ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድጋፍና ምሥጋና በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሠልፍ በወጣው ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን የቦምብ ጥቃት በማስተባበር ተጠርጥረው ላለፉት አራት ወራት በምርመራ ላይ በሚገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋም ሹም አቶ ተስፋዬ ኡርጌን በሚመለከት፣ ፍርድ ቤት ለመርማሪ ፖሊስ ከማስጠንቀቂያ ጋር የመጨረሻ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ትዕዛዙን የሰጠው፣ መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው የምርመራ ተጨማሪ ጊዜ ውስጥ የሠራውንና ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ያቀረቡትን አቤቱታ ከሰማ በኋላ ነው፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በተሰጠው አሥር ቀናት ውስጥ የሦስት ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን በመግለጽ፣ በመስቀል አደባባይ የፈነዳው ቦምብ ቅሪት ከአቶ ተስፋዬ ቢሮ ተገኝቷል ከተባለው ቦምብ ጋር መመሳሰል አለመመሳሰሉን ለመለየት የጠየቀውን የቴክኒክ ምርመራ እየጠበቀ መሆኑን፣ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ ተጨማሪ አሥር ቀናት ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ባቀረቡት አቤቱታ እንዳስረዱት፣ ከታሰሩ አራት ወራት ሆኗቸዋል፡፡ በእነዚህ ወራት ውስጥ ለበርካታ ጊዜ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፡፡ መርማሪው ግን ሁልጊዜ አለመጨረሱን እየገለጸ፣ ተጨማሪ ጊዜ በመጠየቅ መቀጠሉንና ፍርድ ቤቱ ግን ቀደም ብሎ በነበረው ችሎት ለመጨረሻ ጊዜ ብሎ እንደፈቀደለት አስረድተዋል፡፡ አሁንም የመጨረሻ መጨረሻ ተብሎ አጭር ቀን እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም አቶ ተስፋዬ የመገናኛ ብዙኃን እሳቸውን በሚመለከት የሚያስተላልፉት መረጃ ከእውነት የራቀና በየቢሯቸው ተቀምጠው በድረ ገጽ ላይ ያገኙትን በመሆኑ፣ በእሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸው ላይ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቦምብ በቤታቸው ሳይገኝ እንደተገኘ አድርገው በመዘገብ መብታቸውን እየተጋፉ ስለሆነ፣ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ መርማሪው ሥራውን እየሠራ እንዳልሆነ ገልጾ፣ የቴክኒክ ምርመራ ውጤቱን በሰባት ቀናት ውስጥ ከምርመራ መዝገቡ ጋር በማያያዝ፣ ምርመራውን እንዲያጠናቅቅ ከማስጠንቀቂያ ጋር ለጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የመገናኛ ብዙኃንም መርማሪ ፖሊስ በችሎት ከተናገረውና ተጠርጣሪም ከሚናገሩትና ፍርድ ቤት ከሚሰጠው ትዕዛዝ ውጪ እንዳያስተላልፉ አስጠንቅቆ፣ ከዚህ ያለፈ ሪፖርት ቢደረግ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