Friday, June 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ያሽቆለቆለው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ኢትዮጵያን ከደረጃ ውጪ አድርጓታል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ላለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሆና ስለመቆየቷ በርካታ ተቋማት ሲያስተጋቡት የቆየ አንኳር ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ ዓመት ግን የኢትዮጵያ ደረጃ እንደሚጠበቀው እንደማይሆን አመላካች መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ በየዓመቱ ከሚያወጣቸው ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች መካከል የዓለም ኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን የሚቃኘው ሪፖርት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2017 እና በ2018 ከተጠቀሳቸው የውጭ አንቨስትመንት መዳረሻ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድርሻ ነበራት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ከ4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከአፍሪካ ብቻም ሳይሆን፣ ከዓለም ታዳጊ አገሮች ተርታ ቀዳሚ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ያለ የውጭ ኢንቨስተመንት ፍሰት ማስናገዷ አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳ ቅናሽ ቢታይበትም አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ሊባል የሚችል ስለመሆኑ ተመድ አመላክቶ ነበር፡፡ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛውን የኢንቨስትመንት ፍሰት በማስተናገድ ቀዳሚነቱን ይዛ የቆየችው ኢትዮጵያ ከግንባታው ዘርፍ ባሻገር፣ በአውቶሞቢል መገጣጠምና በአነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች መስክ የምታደርገው እንቅስቃሴ የቱርክና የቻይና ባለሀብቶችን በመሳብ ደረጃዋን አስጠብቃ እንድትጓዝ እንደሚያበቋት ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ክምችቷ (በአንድ ዓመት ውስጥ ወይም በየሩብ ዓመቱ የሚገለጽ የወጪና የገቢ ኢንቨስመንት መጠንን ያመላክታል)፣ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆንም ተገምቶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ሰሞኑን የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በመላው ዓለም እየቀነሰ የመጣው የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት በኢትዮጵያም መታየቱን፣ አገሪቱም ከከፍተኛ መዳረሻዎች ተርታ ውጭ የሆነችበትን ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ ‹‹ኢንቨስትመንት ትሬንድስ ሞኒተር፤›› በተሰኘውና ከጥቂት ቀናት በኋላ በስዊዘርላንድ ከሚካሄደው የዓለም ኢንቨስትመንት ፎረም ቀደም ብሎ በተሠራጨው ጠቋሚ ሪፖርቱ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ከውጭ ኢንቨስትመንት ኮከብ ተጫዋቾች ተርታ ውጭ ሆናለች፡፡ 

የዓለም የውጭ ኢንቨስትመንት የ41 በመቶ ቅናሽ ማየቱን፣ ታዳጊ አገሮች ግን የዓለምን ሁለት ሦስተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ድርሻ መሳብ እንደቻሉ በተጠቀሰበት ሪፖርት ውስጥ ኢትዮጵያ አልተካተተችም፡፡ እ.ኤ.አ. የ2018 የመጀመርያ ግማሽ ዓመት ውስጥ እንደተመዘገበ የተጠቀሰው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን 470 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህ ግን እ.ኤ.አ. በ2017 መጀመርያ ግማሽ ዓመት ውስጥ ከተመዘገበው 794 ቢሊዮን ዶላር አኳያ የ41 በመቶ ቅናሽ የተመዘገበበት ሲሆን፣ ለዚህ ዋናው ምክንያትም በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች በሌሎች አገሮች ካሏቸው እህት ኩባንያዎች ውስጥ ያከማቹትን የውጭ ገቢ፣ በአሜሪካ የተደረገውን የታክስ ማማሻያ በመንተራስ ወደ አገራቸው ማስገባት በመጀመራቸው ነው፡፡ ምንም እንኳ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መጠን ያሽቆልቁል እንጂ የትልልቅ ኩባንያዎች ውህደትና የአዳዲስ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መስፋፋት በተቃራኒው ማንሰራራታቸው ተመልክቷል፡፡

የዓለም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ በአብዛኛው ቅናሽ ያሳየው ባደጉት አገሮች ውስጥ ቢሆንም፣ በአፍሪካ በጥቅሉ የሦስት በመቶ ቅናሽ መመዝገቡን ተመድ ይፋ አድርጓል፡፡ በአፍሪካ ከሚጠበቀው የ18 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ውስጥ የሦስት በመቶ ቅናሽ እንደሚጠበቅ ሲገለጽ፣ በአንፃሩ እንደ ደቡብ አፍሪካና ግብፅ ያሉት አገሮች የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰታቸው ሳይቀንስ እንደውም ጭማሪ የታየባቸው አገሮች ተብለዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ዓመት የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ካስመዘገበችው የ1.1 ቢሊዮን ዶላር አኳያ፣ እ.ኤ.አ. በ2018 ተመሳሳይ ወራት የ3.4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በማስመዝገብ በደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና እንደተመዘገ ከሚመገመተው የ40 በመቶ ጭማሪ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ወስዳለች፡፡ በአንፃሩ ከካምቦዲያ፣ ከማይናማር፣ ከባንግላዴሽ፣ እንዲሁም ከሞዛምቢክ በልጣ የ3.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ኢንቨስትመንት ፍስት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ቀዳሚ የነበረችው ኢትዮጵያ በዚህ ሪፖርት ስሟ አልተካተተም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች