Sunday, June 23, 2024

አዲሱ የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀትና አዳዲስ ባህርያቱ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ሁለተኛውን ሹምሽር አድርገውና የአስፈጻሚ አካላትን ብዛትም ቀንሰው ያቀረቡት አዋጅ ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በፓርላማው በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን፣ በአስፈጻሚው አካላት ቁጥርና አደረጃጀትንና በካቢኔ አወቃቀሩ ላይ በርካታ አዳዲስ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተሰየሙ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነበር፣ ካቢኔያቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው ያስፀደቁት፡፡ በወቅቱ ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የተረከቧቸው የካቢኔ አባላት ቢሆኑም፣ አዳዲስ የካቢኔ አባላትንም አካትተው የካቢኔ አባላትን ቁጥር ከ31 ወደ 28 አውርደው ነበር፡፡

በወቅቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበረው ስብሰባ ሦስት የፓርላማ አባላት የካቢኔ አወቃቀሩን የተቃወሙ ሲሆን፣ በአንድ የምክር ቤት አባል ድምፀ ተዓቅቦ መፅደቁ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የካቢኔ አባላት እንዲሆኑ ከተዋቀሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ተመጣጣኝ ተቋማት በአብዛኛው የአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን የካቢኔ አወቃቀር ተከትሎ የሄደ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ የካቢኔ አወቃቀሩን ለመቀየር ጥናት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያቋቋሙት ካቢኔ ቁጥሩ ወደ 20 ሲቀንስ፣ ካሁን ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ሁለት ባህርያት ያሉት ነው፡፡ የመጀመርያው የካቢኔ ቁጥር እጅግ እንዲቀንስ መደረጉ ሲሆን፣ ሁለተኛው ግማሽ ያህሉ ሴቶች የሆኑበት መሆኑ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሴቶችን ወደ ሥልጣን ለማምጣት ያሳሳቸውን ምክንያት ሲያስረዱ ሴቶች በሌብነት ባነሰ ደረጃ የሚታሙ መሆናቸውን፣ በተቋሞቻቸው እህታዊና እናታዊ ባህርያትን በማምጣት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የሚችሉ እንደሆኑ እንደሚተማመኑ ገልጸዋል፡፡

አዳዲሶቹን የካቢኔ አባላት በተመለከተ አስተያየት የሰጡ የፓርላማ አባላት ሙሉ በሙሉ የድጋፍና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያግዙ፣ ብሎም ሙያዊ ብቃትን ያገናዘበ ምደባ እንደተደረገ በማውሳት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም አክለው፣ ‹‹ከእናንተ ሕዝብ የሚጠብቀው ጥቂት ነገሮችን ነው፡፡ የመጀመርያው ሌብነትን መፀየፍ፣ ሁለተኛው ቅንነት የተሞላበት አገልግሎት መስጠት፣ ሦስተኛው ተቋም ቤተሰብ ነውና ቤተሰብ መሆን፣ ተቋማዊ ፎርም በመሥራት ፅዱ የሥራ አካባቢን መፍጠርና ከዩኒቨርሲቲዎችና ከግል ተቋማት ጋር በመተባበር በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መሥራት፣ ሰዓት አክባሪ መሆን፣ ስብሰባን ቀንሶ አብዛኛውን ጊዜ ለሥራ ማዋልና በአለባበስ ያማረ ሆኖ ሥነ ምግባር ያለው መሆንን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተለይ አሥር ሴቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ በእናንተ መሥሪያ ቤት ውስጥ ሌብነት በሐሜት እንኳን እንዳይነሳ ይጠብቃል፤›› ብለው፣ ፓርላማው ካሁን በፊት በአስፈጻሚው ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ ነው በማለት ለሚያነሳው ትችትና ጥያቄ መልስ የሰጠ አወቃቀር እንዳመጡ አስረድተዋል፡፡

