Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በእንስሳት ሀብት ላይ ያተኮረው ዓውደ ርዕይ ለመኖ ዕጦት መፍትሔ አመላካች ጉባዔ አሰናድቷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካ የእንስሳት ሀብት ዓውደ ርዕይና ጉባዔ፣ ለአራተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ከጥቅምት 8 እስከ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲካሄድ መሰናዶው ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ዓውደ ርዕይ ትልቁን ትኩረት ካገኙት ጉዳዮች መካከል የእንስሳት መኖ እጥረት ዋናው እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ላይ ከ13 አገሮች የተውጣጡ ከ60 በላይ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውንና ዘርፉ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ እንደሚያቀርቡ የዓውደ ርዕዩ አዘጋጆች ፕራና ኤቨንትስና የሱዳኑ ኤክስፖርት ቲም አስታውቀዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የእንስሳት ሀብት ተዋጽዖዎችና የዶሮና ለዶሮ ምርት ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች በዓውደ ርዕይ ከሚስተናገዱት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የፕራና ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅና የዓውደ ርዕዩ አዘጋጅ አቶ ነብዩ ለማ እንዳስታወቁት፣ ከቤልጂየም፣ ከቻይና፣ ከጀርመን፣ ከሀንጋሪ፣ ከህንድ፣ ከጣሊያን፣ ከዮርዳኖስ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከፓኪስታን፣ ከስፔን፣ ከአሜሪካ፣ እንዲሁም ከሱዳንና ከኢትዮጵያ የሚሳተፉ ኩባንያዎች የሚታደሙበት ይህ የንግድ ትርዒት የንግድ ልውውጥና የገበያ ትስስር ይካሄድበታል፡፡

በዚህ ደረጃ ከሚካሄደው ዓውደ ርዕይ ጎን ለጎን በኢትዮጵያም ሆነ በተቀረው አፍሪካ የእንስሳት ሀብት ዙሪያ ስለሚታዩ ችግሮችም የሚዳስስ ጉባዔ ይካሄድበታል፡፡ በኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት ዘርፍ ከሚታዩ ችግሮች መካከል መሠረታዊ የሚባሉት አራት ችግሮች ስለመሆናቸው የተናገሩት የእንስሳት መድኃኒትና የመኖ አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አትክልቲ ሀዱሽ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የዝርያ ችግር፣  የጤናና ክብካቤ፣ እንዲሁም የመኖ ችግሮች ሰፊ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡  ባለሥልጣኑ የመድኃኒትና የመኖ አቅርቦትና ጥራት ቁጥጥር ሥራዎች ቢኖሩበትም፣  በተለይ የመኖ ሥራ ላይ ያን ያህል የሚባል ቁጥጥር እንዳላደረገ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ይህም ሆኖ 18 አዳዲስ ደረጃዎችን በመከለስና አሥር አዲስ ደረጃዎች ላይ ጥናት በማካሄድ ለኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ማስረከቡን አታክልቲ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሦስት የእንስሳት መድኃኒት አምራሮች ብቻ በመኖራቸው አብዛኛው የቁጥጥር ሥራው ከውጭ በሚገቡት ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የገለጹት ዳይሬክተሩ፣   ሦስት የእንስሳት መድኃኒት አምራቾች በኢትዮጵያ ካለው ሰፊ ፍላጎት አኳያ ምንም ማለት እንዳልሆኑ፣ ከዓውደ ዕርዩም አዳዲስ የመድኃኒት አቅራቢዎችና አምራሮች ወደ ዘርፉ እንዲሰማሩ የሚያስችል ዕድል ይፈጠራል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡ ሌላው ከአምስት ዓመታት በፊት መሥሪያ ቤቱ ሲቋቋም አብዛኛው መድኃኒቶች የሚመጡት  ከቻይናና ከህንድ እንደነበር ሲገለጽ፣ አሁን ግን የገበያው ትስስር እየሰፋ በዓውደ ርዕዩ በተፈጠረው አጋጣሚም ጭምር ከኬንያና ከሱዳን መድኃኒት እንደሚገባ ተነግሯል፡፡

የዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኅበር ሰብሳቢ ደመቀ ወንድማኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በመስኩ የሚታዩት የምርትና የምርታማነት ችግሮች በርካታ ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡ በተለይ የዶሮ በሽታና የዶሮ ዕርባታ ላይ ችግሩ በሰፊው እንደሚታይ ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የዶሮና የእንቁላል ፍጆታ ዝቅተኛ ስለመሆኑ ገልጸው፣ ዓውደ ርዕዩ እንዲህ ላለው ችግር መፍትሔ ማፈላለጊያ መድረክ ከመሆን በተጨማሪ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም እርስ በርስ በመገናኘት ገበያ የማስፋትና ምርት ለማስተዋወቂያ መድረክ እንደሚሆናቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሥጋ አምራችና ላኪዎች ማኅበር ጸሐፊ አቶ አበባው መኮንን እንደተናገሩት፣ 12 የሥጋ ላኪዎች ቢኖሩም ባለፈው ዓመት 2010 ዓ.ም. ወደ ውጭ ከላኩት 20 ሺሕ ቶን የበግ፣ የፍየልና የከብት ሥጋ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኝተዋል፡፡ ይህንን ለማሻሻል ገበያውን በማስፋት በአገር ውስጥና በውጭ በሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች ላይ በተለይም በዱባይና በሳዑዲ ዓረቢያ በመገኘት ባለሀብቱ እንዲሳተፍ፣ የኢትዮጵያን ምርቶችም በማስተዋወቅ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ዓውደ ርዕይዩ ጠቀሜታው ትልቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ወቅት የውጭ ተሳታፊዎች የተጠበሰ ሥጋ ከጥሬው የሚቃመሱበትንና ፋብሪካዎችን እንዲጎበኙ የሚደረግበት ዝግጅት ስለመኖሩም አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአምራች ኢኮኖሚውንና ሌሎችም የቱሪዝም መስህቦችን በሚገባ ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም እንዳለው የሚነገርለት የኮንፈረንስ ወይም የስብሰባ ቱሪዝም፣ የሚፈለገውን ድጋፍና ትኩረት በመንግሥት በኩል እንዳልተሰጠው የሚገልጹት አቶ ነቢዩ፣ በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በቅጡ እንደማታገኝ አስታውቀዋል፡፡ በጀርመን፣ በዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስና በሌሎችም አገሮች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ከሚጎርፉባቸው ትዕይቶች መካከል የስብሰባ ቱሪዝም ትልቅ ቦታ እንዳለው ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያም ይህ ዘርፍ ትኩረት ቢሰጠው እስካሁን እየገባ ካለው 900 ሺሕ የውጭ ቱሪስት የበለጠ ቁጥር ማስመዝገብ የሚችልበት ዕድል እንዳለ ጠቅሰዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች