Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሌባን ሌባ ለማለት እንድፈር!

ሌባን ሌባ ለማለት እንድፈር!

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

አንድ በሥራው የማከብረውና የምወደው ነባር ጋዜጠኛና የትልቅ መሥሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት መኮንን የነበረ፣ ባልሳሳት መንግሥት ለሲቪል ሰርቪሱ ደመወዝ በዓመት 18 ቢሊዮን ብር  እንደሚያወጣና ሲቪል ሰርቪሱ ግን ስድስት ቢሊዮን ብር ብቻ ሥራ እንደሚያከናውን የሚጠቁም መረጃ በመገናኛ ብዙኃን ሲያስተላልፍ ሰምቻለሁ። የጥናቱ ወጤትና አጠናኑ ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን የሚያስቸግር ይመስለኛል። ጥናቱ ሳይንሳዊና ትክክለኛ ቢሆን እንኳን ዓላማው እንደተለመደው ሲቪል ሰርቪሱን ማብጠልጠልና ረብ የለሽ አድርጎ ማቅረብ ነው። ከዚህ በፊት በተፈለገ ጊዜ የደመወዝ ጭማሪ ሲወረወርለት በማግሥቱ መንግሥት ለዚህ ጭማሬ ምን ያህል ብር እንዳወጣ፣ ቁጭት በሚመስል መልኩ መግለጫ መስጠት የተለመደ ነበር። ግልጽነት እንዳይባል ስለትልልቅ ፕሮጀክቶችና ስሌሎች እጅግ ጠቃሚ ወጪዎች ሲናገሩ አላየናቸውም። ሲቪል ሰርቪሱ ሲነሳ ግን ለምን እንደሚንገበገቡ አይገባኝም።

ብይ አህመድ (ዶ/ር) ሲቪል ሰርቪሱ በነፃ በሚባል ደረጃና በአነስተኛ ደመወዝ አገሩን እያገለገለ እንደሚገኝ መናገራቸውን የሰማሁ ይመስለኛል። ከተሳሳትኩኝ እታረማለሁ። ሲቪል ሰርቪሱ የአገሩን ችግር ተረድቶና አቅሟን አውቆ የሚያገለግል ነው።  ነገር ግን የሚሸከመው አንዳንዴ መጠኑን ያለፈ ነው። ሲቪል ሰርቪሱ ሊከበር እንጂ ሊዋረድ አይገባውም። ሲቪል ሰርቪሱ ችግር የለበትም አልልም። ችግሩን በዋናነት ማስተካከል  ያለበት መንግሥት ይመስለኛል። ትክክለኛ ሥርዓትና አሠራር በመዘርጋት ችግሮችን መፍታት ይቻላል። ከዚህ ውጪ አገሩን እንዳላገለገለና እንደማያገለግል ሊብጠለጠል አይገባውም። ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙኃን የተሠራጨችው መረጃም የዚህ ስሜት ያዘለች ትመስላለች። እየተስተዋለ!” ሲል ይገልጻል።

የእኔ አስተያዬት

እንግዲህ ‹‹ሌባን ሌባ ብለን እንጥራው›› ብለው የለ ለለውጥ የሚታትሩት ጠቅላይ ሚኒስትር? እርግጥ ነው የሲቪል ሰርቪስ ደመወዝን ዝቅተኛነት አምናለሁ። በእጅጉም ያሳዝናል።  ቢያንስ ለቀለብ መሆን መቻል አለበት። ነገር ግን ደግሞ በዚያ ደመወዝስ ቢሆን ተገቢው ሥራ ይከናወናል? ይቅርታ ይደረግልኝና የሚከተሉት ጉዳዮችም በጥብቅ ሊተኮርባቸው ይገባል የሚሉ የመከራከሪያ ነጥቦች አነሳለሁ።

የሲቪል ሠርቪስ ሠራተኞች በቢፒአር ውጤት ተኮር ሥራ እንደሚያከናውኑ ቢገለጽም፣ ከሚኒስትሮች ጀምሮ ሥራን ወደ ታች ስለማያወርዱ፣ የበታቾቻቸውም እንደዚያው ስለሆኑ የሚታቀድም ሆነ የሚከናወንም በዘፈቀደ ነውና መለኪያ የለውም። አለ ከተባለም በአመዛኙ ከክንውን በኋላ ዕቅዱን ዝቅ ክንውን ከፍ በማድረግ የሚወጣ የሸፍጥ ዕቅድ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ዕድገት እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህ የሚሆነው በመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሆኑን ልብ ይባልልኝ። በሁሉም የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ወይም በከፊል የማይጠቀሙበት የእስክርቢቶ፣ የእርሳስ፣ የማስታወሻ፣ የሽንት ቤት ወረቀት ቢሰጥ  የሚወጣውን ወጪ አናክልበት፡፡ 

