ባለረዥም ጭራ ጦጣ ስፓይደር ጦጣ (Spider Monkey) ይባላል፡፡ ስፓይደር ጦጣዎች ከጭራቸው በተጨማሪ እጆቻቸውም ረዣዥሞች ናቸው፡፡ ጭራቸውንና እጆቻቸውን ከዛፍ ዛፍ ለመዝለልና ቆንጥጦ ለመያዝ ይጠቀሙበታል፡፡
እነዚህ ጦጣዎች ከሌሎቹ የሚለዩት በጭራቸው ርዝማኔ ነው፡፡ ጥራቸውንም እንደ አምስተኛ የእጅና እግራቸው አካል ይጠቀሙበታል፡፡ ቀን ላይ ባብዛኛው የሚመገቡትን ፍራፍሬ ይለቅማሉ፡፡ አበባ፣ ቅጠላ ቅጠልና ትናንሽ ነፍሳትን ደግሞ ፍራፍሬ በማይኖሩባቸው ወቅቶች ይመገባሉ፡፡ አብዛኛውን ብርሃናማ ሰዓት የሚያሳልፉት ከዛፍ ዛፍና ከፍታ ካለው ቦታ ላይ በመዝለል ነው፡፡
በጋራ የሚኖሩ ሲሆን፣ በአንድ ቡድን ውስጥም ከ20 እስከ 100 የሚደርሱ ስፓይደር ጦጣዎች አብረው ይኖራሉ፡፡ ቡድናቸው የሚከፋፈለው በምግብ ለቀማ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ሴቶቹ የሚወልዱት በዓመት ወይም በሁለት ዓመት አንዴ ብቻ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ልጅ አይወልዱም፡፡ እናት የወለደችውን ልጅ እስከ 16 ሳምንት ድረስ በሆዷ አዝላ ትቆያለች፡፡ እስከ አሥር ወር ለሚሆን ጊዜም እናት ከልጇ አትለይም፡፡
ስፓይደር ጦጣዎች ብልህ ሲሆኑ፣ የማስታወስ ችሎታቸውም ከፍተኛ ነው፡፡ የመኖር ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 27 ዓመት ነው፡፡