Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ቻይና ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ አስተማሪ ስለሆነ የቻይና ነገር እንደ ሱስ ሆኖብኛል››...

‹‹ቻይና ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ አስተማሪ ስለሆነ የቻይና ነገር እንደ ሱስ ሆኖብኛል›› ወይዘሮ ሊና ጌታቸው

ቀን:

ወይዘሮ ሊና ጌታቸው ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ሲሆን፣ በ18 ዓመቷ አሜሪካ የሚገኘው ዬል ዩኒቨርሲቲ ገብታ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በፖለቲካል ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪዋን በፐብሊክ ኸልዝ ሠርታለች፡፡ ለዓመታት ቻይና ውስጥ የኖረች ሲሆን፣ በአፍሪካና በቻይና ግንኙነት ላይ ጥናቶች ትሠራለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥና ቻይናም በኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዙሪያ የመንግሥትና የግል ተቋሞችን አማክራለች፡፡ ቻይና፣ ቻንግሻ የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥም አስተምራለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ ‹‹ዳሉ ቻይናን በቀላሉ›› የሚል የቻይንኛ መማርያ መጽሐፍ አሳትማለች፡፡ በመጽሐፉና ሌሎችም ሥራዎቿ ዙሪያ ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡- መጽሐፉን ለመጻፍ ምን አነሳሳሽ? የመጽሐፉስ ይዘት እንዴት ይገለጻል?

ሊና፡- ብዙ ከቻይናውያን ጋር የመግባባት ችግር ያለባቸው ኢትዮጵያውያን ስላሉ ሁኔታውን ለመቀየር አስቤ ነው፡፡ መጽሐፉ ለአማርኛ ተናጋሪዎች መሠረታዊ የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በመጽሐፉ ለመማር የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ አያስፈልግም፡፡ እኔ ቻይንኛ ስማር ማስታወሻ የምይዘው በአማርኛ ነበር፡፡ እንዴት ለአማርኛ ተናጋሪ ቀላል እንደሆነ ያወኩት ያኔ ነው፡፡  ምክንያቱም በቻይንኛ ቋንቋ ያሉ ድምፆችን በአማርኛ ቃላት በቀላሉ መግለጽ ይቻላል፡፡ ቻይንኛን ከሌሎች ቋንቋዎች ከሚለዩት ባህሪያት መካከል ድምፀቱና ሆሄያቱ ይገኙበታል፡፡ መጽሐፉ ስለነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ካስተማረ በኋላ ወደ ንግግር ይገባል፡፡ ራስን ማስተዋወቅ፣ ሰላምታ መስጠትና ሌሎችንም ያካትታል፡፡ ከቻይና ስመለስ ብዙ ቻይናውያንና የቻይና ኩባንያዎች ኢትዮጵያ እንዳሉ አየሁ፡፡ ቋንቋውን የመማር ፍላጎቱ እንዳለ ሳይ ዌብ ሳይት ከፈትኩ፡፡ የድምፅ ቅጂ አዘጋጅቼ ቻይኒዝ ፎር ኢትዮጵያ በተባለው ዌብ ሳይት እንዲገኝ አደረኩ፡፡ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በዌብሳይቱ ተመዝግበው ስለ ቻይና ባህልና ሌሎችም መረጃዎች ያገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ቻይናውያን ስምንት ቁጥርን በጣም ይወዳሉ፡፡ አራት ቁጥርን ደግሞ ይጠላሉ፡፡ አራት የሚለው ቁጥር ስ ነው የሚባለው፡፡ ስ ደግሞ ሞት ማለት ነው፡፡ ይሄ ለኛ ጠቃሚ መረጃ ነው፡፡ አንድ ሆቴል ውስጥ ቻይናዊ አንግዳ ቢመጣ አራተኛ ፎቅ ላይ ቢሆን ደስ አይለውም፡፡ ቻይና ውስጥ ከሦስት ወደ አምስት የሚሄዱ ፎቆች አሉ፡፡ ስምንት ቁጥርን ከመውደዳቸው የተነሳ የቤጂንግ ኦሊምፒክ ሲጀምር በ2008 ስምንተኛ ወር ስምንተኛ ቀን ነበር፡፡ ስምንት ቁጥር ጥሩ ዕድል ያመጣል ብለው ያስባሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ ማስተማር የፈለግሽው በየትኛው ሙያ ያሉትን ሰዎች ነው?

ሊና፡- ጥናት ሳደርግ ሁሉም ሙያተኛ በመጠኑ ፍላጎቱ አለው፡፡ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ ሥራ ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ ብዙ የቻይና ኩባንያዎች ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎችን ይቀጥራሉ፡፡ ነጋዴውና የመንግሥት ሠራተኛውም ከቻይናውያን ጋር ለመግባባት ይፈልጋል፡፡ ይኼ መጽሐፍ የተጻፈው ለሁሉም ሙያ በደፈናው ቢሆንም፣ ወደፊት አንድ ሙያ ላይ አተኩሬ መጻፍ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያውያንና በቻይናውያን መካከል ያለውን መግባባት ለመጨመር ቻይናውያን አማርኛ የሚማሩበትን መጽሐፍ የማዘጋጀት ሐሳብ አለሽ?

ሊና፡- የኛ ቻይንኛ ማወቅ ቅርበት እንዲኖረን እንደሚያደርግ ሁሉ፣ የነሱ አማርኛ ማወቅ ሌላው የመግባባቢያ መንገድ ነው፡፡ በቅርቡ አማርኛ መማር የሚፈልጉ ቻይናውያን እንድጽፍ ጠይቀውኛል፡፡ በኢትዮጵያዊነቴ ኢትዮጵያውያንን ብጠቅም ደስ ስለሚለኝ ነው ለአማርኛ ቅድሚያ የሰጠሁት፡፡ ቻይናውያን በዓለም ላይ የሌሉበት ቦታ ስለሌለ ቋንቋቸውን በመቻል ቅርበት መፍጠር ይቻላል፡፡ ሌላው ነገር ቻይንኛን እንደ ኢትዮጵያዊ ስማር ስለማስታውስ በምን መንገድ ቢሰጥ እንደሚቀል አውቃለሁ፡፡ አማርኛን ማስተማሩ ትንሽ ቢከብድም እያሰብኩበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዌብሳይትሽ የቻይናን ባህል ለኢትዮጵያውያን በማስተዋወቅ ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?

ሊና፡- ዌብሳይቱን ዲዛይን ያደረግነው እኔና ባለቤቴ ነን፡፡ ዌብሳይቱ ላይ ለተመዘገቡ ሰዎች የቻይናን ባህል የሚያስረዳ አንድ ነገር በየሳምንቱ በመላክና በየቀኑ አንዳንድ ቃል ኢሜል በመላክ ያስተምራል፡፡ በቀላሉ ብዙ ነገር ለማወቅ የሚያስችል መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ ቻይናውያን ድግስ ሲደግሱ የሚቀመጡበት ሥርዓት አለ፡፡ ጋባዥ ሁልጊዜ ከበር ፊት ለፊት ተቀምጦ የሚወጣ የሚገባውን ያያል፡፡ የጋባዡ ረዳት ደግሞ ጀርባውን ለበሩ ሰጥቶ ይቀመጣል፡፡ በእኛ ባህል እንደዚህ ዓይነት ነገር የለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥቃቅን ነገሮችን ማወቅ አለመግባባቶችን ይቀንሳል፡፡ መጽሐፉን የገዙ ሰዎች መጽሐፉ ላይ የሚያገኙትን ኮድ ዌብሳይቱ ላይ አስገብተው ነፃ የድምፅ ማብራሪያ ያገኛሉ፡፡ ጥያቄ ሲኖራቸውም ማብራሪያ እሰጣለሁ፡፡ አስተያየት ተቀብሎ መጽሐፉን ለወደፊት ለማሻሻልም ይጠቅመኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጽሐፉ ቻይንኛ እየተማሩ ካሉ ሰዎች ያገኘሽው ምላሽ ምን ይመስላል?

ሊና፡- ብዙ  ሰው የእንግሊዝኛ እውቀት ባይኖረውም በአማርኛ ቻይንኛ መማር በመቻሉ ደስ ብሎታል፡፡ ምክንያቱም እኛ ሀገር ብዙ ነገሮችን ለመማር እንግሊዚኛ ማወቅ እንደ ቅድመ ሁኔታ ይቀመጣል፡፡ መጽሐፉ ላይ ቻይንኛን ከአማርኛ ጋር ለማመሳሰል እሞክራለሁ፡፡ አንዳንድ የቻይንኛ ካራክተሮችን ከአማርኛ ጋር በማመሳሰል ወይም በአገራችን በተለመዱ አገላለፆች ለማቅረብ ሞክሬአለሁ፡፡ መስፋፋት ያለባቸውን ምዕራፎች የነገሩኝና ገንቢ ትችት የሰጡኝም አሉ፡፡ ቻይናውያን በመጽሐፉ ላይ ያሳደሩት ፍላጎት ገርሞኛል፡፡ ለሠራተኞቻቸው እንዲሁም ለጓደኛም ስጦታ ሲሰጡ አይቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- መጽሐፉን ከመጻፍሽ በፊት በሠራሽው ጥናት በቻይናውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል የነበረው መግባባት ምን ያህል ከባድ ነበር?

ሊና፡- እንግዳ ተቀባይ ስለሆንን ብዙ አናስቸግርም፡፡ ያን ያህል አለመግባባት ኖሮ ችግር ተፈጥሯል ለማለት አይቻልም፡፡ መግባባት ቢኖር ነው ይሄ ሁሉ ነገር እየተሠራ ያለው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ በሰዎች መካከል ጥሩ መቀራረብ ይፈጥራል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ አንድን ሰው በሚያውቀው ቋንቋ ስታናግረው የሚያስታውስህ በአዕምሮው ነው፤ በአፍ መፍቻ ቋንቋው ስታናግረው ግን  በልቡ ከጥሩ ስሜት ጋር ያስተውልሃል ይላል፡፡ አንድ ሰው እንግሊዝኛ ተናግሮ ከፈረንጅ ጋር መግባባት ቢችልም ፈረንጁ አማርኛ ሲናገር ደስ ይለዋል፡፡ የኛን ቋንቋ አክብሮ ለማወቅ ያደረገው ጥረት ያስደስታል፡፡ ቻይናዎችም ቋንቋቸውን የሚያውቅ ሰው ይቀርባሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቻይንኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል አለ፡፡ ከተቋሙ ወይም ከተማሪዎች ጋር ያደረግሽው ግንኙት አለ?

ሊና፡- በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮንፊሽየስ ኢንስቲትዩት ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን አነጋግሬያለሁ፡፡ ቆንጆ ቻይንኛ ይናገራሉ፡፡ በዓመት የተወሰኑ ተማሪዎች በስኰላርሺፕ ቻይና እየሄዱ ይማራሉ፡፡ ማረጋገጥ ባልችልም ጥሩ ሥራ እያገኙ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ መጽሐፉ ግን በበለጠ ጊዜ ለሌለው ሰው የሚሆን ነው፡፡ በተቋሙ የራሱ መማሪያ ያለው ቢሆንም ተማሪዎች እንደ ተጨማሪ ግብዓት መውሰድ ከፈለጉ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍሪካና በቻይና ዙሪያ ስለምትሠሪያቸው ጥናቶች ብታብራሪልን?

ሊና፡- በቻይናና አፍሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጥናት ከፈለገ ኩባንያ ጋር መሥራት ብጀምርም ሥራውን ስለወደድኩት በየዓመቱ በግሌ ማጥናት ጀምሬያለሁ፡፡ ሜጋ ቲምስ ኢን ቻይና አፍሪካ ሪሌሽንስ የተባለ ኩባንያ ሲሆን፣ በዓመት ውስጥ የተካሄዱ ነገሮችን ይዳስሳል፡፡ እኔ የማሳትመው ጥናት ከ30 እስከ 40 ገጽ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ሁለት የጥናት ተቋሞች በዌብ ሳይታቸው አትመውልኛል፡፡ በቻይናና አፍሪካ መካከል የሚካሄደው ነገር በጣም ብዙ ነው፡፡ አንድ ዘርፍ ብቻ እንኳ ቢመረጥ በውስጡ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እኔ በደፈናው የሰውን ትኩረት የሚስቡና ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አተኩራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአፍሪካ ውስጥ በተለየ የምታተኩሪባው አገሮች አሉ? ጥናቱንስ የምትሠሪው በምን መንገድ ነው?

