሎ ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ የክትትልና ድጋፍ አሠራር መዘርጋት እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ዕቃዎችና ምርቶች መካከል ከአምስት ሺሕ በላይ የሚሆኑትን በአገር ውስጥ መመረትና መተካት እንደሚቻል ዝርዝር አቅጣጫ ተቀምጦ የነበረ ቢሆንም፣ አለመፈጸሙን በመጥቀስ በቀጣይ ከተለዩት ውስጥ የትኞቹ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ መፈጸም እንደሚችሉ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በመለየት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀመርም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የሌላቸውን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለውጭ ኩባንያዎች በመሸጥ የሚገኘውን ውስን የውጭ ምንዛሪ፣ በቁጠባና በውጤታማነት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች ቅድሚያ በመስጠት መጠቀም እንደሚገባም ሌላው የተላለፈ አቅጣጫ ነው፡፡
የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እስኪሻሻል ድረስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚጠይቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠቸውን በመለየት ማስቀደም እንደሚገባ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚጠይቁ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማዘግየት ወይም አለመጀመር ጊዜያዊ የመፍትሔ አማራጭ ሆኖ ተግባራዊ እንዲሆን ጉባዔው ወስኗል፡፡
ግንባታቸው የተጓተቱ ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ተለይተው በከፍተኛ አመራሩ ልዩ ድጋፍና ክትትል አሠራር በመዘርጋት እንዲጠናቀቁ ማድረግ እንደሚገባም፣ ጉባዔው የትኩረት አቅጣጫ ካላቸው መካከል ሌላው ውሳኔ ነው፡፡