በዚህ ጽሑፍ ራሱን በቻለ ‹‹ብኩንነት›› በሚል ንዑስ ርዕስ  የማቀርበው ቢሆንም፣ በጥቅሉ ግን በሁሉም መሥሪያ ቤቶች በቀን 100 ሉክ የታይፕ ወረቀት፣ 100 ስፒል፣ 100 አግራፍ፣ 100 የስቴፕለር ስፒል ቢጠፋ ስንት እንደሚሆን አስቡት። ይህ እንግዲህ በመጠነኛ ስህተት ምክንያት ከታተመ በኋላ የሚጣለውን በሺሕ የሚቆጠር ወረቀት፣  ለልጅ ሥዕልና ለማሰቢያ ወዘተ. የሚሰረቀውን ሳይጨመር ነው። የፈሰሰ ስፒልኮ ባፈሰሰውም ሆነ በፅዳት ሠራተኛው አይለቀምም። አንዳንድ ጊዜ ከእነ ካርቶኑ ሊሆን ይችላል። እዚህ ላይ 1980ዎቹ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ የሕዝባዊ ቁጥጥር ዓምድ አዘጋጅ ሆኜ ስሠራ ‹‹አንዲት ስፒልም ብትሆን›› በሚል ርዕስ ከፊል ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በየቢሮው አንዲት ስፒል ብትወድቅ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት አስመልክቼ ማቅረቤን አስታውሳለሁ። እናም በሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች የሚታየው ብክነት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ሊጤን ይገባል።

ለሥራ ተብሎ የሚመደበው መኪና ለግል መጠቀሚያ ሲሆን፣ ነዳጁ ሲሰረቅ፣ ጎማውና መቀያየሪያው በሕገወጥ መንገድ ሲቀየር አንድ መጠነኛ ድልድይ ለመመረቅ በአንድ መኪና ሦስት አራት ሆኖ መሄድ ሲቻል የቢሮ ኃላፊው፣ የክፍል ኃላፊው፣ ወዘተ. በየመኪናው ብዙ ኪሎ ምትር ሲሄድ የሚወጣው ነዳጅ፣ የንብረት ዋጋ መቀነስ፣ መበላሸት ወዘተ.፡፡ እያንዳንዱ ሰው በቀን ሁለት ሰዓት ባይሠራ ከዓመት ፈቃዱ ውጪ በዓመት ቢያንስ አሥር ቀን ቢቀር ለግብዣና ፋይዳው ለማይለካ ሥልጠና የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ፣ ያላግባብ እየፈሰሰ ለሚውለው ውኃና ከሚያስፈልገው በእጅጉ የላቀ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለግል ጉዳይ ሲቀጠቀጥ የሚውለውን ስልክ አስቡት፡፡ ይህን በሚመለከት በመንግሥት መሥሪያ ቤት ከሚታየው ቀጥዬ የማቀርበው ቢሆንም ዓይኑን ያፈጠጠ ጉቦኝነት፣ ሙስና፣ ሌብነት፣ ስንፍና የት ነው ያለው? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡

እናም የቀረበው ሥሌት እንዴት ነው የሚገናኘው? ነው ወይስሥራ ማስኬጃው ከውቅያኖሶች እየተቀዳ የሚመጣ ገቢ ስለሆነ ይሆን? ስለሆነም ማደግና ማሳደግ ብቻ ሳይሆን አለመሥራትና አለማሠራትም እኩል ሊያንገበግበን ይገባል። መብትና ግዴታ አብረው ሊሄዱ ይገባል እላለሁ። ምንም እንኳን ከአንድ እስከ ዘጠኝ የተዘረዘሩት በስፋት ሊተነተኑ ቢችሉም፣ በተራ ቁጥር ሦስት ዘጠኝ የተጠቀሱትን ብቻ እንደሚከተለው እንመልከት።

