Saturday, July 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የማንበብ “አፒታይታችን” ለምን ተዘጋ?

ራኔ ዊሌክ የተባሉት ዕውቅ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያ የሥልጣኔ መሠረቱ “ማንበብ ነው” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ ማንበብ የነገሮች ሁሉ መሠረት ነው፡፡ የማኅበራዊ፣ የምጣኔ ሀብታዊና የፖለቲካዊ ሁነቶች ለውጥ ማምጫ መሣሪያ ነው፡፡ የማያነብ ትውልድ ለራሱም ሆነ ለአገሩ ረብ ያለው ሥራ ሊሠራ እንደማይችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡

ለአብነት ያህል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ በሁለቱ የጃፓን ከተሞች (ሔሮሺማና ናጋሳኪ) ላይ በጣለችው አቶሚክ ቦምብ ዜጐች ለከፋ የሥነ ልቦና ቀውስና ከተሞቹም ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረው እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ይኼ የሥነ ልቦና ችግርና የከተሞቹ መፈራረስ ጥሎ ያለፈው ጥቁር ጠባሳ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ግን መፍትሔ እንደተበጀለት ከዛሬዋ ጃፓን መረዳት እንችላለን፡፡ ጃፓን ከደረሰባት የሥነ ልቦናና ሌሎች ምጣኔ ሀብታዊ ቀውሶች አገግማ ዛሬ የዓለም የሥልጣኔ ማማ ወደ መባል ደረጃ ላይ እየተሸጋገረች ነው፡፡

ይኼ ትናንት ኢትዮጵያና ጃፓን ተመሳሳይ የምጣኔ ሀብት ላይ የነበሩበት ታሪክ ተሽሮ የሁለቱ አገሮች ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ተራርቋል፡፡ የእዚህ ዋነኛ የልዩነት መንስዔው ምንድነው? ብለን ስንጠይቅ ጃፓን ከዚያ ሁሉ ማጥ ለመላቀቅ ቁርጠኛ ሆና ዜጐቿን ልምድ እንዲቀስሙ ወደ ሠለጠኑ አገሮች በመላኳ፣ ወጣቱ ትውልድም የማንበብ ባህሉን በማዳበር ተመራማሪና የአዳዲስ ግኝቶች ባለቤት እንዲሆን በተወሰደው ዕርምጃ እንደሆነ የጃፓን ታሪክ ያስረዳል፡፡

ማንበብ የሁሉ ነገሮች መሠረት እንደሆነ ለአብነት ያህል ከወሰድነው የጃፓን ታሪክ እንረዳለን፡፡ ይሁን እንጂ የዛሬዋ ኢትዮጵያ አይደለም የሥልጣኔ ማማ ልትባል ይቅርና በልመና የምትታወቅበት ስሟ እንኳ መሻር አልቻለችም፡፡ የብዙ ሺሕ ዓመታት ባለቤት የሆነችው አገራችን እስከ ዛሬ ድረስ በድህነትና በኋላ ቀርነት የዓለም ተምሳሌት ነች፡፡

ተፈጥሮ ያደላት ምንጩ፣ ወንዙ፣ ተራራው፣ ሸለቆው፣ ጫካው፣ጋራው፣ ሸንተረሩ፣ የአየር ንብረቱ፣ ወዘተ. ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ቢሆንም ዜጓቿ ግን እስከ ዛሬ ድረስ በልተው ማደር አልቻሉም፡፡ የሰው አገር ናፋቂዎችና ዓላሚዎች ብቻም ሳይሆኑ የባህር ሰለባዎች ሆነው ብዙ ሺሕ ዓመታት አልፈዋል፡፡

