Monday, February 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቡራዩና ዙሪያው የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ድርጊት ምርመራ እንዲቀጥል ውሳኔ ተሰጠ

በቡራዩና ዙሪያው የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብር ድርጊት ምርመራ እንዲቀጥል ውሳኔ ተሰጠ

ቀን:

ማስረጃ ያልቀረበባቸው ተጠርጣሪዎች ሊፈቱ ይገባል ያሉ ዳኛ በሐሳብ ተለይተዋል

ከአንድ ወር በፊት በቡራዩና ዙሪያው ከተፈጸመ ግድያ፣ አካል ጉዳትና ንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙ ከ20 በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ፣ ምርመራው መቀጠል ያለበት በሽብር ድርጊት ወንጀል መሆን እንዳለበት ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጠ፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ እንደገለጸው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተጠርጣሪዎቹ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ፣ በአገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ባለመቀበልና የተቀሰቀሰው ግጭት እንዲስፋፋና እንዲባባስ አድርገዋል፡፡ በድርጊቱ በመሳተፍና የገንዘብና የተለያዩ ዕርዳታዎችን በማድረግ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድልና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል ብሏል፡፡

በመሆኑም የሽብር ድርጊት መፈጸማቸውን በመግለጽ፣ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀናት እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ እንዳመለከቱት፣ መርማሪ ፖሊስ እየከሰሳቸው የሚገኘው ባልፈጸሙት ድርጊት ነው፡፡ በተሳትፎም ሆነ በገንዘብ ድርጊቱን ረድተዋል መባሉ ሐሰት መሆኑን በማስረዳትና የሽብር ተግባር ፈጽመዋል የሚያስብላቸው አንድም ማስረጃ ያልቀረበባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ በሽብር ተግባር ሊያስጠረጥራቸውም ሆነ ጊዜ ቀጠሮ ሊያስጠይቅባቸው የሚያስችል ነገር ስለሌለ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት ድርጊት ሽብርተኝነት ነው? ወይስ አይደለም?›› የሚለውን መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተጠርጣሪዎች አቶ አብርሃም ተረፈ፣ አቶ መንግሥቱ ዋቆ፣ አቶ ፀጋዬ ተረፈና አቶ ቢሉሱማ ደበበ በተባሉት ግለሰቦች ላይ፣ ላይ መርማሪ ፖሊስ ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ሲመረምር ከአንደኛው ተጠርጣሪ ቤት ኮምፒዩተር ሲወጣ በእማኝነት ያየ ምስክር ከመኖሩ በስተቀር፣ ፖሊስ ያቀረበባቸው ማስረጃ የለም፡፡ ድርጊታቸው የሽብር ሊባል እንደማይችልና ተጨማሪ የቀጠሮ ጊዜ ሊጠየቅባቸው እንደማይገባ በመጥቀስ ዳኛ አበራ አማረ በውሳኔ ሐሳብ ሲለዩ፣ ‹‹ድርጊታቸው ሽብርተኝነትን ያሳያል›› በማለት በዳኛ ሙሉቀን ተሻለና በዳኛ ከበደ ታደሰ አብላጫ ድምፅ ተወስኗል፡፡

በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ሲመረምር ፖሊስ ያስረዳው የተጠርጣሪዎቹ ድርጊት ሽብርን የሚያመላክት በመሆኑ፣ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2011 መሠረት የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት መጠየቁን ጠቁሟል፡፡

በሁከትና ብጥብጥ ንብረት መውደሙና በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ፣ ሽብር መፈጸሙን እንደማያመለክትና አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (3)ን የማያሟላ በመሆኑና የሽብር ተግባር ሊያስብል ስለማይችል፣ መርማሪ ፖሊስ በቂ ማስረጃ ሳይኖረው ተጠርጣሪዎችን አስሮ ማቆየት ስለሌለበት የዋስ መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲፈቱ መጠየቃቸውንም ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከመርማሪዎች የወሰደውን ስድስት የምርመራ መዝገብ መርምሮ የደረሰበት ድምዳሜ፣ መርማሪ ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ያገኘው የስልክ መረጃ፣ ተጠርጣሪዎች ከማን ጋር ተደዋውለው እንደተነጋገሩና እንደተገናኙና ብጥብጥ ለማስነሳት ይነጋገሩ እንደነበር መረጃው እንደሚያሳይ መረዳቱን ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም በመደራጀት የተወሰኑ ሰዎችን በድንጋይና በዱላ በመደብደብ ጉዳት ማድረሳቸውንም ፍርድ ቤቱ ከምርመራ መዝገቡ መረዳቱን በመግለጽ የሽብር ድርጊትን የሚያመላክት በመሆኑ፣ ምርመራው በሽብር ድርጊት ወንጀል እንዲቀጥል በአብላጫ ድምፅ ውሳኔ ሰጥቶ ለኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

ተጠርጣሪ አቶ አብርሃም ተረፈ፣ አቶ ቢሉሱማ ደበበና አቶ መንግሥቱ ዋቆ ግን በመርማሪ ፖሊስ በአንድ ወር ውስጥ የቀረበባቸው ማስረጃ አለመኖሩን በመጠቆም፣ ሊታሰሩ የሚገባው ሕግን መሠረት ባደረገ ሁኔታ መሆኑን በመጥቀስ በሐሳብ የተለዩት ዳኛ የልዩነት ሐሳባቸውን ለችሎት በንባብ አሰምተዋል፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ዋስትና ተከልክሎ በእስር ሊቆይ የሚችለው በሕጉ ተደንግጎ በሚገኘው መሠረት እንጂ፣ ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን ዋስትና ተነፍጎ መሆን እንደሌለበትም አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያቀረበው ምንም ማስረጃ አለመኖሩ ነው፡፡ በቂ የሆነ ጥርጣሬ ስለሌለ በዋስትና ከእስር ሊለቀቁ እንደሚገባም በመጠቆም በሐሳብ ተለይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...