Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅየሦስተኛው ፓትርያርክ አዲስ ሐውልት

የሦስተኛው ፓትርያርክ አዲስ ሐውልት

ቀን:

ኢትዮጵያ የራሷን ፓትርያርክ መሾም ከጀመረች ወደ ስድስት አሠርታት ይጠጋል፡፡ በ57 ዓመት ውስጥ የአሁኑን ቅዱስ ፓትርያርክ ጨምሮ ስድስት ቅዱሳን አበው ቤተ ክርስቲያኒቱን መርተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከ27 ዓመት በፊት በዛሬው ዕለት ግንቦት 28 ቀን 1980 ዓ.ም. ያረፉት ሦስተኛው ፓትርያርክ (1968-1980) ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይገኙበታል፡፡ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው መካነ መቃብራቸው ላይ የቆመው ሐውልታቸው፣ በዘመን ብዛት የማርጀቱና በመጐሳቀሉ እንደ አዲስ ተሠርቶ ባለፈው ሳምንት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ተመርቋል፡፡ አዲሱን ሐውልት በግል ገንዘባቸው በ1.5 ሚሊዮን ብር ወጪ ያሠሩት በጎ አድራጊው አቶ ቁምላቸው ገብረ ሥላሴ መሆናቸው በምረቃው ዕለት ተነግሯል፡፡ በቀድሞ መጠርያቸው አባ መልአኩ ወልደ ሚካኤል ይባሉ የነበሩት አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ የተወለዱት በቤገምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት፣ ማኅደረ ማርያም ገዳም አካባቢ፣ ጋዠን በሚባል ቦታ መስከረም 10 ቀን 1910 ዓ.ም. መሆኑን ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡ (በሔኖክ ያሬድ)  

******

ምሳሌያዊ አነጋገሮች ከደራሲዎቻችን ብዕር

ለአንቺ ብርቅሽ፣ የዘንጋዳ ሙቅሽ። – አሌክስ አብርሃም
ለወገን ጽናት፤ ለጠላት ቅናት። – አቤ ቶኪቻው
ለዶሮ አጥንት፣ መጥረቢያ አያስፈልገውም። – በጋሻው ሐዲስ
ልብ ያሰበውን፣ ኩላሊት ያመላለሰውን ያውቃል። – ንቡረዕድ ኤርምያስ ከበደ
ልጅ በጡት፤ እህል በጥቅምት። – ካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር
ሙት አይሰማም፣ አይለማም። – አዳም ረታ
ሲመች በእጅ፣ ሳይመች በመጅ። – ሔኖክ የሺጥላ
ቢጨብጧት ትሞታለች፣ ቢለቋት ትበራለች። – አጥናፍ ሰገድ ይልማ
አለንጋ ባይገርፉበት ያስፈራሩበት። – ኤፍሬም እሸቴ
አይቴ ቁርጠቴ፣ ደፋ በይ ከፊቴ። – ዶ/ር እንዳላማው አበራ
አዳም በበደለ መድኃኒዓለም ካሰ። – ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ከአሥር ዲግሪ፣ አንድ ግሮሠሪ። – ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ
ከደሃ ቤት ጥቅስ፤ ከሀብታም ቤት ጥብስ። – በዕውቀቱ ሥዩም
የሮጠ አመለጠ፤ የቆመ ቀለጠ። – ዓለማየሁ ገላጋይ
የተቀማጭ፣ አፉ ምላጭ። – አቡነ መልከ ጻዴቅ
ጋን በጠጠር ይደገፋል። – ኃይለ መለኰት መዋዕል

– ዳንኤል ኤ. አበራ በድረ ገጹ እንደቀመረው

*******

‹‹እርኩምን ሊበሉ ጅግራ ነው አሉ››

ራስን መደለል በእንስሳትም መካከል በጥቂቶች ላይ የተደረገ ሆኖ፤ በምሳሌ ዓይነት እንደ ተረት የሚነገር ቃል እናገኛለን፡፡ ተረቱም እንደሚከተለው ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የተራበች ጦጣ ባንድ የወይን ስፍራ አጠገብ ስታልፍ ቁመቷ ከማይደርስበትና ዘልላም ልታወርደው ከማይቻላት አስቸጋሪ ከሆነ ካንድ ከፍተኛ ስፍራ ላይ በስሎ መልኩ ብቻ እንኳን የሚያስጐመጅ አንድ የወይን ዘለላ ተንዠርጐ ተመለከተች፡፡ ለማውረድም ሞክራ ሳይሆንላት ስለቀረ ልቧ እያወቀ፣ ራሷን በማታለል  ወይኑ እኮ እንደሆን በእውነቱ ገና አልበሰለም፤ ለጊዜው የደረሰ መሰለ እንጂ ጥሬ ነው፡፡ ስለዚህ ላንድ ጥሬ ለሆነ ላልበሰለ ወይን ይህን ያህል ምን ያደክመኛል? የሱን ዓይነት ከሌላስ ስፍራ አጥቼ ነውን? በማለት ራሷን ደልላ ይኸንኑ ቃል በመደጋገም ራሷን እየነቀነቀች ነገሩን አኳስሳ ትታው ሄደች ይባላል፡፡

