ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ካቢኔያቸውን እንደገና አደራጅተው፣ ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ሃያ አባላት ያሉትን ካቢኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አፀድቀዋል፡፡ አሥር ሴቶች የተካተቱበትና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንደሆነ እየተነገረለት ያለው ይህ ካቢኔ ከፊቱ ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቀዋል፡፡ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው የማሻሻያ አዋጅ መሠረት የታጠፉና ካሁን በኋላ የማይኖሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ይፋ የተደረጉ ሲሆን፣ አዳዲስ መሥሪያ ቤቶች ተዋውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት እንደገና የተደራጁት ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተሿሚዎች በትምህርት ዝግጅት፣ በሥራ ልምድ፣ በብቃትና በሥነ ምግባር ተመርጠው ለኃላፊነት ታጭተው መቅረባቸው ከተረጋገጠ አመርቂ ውጤት መጠበቅ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በተሿሚዎች ማንነት ላይ መግባባት ከተቻለም፣ የተሻለ የሥራ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ያግዛል፡፡ ከዚህ ቀደም የኮታ ሹመት ያደረሰውን ጥፋት የሚገነዘብ ማንም ቅን ሰው፣ በአዲሱ አደረጃጀትና አሿሿም ላይ የመግባባትን አስፈላጊነት ይረዳል፡፡ ማንም ሰው በብሔሩ ወይም በእምነቱ ሳይሆን በብቃቱ መሾም እንዳለበት መለመድ አለበት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ማሻሻያ ለወራት ሲሠራበት እንደነበር ጠቁመው፣ ጠንካራ አስፈጻሚ አካላትን ለማደራጀት እንደሚያስችል አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሰላምን ማረጋገጥ፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ሕገ መንግሥቱና የሕግ የበላይነት ተከብረው ከሌብነት የፀዳ አሠራር እንዲሰፍን የሕዝብ ፍላጎት እንደሆነ መንግሥታቸው መረዳቱን አክለዋል፡፡ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ማለትም የምርጫ ቦርድ፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የመሳሰሉት አደረጃጀታቸው ተፈትሾ እንደገና እንደሚደራጁ ጠቁመዋል፡፡ ለአሠራርም ሆነ ለአመራር ያስቸገረ መዋቅርንም ሆነ ተቋምን አስተካክሎ ማደራጀት ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በየጊዜው አዳዲስ አደረጃጀቶችን ማስተዋወቅ አንድ ቦታ ላይ ሊገታ ይገባል፡፡ የአሁኑ አደረጃጀት በእርግጥ በሚገባ ጥናት ተደርጎበት ከሆነ ተሿሚዎቹ ተረጋግተው እንዲሠሩ ከማስቻሉም በላይ፣ ተቋማት የበለጠ ተጠናክረው እንዲወጡ ያግዛል፡፡ መዋቅር በማፍረስና መልሶ በማደራጀት ምክንያት በርካታ ችግሮች ማጋጠማቸው አይዘነጋም፡፡
ወደ ተሿሚዎች ጉዳይ ስንመለስ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምናወሳው የብቃት ጉዳይን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህ የብቃት ጉዳይ መሠረታዊ መሆኑንና ለዚህም የሚያስፈልገው የትምህርት ዝግጅት ወሳኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋማቱ ከሌብነት የፀዳ አመራር እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቀዋል፡፡ ይህ በተግባር ከተሳካ ማንንም ቢሆን ያስደስታል፡፡ ተሿሚዎች ከላይ ከተጠቀሱት መመዘኛዎች በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ተነሳሽነትና ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ጋር የሚመጣጠን አስተሳሰብ ባለቤት ሊሆኑ ይገባል፡፡ በራሳቸው የሚተማመኑና የሚወስኑ፣ ላመኑበት ዓላማ ወደኋላ የማይሉ፣ አለቃቸው የሚላቸውን ብቻ ሳይሆን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ቀድመው መገኘት የሚችሉ፣ የበታቾቻቸውን በአርዓያነት የሚመሩ፣ በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ ፈጣን ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚተጉ፣ በአድርባዮችና በአስመሳዮች የማይታለሉ፣ የግል ጥቅማቸውን የማያሳድዱ፣ የሰዎችን ግላዊ ነፃነት የሚያከብሩና አገራቸውን ሌት ተቀን ለማገልገል ፍፁም ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት በቢሮክራሲው ውስጥ የሚታወቁ ብልሹ አሠራሮችን በማስወገድ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን እንጂ የተወሰነ ቡድን ለማገልገል የተሾሙ እንዳልሆኑም በቅጡ ማሰብ አለባቸው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ በአሥር ሴቶች (ሃምሳ በመቶ) መሞላቱ አዲስ ክስተት ነው፡፡ ተሿሚዎቹም የሚመሯቸውን ተቋማት ከሌብነትና ከብልሹ አሠራር እንደሚያፀዱም ተስፋ እንደተጣለባቸው ተገልጿል፡፡ የሴቶች በመንግሥት ሥልጣን ትልቅ ኃላፊነት ላይ መገኘት ጥሩ ነው፡፡ ይህም ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያነት አልፎ አድናቆትም እየተቸረው ነው፡፡ የአገሪቱን ክብረ ወሰን በሰበረ የካቢኔ አደረጃጀት ለሴቶች ትልቅ ሥፍራ የመስጠት ውሳኔ፣ ሴቶች አመራር መስጠት አይችሉም የሚለውን የተለመደ አባባል ውድቅ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡ የወንድ የበላይነት በነገሠበት ኅብረተሰብ ውስጥ የሴቶች ወደ ሥልጣን በብዛት መምጣት፣ የወደፊቶቹን ታዳጊዎች የበለጠ የሚያነቃቃና የሚያደፋፍር እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበትና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማለፍን የሚጠይቅ ጭምር በመሆኑ፣ ተሿሚዎቹ በፆታ ተዋጽኦ ብቻ ለዚህ ኃላፊነት እንደበቁ ማሰብ የለባቸውም፡፡ ሥልጣን ፍትሐዊ ሆኖ ለዜጎች እንዲዳረስ የሚፈልግ ማንም ቅን ዜጋ፣ ብቃት በምንም ዓይነት ሁኔታ ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት ይገነዘባል፡፡ ሴት ተሿሚዎችም በዚህ ስሜት ብቃታቸውን በሚገባ አሳይተው ለቦታው እንደሚመጥኑ ማሳመን አለባቸው፡፡ ይኼንን ሲያደርጉ ሌሎች የፆታ አቻዎቻቸውም ሆኑ ወጣቶች ጠንክረው ወደ ኃላፊነት ይመጣሉ፡፡ ሴቶች ከማንም ድጋፍ ጠባቂ መሆን እንደሌለባቸው ተገቢውን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የመከላከያና የደኅንነት ተቋማትን በበላይነት በብቃት መምራት እንደሚችሉ ጭምር ማስመስከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በብቃት እንጂ በድጋፍ መታመን እንደሌለበት በተግባር የማሳየት አደራ አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ነው፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› በሚባለው ኋላቀርና አሮጌ አስተሳሰብ፣ ተሿሚ ቢጤዎቹን ለመጥቀም ብቻ ሥልጣን ላይ የሚንጠላጠልበት አባዜ ሊቆም ይገባል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥም ሥልጣንን ከብሔር፣ ከሃይማኖትና ከተለያዩ ፍላጎቶች አንፃር እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቃረጥ ያለመ ዘመን ያለፈበት አስተሳሰብ መወገድ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹን ያለ አድልኦና መድልኦ የሚያገልግል ጠንካራ ሹም ሥልጣን እንዲይዝ በርትቶ መታገል ሲገባ፣ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚል አላስፈላጊ አጀንዳ ፈጥሮ መወዛገብ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ይልቁንም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እያንዳንዱ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤት አመራር ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት መንገድ እንዲያከናውን ማገዝ፣ ሲያጠፋ ደግሞ የሰላ ሒስ በማቅረብ ማስተካከል ለአገር ይጠቅማል፡፡ አለበለዚያ የመንግሥት ሥልጣንን በብሔርና በሃይማኖት መሥፈርት ውስጥ ለመቀርቀር መሞከር አገር ያጠፋል እንጂ ጥቅም የለውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ቁማር ደካሞችን መቀፍቀፊያ ነው፡፡ እያንዳንዱ ወይም እያንዳንዷ ተሿሚ በተነገረላቸው መጠን አፈጻጸማቸውን እያሳዩ ነው? ወይስ ፋይዳ ቢስ ሆነዋል? የሚለውን ጊዜ ሰጥቶ በአንክሮ ማየት ለእርምት ይበጃል፡፡ ተሿሚዎችም ነቃ ብለው ኃላፊነታቸውን በብቃት የሚወጡት ብርቱ ቁጥጥር እንዳለባቸው ሲረዱ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ሥልጣን ከተረከቡ ስድስት ወራት አስቆጥረው ሰባተኛው ውስጥ ናቸው፡፡ እነዚህ ጊዜያት በርካታ መልካም ነገሮች የታዩባቸውን ያህል ፈታኝም ነበሩ፡፡ የሥልጣን ሽግግሩ ከተከናወነ በኋላ ኢትዮጵያ ወዴት መጓዝ እንዳለባት ካመላከቱበት የመጀመርያው የፓርላማ ንግግራቸው አንስቶ ከሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ የማይደፈሩ ውሳኔዎችንም በማስተላለፋቸው ይበል ተብለዋል፡፡ አንድ የታፈነ ኅብረተሰብ በአንፃራዊ ነፃነት መኖር በሚጀምርበት ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮችም በስፋት ይስተዋላሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከገባችበት ማጥ ውስጥ ወጥታ ወደፊት መገስገስ የምትችለው ብቃት ባለው አመራር ብቻ ነው፡፡ ይህ አመራር ደግሞ በግልም ሆነ በጋራ ለወቅቱ ፈተናዎች ምላሽ የመስጠት አቅሙ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር እንደ መሆኗ መጠን፣ አመራሩ እንደ ወርቅ በእሳት ይፈተናል፡፡ በዚህ ደግሞ ሕዝብን ከጎኑ የማሠለፍ ብቃቱና ንቃቱ ከፍተኛ መሆን አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ተከብሮ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥርጊያውን ማመቻቸት የሚቻለው፣ በግልም ሆነ በቡድን ብርቱና ጠንካራ መሆንን ማስመስከር ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትቶ ለታይታ ያህል ሥልጣን ላይ መቀመጥ ፋይዳ የለውም፡፡ የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ዋና ተቆጣጣሪ መሆናቸውን በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የአሁኑ ሹመትም ሆነ የተሿሚዎች ጉዳይ በዚህ መንገድ ሊታይ ይገባል!