Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ብስልና ጥሬው ተቀላቀሉ እኮ?

እነሆ መንገድ! ከቦሌ ጫፍ ወደ ካዛንቺስ ልንጓዝ ነው። ያ ትናንት የነጎድንበት መንገድ ዛሬም ይዞናል። በመዳህ ዘመናችን በመዳፋችን አፍሰን የቃምነው አፈር ዛሬ በዕውቀትና በዕድሜ እንደ ባዳ ፊቱን እያዞረብን፣ ያ ያመነው ጎዳና በሠፈር ቀዬያችን በቀና መንፈስ የተሯሯጥንበት መንገድ ዛሬ በአደባባይ እየጎረበጠን፣ እያናከሰን፣ እያስነከሰን፣ እያንከራተተን ከታክሲ ወርደን ታክሲ እንሳፈራለን። የተሳፈርንባት ታክሲ መቀመጫዎች እንደ ወትሮው ዓይነት አይደሉም። ሦስት ሰው የሚይዙ መቀመጫዎች ያሉት ዘመናዊ ሚኒባስ ውስጥ ነን። በአውቶብስ፣ በሴይቼንቶ፣ በዲ፣ በውይይትና በሚኒባስ ጥርሱን የነቀለ ተረበኛ፣ “ፓ! እውነትም ይህች አገር እያደገች ነው!” እያለ አሽሟጦ ይቀመጣል። “ምን ትፈልጋለህ? ያውልህ ደግሞ ቴሌቪዥንም አለው! አልወርድም እንዳትል እንጂ!” ይላል ቀድሞ ተሳፍሮ ታክሲው ሞልቶ እስኪያፈተልክ የሚቁነጠነጠው። ሩቅ አልሞ የማይቁነጠነጥ የለም!

 ከሾፌሩ ጀርባ እማወራና አባወራ አዛውንቶች አሉ። አጠገባቸው ደግሞ የቀይ ዳማ ልጅ ተቀምጣለች። ‘ከወደዱም አይቀር ይወዳሉ ቀይ፣ እንደ ዓላማ ሰንደቅ ከሩቅ የሚታይ’ ይላል ወያላው እሷን እያየ። “ለምን ይሆን ግን እኛ በቀይ የተለከፍነው? ሴት ቢሉ ቀይ ሞንዳላ! ሥጋ ቢሉ ቀይ ብሩንዶ! በዘር የመከፋፈል አባዜያችን ወደ ቀለም ዞሮ ይሆን እንዴ?” ሲል የምሰማው ከአላፊ አግዳሚው አንዱን ነው። እዚህ ጎዳና ላይ የማይሰማ ነገር የለም! መሀለኛው መቀመጫ ላይ ደግሞ ሁለት ተማሪዎች መንገድ ካገናኛቸው አስተማሪያቸው ጋር ይታዩናል። ከእነሱ ጀርባ እኔና አንድ የታሰረ ዘመዱን ሊጠይቅ የሚጓዝ ጎልማሳ፣ ባሻገር ዓይኑ ቁልጭ ቁልጭ የሚል ሥራ ፈላጊ ወጣት (ኋላ እንደተረዳነው መሆኑ ነው) ተሰይመናል። የኑሮ ዳና የጠፋበትንና የሚወደውን ሰው በአንድም በሌላም ያጣውን ቤት ይቁጠረው ነው የሚባል።

የኋለኛው መቀመጫ እስኪሞላ ይጠበቃል። “ሾፌሩ የት ሄዶ ነው? እስኪ ክፈተው በለው!” አሉ አባወራው አዛውንት እንደ መለማመጥ እያሉ። “ምኑን ነው የሚከፍተው?” ወያላው ደረቅና ደንታ ቢስ ነገር ነው። “ቴሌቪዥኑን ነዋ! ነው እንደ እኛ ቤት እዚህም መብራት ጠፍቷል? እንዲያው መሠረታዊ ነገር የሚጠፋው እኛ ዘንድ ብቻ ነው? ወይስ ሌላውም ዘንድ ነው?” አዛውንቷ በተራቸው ጠየቁ። ስለቤታቸውና ስለአገራቸው ጣጣ ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ቢናገሩ የሚይጠግቡ አይመስሉም። ወያላው ሰምቶ እንዳልሰማ ፊቱን ያዞራል። ፊት ማዞር ያዛልቅ ይመስል የዘመኑ ፋሽን ተደርጎ ተይዞ ነው መሰል፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ገሸሽ በማለት ያልሠለጠነ የለም! እንዲያው እኮ! “አንተ ምናለበት እሺ ብትል? ብርቅ ነው እንዴ ቴሌቪዥን? ጥቁርና ነጭም ቢሆን አንተ ሳትወለድ ዓይተናል ነፍሳቸውን ይማረውና ጋሽ ማንደፍሮ ቤት! አይ ሰው! ሰውማ አለቀ!” እያሉ ወደ ራሳቸው ትውስታ እየተንሸራተቱ ወያላውን ይነቁሩታል አዛውንቱ።

ባለቤታቸው ከትውስታቸው ውስጥ ዘለው ገብተው “ሞት ክፉ ነገር! እኛ እኩያ ያጣነው አንሶ ደግሞ መብራቱ፣ ውኃውና ትራንስፖርቱ ችግር ሆነ! ምን አደረግንህ ግን አንተ ፈጣሪ? ምናለበት ኑ ብትለን?” አሉ ቀና ብለው የታክሲዋን ጣሪያ እያዩ። የመጨረሻው ወንበር በሁለት ጓደኞች፣ በአንዲት ቆሎ አዟሪና በደላላ ሲሞላ ወያላው “ሳበው!” ብሎ በሩን ዘጋው። ጋቢና በከፊል የሚታዩን ሁላችንንም ቀድመው የተሳፈሩ ሁለት ወጣቶች አሉ። “አንቱ አሁን ሞትን የሚያስጠራ ምን ነገር መጣ? በእውነት ያበዙታል እኮ አንዳንዴ!” አባወራው በባለቤታቸው ክፉኛ ሲወቀሱ እየሰማን ነው። መዓዛዋ ታክሲያችንን እንደ ከርቤ ያጠነው አጠገባቸው የተሰየመች መልከ ቀና በአዛውንቶቹ ንትርክ ፈገግ ትላለች። “ተቃጠልን! ተቃጠልን!” እያሉ አባወራው አዛውንት ተበሳጩ። አጠገቤ የተሰየመው ጎልማሳ ይኼን ጊዜ ጎሰም አድርጎኝ፣ “ስማ ህንድ አገር አንድ ሐበሻ ወንድማቸው የሞተ ዳያስፖራዎች አስከሬኑን ወደ አገር ቤት ሊልኩ ገንዘብ ያሰባስባሉ። ቀልድ ነው የማወራህ ገባህ? እና ህንዶቹ ሰምተው ‘ምንድነው ደግሞ ሬሳ በሳጥን ማስቀመጥ? በእሳት አቃጥላችሁ አመዱን በውኃ አትሸኙትም ወይ?’ ሲሏቸው፣ የእኛዎቹ ምን እንዳሉ ታውቃለህ? ‘እኛ ሰው ከሞተ በኋላ የማቃጠል ባህል የለንም። ባይሆን በቁሙ ደህና አድርገን ማቃጠሉን እናውቅበታለን!’ ታዲያስ ልክ ናቸው እኮ።  በቁም አልቀህ እኮ ነው በድንህ የሚቀበረው እዚህ አገር፤” ሲል ግማሹ በሳቅ ያውካካል። ግማሹ በመገረም ወቸ ጉድ ይላል፡፡ ‘የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩትን ያህል ይስቃል’ ሳይሆን ቀረ ብላችሁ ነው?!

ጉዟችን ከተጀመረ ቆያይቷል። ወያላው ሒሳቡን እየሰበሰበ ነው። በአዛውንቶቹ ጉትጎታና ተማፅኖ ትንሿ የቴሌቪዥን መስኮት የተጥበረበረ ምሥል ይታያል። በባህል ሙዚቃ ዳንኪራ የሚያስነኩ ተወዛዋዦች የተሳፋሪዎችን ቀልብ በከፊል ገዝተዋል። እኛ የተሰየምንበት መጨረሻ ወንበር አካባቢ ቆሎና ማስቲካ የምታዞረው ምስኪን ልጅ፣ ለአንዳንዶቻችን ከኑግ ጋር ቀላቅላ ቆሎ ትቸበችባለች። “ኑግ ከየት አገኘሽ በፈጣሪ? ዘንድሮ አልገባን ያለው የማይገኘው መገኘቱ፣ መገኘት ያለበት አንገብጋቢው ጉዳይ ደግሞ መታጣቱ ነው!” ይላታል አጠገቧ የተቀመጠው ደላላ። ወያላው ጣልቃ ገብቶ፣ “የተሳፈርሽው እኮ ለመጓዝ እንጂ ለመነገድ አይደለም!” አላት። “አቦ አንተ ደግሞ! አንተም እንደ መንግሥት ደሃ ላይ ልትበረታ ያምርሃል? ነው ወይስ የንግድ ፈቃድ አሳይኝ ልትለኝ አማረህ? በላ ደግሞ ታክስ አስከፍለኝ!” አለች፣ ብው ብላለች። ወያላው ደንግጦ ዝም። ቆያይቶ ነገር እንዳይፈልጋት ይመስላል፣ “ሰው ሠርቶ መብላት አይችልም? ስንቱ አጋጣሚ ሲያገኝ በሕዝብ ሀብትና ንብረት እየቀለደ እየኖረ ፀሐዩም ጨረቃውም፣ ቀኑም ጨለማውም እኛ ላይ ጥርስ ይነክሳል። ቆይ ግድ የለም!” ዛቻዋ የተማመነው አሻጥር ያለ ይመስላል። “ዝም በይው እኛ አለን። ይልቅ ከምርቃቱ ጋር ጨመር አድርጊና ለዚህ ለወንድሜም ዝገኝለት። ዘመኑ የመጠቃቀም ስለሆነ ምርቃቱን አደራ እንዳታሳንሽው፤” ጎልማሳው እኔን እየጠቆመ ይነግራታል።