ፓርላማው ለነበረው ጥያቄ ምላሽ ይሆናል ብለው ያሰቡትን ካቢኔ ሲያቀርቡ በበጎ ስለተቀበሉ አመሥግነው፣ የሰላም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊነት በዛ ሲሉ አስተያየት ለሰጡ የምክር ቤት አባላት መሥሪያ ቤቱ በዓለም የመጀመርያው በመሆኑ ጭምር አከራካሪ እንደሚሆን በመግለጽ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ከዴሞክራሲና ከልማት እኩል ሰላም አስፈላጊ ነው፤›› በማለት፣ የሰላም ሚኒስቴርን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት 12 ሚኒስትሮች ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን፣ አራቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባሉበት እንዲቀጥሉ የተደረጉ ናቸው፡፡ ከአፈ ጉባዔነታቸው ለቀው የሰላም ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት አይሻ መሐመድ (ኢንጂነር)፣ የገቢዎች ሚኒስትር የሆኑት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽነር የሆኑት ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር የሆኑት ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር)፣ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ያለምፀጋይ አሰፋ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር በመሆን የተሾሙት ሒሩት ካሳሁን (ዶ/ር) እና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ሴት የካቢኔ አባላት ናቸው፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር የሆኑት አቶ አህመድ ሽዴ፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት አቶ ኡመር ሁሴን፣ የትምህርት ሚኒስትር ጥላዬ ጌቴ (ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የሆኑት ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር በመሆን የተሾሙት አቶ ጃንጥራር ዓባይና የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር የሆኑት ሳሙዔል ሆኮ (ዶ/ር) አዳዲስ የተጨመሩና የተሸጋሸጉ ሚኒስትሮች ናቸው፡፡

ከፓርላማው ስብሰባ ማብቂያ በኋላ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት ወ/ሮ ሙፈሪያት ዞሮ ዞሮ የተቀበሉት የሕዝብ አደራ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ ይህ የካቢኔ አባላት ሹመት ታሪካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

‹‹ይህ የመሪያችንን ቁርጠኝነት ያየንበትና 50 በመቶ ሴት የአስፈጻሚ አባላትን ያየንበት ነው፡፡ ይህ በብዙ አገሮች የሚሞከር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ከአፈ ጉባዔነታቸው መነሳታቸው እንዳለ ሆኖ ከደኢሕዴን ሊቀመንበርነታቸው ጋር አዲሱ ኃላፊነት የባሰ የሥራ መደራረብ አይኖረውም ወይ ተብለው የተጠየቁት ወ/ሮ ሙፈርያት፣ ‹‹ያለን ኃላፊነት ማጣጣም ብቻ ነው ዋናው፡፡ ለሁላችንም የተሰጠን ጊዜ እኩል ነው፡፡ ጊዜን ለሕዝብ ኃላፊነት በአግባቡ መጠቀም ነው ዋናው፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዲሱ የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ላይ ሦስት ዋና ዋና ባህርያት ታይተዋል፡፡ አንደኛው አዲስ መሥሪያ ቤት መቋቋም፣ ሁለተኛው ደግሞ መሥሪያ ቤቶችን መቀላቀል ሲሆን፣ ሦስተኛው መሥሪያ ቤቶችን ማጠፍ ናቸው፡፡

እነዚህ ተቋማት ሲደራጁ ሁለት ጉዳዮችን ታሳቢ እንዳደረጉ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ተቋማዊ ባህርይና ተቋማዊ ዓላማ ዋነኛ መመዘኛዎች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በዓላማቸውም መሠረት እነማን ቢሰባሰቡ የሚጠበቅባቸውን ያሳካሉ የሚለው መታየት አለበት የሚለው እንደተጤነ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ጥናቱን ስንጀምር አሁን ባለው አደረጃጀት ሥራ ለመሥራት መመርያ ማሻሻልና የሰው ኃይል ብቻ በቂ አይሆንም ወይ ብለን ተወያይተን ነበር፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተቋማት እንደ ሰዎች ከጊዜው ጋር የሚቀያየሩ ስለሆኑ አዲስ አወቃቀር ለማምጣት መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ባለፉት ጥቂት ወራት ስንሠራ በቆየነው የሪፎርም ሥራ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥ የኢትዮጵያውያን ፍላጎት በመሆኑ፣ ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ አንገብጋቢ ስለሆነ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የኢትዮጵያ ፍላጎት በመሆናቸው፣ ቅን አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት መገንባት የኢትዮጵያ ፍላጎት በመሆኑና አሁን ያለውን አስፈጻሚ ወጪ ቆጣቢ ሆኖ የሚሰጠን ኃላፊነት የሚወጣ እንዲሆን›› ታልሞ ላለፉት አምስት ወራት ጥናት ተካሂዶ አዲሱ አደረጃጀት መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚታየው የፖለቲካና የማኅበራዊ ቀውስ ከሰዎች መሞት በዘለለ መዋቅራዊ ችግሩን መለየት አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሥርዓት፣ መዋቅርና ስትራቴጂ ካልቀየርን አሁን ያለውን ፍላጎት ማሟላት አንችልም፤›› ሲሉ የተደረገው ለውጥ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዲስ ከተቋቋሙ የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የሰላም ሚኒስቴር ትኩረትን የሳበ ሲሆን፣ በዓለም የመጀመርያው እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ መሥሪያ ቤት የተሰጡት ኃላፊነቶች ካሁን ቀደም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የነበሩትን ተቋማት ተጠሪ ማድረግን ያጠቃልላል፡፡ በዚህም መሠረት በጄኔራል አደም መሐመድ የሚመራው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ በአቶ ተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ)፣ በአቶ ገመቹ ወዩማ የሚመራው የፋይናንስ ደኅንነት መረጃ ማዕከል፣ በአቶ  ዘይኑ ጀማል የሚመራው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ በአቶ ገብረ ዮሐንስ ገብሩ የሚመራው የኤሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ (ወሳኝ ኩነቶች አዲስ የተጨመረ ነው)፣ በአቶ ምትኩ ካሳ የሚመራው የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠሪነታቸው ለሰላም ሚኒስቴር እንዲሆን ተደንግጓል፡፡