የዛሬው ትውልድ ‹‹ትናንት አክሱምን ገንብተናል፣ ላሊበላን አንፀናል፣ የፋሲልና የጀጐል ግንብን አቁመናል፣›› ወዘተ. እያለ ከማውራት ውጭ ለአገሪቱ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ በሚችል ሥራ ላይ ተሠማርቶ አይታይም፡፡ ይባስ ብሎ ለጫትና ለሺሻ ተገዥ ሆኖ ወርቃማ ጊዜውን ባልባሌ ቦታዎች እያዋለ እንደሆነ ምስክር ሳያስፈልግ ከቀኑ አምስት ሰዓት በኋላ እንደ መርካቶ ገበያ ተደርድረው ወደ ሚገኙበት ጫት ቤቶች ጐራ ማለት በቂ ነው፡፡ የዚህ ወጣት አዕምሮ በማንበብና በፈጠራ ሥራዎች ቢሠማራ አገሪቱ የት ትደርስ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ዓመታዊ ጉባዔውን ሲያካሂድ ለውይይት መነሻነት ያቀረበው አንድ ጽሑፍ ነበር፡፡ የእዚህ ጽሑፍ ጭብጥ “የዛሬው ትውልድ በተለይም ወጣቱ  የማንበብ ባህሉ እየቀነሰ እንደመጣ” የሚገልጽ ነበር፡፡ ለዚህ ችግር እንደ መነሻነት ያስቀመጠው ጉዳይም የበሳል ጽሑፎች አለመታተም፣ የአሳታሚዎች ቁጥር ማነስ (ያሉትም ቢሆን ትኩረታቸው በሥነ ጽሑፍ መጻሕፍት ላይ ሳይሆን ባቋራጭ ገንዘብ የሚያገኙበትን መጻሕፍት ማሳተም ላይ ትኩረት ማድረግ ለምሳሌ አጋዥ የትምህርት መፅሀፍትን) እና ወጣቱ ትውልድ በማንበብ ከሚያሳልፍ ይልቅ በሌሎች ሱስ አስያዥና መሰል ጉዳዮች ላይ ጊዜውን ማሳለፍ የሚመርጥ መሆኑ የሚሉ ነበሩ፡፡

ይኼ የዳሰሳ ጽሑፍ በጣም ጥሩና አሁንም በባለድርሻ አካላት (በደራሲያን ማኅበር፣ በመንግሥትና በሌላው ኅብረተሰብ) ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራበት የወጣቱን ባለማንበብ በሽታ ተይዞ እየተሰቃየ ካለበት አባዜ ማውጣት ይቻል ነበር የሚል አስተያየየቴን እያቀረብኩ፣ ለአብነት ያህል በአገራችን ውስጥ የታተሙ መጻሕፍትንና የተደራሲያኑን አቀባበል በወፍ በረር ለመቃኘት ልሞክር፡-

በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ላለው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ባለውለታ ተደርገው ከሚወሰዱ ደራሲያን መካከል ጥቂቶች መንግሥቱ ለማ፣ ታደሰ ሊበን፣ መንግስቱ ገዳሙ፣ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ አቤ ጉበኛ፣ ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የእነዚህ ደራሲያን ሥራዎች ወጣቱን ትውልድ በማነፅና የንባብ ባህሉን በማጐልበት በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ እነዚህ ደራሲያን በሚጽፋበትና በሚያሳትሙበት ወቅት ተደራሲያኑ አነፍንፎ የማንበብና ሒስ የመስጠት ልምድ እንደነበረው አንዳንድ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ለምሳሌ የሐዲስ ዓለማየሁን “ፍቅር እስከ መቃብር” ብንወስድ ይኼ ፖለቲካዊ ይዘት የነበረው መጽሐፍ ወጣቱን ትውልድ የንባብ ፍቅር እንዲኖረው አስችሏል፡፡ ያኔ በፊውዳሉ ሥርዓት እንኳ “ንጉሥ አይከሰስም ሰማይ አይታረስም” እየተባለ በሚታመንበት ወቅት የመንግሥቱን የአስተዳደር ሥርዓትና ጨቋኝነት በተዘዋዋሪ መንገድ በመንቀፍ የኮነኑበት ወቅት እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ብቅ ብለው በመንግሥቱ እንደተገደሉ ከሚታማው ደራሲያን መካከል ደግሞ በዓሉ ግርማ አንዱ ናቸው፡፡ በዓሉ ግርማ “በኦሮማይ” መጽሐፋቸው የደርግን ጭቆናና የአምባገነንነት ባህሪ በድፍረት በመጻፍ የአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ ይኼ መጽሐፋቸው በዚህ ትውልድም በተደጋጋሚ ጊዜ ታትሟል፡፡