ብኩንነት በሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤት

በመሠረቱ ብኩንነት በግለሰብም ሆነ በኅብረተሰብ ሊቀር የሚገባው መጥፎ ማኅበራዊ ልማድ ነው፡፡ የብኩንነት ጉዳይ ሲነሳ የበርካታ ግለሰቦች ሥነ ባህሪያዊ ዕድገታቸው ጭምር መታየት ያለበት ጉዳይ ሲሆን፣ በብኩንነት በተለይም የወልን ሀብት በግል የሚያባክኑ ግን ሕዝባዊ ቁጥጥር የሚሻቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ አንድ ግድ የለሽ ግለሰብ የቢሮ መብራት ሳያጠፋ ወይም የውኃ ቧንቧ ሳይዘጋ፣ ወይም ሌላ ነገር ቢያደርግ የመላው የመሥሪያ ቤቱን ሠራተኞች የሚፃረር ድርጊት መፈጸሙ ነው፡፡ ይልቁንም በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚገኙ ተመሳሳይ የሆነ የማባከን ልማድ ያላቸው ግለሰቦች የሚፈጽሙት ጥፋት ተደምሮ የሚሰጠው ውጤት፣ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሚሆን ግልጽ ይሆናል፡፡

አንዳንድ ጉዳዮች በግለሰብ ሲፈጸሙ በግለሰቡ ዙሪያ ብቻ የሚያበቁ እየመሰላቸውእኛ ምን ቸገረን?›› ሲሉ ይሰማሉ፡፡ በመሠረቱ ግን አንዱ ከሌላው ጋር ተደጋግፎ የሚኖር እንጂ ራሱን ችሎ በነፃነት የሚኖር እንደሌለ መታወቅ አለበት፡፡ በአዲስ አበባ 600,000 ቤቶች ቢኖሩና እያዳንዱ በቀን አንድ ዋት ኤሌክትሪክ ቢቆጥብ፣ ይኸው የአንድ ቀን ቁጠባ ለአንድ ወረዳ ከተማ እንደሚበቃ የታወቀ ነው፡፡ ይህም ማለት ግለሰቦች ‹‹በየወሩ ለምንከፍለው ኪራይ ማንስ ቢሆን ምን ጥልቅ አደረገው?›› ሊሉ ቢችሉ እንኳን፣ ከሚፈልጉት በላይ መጠቀማቸውን ቢያቆሙ ሌሎች መብራት ላላገኙ ሊዳረስ ይችላል፡፡ 

በየመንግሥቱ መሥሪያ ቤት የሕንፃ ፎቅ የፀሐይ ብርሃን ገብቶ ሦስትና አራት አምፖሎች ካላበሩ ቢሯቸው የማይደምቅላቸውም የሚመስላቸውም አይጠፉም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ በቢራ ምንም አይደለም፡፡ ነገር ግን የሚበራውን ያህል እንኳን ጥቅም የማይገኝበት ከሆነ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ ወይም ብኩንነት ነው፡፡ ብዙዎቻችን የቧንቧ መዝጊያና መክፈቻ መበላሸት የግልም ሆነ የመንግሥት ውኃ ያለ ገደብ ሲፈስ እናያለን፡፡ በአንድ የመንግሥት  መሥሪያ ቤት አንድ አውቶሞቢል ለማጠብ የሚፈሰው ውኃ ምን ያህል እንደሆነ ታዝበናል፡፡ አንድ አነስተኛ ቆሻሻ ለማጠብ ስንፈትግ እንውላለን፣ ለመታጠብ የከፈትነው ቧንቧ ሳንዘጋው የምንወጣም አለን፡፡ በቤታችን ውስጥ ቆጥበን መጠቀም ስንችል ‹‹በየወሩ ለምንከፍልበት›› እያልን ከሚስፈልገን በላይ እናባክናለን፡፡ ችግሩ ግን መንግሥት ወይም ግለሰብ በሚከፍለው የውኃ ኪራይ ተወስኖ የሚቀር አይደለም፡፡ የተጠራቀመውን ወይም የምንጩን ውኃ ባለማግኘታቸው በከፍተኛ ችግር ላይ የሚገኙትን ሰዎች ጥቅም የሚፃረርና ለእነሱ ሲባል ሌላ ወጪ ማውጣት የማያስገድድ ነው፡፡

እኛ የብረት ማዕድን ማውጫ ፋብሪካ የለንም፡፡ የምንጠቀመው ብረት ሁሉ በውጭ ምንዛሪ እየገዛን የምናስገባው ነው፡፡ ነገር ግን ሥራዬ ብሎ ብረት ለመልቀም አንድ ግብረ ኃይል ቢሠማራ፣ በቀን በብዙ መቶ ቶን የሚመዝን ሰብስቦ እንደሚመጣ የታወቀ ነው፡፡ መኪኖች በየጋራጁ ይገባሉ፡፡ የተሰበረ ዕቃቸው ይለወጣል፡፡ ስባሪው ይጣላል፡፡ ብረታ ብረት ይቆራረጣሉ፣ በዚያ የተወሰነ ወቅት የማያስፈልገው ቁራጭ ይጣላል፡፡ ሚስማሮች አገልግሎት በሚሰጡበት አካባቢ ሁሉ በመዶሻ ይደበደባሉ፣ ሲጣመሙ እየተነቀሉ ይጣላሉ፡፡ ሰሃን፣ ብረትና ድስት የመሳሰሉት የቤት ቁሳቁሶች ሲያረጁ ከቆሻሻ ጋር ይጣላሉ፡፡ የተለያዩ የመጠጥም ሆነ የቅባት ጠርሙሶች በቆርኪ ይከደናሉ፡፡ ከዚያም ይዝጋሉ፡፡ አፈር ይሆናሉ፡፡ በአንፃሩ ግን ብዙ ብረት የሚፈልጉ ሥራዎች አሉን፡፡ እናም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚባክነው ብረት ወደ ተለያየ ቅርፅ እየተለወጠ ለአገልግሎት ለመዋል በቻለ ነበር፡፡

ሌላው ምሕረት የለሽ የብኩንነት ዕድሜ የሚገጥመው ጠርሙስ ነው፡፡ ጠርሙስ በልዩ ልዩ ዘርፎች የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ መጠጦች፣ ሽቶዎችና ቅባቶች የመሳሰሉት ፈሳሾች በጠርሙስ መቀመጣቸው የሚመረጥበት ራሱን የቻለ ምክንያት አለው፡፡ በጣሳ፣ ወይም በሽክና ወይም በፕላስቲክ ከመጠጣት ይልቅ በብርጭቆ ቢጠጣ የሚመረጥበት ጊዜ አለ፡፡ የጠርሙስ ዝርያ የሆነው መስተዋት በቁሳቁስነቱ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር፣ ባህልንም በማስፋፋት ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የቻይናውያንን አለባበስ፣ አበላል፣ አኗኗር በአጠቃላይ ማኅበራዊ ኑሯቸውን ከጠርሙሶቻቸው ወይም ከብርጭቆዎቻቸው እንረዳለን፡፡ ይህም ቢሆን የምንገዛው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አውጥተን ነው፡፡ ነገር ግን ስብርባሪውን ጠርሙስ እየሰበሰብን ወደ ጥቅም እንዳስፈላጊነቱ ለመለወጥ ባለመቻላችን ምክንያት በየሥፍራው ወድቆ እናያለን፡፡ መስታዋት ሠሪዎችም በትክክል ለመጠቀም ከሚችሉበት ደረጃ ላይ ባለመድረሳቸው፣ ገንዘባቸውን አውጥተው የገዙትን ንብረት ሲያባክኑ ይታያሉ፡፡ ይህ ሁሉ ብክነት ግን በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪና በሕዝብ ጥቅም ጭምር ተፅዕኖ ያለው እንጂ፣ በእነሱ ዙሪያ ብቻ የሚሽከረከር አይደለም፡፡

በኤሌክትሪክ፣ በውኃ፣ በብረትና በጠርሙስ አኳያ የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣ የቢሮ ውስጥ መገልገያዎችን፣ የቤት ውስጥ ዕቃዎችን አንድ በአንድ እያነሳን ማየት እንችላለን፡፡ ሁሉም ግን የግል ባህሪ ቢኖራቸው እንኳን የወልም እንዳላቸው ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ ቤንዚን በራሽን እንዲሰጥ ቢፈለግ ግለሰቦች በመኪናቸው እንደፈለጋቸው እንዳይሄዱበት ለማድረግ አይደለም፡፡ ከአቅም በላይ የምናወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ፣ ብኩንነትን ለመዋጋት ነው፡፡ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካላት ብኩንነት የሚታገሉት ሲጠፉ ብቻ ሳይሆን ለዚሁ ምክንያት የሚሆኑትን ቀዳዳዎች በመድፈን ጭምር ነው፡፡ የብሔራዊ ሀብታችን በሕዝባዊ ቁጥጥር ይጠበቃል የማለት ትርጉሙም ይኸው ነው፡፡

ሥጦታና ጉቦ

‹‹በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ስላለው ጉቦና ጉቦኝነት ስናነሳ ጠለቅ ብለን ማየት ያለብን ዓበይት ነጥቦች አሉ፡፡ ችግሩ በአንድ አገር ዳር ድንበር ተከልሎ የሚቀር ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ በህሪ ያለው እንደ መሆኑ መጠን ሥረ መሠረቱን መመርመር ለሚወሰደውርምጃ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ‹‹ሥጦታ›› የሚለው ቃል በደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት ትርጉም መሠረት አምሐ፣ ገፀ በረከት፣ መተያያ፣ እጅ መንሻ፣ ፊት መፍቻ የሚል ነው፡፡ በሌላው ትርጉሙ ደግሞ ደስታ መግለጫ ቁሳቁስ፣ አንዱ ለሌላው በነፃ የሚሰጠው ዕቃ፣ ንብረትና ሀብት ነው፡፡ ሥጦታ ግን ለአንድ ጊዜም ሆነ ለዕድሜ ልክ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ይሁንና የልደት በዓል፣ ወይም የዓመት በዓል ወይም የሌላ በዓል ደስታ መግለጫ የወረቀት ሥጦታን ከሙክት፣ ከገረወይና ቅቤ፣ ከቤት ወይም ከሌሎች ከፍተኛ ሥጦታዎች እኩል ማየት ያስቸግራል፡፡ ያለ ምስክርና በምስክር ፊት የሚሰጡ ስጦታዎች እንዳሉ ሁሉ፣ መንግሥትን በሚወክል መሥሪያ ቤት በሕግ መፅደቅ ያለበት ስጦታ እንዳለም የታወቀ ነው፡፡ ማርሴይ ማውስ የተባለው የፈረንሣይ ፈላስፋ እንደገለጸው ሥጦታ በጥንት ሰዎች ዕቃን በዕቃ ከመለወጥ ልማድ የመጣ ነው፡፡ ‹‹ዕቃን በገንዘብ መሸጥና መለወጥ ባልነበረበት ጊዜ ሕዝቡ ዕቃውን በዕቃ በመለወጥ ወይም በመሰጣጠት ይጠቀም ነበር፡፡ ይህም ሥጦታ ወይም ልውጫ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ፈቃደኝነት፣ በተግባር ግን ግዴታ ነው፤›› ሲል ይተነትናል፡፡ ሥጦታን ሁሉ በጉቦ መልክ ማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሥጦታ ያዘነን ሰው ለማስደሰት፣ የቀን ጨለማ የዋጠውን ከችግሩ ለማውጣት፣ በሕይወት እምነት ያወጣውን የወደፊት ተስፋውን ብሩህ ለማድረግ ከሆነ ጀምስ ቶማስ የተባለው ባለቅኔ፣ ‹‹ስጡት ድንጉል ፈረስ ይጋልብበታል፣ ስጡት መልካም ጀልባ ይንሳፈፍበታል፣ በባህሪም ሆነ በባህር ዳርቻ ይደሰትበታል፡፡ ስጡት ጥሩ መጽሐፍ እንዲያገኝ ዕውቀት፣
ምንም ደሃ ቢሆን ልብሱ ቢደረት፣ አይጠላም መዝናናት አይጠላም ቅኝት፤›› በማለት ስለጥሩ ሥጦታ ይገልጽልናል፡፡

ስለ ሥጦታ ከጻፉት ሌሎች ምሁራን አንዱ አሜሪካዊው ደራ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን ሲሆን ይህም ሰው ‹‹ሥጦታ›› በሚል ርዕስ የጻፈውን ድርሰት የሚጀምረው፣ ‹‹የሥጦታን ሕግ በተመለከተ አንዱ ጓደኛዬ እንዳለው የሥጦታ አመልካቹን ባህሪና አስተሳሰብ የሚመሳሰል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሁንና የብዙዎቻችን የሥጦታ ምርጫ ከእኛ ጋር ዝምድና የሌላቸውና እኛን የማይክሱ ናቸው፡፡ ሥጦታዎች እኛን፣ እኛን ማለት ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህም ባለቅኔ የግጥሙን በግ አርቢ ጠቦቱን፣ ገበሬው ጥሬውን፣ ሠዓሊው ሥዕሉን፣ ልጃገረድ የሠራችውን የእጅ መሐረብ ማምጣት ሲችሉ ብቻ ነው ሥጦታ፣ ሥጦታ ሊባል የሚችለው፡፡ ትክክሉና አስደሳቹ ሥጦታም ይኸው ነው፡፡ እንደ እኔ እንደ እኔ ስጦታ የሚያበረክትልኝ ሰው አንጥረኛ ቤት ሄዶ ወርቅ ገዝቶ ቢያመጣልኝ፣ የአንጥረኛውን የፈጠራ ሥራ እንዳደንቅ ያደርገኛል፡፡ ምናልባት እንደዚህ ያለውን ሥጦታ ነገሥታትን ወይም ራሳቸውን እንደ ንጉሥ የሚቆጥሩ ትልልቅ ሰዎች ያስደስት ይሆናል፡፡ ለእኔ ቢቀርብልኝም ግን እንደ ርካሽ ብቻ ሳይሆን ስሜን ለማጥፋት እንደተሰጠኝ አድርጌ አየዋለሁ፤›› ብሏል፡፡

ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን ቀጥሎም፣ ‹‹ጥቅምን ለማግኘት ሲባል በተለይ በቢሮ ውስጥ ለሚሠራ ሰው የሚሰጠው የሥጦታ ዓይነትና የአሰጣጥ ሁኔታ ግን እንዴት ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ ስጦታው በተሰጠው ሥልጣን እንዲባልግ ለማድረግ ከሆነ ተቀባዩን ብቻ ሳይሆን አቀባዩንም ቢሆን ይቅርታ ልናደርግለት አይገባም፡፡ በጉቦ መልክ የሚመጣውን ስጦታ የምንቀበለው በወዳጅነት መልኩ መስሎን ከሆነም፣ በማር የተጠቀለለ መራራ ምግብ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ስለዚህም ከወዳጆቻችን የሚቀርቡልንን ሥጦታዎች እኛ የገዛነውን ያህል በደስታ ብንቀበላቸውም ሰጪያችን በሥጦታ መልኩ ሳይሆን በሚፈልገው መንገድ ውለታውን እንድንመልስለት ያበረከተው ተቀማጭ ሀብት መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፤›› ሲል ያስጠነቅቃል፡፡ ኢመርሰን ስለሥጦታ ባቀረበው አስተያየት ሕገወጥ ሥጦታ ከጉቦ ጋር የተገናዘበ እንደሆነ፣ ጉቦ ተቀባይነት ደግሞ ከሰጭው የበለጠ እንደሚከፍልና ጉቦ ተቀባይነትም ሆነ ሰጭነት የሚፈልጉትን እስኪያገኙ ድረስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ አመልክቷል፡፡ ‹‹ታላቅ ሰው ቁሳዊ ፍላጎቱን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎቱንም የሚያጤን ነው፤›› ብሏል፡፡

ሥጦታን በሚመለከት ብዙዎቻችን ብዙ የምናውቀው ጉዳይ አለ፡፡ ልጆቻቸው ቢታመሙ ወይም ራሳቸው አደጋ ላይ ቢወድቁ ወይም በጣም የሚፈልጉት ነገር ቢኖር፣ ለማንም ይሁን ለምን ‹‹ሕይወቴን ሳይቀር እሰጣለሁ›› የሚሉ አሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተን ሥጦታም ከመስዋዕት ጋር ዝምድና እንዳለው ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የጥቂት ሰዎችን ፍላጎት ለማርካት ሲባል የብዙኃንን ጥቅም የሚፃረር ሥጦታ እንደ ሌሎቹ ማኅበራዊ ጠንቆች ሁሉ ሊወገድ የሚገባው ልማድ ነውና ይህንን ለረዥም ጊዜ የቆየ አጉል ልምድ ለማስቀረት ሕዝባዊ ቁጥጥርና ትግል ያስፈልገዋል፡፡ የሕዝባዊ ቁጥጥር ዓላማም በማንኛውም መንገድ የሚከሰቱት የአስተዳደር በደሎችን፣ ሕገወጥ ብልፅግናን፣ ምዝበራንና በሥልጣን መባለግን መዋጋት ነው፡፡ በሥጦታ መልክ በሚቀርብ ጉቦ ፍትሕን ማዛባት፣ ሕግንና ደንብን መጣስ የብዙኃንን ጥቅም ስለሚጎዳ የዕድገት ፀር መሆኑም መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ሌባን ሌባ ማለት ይገባናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...