ሊና፡- አፍሪካን እንደ አኅጉር የሚያሳዩ ነገሮች ላይ አተኩራለሁ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ወይም እንደ ኢጋድ ያሉ ተቋማት የሚወስኗቸው ውሳኔዎችን ሊመረኰዝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኢቦላ በተከሰተበት ጊዜ፣ ቻይና ለኢቦላ ስላደረገችው አስተዋጽኦ ሲነሳ ጥናቱ በምዕራብ አፍሪካ አተኩሯል፡፡ የኢትዮጵያ ቀላል ባቡርም ትልቅ ጉዳይ ነበር፡፡ በእርግጥ አንድ ሀገር ቢመረጥ እንኳን ሁሉም ነገር ተጠንቶ ስለማያልቅ ሰው አንብቦ መሠረታዊ ነገር የሚይዝባቸው ጉዳዮችን ነው የምመርጠው፡፡ በፎረም ኦን ቻይና አፍሪካ ኮኦፕሬሽን (ፎካክ) በየሦስት ዓመቱ አንዴ ቻይና ሌላ ጊዜ በአፍሪካ አገሮች እየተካሄደ ስምምነቶች ይፈረማሉ፡፡ ከስብሰባው ብዙ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ በአሁን ወቅት የአፍሪካ ዝሆኖች ጥርስ ወደ ቻይና እየሄደ ስለሆነ የአፍሪካ ዝሆኖች እያለቁ ነው የሚል ጉዳይ አለ፡፡ በየጊዜው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማተኰር ይቻላል፡፡ አንዳንዴ በቀላሉ መረጃ የማይገኝባቸው ሚስጥራዊ ጉዳዮችም ይኖራሉ፡፡ ጥናቶችን የምሠራው በግሌ ነው፡፡ ከድርጅቶች እርዳታ ለመጠየቅ ያሰብኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ነገር ግን በድርጅቶች ሥር የሚሠሩ ሥራዎች በድርጅቱ ፍላጎት ተፅዕኖ ሥር ሊወድቁ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በነፃነት መሥራቱን እፈልገዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ቻይና ውስጥና በኢትዮጵያ የማማከር ሥራዎች ሠርተሻል፡፡ የትኩረት አቅጣጫሽ የትኞቹ የሙያ ዘርፎች ናቸው?

ሊና፡- አንድ ጊዜ በቻይናውያን ዘንድ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ በሚደረግ ጥረት ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ጋር ሠርቼ ነበር፡፡ ቻይናውያን ለመዝናናት ለምን ኢትዮጵያ መምጣት ይፈልጋሉ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እየሞከርን ነበር፡፡ ብዙ አገሮች የቻይናን ትኩረት ለመሳብ ይጥራሉ፡፡ ይሄን ጥረት ሳይ እኛም ትኩረታቸውን ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል ብዬ አሰብኩ፡፡ እነሱ ብዙ ገንዘብ አላቸው፡፡ ብዙ ፈላጊ ስላላቸው ምርጫቸውም ብዙ ነው፡፡ ይኼንን ሁሉ ፉክክር አልፎ የነሱን ቱሪስቶችና ኢንቨስትመንት ለማግኘት ዝግጁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በቱሪዝም ዘርፍ አገራቸው የሌሉ ነገሮችን ማስጎብብኘት ያስደስታቸዋል፡፡ ፍላጎታቸው ከምዕራባውያን የተለየ ነው፡፡ አብዛኞቹ ምዕራባውያን የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ስለሆኑ ቤተ ክርስቲያናትን ሲያዩ ደስ ይላቸዋል፡፡ ቻይናውያን ግን ወደ ደቡብ ሄደው የአርባ ምንጭን አዞ ሲያዩ አገራቸው የሌለ ነገር ስለሆነ ይደሰታሉ፡፡ ቻይናውያን የራሳቸውን ምግብ በየሄዱበት ቦታ መብላት ይፈልጋሉ፡፡ በጥቂት ዓመታት ብዙ የቻይና ሬስቶራንቶች የተከፈቱትም ለዚህ ነው፡፡ እንጀራና ወጥን አንዴ ይቀምሱታል እንጂ በቆይታቸው ሁላ አይበሉም፡፡ ቀዝቃዛ ነገር ስለማይወዱ ቀኑን ሙሉ ሻይ ሲጠጡ ነው የሚውሉት፡፡ በቻይና ሆቴልና ባቡር ውስጥም ሳይቀር በፔርሙስ ሙቅ ነገር ይኖራል፡፡ ስለዚህ አንድ የቱሪዝም ድርጅት ይህን ፍላጎታቸውን አሟልቶ አገልግሎት መስጠት አለበት፡፡ በኢንቨስትመንት በኩል ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዲያድርባቸው በመንግሥት የወጣ ፖሊሲ አለ፡፡ በተጨማሪም የሰው ኃይል ሀብት አለን፡፡ የነሱን ትኩረት ለማግኘት የሚደረጉ ነገሮች መኖር ቢኖርባቸውም የእኛን ማንነት የሚያሳጣ መሆን ግን የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝሙ ዘርፍ በማማከር ከነበረሽ ተሞክሮ ተነስተሽ፣ በዘርፉ ያለው እንቅስቃሴ ቱሪስቶችን ለማሰብ ጠንካራ ነው ብለሽ ታምኛለሽ?

ሊና፡- ራሴን እንደ ቱሪዝም ኤክስፐርት ላደርግ አልችልም፡፡ ከቻይናውያን ጋር በተያያዘ የተሻለ ግንዛቤ ይኖረኛል ብዩ ስመሳብ ነው እንጂ የተሻለ ምልከታ ያላቸው ባለሙያዎች አሉ፡፡ ባጠቃላይ ስናየው ግን ብዙ ስለቻይናውያን መማር ያሉብን ነገሮች አሉ፡፡ ሁሉንም የውጪ ሀገር ዜጋ አንድ ዓይነት አድርጎ የማየት ነገር አለ፡፡ በቱሪዝሙ ለቻይናውያን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጐብኚ የማይመቹ ነገሮች አሉ፡፡ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አለመሟላት አንዱ ነው፡፡ አሁን ግን ብዙዎች ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ ቻይናውያንን እየቀጠሩ ወይም አስተርጓሚ እያሠለጠኑ የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን አስጎብኚ ድርጅቶች እየበዙ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ወይም ወደተለያዩ አፍሪካ ሀገሮች ለመሄድ እንደ ትራንዚት ሲጠቀሙን እንዲጎበኙ የማነሳሳት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ብዙ ቻይናውያን ኬንያና ግብፅ ነው የሚሄዱት፡፡ ቻይናውያን ሐይኪንግ ይወዳሉ፡፡ የኛ ሀገር የተመቸ ስለሆነ የሃይኪንግ አማራጭ ብንሰጣቸው ጥሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቻይና ጋር የተያያዙ ነገሮች ላይ ማተኮር የጀመርሽው እንዴት ነው?

ሊና፡- ዬል ሳለሁ አተኩር የነበረው በፈረንሣይኛና ስፖኒሽ ቋንቋ ነበር፡፡ ለአፍሪካ የሚቀርበውም ፈረንሣይኛ ነው ብዬ አስብ ነበር፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬን ስሠራ አሜሪካ ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ነበር፡፡ እንኳን እኔ የአሜሪካ ዜግነት የሌለኝ ቀርቶ ዜጎችም ሥራ ያጡበት ነበር፡፡ የአሁን ባለቤቴ ያኔ በዛው ዩኒቨርስቲ ይማር ነበር፡፡ ከተመረቀ በኋላ ቻይና እንደሚሄድ ነገረኝ፡፡ ብዙ የሥራ አማራጮች ያሉበት ቆንጆ ሀገር መሆኑንም ነገረኝ፡፡ ከ1901 ጀምሮ የዬል ተማሪዎችን ቻይና እየላከ እንዲያስተምሩ የሚያደርገው ዬል ቻይና አሶስየሽን ያወጣውን ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ተወዳደርኩና ሳልፍ ወደ ቻይና ሄድኩ፡፡ ከዛ ቻይንኛን በጣም አስደሳች ነገር ሆኖ አገኘሁት፡፡ ቻይና ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ አስተማሪ ስለሆነ የቻይና ነገር እንደ ሱስ ሆኖብኛል፡፡ የሰዎቹ አቀባበልም በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ የቋንቋው አጸጻፍ ጥበብም በጣም አስገራሚ ነው፡፡ ለአንድ ዓመት ብዬ ሄጄ ብዙ ዓመት ቆየሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የማውቃቸው ሰዎች ከቻይና ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲኖራቸው ሲጠይቁኝ ወደ ማማከሩ ሥራ ገባሁ፡፡ ቤጂንግ እያለሁም ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዴት ቻይና ውስጥ እንደሚሠሩ አማክር ነበር፡፡ የምሠራበት ድርጅት ማይክሮሶፍት፣ ቶታል፣ አዲዳስና በሀገር ደረጃ ኒውዝላንድና ሌሎች አገሮችንም ያማክር ነበር፡፡ በማማከር ሥራ አንድ ድርጅት ምክሩን ምን ያህል እንደሚጠቀምበት ማወቅና መቆጣጠር ስለማይቻል አስቸጋሪ ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ በማማከር ለመሥራት ከባድ ነው፡፡ የወደፊት ሐሳቤ ትምህርት ላይ ማተኰር ነው፡፡ በተለይ ሕፃናትን ቋንቋ ማስተማር ስለሚቀል በዛ ዙሪያ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...