እንደዚሁም አንዲት ሰጐን አንድ አዳኝ ጠመንጃውን ደግኖ ሊተኩስባት ሲያነፃፅርባት እያየች፤ ሮጣ  ሕይወቷን ለማዳን ከመሞከር ይልቅ፤ እዚያው ሁና ተደፍታ ዓይኖቹዋ እንዳያዩ ወደታች አቀርቅራ፤ የት አለና ነው አዳኝ? ቢኖር ለምን አላየውም? ይኸው ምንም ነገር አላይም እያለች በሐሳቧ ራሷን ደልላ ከዚያው አንገቷን ደፍታ ተቀመጠች ይባላል፡፡    

የቀድሞ አባቶቻችን፤ ሰው ያልኾነውን ነው በማለት ራሱን የሚደልል ከንቱ መኾኑን ተመልክተው ‹‹እርኩምን ሊበሉ፤ ጅግራ ነው አሉ›› ብለው ይተርኩት የነበረ ቃልም ይገኛል፡፡

ስለዚህ ሰው ራሱን በራሱ እንደ ሕፃን  ልጅ በመደለል በሐሳቡ የተመኘውን ነገር ሁሉ ሲፈጽም መታየቱ የቆየ እንጂ፤ አዲስ አይደለም፡፡

  • ዶ/ር የማነ ገብረማርያም ‹‹የፍልስፍና ትምህርት›› (1955)

******

ቻይና ለሴቶች የተለየ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ አዘጋጀች

በቻይና ሴት አሽከርካሪዎች መኪናቸውን ለማቆም፣ ካቆሙበት ሥፍራ ለማውጣት የሚገጥማቸውን ችግር ለማቃለል ሲሉ፣ ለነርሱ ብቻ የሚያገለግለውን  ማቆሚያ ከሌሎቹ ስፍራዎች 50 በመቶ ያህል ሰፍቶ እንዲሠራ መደረጉን ዩፒአይ ዘገበ፡፡

ከመደበኛ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ በተለየ መልኩ በሐንግዙ ታንግሉ አውራ ጎዳና አካባቢ ፓርኪንጉ የተሠራው ሴቶች መኪና ለማቆምና መልሶ ለመውጣት መቸገራቸውን ከግምት በማስገባት ነው፡፡

መኪና ለብቻ የሚያቆሙበት ስፍራ መዘጋጀቱ ግን፣ ለጾታ ትንኮሳ ያጋልጣቸዋል የሚሉ ትችቶች በማኅበራዊ ድረ ገጾች እየተሰነዘሩ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2009 በደቡብ ኮሪያ ሲዖል ተመሳሳይ የሴቶች መኪና ማቆሚያ የተሠራ ቢሆንም፣ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ተብሎ በንግድ ማዕከላት በሮች አካባቢ መሠራቱ ከቻይናው ለየት ያደርገዋል፡፡

******

ቻይና ሰዉ በቀን ከ200 ግራም በላይ ሥጋና እንቁላል እንዳይመገብ አቀደች

ቻይናውያን እያጋጠማቸው ያለውን ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለመከላከል፣ የሥጋና የከብት ተዋፅኦ ምግባቸውን እንዲቀንሱ የቻይና መንግሥት ጠየቀ፡፡ የጤና ባለሙያዎችም አንድ ሰው በቀን ከ200 ግራም በላይ ሥጋና እንቁላል እንዳይበላ ዕቅድ አውጥተዋል፡፡

ኢንዲፐንደት ዩኬ እንደዘገበው፣ ቻይናውያን በቀን የሥጋና እንቁላል አመጋገብ መጠናቸው ከ200 ግራም እንዳይበልጥ የጤና ባለሙያዎቹ ዕቅድ ያወጡት፣ አንድ ቻይናዊ በቀን በአማካይ የሚመገበውን 272 ግራም ሥጋና 235 ግራም የከብትና የዶሮ ተዋጽኦ ለማስጣል ነው፡፡ የጤና ባለሙያዎች ዕቅድ ግን አሜሪካ ወደ ቻይና የምትልከውን የሥጋ መጠን ያሽቆለቁለዋል ተብሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...