የታዋቂዋ ነጋዴ ወ/ሮ አኪኮ ሥዩም ድርጅት የሆነው ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ፣ በዜግነት ጀርመናዊ ከሆኑት አቶ ዮናስ ካሳሁን ጋር ለሰባት ዓመታት ባደረጉት የፍትሐ ብሔር ክርክር ተረታ፡፡
ክርክሩ የተካሄደው አቶ ዮናስ ከውጭ ያስገቧቸው ሦስት የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች በስማቸው ተመስግበውና ሕጋዊ ከሆነ አካል የባለቤትነት ማረጋገጫ (ሊብሬ) ተሰጥቷቸው ሳለ፣ ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ግን ማሽነሪዎቹ በአቶ ዮናስ ስም የገቡ ቢሆንም ክፍያውን የፈጸመው ድርጅቱ መሆኑን በመግለጽ ነበር፡፡
ክርክሩ የተጀመረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በወቅቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ ለኦርኪድ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡
ይሁንና አቶ ዮናስ ውሳኔውን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢሉም፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቶ ነበር፡፡ የፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ተፈጽሞበታል በማለት አቶ ዮናስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን በማቅረብ የቃል ክርክር አድርገዋል፡፡
የሰበር ሰሚ ችሎት የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔና በችሎቱ ያቀረቡትን ክርክር ከሰማ በኋላ ባደረገው ምርመራ፣ ማሽነሪዎቹ በአቶ ዮናስ ስም ወደ አገር ውስጥ የገቡ መሆናቸውንና ከሕጋዊ ተቋም የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ (ሊብሬ) የተሰጣቸው መሆኑንና ንብረትነቱ የአቶ ዮናስ መሆኑን በማረጋገጥ፣ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ሰጥቷል፡፡
ንብረቶቹ በወቅቱ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዋጋ የነበራቸው በመሆኑ፣ የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ መሣሪያዎቹን የወሰደው በኪራይ ስለሆነ በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር የኪራይ ዋጋ እንዳለበትም ተገልጿል፡፡