የዳያስፖራ ኤጀንሲም አዲስ የተቋቋመ ሲሆን፣ ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሆን ተደንግጓል፡፡

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከከተማና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር ተመልሶ የተቀላቀለ ሲሆን፣ የሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር እንደ ቀድሞው ወጣቶችን ሲያቅፍ፣ ስፖርት ራሱን ችሎ በኮሚሽንነት እንዲቋቋም ተደንግጓል፡፡ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴሮች የግብርና ሚኒስቴር በሚል የተዋቀሩ ሲሆን፣ በሥሩ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣንና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲን ጨምሮ 11 ተጠሪ ተቋማትን በሥሩ ይዟል፡፡

አዲሱ የካቢኔ አወቃቀር ካሁን ቀደም ለሁለት ተከፍሎ የነበረውን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ወደ ቀድሞ ቦታው በመመለስ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን አቋቁሟል፡፡ የተለያዩ ኢንስቲትዩቶችን፣ የደረጃዎች ኤጀንሲን፣ የአክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤትን፣ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩትን፣ የተስማሚነት ምዘና ኤጀንሲንና የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ልማት ድርጅትን ጨምሮ 14 ተጠሪ መሥሪያ ቤቶችን አቅፏል፡፡

ምንም እንኳን ይህ አደረጃጀት በፓርላማው በሙሉ ድምፅ ቢፀድቅም፣ ከምክር ቤቱ የአስፈላጊነትና የአግባብነት ብሎም የሥራ መደራረብ ሥጋት ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል፡፡

ልክ እንደ ኢንቨስትመንስ ኮሚሽን ሁሉ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ እንደሚያደርግ በሚኒስቴሩ ሥልጣንና ተግባራት ውስጥ የተጠቀሰ መሆኑ፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሥራ እንቅስቃሴዎች አንፃር ግጭት ይፈጥራል ያሉ የምክር ቤት አባል ሥጋታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

‹‹ንግድና ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ወደ ልማት ከገቡ በኋላ የሚያደርገው ድጋፍ አግባብ ነው፡፡ ግን ቀደም ብሎ ኢንቨስትመንት ማስገባት ላይ ይጋጫል፤›› ሲሉም አንድ የምክር ቤት አባል ጠይቀው ነበር፡፡ በተመሳሳይም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ተጠሪነት ለኢንቨስትመንት ኮሚሽን መሆኑ የቅሬታ ሥርዓት ላይ ችግር ይፈጥራል የሚል ጥያቄም ተሰንዝሮ ነበር፡፡

በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የአደረጃጀቱን ጥናት የመሩት አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ‹‹የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዋናነት በአገር ውስጥ ባለሀብት ላይ ትኩረት እንዲያደርግና የኢቨስትመንት ኮሚሽን ደግሞ በውጭ ባለሀብቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ሆኖ ነው የተዋቀረው፤›› ብለው፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽንን በሚመለከት የፓርኮች ግንባታ በአብዛኛው እየተጠናቀቀ ስለሆነ ቀሪው ሥራ ባለሀብት ማስገባት ስለሆነ፣ ተጠሪነቱ መቀየሩን አስረድተዋል፡፡