“ምርቃት እንኳ ድሮ ነበር የቀረው! መቼስ እናንተ ስለሆናችሁብኝ ምን አደርጋለሁ?” ብላ መስፈር ስትጀምር አባወራው አዛውንት፣ “እግዚኦ! አሁን ይኼ ምን የሚሉት ጭፈራ ነው? እውነት የአገሬው ሰው እንዲህ ይጨፍራል? ምነው ግን የዘንድሮ ልጆች የሚለወጠውንና የማይለወጠውን ነገር ለይታችሁ ብታውቁ? ስንት የሚስተካከልና የሚሞረድ ነገር እያለ፣ አወቅን እያላችሁ ደህናውን ነገር ባትበርዙት?” ብለው ቆንጅት ላይ አፈጠጡ። የሚለወጥና የሚሞረድ ያሉትን ነገር ከአሁን አሁን ያብራሩታል ስንል ብዙ ስለሄድን ተረሳ። ሒደት የማያረሳሳን ነገር የለም። ምናልባት ታዲያ ክፉን እያስረሳ ደህናውን ቢተውልን ጎበዝ?! ቆሎ አዟሪዋ ወርዳለች። በምትኳ አንድ ቻይናዊ ተሳፍሯል። ከኋላችን የተቀመጡት ተሳፈሪዎች የንግድ ወሬያቸውን አቋርጠው ቆሎ በምትሸጠው ልጅ ከንፈር ሲመጡ ሲሰማ አጠገባችን የተቀመጠው ወጣት፣ “እኔ እኮ እዚህ አገር ሠርቶ የሚያድር ሰው ምኑ ከንፈር ያስመጥጣል እስኪ አሁን? ስንት መሥራት ሲችል የሚለምን እያለ? እንደ እኛ ዓይነቱ ተምሮ በዲግሪ የተመረቀ ሥራ ፈት ቦዘኔ እያለ?” ብሎ ተበሳጨ።

“ምን ታደርገዋለህ?” ይመልሳል ጎልማሳው። “አይገርምህም? ሰው ባለችው ነገር ተጣጥሮ ሰው ሊሆን ሲደክም የማያበረታታ ባህል እኮ ነው ያለን! በስንት ስቃይ ጥቂቶች ከድህነት አረንቋ ሲወጡ ካየንም መከራ ነው። ያው ታውቃለህ አፋችንን? ሰርቆ ነው፣ በእነ እከሌ ተጠቅሞ ነው፣ የራሱ አይደለም. . .  ኧረ ምን የማንለው አለ? አሁን እኛ ነን የሚያልፍልን?” ሲል ከኋላችን ጆሯቸውን አንቅተው የሚያዳምጡት አዛውንት፣ ‹‹‘ተወደድኩኝ ብለሽ አትበይ ውንግር ውንግር፣ እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አድርጎን ነበር’ አለ የአገሬ ሰው። እንዲያው የአንዳንዱ ሰው አጉል መመፃደቅ አይገርምም? አሁን ይህች ልጅ ቢያድላት መማሪያ መመራመሪያ ጊዜዋ እንጂ ጎዳና ለጎዳና እየዞረች ቆሎ መሸጫ ዕድሜዋ ነው?›› አሉ። ከዕድሜና ከትምህርት ጨዋታ እንዳንላቀቅ ይመስላል ደግሞ ከፊታችን የተቀመጡት ተማሪዎች ከአስተማሪያቸው ጋር በነፃነት ያወራሉ። “ቲቸርዬ! አሁን እዚህ አገር አስተምሮና ተምሮ ማን አለፈለት? ይንገሩን እስኪ!” ስትል አንደኛዋ ጓደኛዋ ቀበል አድርጋ፣ “እኮ! ባይሆን አውሮፓና አሜሪካ ስለትምህርት ቢያወሩ ያምርባቸዋል። እኛ አፍሪካ ውስጥ እየኖርን እንኳን ትምህርቱ ሊገባን አፈጣጠራችን ራሱ መቼ ገባን? አይደል እንዴ ቲቸርዬ?” ትላለች። መምህሩ አጉል ሙግት መግጠም የፈለገ አይመስልም። እየሰማቸው ይስቃል። ማስተማሪያ ክፍል ውስጥ ያላቃናውን አስተሳሰብ መሀል መንገድ፣ መሀል አደባባይ ላይ ‘ኤክስ’ እና ‘ራይት’ ሰጥቶ እንደማይለውጠው ያመነ ይመስላል። የቸገረ ነገር መብዛቱ!

ጉዟችን ወደ መገባደዱ ነው። አጠገብ ላጠገብ የተቀመጡት ደላላና ቻይና ከምኔው እንደ ተግባቡ ሳይታወቅ ስለሚከራይ ቤት ያወራሉ። “አይጠፋም ብቻ ይኼን (በእጁ ገንዘብ እንደሚቆጥር እያሳየ) ማዘጋጀት ነው. . . ” ይላል ደላላው። መናገር ይተናነቀዋል እንጂ አማርኛ ጥርት አድርጎ የሚያዳምጠው ቻይናዊ ራሱን በእሺታ ይነቀንቃል። “አየህልኝ ኢትዮ- ቻይና ወዳጅነት? አዲስ ብሔረሰብ ከቀላቀልን ቆይተናል እኮ?” ይለኛል አጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ እየሳቀ። ሁለቱ ስልክ ሲለዋወጡ ቃል ከአንደበቷ ቢወጣ የምትረክስ ትመስል የነበረችው ቆንጅዬ “ወራጅ!” አለች። ታክሲው ሲቆም፣ “እስኪ ይቅናህ በሉኝ!” ብሎ አጠገባችን ተቀምጦ የነበረውም ወጣት ተከትሏት ወረደ። “ድንቄም ሥራ ፈላጊ!’ አለ ከልጁ ጋር ከተነጃጀሱት አንደኛው። ወዲያው ደግሞ ጓደኛው ቀበል አድርጎ፣ “ደግሞ ከዚህ በላይ ምን ሥራ ያስፈልገዋል? መቼም ድንጋይ ከመፍለጥ ዘምቢል ካላት ቢሸከምላት ይሻለዋል፤” ብሎ በሳቅ ተንከተከተ (እያደር ከሚደረደረው የሽርደዳና የማሽሟጠጥ ባህል የምንወጣው መቼ ይሆን ግን?)፡፡ አፍታም ሳይቆይ ታክሲያችን ጥጉን ይዞ ወያላው “መጨረሻ!” ሲል አዛውንቶቹ ‘ባህል አታዳቅሉ. . . አታበላሹ. . . ’ እያሉ ይወርዳሉ። ደላላው ‘ኔትወርክ’ እንቢ ስላለው ለቻይናው የገባውን ቃል ቶሎ ለመፈጸም አቅቶት ያብዳል። ተማሪዎቹ አስተማሪያቸውን ቀድመው ወርደው ከመቅፅበት ተሰውረዋል። አጠገቤ ተቀምጦ የነበረውም ጎልማሳ ቆሎ እንዳልጋበዘኝ ሁሉ መውረጃው ሲደርስ፣ ታሰረ ስለተባለ ወዳጁ የሚያውቀውንም የማያውቀውንም እየለፈለፈ ሳይሰናበተኝ ተፈትልኳል። መምህሩ ብቻ በጥሞና ሁሉንም አስቀድሞ አስወርዶ ለአፍታ ወደ እኔ ዘወር ብሎ፣ “ከፍሬው ገለባው አልበዛም እንዴ?” አለኝ። እኔ ደግሞ በሆዴ ‹የዘሩትን ማጨድ ማለትም ይኼም አይደል› እያልኩ መንገዴን ስቀጥል፣ የአገሬም ጉዳይ ከዚህ እንደማይለይ አልተዘነጋኝም ነበር፡፡ እሱ ግን አልተወኝም፡፡ አንድ ነባር ግጥም ድንገት አምጥቶ፣ ‹‹ብስልና ጥሬ አብሮ ቢቀላቀል፣ ብስሉ አረረ ጥሬው እስኪበስል፤›› ሲለቅብኝ በፀጥታ መንገዴን ተያያዝኩት፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት