Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሃይማኖት ልዩነትና ፍቅር

የሃይማኖት ልዩነትና ፍቅር

ቀን:

ትዳር ከመሠረቱ 35 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ እማ ወራዋ የካቶሊክ አባወራው ደግሞ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ናቸው፡፡ የጥንዶቹ የሃይማኖት ልዩነት ግንኙነታቸው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ስለሌለ ትዳራቸው ከሞላ ጎደል ሰላማዊ የሚባል ነው፡፡ ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት ሚስትየው ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ የሚወልዷቸው ልጆች የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንዲሆኑ ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህም ባልና ሚስት የየራሳቸውን ሃይማኖት በነፃነት ለዓመታት አራምደዋል፡፡ በሰላማዊ ትዳራቸው ያፈሯቸው አምስት ልጆች ደግሞ ካቶሊኮች ናቸው፡፡

ተመሳሳይ በዓሎችን በብዛት መጋራታቸው ነገሮችን ቀለል አድርጐላቸዋል፡፡ ጥንዶቹ አንዳቸው በሌላቸው ሃይማኖት የማይገቡ፣ የየሃይማኖታቸውን ሕግጋት በመከተል ሕይወታቸውን የሚመሩና ትዳራቸውን ሲመሠርቱ የሃይማኖት ልዩነት የፍቅራቸው እንቅፋት እንደማይሆን መስማማታቸው ለሰላማቸው መሠረት እንደሆነ ይታያል፡፡

ሌሎቹ ጥንዶች ሙስሊምና ኦርቶዶክስ ናቸው፡፡ ከ30 ዓመታት በፊት የፍቅር ግንኙነት ሲጀምሩ ከቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ ትዳር ለመመሥረት ሲወስኑ ባለቤትየው ሃይማኖቷን ወደ ኦርቶዶክስ እንድትቀይር ይጠይቃትና ትቀበላለች፡፡ ቤተሰቦቿና ዘመድ አዝማድ በሁኔታው ደስተኛ ባይሆኑም ጥንዶቹን መለያየት ስላልተቻለ ትዳራቸውን ተቀብለው ለመኖር ተገደዱ፡፡ ጥንዶቹ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች የሚጠበቀውን ሁሉ እያደረጉ ለሦስት አሥርታት በትዳር ሲኖሩ ሦስት ልጆች አፍርተዋል፡፡

በቅርቡ ሚስት እህቶቿን ለመጠየቅ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ አመራች፡፡ ለጥቂት ወራት ብቻ የታቀደው የሳዑዲ ዓረቢያ ቆይታዋን ከአንድም ሁለቴ አራዘመች፡፡ በቆይታዋ ከእህቶቿ ጋር ታሳልፍ የነበረው ጊዜ ልጅ ሳለች የኖረችበት የእስልምና አስተምህሮት አስታዋሽ ነበር፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያስተዋለቻቸው እንቅስቃሴዎችም እንዲሁ፡፡ ከአንድ ዓመት ከግማሽ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ወደ ቀደመ ሃይማኖቷ ተመልሳ ጭምርም ነበር፡፡ ይኼኔ ከባለቤቷ ጋር ፈጸሞ መስማማት ተሳናቸው፡፡ አንዳቸው የሌላቸውን ሃይማኖት ለማስቀየር የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ሁለቱም ግን ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ በሁለቱም ወገን ያሉ ዘመድ አዝማዶች ትዳራቸውን ለመታደግ ያደረጉት ጥረትም ፍሬ አላፈራም፡፡ ትዳራቸው እንዳይሆን ሲሆን ለመፋታት ወሰኑ፡፡

የፍቅር ጓደኝነትም ይሁን ትዳር ሲመሠረት ከግምት ከሚገቡ ነገሮች ሃይማኖት አንዱ ነው፡፡ አንዳንዶች የፍቅር ግንኙነት ሲጀምሩ የሃይማኖት ልዩነት ባያሳስባቸውም፣ በተቃራኒው ከሚከተሉት ሃይማኖት ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት ውስጥ ለመቆየት የሚቸገሩ ብዙ ናቸው፡፡ የሃይማኖት ልዩነት በፍቅር ግንኙነት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ እንደሌለ በማመን አብረው የዘለቁ፣ በተቃራኒው የተለያዩ ጥንዶችም ገጥመውናል፡፡

በዓለም ላይ ከ4,200 በላይ ሃይማኖቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ የየሃይማኖቶቹ ተከታዮች በሌላ ሃይማኖት ውስጥ ካለ ሰው ጋር በፍቅር የሚወድቁበት አጋጣሚም አለ፡፡ በየሃይማኖቱ ያሉ ሕግጋትና እሴቶች መለያየት የሰዎችን ምልከታ የተለያየ ስለሚያደርጉት ግንኙነቶች ፈታኝ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ከእነሱ በተለየ ሃይማኖት ውስጥ ካለ ሰው ጋር በተለያየ እሴት መኖርን ባለመቀበል ግንኙነታቸውን የሚያቋርጡ ሰዎች እንደ ምክንያት የሚያቀርቡትም ይህንኑ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የሚወዱትን ሰው ወደ ሃይማኖታቸው ለማምጣት ሲሞክሩም ሊታዩ ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል በአኗኗር፣ በልጆች አስተዳደግና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁለቱንም አካላት የሚያስማማ ነጥብ ላይ ደርሰው በየሃይማኖታቸው የሚኖሩ ጥንዶች ይጠቀሳሉ፡፡ አንዳቸው ስለሌላቸው ሃይማኖት መሠረታዊ ሐሳቦችንና ሕግጋት በመረዳት ተግባብተው ይኖራሉ፡፡

ያፈቀሩትን ሰው ላለማጣት ሃይማኖት መቀየር ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ ሲራክ ሲሳይ (ስሙ ተቀይሯል) ወደ ባሃኢ እምነት ከመቀየሩ ከሦስት ዓመት በፊት አድቬንቲስት ነበር፡፡ በሥራ አጋጣሚ ከተዋወቃት ሴት ጋር ጓደኛሞች የሆኑት በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀራረቡ ሲሄዱ፣ በአመለካከቷና በሃይማኖቷ መሳብ ጀመረ፡፡ ሃይማኖቱን ለመቀየር የወሰነው ግን ጓደኝነታቸው ወደ ፍቅር ሲለወጥ መሆኑን ይናገራል፡፡

ሲራክ እንደሚለው፣ የሃይማኖት ልዩነት በፍቅር ግንኙነት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ በሃይማኖት ውስጥ ያሉ ሕግጋትን አክብረው ለሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ፈተናው ይከብዳል፡፡ የፍቅረኛውን ሃይማኖት አምኖበት ሃይማኖቱን እንደለወጠ ቢናገርም፣ ለእሷ ያለው ፍቅር አስተዋጽኦ እንዳለውም ይናገራል፡፡ ቤተሰቦቹ ውሳኔውን ለመቀበል በመቸገር ዓይንህን ለአፈር ብለውታል፡፡ ቤተሰቡን መልሶ መቀላቀል ከፈለገ ሃይማኖቱን መቀየር እንዳለበትም አሳውቀውታል፡፡ ስላልተቀበላቸው አሁን እጮኛው ከሆነች ፍቅረኛው ጋር አብረው እየኖሩ ነው፡፡

‹‹ቤተሰቦቼ ከጊዜ በኋላ ተረድተውኝ ይቅር እንደሚሉኝ እገምታለሁ፤ የምወዳትን ሴት በሃይማኖት ልዩነት ማጣት የማይታሰብ ነገር በመሆኑ ሃይማኖቴን በመለወጤ ግን አላዝንም፤›› ይላል፡፡ በሃይማኖት መለያየት ሳቢያ የሚመጡ ፈተናዎችን ቻል አድርገው በተለያየ ሃይማኖት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቢኖሩም፣ የእምነት ልዩነታቸው የፍቅራቸውን መጠን ይቀንሰዋል ብሎ ያስባል፡፡

ሰዓዳ ሐሰን (ስሟ ተቀይሯል) በሲራክ ሐሳብ አትስማማም፡፡ ሰዎች ይህን ምድር የፈጠረ ኃያል አምላክ እንዳለ እስካመኑ ድረስ በተለያየ መንገድ ማምለካቸው ለፍቅር ግንኙነት እንቅፋት አይሆንም ትላለች፡፡ እናቷ ኦርቶዶክስ አባቷ ሙስሊም ቢሆኑም በትዳር ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ ቤተሰባቸው የሁለቱንም እምነቶች በዓላት በድምቀት ያከብራል፡፡ ልጆቹ በሙሉ ሙስሊሞች ቢሆኑም፣ በእናታቸው ወገን ካሉ ኦርቶዶክስ ዘመዶቻቸው ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው፡፡ እሷ እንደምትለው፣ የሃይማኖት ልዩነትን በፍቅር ግንኙነት ወቅት ጥያቄ ውስጥ አታስገባም፡፡ ቤተሰቦቿም ተጽእኖ አያሳድሩባትም፡፡

‹‹በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያለና የሃይማኖቱን ሕግጋት የሚተገብር ሰው የእኔን እስካልተጋፋ ድረስ አብረን መኖር እንችላለን፤›› ትላለች፡፡ ጓደኛዋ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነው፡፡ በሃይማኖት ጉዳይ ሲያወሩ ሁለቱም በፈጣሪ በማመናቸው ይግባባሉ፡፡ በየሃይማኖቶቻቸው ባሉ አስተምሮቶች የሚኖሩ ሲሆን፣ ተጋብተው ልጆች ቢወልዱ፣ በአንዳቸው እምነት መንገድ ማሳደግ እንደሚችሉ ታምናለች፡፡

እንደ ሰዓዳ ቤተሰቦች፣ የልጆቻቸውን ምርጫ የሚቀበሉ ቢኖሩም፣ አንዳንዶች ደግሞ ልጆቻቸው የወላጆቻቸውን እምነት ይዘው እንዲዘልቁ ስለሚፈልጉ ከሌላ ሃይማኖት ተከታይ ጋር እንዲጎዳኙ አይፈልጉም፡፡

አንዲት ወጣት ቤተሰቦቿ ኦርቶዶክስ ቢሆኑም እሷ ከጊዜያት በኋላ ፕሮቴስታንት ሆናለች፡፡ ይህንንም ለቤተሰቦቿ ስታሳውቃቸው ከቤታቸው ያስወጧታል፡፡ ከዓመት በኋላ በሽምግልና ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ብትመለስም፣ ፕሮቴስታንት ሰው ልታገባ እንደሆነ ስታሳውቃቸው ዳግም ተጣሉ፡፡ ልጃቸውን ለጋብቻ የሚጠይቁ ሽማግሌዎች ወደ ቤታቸው እንዳይመጡ ከለከሉ፡፡ የሠርጉ ጉዳይ እንደማይመለከታቸውና በውጪ እንዲጠናቀቅም አሳሰቡ፡፡ ወጣቷ ቤተሰቦቿ ከእጮኛዋ የተላኩ ሽማግሌዎችን እንዲቀበሉ ሽማግሌ ለመላክ አስባለች፡፡

ኦርቶዶክስ ልጃቸው ሙስሊም ባል ልታገባ እንደሆነ ሲያውቁ ከፍተኛ ውጥንቅጥ ውስጥ የገቡት ቤተሰቦችም ይጠቀሳሉ፡፡ ከልጅቷ እናት በስተቀር መላው ቤተሰብ ሊቀበሏት አልፈቀዱም፡፡ ሠርጓ ላይ ካለመገኘት አንስቶ ልጆች ስትወልድ እስካለመጠየቅ ደርሰዋል፡፡ እናቲቱ ዘመድ አዝማድ ልጃቸው ላይ በመጨከኑ አዝነው ተጣልተዋል፡፡ ሠርጓ ላይ ካለመገኘታቸው በላይ እንዴት ልጄን መልስ አይጠሯትም በሚልም ተቀያይመዋል፡፡ በልጅቷ አማቾች በኩል ግን ቅሬታ አልነበረም፡፡ ኩለው ድረዋት ስትወልድም አርሰዋታል፡፡ ከወለደቻቸው ልጆች አንዷ በጠና ታማ በአገር ውስጥና በውጭ ሕክምና መከታተል ስትጀምር ግን ከራቁት ዘመዶቿ መካከል አንዳንዶቹ ቅያሜያቸውን ትተው ጠይቀዋታል፡፡  

በተለያየ ሃይማኖት ውስጥ ባሉ ሰዎች መካከል ስላለው የፍቅር ግንኙነት በርካታ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡ በዚህ መንገድ የሚኖሩ ጥንዶች ቁጥር ስለመበራከቱ ሁለት ንድፈ ሐሳቦች ይደመጣሉ፡፡ አንዱ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቻችሎ የመኖር ምልክት ተደርጎ መወሰዱ ነው፡፡ ሌሎች ተመራማሪዎች ሃይማኖትና ሃይማኖተኛነት እየላላ መምጣቱን ያሳያል ይላሉ፡፡ የሥነ ልቦናና የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች ለፍቺ እንደ ምክንያት ከሚያስቀምጧቸው አንዱ የሃይማኖት ልዩነት ነው፡፡ በሌላ በኩል በተለያየ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ ጥንዶች ስኬታማ የተባለ ሕይወት የሚመሩባቸውን መንገዶችም ያስቀምጣሉ፡፡

ከመንገዶቹ አንዱ የሁለቱም ጥንዶች ሃይማኖት ትክክለኛ መንገድ እንደሆነ መቀበልና እርስ በርስ አለመነቃቀፍ ነው፡፡ አንዳቸው ሌላውን ለመለወጥ አለመሞከርም ይመከራል፡፡ በእርግጥ በሃይማኖታዊ በዓላት፣ በአመጋገብ፣ በንግግርና በጥቃቅን ዕለታዊ እንቅስቃሴዎች ሳይቀር የሚለያዩ ሰዎች ኅብረት ለመፍጠር ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ ስለሕይወትና ስለሞት ያላቸው አመለካከት ልዩነት ሌላው ፈተና ነው፡፡ ብዙ ባለሙያዎች እነዚህና መሰል ፈተናዎች ሲገጥሙ ጥንዶች ያላቸው ፍቅር ምን ያህል በአብሮነት ያዛልቃቸዋል? የሚለው ጥያቄ እንደየጥንዶቹ ማንነት ይወሰናል የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡

በሃይማኖት ሕግጋት ረገድ በሌላ ሃይማኖት ውስጥ ካለ ሰው ጋር በፍቅር መጣመርን የሚከለክሉ ሃይማኖቶች ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሃይማኖቶች ለጋብቻ የማይፈቅዷቸው ሃይማኖቶች ያሉ ሲሆን፣ የፍቅር ጓደኛቸውን ከማግባታቸው በፊት ወደ አንድ እምነት ማምጣትን የሚያበረታቱም አሉ፡፡

መልካም ዮሐንስ በቤተሰቧ ከአያቶቿ ጀምሮ በሃይማኖት የተለያዩ ጥንዶች እንዳሉ ትናገራለች፡፡ በእናቷ በኩል ካሉ አክስቶቿ አንዷ ሙስሊም አግብታ ሃይማኖቷን ቀይራለች፡፡ የእሷ እናት ፕሮቴስታንት ሲሆኑ፣ አባቷ ኤቲስት (ሃይማኖት አልባ) ናቸው፡፡ ‹‹ዘመድ አዝማድ የሚገናኙባቸው መርሐ ግብሮች በመነቋቆር የተሞሉ ናቸው፡፡ አንዱ ሌላውን ቤተሰብ አበላሻችሁ እስከ ማለት ይደርሳሉ፤›› ትላለች፡፡

እንደ ለቅሶና ሠርግ ያሉ ክስተቶች ካልተፈጠሩ ቤተሰቦቿ የመገናኘት ፍላጐት የላቸውም፡፡ በሠርግ ላይ ደግሞ ሁሉም የየራሳቸውን ሃይማኖት መገለጫ ለማሳየት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ሃይማኖታዊ ዝማሬዎችና አጽዋማትን በመጠቀም ልዩነታቸውን ለማሳየት ይጣጣራሉ፡፡ ልጆቻቸው መካከል ያለው ግንኙነት ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ሳያሳውቁ ይገናኛሉ፡፡

እሷ እንደምትለው፣ ልጆቹ እንደ ዝምድናቸው እርስ በርስ ቢገናኙም፣ ሁሉም በየሃይማኖታቸው ካለ ሰው ጋር ነው ግንኙነት የሚመሠርቱት፡፡ እሷ ፕሮቴስታንት ስትሆን ትዳር የመሠረተችው ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ጋር ነው፡፡ ‹‹የሁለታችንም ሃይማኖት መነሻው ምን እንደሆነ እናውቃለን፤ ልዩነቶቻችንን አቻችለን እየኖርን ነው፤›› ትላለች፡፡

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...