እነዚህ ተወዳጅ የሆኑ ደራሲያን ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ ብዕርና ወረቀታቸውን አገናኝተው የዛሬዋን ኢትዮጵያ የሚገልጹበት ብዕራቸው ደርቋል፣ አንደበታቸው ተዘግቷል፡፡ ስለሆነም ያሁኑ ትውልድ  “ጽሑፍ ድሮ ቀረ” እያለ በአጓጉል ሥፍራዎች ጊዜውን ከማባከን የዘለለ ሥራ ሲሠራ አይታይም፡፡ ዛሬ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ የሕዝብ ቁጥር ይዘን የሚታተሙ መጸሐፍትን የኮፒ ብዛት ብንመለከት ከ5,000 ግፋ ቢል 10,000 ኮፒ አይበልጥም፡፡ ይኼ ደግሞ ካለን የሕዝብ ብዛት በተለይ 70 በመቶ ወጣቱ እንደመሆኑ መጠን የማንበብ “አፒታይታችን” እንደተዘጋ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ዓለማየሁ አበበ የተባሉ የታሪክ ባለሙያ የኢትዮጵያን የመጻሕፍት ገበያና የዛሬውን ትውልድ አንባቢነት ሲገልጹ “አሳዛኝ ክፍተት አለ” ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ እንደሳቸው አገላለጽ በአሁኑ ወቅት የትውልዱ አንባቢነት  ጥያቄ ምልክት ውስጥ የገባ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

በሌላ በኩል የዚህ ትውልድ ቀንዲል ተደርገው የሚወሰዱ በጣት የሚቆጠሩ ደራሲዎቻችንና መጸሐፍቶቻቸውን ስንመለከት ቁጥራቸው እጅግ የሳሳ ነው፡፡ አሁንም የበሳል ደራሲዎቻችን ቁጥር ካለን የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲመዘን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ እዚህ ላይ የደራሲያን ቁጥር ማነስ ምክንያቱ ምንድነው? ብለን ጥያቄ ብናነሳ የመጀመርያ ሊሆን የሚችለው መልስ የኑሮ ውድነቱ ባስከተለው ችግር ምክንያት የማሳተሚያ ዋጋ (Printing cost) ከፍተኛ መሆንና የአሳታሚዎች ቁጥር ማነስ የሚል መልስ ልናገኝ እንደምንችል እረዳለሁ፡፡ ሌላውና ዋናው ችግር ተደርጐ የሚወሰደው ደግሞ ወጣቱ ትውልድ የማንበብ ባህሉ አነስተኛ መሆንና በአጓጉል ባህሎችና ሱሶች ተጠምዶ ጊዜውን የሚያባክን መሆኑ ነው የሚል መልስ እናገኛለን፡፡

ማጠቃለያ፡-

መጻሐፍት ዝምተኛ ጌቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ዝምተኛ ጌቶች ስንገልጣቸው እንደ ውቅያኖስ ጥልቅ እንደ ሰማይ ሩቅ የሆነ የሐሳብ ጅረት ባለቤቶች እንሆናለን፡፡ ከያዙን የሱስና የሌሎች መጥፎ አባዜዎች ነፃ እንወጣለን፡፡ እንደ ጃፓን ወጣት አንባቢ ትውልድ በመፍጠር ዛሬ አገራችን ከምትታወቅበት ኋላቀርነትና መኃይምነት ተላቅቀን የነፃይቱ ምድርን የኋላ ቀርነት አባዜ ማላቀቅ እንችላለን፡፡ ጊዜያችንን በሆነ ባልሆነው ከማባከን ወጥተን በጥናትና በምርምር ላይ ተሰማርተን አገራችን ከፍ ወደምትልበት ደረጃ ማሸጋገር አለብን፡፡

እርስ በርስ ከመወነጃጀልና ሌሎች አጓጉል ልማዶች ወጥተን ለመጪው ትውልድ የፍቅርንና የማንበብ ባህልን ማስተላለፍ አለብን፡፡ ለዘመናት ከምንታወቅበት የእርስ በርስ ጦርነት ዛሬ ላይ ነፃ ብንሆንም፣ ነፃ ልንወጣባቸው ከሚገቡ ብዙ ነገሮች ነፃ መውጣት አለብን፡፡ ከሁሉ በላይ የማንበብ አፒታይታችንን ከፍተን መጻሕፍትን የዕለት ከዕለት ኑሮአችን መሠረቶችና የሕይወታችን በር ከፋቾች አድርገን ማንበብ አለብን፡፡ አንባቢ ትውልዶች ከሆንን በጥናትና በምርምር ሥራዎች ላይ በመሳተፍ የአገራችንን መጠነ ሰፊ ችግሮች እንፈታለን፡፡ ያኔ አገራችን ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ማማ ተምሳሌት ሆና ስሟን እንደገና ታድሳለች፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles