Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ33 ሚሊዮን ዶላር የብረት ፋብሪካ ተገንብቶ ተመረቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች የተቋቋመው ኢኮስ የብረታ ብረት ማምረቻ ኃላፊነቱ የግል ማኅበር፣ በ33 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባው ፋብሪካ በይፋ ተመርቆ ተከፈተ፡፡

ኩባንያው በዱከም ከተማ ያስገነባውን ፋብሪካ ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲያስመርቅ፣ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጨምሮ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ኩባንያው የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል ከዓመታት በፊት በራሳቸው አማካይነት በተደረገለት ግብዣ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ ፋብሪካው ተጠናቆ በማየታቸው ደስተኛ እንደሆኑና በመንግሥትም በኩል አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግለት አስታውቀዋል፡፡

ኢኮስ ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስዶ መንቀሳቀስ የጀመረ ሲሆን፣ የፋብሪካውን ግንባታ በማጠናቀቅ ሥራ ጀምሯል፡፡ ኩባንያው በመጀመሪያው የፕሮጀክት ምዕራፍ በዓመት 210 ሺሕ ቶን የግንባታ ብረቶችንና ገመድ ተሸካሚ ምሰሶዎችን የማምረት አቅም እንዳለው ታውቋል፡፡

ነገር ግን ኩባንያው አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ከውጭ ጥሬ ዕቃዎችን ማስገባት ስለማይችል፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት እስከ 15 ሺሕ ቶን ብቻ ለማምረት እንደሚገደድ አስታውቋል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግሩ እንደሚፈታ ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሼል ሲ.ቾ፣ ችግሩን ለመፍታት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዋናነት የሚያስፈልጉትን የጥሬ ዕቃዎች ከደቡብ ኮሪያ፣ ከዩክሬንና ከቱርክ ኩባንያዎች እየተረከበ የሚገኘው ኩባንያው፣ በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምር የምርቱን መጠን እንደሚጨምር ተገልጿል፡፡

 በሁለተኛ ምዕራፍ የግንባታ ፕሮጀክቱ በዓመት 500 ሺሕ ቶን የአርማታ ብረትና የተለያዩ የብረታ ብረት ምርቶችን ለማምረት የሚያገለግለውን የቢሌት ጥሬ ዕቃ የሚያመርት ፋብሪካ የመክፈት ዕቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

በዓመት እስከ 200 ሺሕ ቶን የሚሆኑ ውድቅዳቂ ብረቶችን ከአገር ውስጥ በመሰብሰብ እንደ ጥሬ ዕቃ ለመጠቀም ኩባንያቸው ዕቅድ እንዳለው፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናግረዋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት እንደ ዕቅዱ ስኬታማ ከሆነ መንግሥት በዓመት ለብረታ ብረት ጥሬ ዕቃዎች ከሚያወጣው ከፍተኛ ወጪ እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ያድናል ተብሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት 14 ያህል የአርማታ ብረት አምራቾች በሥራ ያሉ ሲሆን፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መንግሥት የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት የተለያዩ የቀረጥና የታክስ እገዛዎች ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አምራቾቹ ያላቸውን አቅም ገንብተው የአገር ውስጥ ገበያውን እንዲቆጣጠሩና ከውጭ የሚመጣውን ብረት እንዲተኩ ቢጠበቅም፣ አሁንም ከፍተኛ መጠን ያለው የብረት ጥሬ ዕቃ በውጭ ምንዛሪ እየተገዛ ወደ አገር ውስጥ እየገባ ነው፡፡

የብረት አምራቾቹም የሚያስፈልጉዋቸውን ጥሬ ዕቃዎች ማለትም የወዳደቁ ብረቶችን ከአገር ውስጥ ተጠቅመው እንዲያመርቱ ቢጠበቅም፣ አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች የወዳደቁ ብረቶችን በብዛትና በጥራት ማግኘት አዳጋች መሆኑ ይነገራል፡፡

በዚህም ምክንያት የአገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ለብረታ ብረት  ጥሬ ዕቃዎች ግዥ እየወጣ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች