Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሰንደቅ ዓላማችን ኮከብ በኢትዮጵያ ካርታ ቢተካስ?

የሰንደቅ ዓላማችን ኮከብ በኢትዮጵያ ካርታ ቢተካስ?

ቀን:

በመላኩ ሙሉዓለም ቀ.

በዓለም ላይ የሚገኘው የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም ታሪክ በእስያ አኅጉር የተጀመረ እንደሆነ አንዳንድ የታሪክ መረጃዎች ያሳዩናል፡፡ ይህ አጠቃቀም ወደተለያዩ አኅጉሮች ለመስፋፋት በቅቷል፡፡ ነፃ መንግሥታትም በሰንደቅ ዓላማቸው ቀለምና አቀማመጥ የሚለዩ ሲሆን፤ የአንድ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ከሌላው መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ጋር አንድ ዓይነት መሆን አይችልም፡፡

የሉዓላዊነት መገለጫ ከመሆኑ በተጨማሪ ሰንደቅ ዓላማ ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች አሉት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የደስታና የሐዘን መግለጫ በመሆንም ያገለግላል፡፡ ለአብነት ያህል ስፖርተኞች ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ ደስታቸውን የሚግለጹት ሰንደቅ ዓላማውን ለብሰው በመሮጥ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ክለቦች በጨዋታ ላይ የሁለቱም ተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ደስታቸውን የሚገልፀጹት በማውለብለብ ነው፡፡

በአገሮች ውስጥ ከፍተኛ አደጋ ሲያጋጥም የመሪዎች በሞት መለየትና የመሳሰሉት ሐዘኖች ከሚገለጹባቸው ውስጥ አንዱ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል ዝቅ በማድረግ ነው፡፡ ይህም አሠራር በአለም አቀፍ ደረጃ ሥራ ላይ የሚታይ ነው፡፡ በብዙ አገሮችም ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲሞቱ የሬሳ ሳጥናቸው ሰንደቅ ዓላማ እንዲለብስ ይደረጋል፡፡ አገር በጠላት ሲወረር ቀድሞ የሚታየው ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ከጦርነት ድል ሲገኝም ቀድሞ የሚታየው አሁንም ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ በመሆኑም ሰንደቅ ዓላማ ማለት ሁሉም ነገር ነው ለማለት ያስችላል፡፡ ስለዚህ የሚገባውን ሥነ ሥርዓትና ክብር መስጠት የብዙ ጥያቄዎችን መልስ በአንድ አድርጎ መመለስ ነው፡፡

ኢትዮጵያም የሰንደቅ ዓላማ ተጠቃሚ መሆን ከጀመረች አያሌ ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓላማን አጠቃቀም ጀማሪ ባትሆንም፣ ከእሷ በኋላ ጀማሪ ተጠቃሚ ለሆኑት ብዙ የአፍሪካ አገሮች የተምሳሌት አገር መሆኗን ታሪክ ያሳየናል፡፡ በመሆኑም የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት በአንዳንድ አገሮች ላይ ተፅዕኖ ከማሳደርም በተጨማሪ የፓን አፍሪካ ቀለማት እስከመባል ደርሷል፡፡

ከዚህም በተጓዳኝ ለሰንደቅ ዓላማ የሚውሉ ቀለማትንና አደራደራቸውን ስንመለከት አንድ አገር ከሌላው አገር ሲገለብጥ ይታያል፡፡ በተመሳሳይ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የመወራረስ ሒደት እንደነበር ይታያል፡፡ ሁሉም ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ማለት ይቻላል ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማቸውን ያወጡት ... 1950ዎቹና 1960ዎቹ ነበር፡፡ በእነዚህ ዓመታት የሆነበት ምክንያት ከቅኝ ግዛት የተላቀቁባቸው ጊዜያት በመሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወራሪውን የጣሊያን ፋሽስት መንግሥት በተለያዩ ዓውደ ጦርነቶች አሸናፊ በመሆኗና ለሌሎች አፍሪካ አገሮች ተምሳሌት በመሆኗ ብዙ የአፍሪካ አገሮች የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ እንዲይዙ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሦስት ቀለማትም የፓን አፍሪካ ቀለም በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህን ሦስት ቀለማት ከሚጠቀሙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ማሊ፣ ሴኔጋል፣ ወዘተ ይገኛሉ፡፡ የቅኝ ግዛትም ተፅዕኖ በመኖሩ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች የሰንደቅ ዓላማቸው የቀለም አደራደር ወደ ጎን (Horizontal tricolours) ሲሆን፤ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ሥር የነበሩት በአብዛኛው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን ያካተተ በተዋረድ (vertical tricolours) በመደርደር ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማቸውን መሥርተዋል፡፡

ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ መንግሥትና ሕዝብ ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና ሥልጣን ተምሳሌት ነው፡፡ ይህን ከፍተኛ ቦታ የያዘ ተምሳሌት የአጠቃቀሙን ሥርዓት በአዋጅ በመደንገግ ሥራ ላይ ማዋል በብዙ አገሮች የተለመደ ነው፡፡ በእኛም አገር በተለያዩ መንግሥታት ጊዜ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀማችን ምን መምሰል እንዳለበት የሚጠቁሙ አዋጆችን በማውጣት በሥራ ላይ እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

አንድ አገር ውስጥ የሚኖር ሕዝብ ሊግባቡበት ከሚገቡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የአገር ባንዲራ ላይ ነው፡፡ የአገር መከላከያ ወታደሮችም ለአገራቸው ሰላምና ደኅንነት ሲሉ ከወራሪ ኃይል ጋር ሲፋለሙና ከዚህ ዓለም ሲያልፉ ለአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ሲሉ የተሰው ይባላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአንደ አገር ሰንደቅ ዓላማ የአገሮች መወከያ በመሆን በዲፕሎማሲው፣ በስፖርት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ጉዳዮችና በመሳሰሉት መድረኮች ላይ ይውለበለባል፡፡

አሁን በአገራችን በሚታየው ሁኔታ ሰንደቅ ዓላማ የአንድነት ሳይሆን የግጭት መንስዔ እየሆነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ / ሽታዬ ምናለ በሚዲያ በዚህ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ሥርዓት ውስጥ ሕዝቡ ስለሰንደቅ ዓላማው እንዲወያይና ሐሳብ አንዲንሸራሸር ይደረጋል ብለዋል፡፡ የዚህ ጹሑፍ መነሻም በሰንደቅ ዓላማችን ላይ ሐሳብ ለመስጠት ነው፡፡ የኢፊዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 3 በግልጽ እንደ ደነገገው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ይሆንና በመሀሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖርዋል ይላል፡፡ ምን ዓይነት ዓርማ የሚለውን ግን አይገልጽም፡፡ ይህንን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ የሰንደቅ ዓላማ ሕግ የወጣ ሲሆን፣ በሕጉ መሠረት ሰንደቅ ዓላማው መሀል ላይ የሚኖረው ዓርማ ኮከብ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡

አሁን ባለንበት ሁኔታ አንዱ አጨቃጫቂ ርዕስ ከሆነው ውስጥ ኮከብ ይውጣና አረንጎዴ ቢጫና ቀይ ብቻ ይሁን የሚል የመኖሩን ያህል፣ ሙሉ በሙሉ የሰንደቅ ዓላማና ቀለምና ይዘት በሌላ ይተካ የሚልም አለ፡፡ በእርግጥ መንግሥት በሚዲያ በተደጋጋሚ መግለጽ ያለበት አሁን ያለው የአገራችንና የክልል ሰንደቅ ዓላማዎች ሕጋዊ መሆናቸውንና ሌሎች የሚውለበለቡ ግን ሰንደቅ ዓላማ ሳይሆኑ ዓርማ ናቸው በሚል ሰፊ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሕጋዊ ሰንደቅ ዓላማ በኃይል ወርዶ በተለያዩ ዓርማዎች እንዲተካ መፍቀድ ተገቢ ባለመሆኑ፤ በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በስፖርት ቦታ፣ በተለያዩ ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ መድረኮች የተሰቀሉትን ማውረድ የሚያስቀጣ መሆኑንና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚያስወስድ ግልጽ መደረጉ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ሌሎች ዓርማዎች እንዳይታዩ ይገደቡ ማለት አይደለም፣ የዓርማ ደረጃ እስካላቸው ድረስ፡፡

በዚህ ጽሑፍ ለመግለጽ እንደተሞከረው የአገር ሰንደቅ ዓላማ ከሌሎች አርማዎች በላይ የሆነ መሆኑን ለሕዝብ ግንዛቤ በተደጋጋሚ መግለጽ ተገቢ መሆኑን ሲሆን፤ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማ ግን ብሔራዊ መግባባት ያልፈጠረ ከሆነ እንዴት ይፍጠር? የሚል ሐሳብ በምሁራንና በሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ውይይት በስፋት ማከናወን ችግሮችን ለመፍታት ያግዛል፡፡

እኔ የማቀርበው ሐሳብ ከሕገ መንግሥቱ በመነሳት ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ሕገ መንግሥቱ ስለሰንደቅ ዓላማ ሲደነግግ መሀሉ ላይ ዓርማ ይኖረዋል ይበል እንጂ ምልክቱ ኮከብ ይሁን አይልም፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ እስኪሻሻል ድረስ በሰንደቅ ዓላማችን ላይ የሚኖረው ምልክት ኮከብ ከሚሆን ይልቅ፣ በሰማያዊ ቀለም የተዘጋጀ የኢትዮጵያ ካርታ ቅርጽ በኮከቡ ቦታ ላይ ቢተካስ? የሚል ግላዊ ሐሳቤን አቀርባለሁ፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ካርታ ክልሎችን በሚያሳይ መልኩ ሳይሆን፣ በድፍን ሰማያዊ ቀለም የተሞላ ቢሆን የሚል ተጨማሪ ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡ የአገራቸውን ካርታ ቅርፅ በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ ያስቀመጠ አገሮች ስንመለከት ኮሶቮና ሳይፕረስን እናገኛለን፡፡

ይህንን ሐሳብ ያቀረብኩበት ምክንያት የአገራችን ካርታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠ በመሆኑና ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ሁሉ በአንድነት የሚወክል በመሆኑ ነው፡፡ ካርታው እኔን አይወክልኝም የሚል እስከሌለ ድረስ በሰንደቅ ዓላማችን ዙሪያ ያለውን ችግር ሊፈታ ይችላል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ የአገራችን ካርታ በሰንደቅ ዓላማው መሀል ላይ ሲሆን፤ አሁን እንዳለው ኮከብ በትልቅ መጠን (Size) ሳይሆን አነስተኛ ሆኖ አረንጎዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ጎልቶ የሚወጣበት ቢሆን የሚል ተጨማሪ ሐሳብ አለኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...