በዚህ የአስፈጻሚ አካላት አዋጅ ላይ የታየው አዲሱ ነገር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች እንዲኖሩ መወሰኑ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ ስምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተግባሩን ለመወጣት ይረዳው ዘንድ የምክር ቤቱ አባላት የሚገኙባቸው ልዩ ልዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ሊያቋቁም ይችላል የሚል ድንጋጌ ሲኖረው፣ የቋሚ ኮሚቴዎቹ ሥልጣንና ተግባር በምክር ቤቱ የውስጥ ደንብ ይወሰናል ይላል፡፡

ይሁንና በፓርላማ ይህ አሠራር የተለመደ ስለሆነ፣ ምን ዓይነት አሠራር ሊኖረው እንደሚችል በግልጽ ስላልተቀመጠ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ አንስተውበታል፡፡

በዚህ ላይ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ታገሰ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚኖረው ቋሚ ኮሚቴዎች በሲኒየር ሚኒስትሮች የሚመሩ ስለሚሆኑና በዋናነት ሥራቸው የምክር ቤቱን አሠራር ማቀላጠፍ ስለሆነ፣ ከፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር እንደማይጋጩ አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም አባላቱ ሚኒስቴር የነበረው የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ወደ ኮሚሽንነት መቀየሩን የተቹ ሲሆን፣ በአፍሪካና በዓለም መድረክ አድናቆትን ያስገኘው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት አሁን ላይ ትኩረት ተነፍጎታል ማለት ነው ያሉ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በዓለም የምንደነቀውና በአፍሪካ የምንከበረው የደን ሚኒስቴር ስላለን ሳይሆን፣ በምንሠራው ሥራ ነው፤›› በማለት፣ ‹‹የደን ሥራ አስፈላጊና የተሠራውም ሥራ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራውን በኮሚሽን ደረጃ ማከናወን ይቻላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ተቋማት ደካማ ስለሆኑ ብቻ እንደማይፈርሱና ‹‹በኢትዮጵያ ካሉ ተቋማት ከአማካይ ከፍ ብሎ ሥራውን በብቃት የሚወጣ አንድም ተቋም የለም፡፡ ዓላማ የሌለው ተቋም መፍጠር ልክ ቁጭ ብሎ እንደሚቀለብ ሰው ነው፡፡ ለመለካትም ከባድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አወዛጋቢው የአስፈጻሚው አካል ሥልጣን

በፓርላማው 1097/2011 ሆኖ የፀደቀው አዋጅ፣ ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት ማንኛውም አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሀድ ወይም እንዲከፈል በማድረግ፣ ተጠሪነቱ ወይም ሥልጣንና ተግባሩ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን በዚህ አዋጅ ተሰጥቶታል፤›› የሚል ድንጋጌ የያዙና በፓርላማ አባላትም ሆነ በሕግ ባለሙያዎች ትችት የቀረበበት ነበር፡፡

አንድ የፓርላማ አባል፣ ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አውጥቶ ማንኛውንም መሥሪያ ቤትና አስፈጻሚ አካል ማጠፍ፣ ማቋቋምና ማዋሀድ፣ እንደሚችል ሥልጣን ይሰጣል፡፡ እንዴት ነው የታሰበው? በአዋጅ የተቋቋሙ ወሳኝ መሥሪያ ቤቶችንም ጭምር የማጠፍ ሥልጣን የሚሰጥ ከሆነ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ መዋቅር ውስጥ ይህንን አደረጃጀት የማፅደቅ ሚናው እንዴት ነው የታየው? ይህ አንቀጽ አተገባበሩ እንዴት ሊገመገምና ወደ ተግባር ሊቀየር ታስቧል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ አሊ ሒጅራ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ሕገ መንግሥቱን የጣሰና የሕግ አውጪውን ሥልጣንና ኃላፊነት ያላግባብ አሳልፎ የሚሰጥ ነው፤›› ሲሉም ይተቻሉ፡፡

ይሁንና በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ አዳዲስ ተቋማትን በተለይ አጠቃላይ የለውጥ እንቅስቃሴ ማዕከል በማድረግ መፍጠር በሚያስፈልግበት ጊዜ፣ እንዲሁም አሁን ያለንን ሀብት አጠቃቀም በሚመለከት በየጊዜው እየታየ ተቋማትን ለማስተካከል የሚያስችል ሥልጣን ቢሰጠው አሁን በፌዴራል ደረጃ ያሉ ተቋማትን በዝርዝር ለማየት ዕድል ይሰጣል፤›› ሲሉ አስረድተው፣ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችል ዕድልም ይሰጣል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -