Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመሬቱ ቁማር

የመሬቱ ቁማር

ቀን:

አፍራሽ ግብረ ኃይል የቤቱን ቆርቆሮ በመነቃቀል ላይ ነው፡፡ ጣሪያው ሙሉ ለሙሉ ተነቅሎ አልቋል፡፡ ነገር ግን አሁንም የቀረ ነገር በመኖሩ የአፍራሽ ግብረ ኃይሉ አባላት በዚህ በዚያ እያሉ ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ የግድግዳ ቆርቆዎችም ከሞላ ጐደል በመነቀላቸው ቤቱ ውስጥ ያሉት ዕቃዎች ይታያሉ፡፡ የእንጀራ መሶብ፣ ሶፋ ሌላም ሌላም ዕቃዎች ይታያሉ፡፡ ተነቅሎ ምልክቱ ብቻ ከቀረው በር በላይ ቡኒ ቀለም የተቀባውና ያልተነቀለው ቆርቆሮ ላይ ‹‹ዕድገት በኅብረት›› በሚል በቢጫ የተጻፈ ጽሑፍ ይታያል፡፡

ረቡዕ ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ አሥር ሰዓት ገደማ፣ ከጥቂት ቀናት በፊት መንግሥት ሕገወጥ ያላቸውን ቤቶች ማፍረስ በጀመረበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተለምዶ ወረገኑ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ በወቅቱ ቦታው ላይ እየሆነ የነበረው ነገር ቆርቆሮው ላይ ከሠፈረው ጽሑፍ ሐሳብ ጋር ፈጽሞ አብሮ የሚሔድ አይመስልም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሕገወጥነት፣ የንብረት ውድመት፣ ያንዱ ጥፋት፣ የሌላው ሥራና እንጀራ በሚሆንበት ሁኔታ ውስጥ በኅብረት ማደግ የሚቻል አይሆንምና፡፡

በመፍረስ ላይ ያለው ቤት ባለቤት ልጅ ያዘለች እናት ምንአልባትም ለሠፈሩና ለቤቷ እንግዳ የሆኑ ሰዎች ወዲያ ወዲህ ሲሉ በገዛ ቤቷ እንግዳ የሆነች ያህል መሀል ላይ ቆማ ግራ በመጋባት ቤቷ ውስጥ ሽርጉድ የሚሉትን ሰዎች እንቅስቅሴ ተመለከታለች፡፡ ደጃፍ ላይ የነበሩ ሰዎች ስሜትና እንቅስቃሴም ሁለት ዓይነት ነበር፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ፍጥነት በተሞላበት ሁኔታ ኃይላቸውን ሳይቆጥቡ ቆርቆሮ በመነቃቀልና በማሠር ሥራ ተጠምደዋል፡፡ ተመሳሳይ የአካል ብቃት ያላቸው ወጣትና ጐልማሳ ወጣቶች ደግሞ በተቀዛቀዘ ስሜት ባሉበት ሆነው ነገሩን ይከታተላሉ፡፡ እጃቸውን ፊታቸው ላይ በማድረግ በዝምታ የተዋጡ ወጣትና ጐልማሳ ወንዶችም ጥቂት አልነበሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አንዱን ቤት አልፈው አንዱ ጋር ሲደርሱ የሚታየውና የሚሰማው ነገር እንዲሁ ሊያልፉት የሚቻል አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ ለቅሶ ላይ እንደሚታየው አካባቢው ላይ ወገባቸውን ያሠሩ፣ በእንባ ዓይናቸው የቀላና የደፈረሰ፣ እየተንሰቀሰቁ የሚያለቅሱ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ሴቶች ቤታቸው የፈረሠባቸው ብቻ ሳይሆኑ የእነሱ ሕጋዊ ነው ተብሎ ከመፍረስ ቢድንም ቤታቸው ከፈረሰባቸው ጐረቤቶቻቸው ጋር መለያየት ያስጨነቃቸውም ናቸው፡፡

ያነጋገርናቸው አንድ እናት፣ በአንድ ወቅት ታምመው ሆስፒታል ሃያ ቀናት በተኙበት ወቅት ማንም እንዳልነበራቸውና ያስታመሟቸው ጐረቤቶቻቸው እንደነበሩ፤ አሁን የጐረቤቶቻቸው ቤት በመፍረሱ መለያየታቸው በጣም እንዳሳዘናቸው ገልጸውልናል፡፡

የቤታቸው ጣሪያና የአጥር ቆርቆሮ ከመነቀሉ ውጭ የቤታቸው ዕቃ ሁሉም ባለበት እንዳለ፤ የተወሰኑት ሶፋ ላይ፣ ሌሎች ወንበር ላይ እንዲሁም ደጃፍ ላይ በዝምታ የተቀመጡ የቤተሰብ አባላትንም ተመልክተናል፡፡ ብዙዎቹ የት እወድቃለሁ? ምን ቀረኝ? የሚል ጥያቄ ያስጨነቃቸው ይመስላሉ፡፡ በረዥም ጊዜ የገነቡትና ተደጋግፎ ለመኖር ያስቻላቸው ማኅበራዊ ትስስር መቆረጥም ያሳዘናቸው አሉ፡፡ በአጠቃላይ ቦታው ላይ የሚታየው ነገር ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሱ ግድ የሚል ነው፡፡

ሕገወጥ ቤቶች እንዲህ ሰፊ ቦታ ከመሸፈናቸው ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ ለግንባታም የአገር ሀብት የሆነ ወጪ ከመባከኑ በፊት ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ አይቻልም ነበር ወይ? የሚለው ቀዳሚ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ቤታቸው ሕጋዊ ሆኖ ሳለ ሕገወጥ ተብሎ እንደፈረሰባቸው፣ በተመሳሳይ ጊዜ የተያዙ ቦታዎች ሆነው ሳለ አንዱ ፈርሶ ሌላው የሚቀርበትና ሌሎችንም ቅሬታዎች የሚያሰሙ ተነሽዎችም አሉ፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት መንግሥት እዚህ ቦታ ላይ ሕገወጥ ቤቶችን ማፍረስ ሲጀምር በኗሪውና በደንብ ማስከበር ኃይሎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በግጭቱ የሰዎች ሕይወትም አልፏል ሲባል ነበር፡፡ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ግን ምንም እንኳ ግጭቱ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም የሞተ ሰው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በልማት የሚነሱ ቦታዎችንም የማፍረስ እንቅስቃሴ ሲጀመር በኗሪዎች በኩል ተቃውሞ ይነሳል፡፡ ለዚህ እንደ አሜሪካ ግቢ ያሉ ሌሎች ሠፈሮችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የወረገኑ ግጭትና ከላይ የተጠቀሰው አካባቢ እውነታ፣ መንግሥት ሰዎችን ባንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ከመኖሪያቸው የሚያስነሳው እንዴት ነው? ሒደቱስ ምን ይመስላል? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ አካባቢዎቹ ከመነሳታቸው በፊት መከናወን ያለባቸው ዝግጅቶችስ ምንድን ናቸው?     

በተለይም የጨረቃ ቤቶችን በሚመለከት ሰዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በያዙት ቦታ ላይ እንዴት ገንዘባቸውን አፍስሰው ግንባታ ሊያካሂዱና ለዓመታት ተረጋግተው ሊኖሩ ይችላሉ? የሚለውም ጥያቄ መሠረታዊ ነው፡፡ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በወረገኑ የኖረው የ37 ዓመቱ ጐልማሳ ‹‹ሕገወጥ መሆኑን እናውቃለን አንድ ቀን የእኛ ይሆናል፣ ከኪራይ ቤትም የራስ ይሻላል በማለት ነው›› ይላል፡፡ ይህ የእሱ ብቻ ሳይሆን ከሞላ ጐደል አካባቢው ላይ የጨረቃ ቤት ሠርተው የሠፈሩ ሰዎች ሁሉ እሳቤ ነው፡፡ እንዲህ ያሰቡት ደግሞ አንድም መሬቱ የሸጡላቸው ገበሬዎች ሕጋዊ ይዞታ ስለነበር እንዲሁም በአንድ ወቅት ቀደም ብለው የተያዙ የጨረቃ ቤቶች ሕጋዊ መሆን የቻሉበት አጋጣሚም በመኖሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ሁለገብ የግንባታ ሠራተኛ የሆነው ጐልማሳው የሁለት ሕፃናት አባት ነው፡፡ ትልቋ ልጁ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ትንሿ ደግሞ መዋዕለ ሕፃናት ነች፡፡ ስምንት ሺሕ ብር መሬቱን ከገበሬ ላይ በመግዛት ሠርተው የገቡት 2002 ዓ.ም. ላይ እንደሆነ ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ የሠራው ትንሽ ቤት እሱ እንደሚለው ‹‹የአየር ካርታ›› ስላለው ያልፈረሰ ሲሆን፣ አስፋፍቶ የሠራውና ዋና መኖሪያ ቤቱ የነበረው ቤት ግን ፈርሷል፡፡ ብዙዎች መጀመሪያ የሠሩት ቤት ተርፎ ከጊዜ በኋላ አስፋፍተው በተሻለ ሁኔታ የሠሯቸው ቤቶች መፍረሳቸውን ይገልጻሉ፡፡

እሱ እንደገለጸልን ውኃም የኤሌክትሪክ ኃይልም አልገባላቸውም ነበር፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማስገባት ተደራጅተው ያደረጉት ዕርምጃም ቤቶቹ ሕጋዊ አይደሉም በሚል እንዲያቋርጥ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ከሆኑና የኤሌክትሪክ ኃይል ካላቸው ቤቶች ላይ ጠልፈው መብራት ይጠቀሙ፤ በቅርቡም የቦኖ ውኃ ገብቶላቸው ነበር፡፡

ሌላዋ ያነጋገርናት የሦስት ልጆች እናት ወረገኑ ላይ መኖር የጀመረችው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ ቦታውን ከገበሬ ላይ የገዛችው 2002 ዓ.ም. ላይ ሲሆን፣ ቤት የሠራችበት ደግሞ በቀጣዩ ዓመት ነበር፡፡ መብራትና ውኃ ባለመኖሩ፣ መንገዱም አስቸጋሪ ስለነበር ትኖር የነበረው ገርጂ አካባቢ ተከራይታ ነበር፡፡ ወረገኑ ላይ በቀለሰቻት ቤት ውስጥ ደግሞ ዘመዷ ይኖርበት ነበር፡፡

‹‹አራት ሺሕ ብር ግቢ ተከራይቼ ከዚያው ላይ አከራይቼ የባልትና ውጤቶችን እያዘጋጀሁ፣ ዳቦ እንደመጋገር ያሉ ሥራዎችንም እየሠራሁ ነበር ቤተሰብ የማስተዳድረው›› የምትለው እናት በመጨረሻ በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺሕ ብር በላይ ሲጨመርባት ስላልቻለች ወረገኑ ካለው ቤቷ መግባቷን ትናገራለች፡፡

በወቅቱ 250 ካሬ ቦታ በሀምሳ ሺሕ ብር ነበር የገዛችው፡፡ ‹‹2005 ዓ.ም. ላይ ይመስለኛል ፈርሶብን ነበር፤›› ትላለች፡፡ ከኑሮ ሁኔታ አስገዳጅነት የተነሳ እንጂ ተግባሩ ሕገወጥ መሆኑን እንደምታውቅ ‹‹ላለፉት ሁለት ሦስት ዓመት ምንም ስላላሉን ኮንዶሚኒየም ልንመዘገብ ስንልም አይሆንም ስላሉን ሕጋዊ ይሆናል ብለን ነበር›› በማለት ትናገራለች፡፡

ወረገኑ ላይ ብቻም ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች ምንም እንኳ የጨረቃ ቤቶች በተደጋጋሚ በደንብ ማስከበር ቢፈርሱም ኗሪዎቹ ደግመው ሠርተው ከመቀመጥ ወደኋላ አይሉም፡፡ ይህ መሔጃ ከማጣት ወይም አንድ ወቅት ላይ ይዞታችን ሕጋዊ ይሆናል ከሚል ጠንካራ እምነት የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕገወጥ ቤቶችን ከፈረሱ በኋላ ተከታዩን ዕርምጃ ወይም አስፈላጊውን ክትትል ከማድረግ ይልቅ ለድጋሚ ግንባታ ጊዜ ሰጥቶ ለድጋሚ ፈረሳ መመለስ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ላይም ጥያቄ ያስነሳል፡፡  

ብዙዎቹ ቦታው ላይ የሠፈሩ ሰዎች የሠፋሪው መጨመርን፣ ዋጋ የሚያወጡ ግንባታዎች እየተካሔዱ ዓመታት መቆጠራቸውን በሒደት ቦታው ሕጋዊ እንዲሆን ግድ የሚል ምክንያት አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ይመለከተዋል ባሉት አካል ተደራጅተው መንገድ ማውጣትና ገረጋንቲ እንዲለብስ ማድረጋቸው፣ ‹‹በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የያዛችሁት ቦታ›› አለ በሚል ኮንዶሚኒየም ቤት ምዝገባ ላይ እንዳይሳተፉ መደረግን የመሳሰሉ ነገሮችን የቤታቸው በሒደት ሕጋዊ የመሆን ምልክት አድርገው ያዩም አጋጥመውናል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚያዝያ 1988 እስከ ግንቦት 1997 ዓ.ም. የተገነቡ ሕገወጥ ቤቶችን ሕጋዊ የሚያደርግ መመርያ ከጥቂት ዓመታት በፊት አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህም ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር የሚጣጣሙ ግንባታዎች ሕጋዊ እንዲሆኑ ባልተጣጣሙት ደግሞ ተለዋጭ ቦታ ይሰጥ የሚል አካሔድ ነበር የተቀመጠው፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ቤቶችን ሕጋዊ ከማድረግ ዕርምጃ ጀርባ የነበረው ነገር መንግሥት ለመኖሪያ ቤት ግንባታ መሬት በተደራጀ መልኩ የሚያቀርብበት አሠራር ስላልነበር፣ ሰዎች በራሳቸው ዕርምጃም ቢሆን የቤት ባለቤት ለመሆን ያደረጉትን ጥረት ከንቱ ላለማድረግ ሲባል ነበር፡፡ በዚህም 45 ሺሕ ያህል አባወራዎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የመኖሪያ ቤት ልማት ፕሮጀክቶችን ስለጀመረ በራስ ዕርምጃ መሬት መያዝና የቤት ባለቤት ለመሆን መሞከርን መንግሥት ከልክሏል፡፡ ቢሆንም ግን እንደ ወረገኑ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ቀርሳ ቶምካ ባሉ አካባቢዎች አስተዳደሩ ሕገወጥ ወረራ የሚላቸው የጨረቃ ቤቶች በሰፊው ተገንብተዋል፡፡

በሕገወጥ መንገድ ቦታ ይዘው ይዞታችን ሕጋዊ ይሆናል የሚል እምነት እንዳያሳድሩ፣ የዜጐችና የአገር ሀብት፣ ጊዜና ጉልበት በማፍረስ እንዳይባክን ማድረግ አልያም ኪሳራውን መቀነስ የሚቻልበት መንገድ አልነበረም ወይ የሚለው ከጨረቃ ቤቶች ግንባታ ፈረሳም ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

በሌላ በኩል ለመልሶ ማልማት መንደሮችን ከማንሳት ጋርም የተለያዩ ችግሮች ይነሳሉ፡፡ በልማት ተነሽ የቀበሌ ቤት ኗሪዎችን መሠረተ ልማት ያልተሟላላቸው፣ ሥራቸው ያልተጠናቀቀ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እንዲገቡ ይደረግ እንደነበር ሪፖርተር ቀደም ባሉ ዘገባዎቹ አመልክቶ ነበር፡፡ የካሳ ጥያቄም ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡

ከካዛንቺስ ቁጥር ሁለት ተነሽዎች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ የአካባቢውን ለልማት መነሳትን በሚመለከት መንግሥት በተደጋጋሚ ኗሪዎችን እንዳነጋገረ ያስታውሳሉ፡፡ የእሳቸው መኖሪያ ቤት የግል ስለነበር ካሳ ከተቀበሉ አንድ ዓመት ሆኗል፡፡ ነገር ግን መንደሩ ፈርሶ ኗሪዎች ከለቀቁ ወራት ቢቆጠሩም እሳቸውና በጣት የሚቆጠሩ ሌሎች ቤታቸው ሳይፈርስ የታጠረ ፍርስራሽ መንደር ውስጥ እየኖሩ ነው፡፡ የታጠሩ ፍርስራሽ መንደሮች የቆሻሻ መድፊያ፣ የወንጀለኞች መደበቂያ እየሆኑ እንዳለ እየተሰማና እየታየ ባለበት ሁኔታ በዚህ ፍርስራሽ መንደር ውስጥ መኖራቸው ለጤናቸውም ለደኅንነታቸውም ሥጋት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡

ካሳ ከተከፈላቸው ዓመት ካለፈ እስካሁን ለምን ቦታውን እንዳለቀቁ የጠየቅናቸው ወይዘሮ መልሳቸው ‹‹ዕጣ አውጥተን የካ አያት ከሚባል ቦታ ምትክ ቦታ ቢደርሰንም እስካሁን ቦታውን መረከብ አልቻልንም፡፡ በአካል ሔደን ቦታውን አይተን እየተለካ ሊሰጠን ሥራ ከተጀመረ በኋላ አንድ ጊዜ የኮድ ስህተት አለ፣ ቦታውን ለሊዝ እንፈልገዋለን በሚል ሥራው ተቋረጠ፤›› የሚል ነበር፡፡

እሳቸው እንደሚሉት የሚሰጣቸው ቦታ የካ አያት ነው ተብለው ላለፉት ወራት የቀድሞው፣ ያሁኑ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ ትተው እየተመላለሱ ነው፡፡ ጉዳዩን ለማስፈፀም ቢያንስ በሳምንት ሦስት ቀን የጠቀሷቸውን ቢሮዎች ደጃፍ ይረግጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ ኑሯቸው ላይ ጫና እንደሚያሳድር ጥያቄ የለውም፡፡

ረዥም ዓመት ከኖሩበት፣ ሱቆችን በማከራየት ጥሩ ገቢ ያገኙ ከነበረበት ቦታ መነሳታቸው የሚያሳድረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ላይ እንደዚህ ያለ ውጣ ውረድና ችግር መጋፈጥ ከባድ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ‹‹የውይይቱ ጥቅም ከምን ላይ ነው›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

የተለያዩ አካባቢዎች በልማት ሲነሱ ተራ በተራ ኗሪዎችን የማሳመን ሥራ እየተሠራ፣ የኗሪው የገቢ አቅምም ከግምት እየገባ እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የመልሶ ማልማትና የጥናትና ትግበራ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ብርሃኑ ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡ ለኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ፣ ለአረንጓዴ ቦታዎች፣ ለወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠሪያ፣ ለጤና ተቋማት ግንባታ፣ ለኤምባሲዎች፣ አህጉራዊ ድርጅቶች ግንባታና ለሌሎችም ዓላማዎች እንደሚውል የተገለጸው የ360 ሔክታር መሬት መልሶ ማልማትም በጠቀሱት መንገድ የሚከናወን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ኅብረተሰቡ ምንም ወደኋላ ሳይል መልሶ ማልማቱን ስለሚደግፍ ከኗሪዎች በኩል ምንም ዓይነት ያጋጠመ ችግር የለም፡፡ ስለዚህም ከኗሪዎች ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶና ኮሚቴ ተቋቁሞ በየካ፣ ቂርቆስ፣ አቧሬ፣ ካዛንቺስ፣ ልደታ፣ ጐላ፣ ጌጃና አሜሪካን ግቢ አካባቢዎች ላይ ምትክ ቦታ የማስመረጥ ሥራ ተጀምሯል፡፡

ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታው እንዳሉት ደግሞ ከልማት ተነሽዎች ጋር በተያያዘ ችግሮች ነበሩ፡፡ አሁን ግን የቀበሌ ቤት ይኖሩ ለነበሩ ከመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ተከራይተው የሚኖሩም ሌላ የቀበሌ ቤት ወይም ኮንዶሚኒየም እንዳማራጭ ይቀርብላቸዋል፡፡ የግል ቤት ያላቸው ተነሽዎችም ምትክ ቦታ፣ ካሳና የአንድ ዓመት ኪራይ ዋጋ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ አዲስ አካሄድ ነገሮችን የተሻለ እንደሚያደርግም ያምናሉ፡፡

ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣ ሐሙስ ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በተለምዶ ወረገኑ እየተባለ የሚጠራው ቦታ ላይ ሕገወጥ የመሬት ወረራ እስኪስፋፋ ለምን ዝም ተባለ የሚል ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡፡ ከንቲባው እንዳሉት በዚህ መጠን ሕገወጥ ግንባታ ሲካሄድ የወረዳው አስተዳደር ምን እየሠራ እንደነበር የሚታይ ጉዳይ እንደሆነ፤ ምንም ይሁን ግን አስተዳደሩ በሕገወጥ መሬት ወረራ ጉዳይ እንደማይደራደርና ማንኛውንም ዕርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት አስናቀ፣ በንፅፅር ቂርቆስ ክፍለ ከተማን ያክላል የሚሉት ወረዳ 12 በጣም ሰፊ በመሆኑ ቦታውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የደንብ ማስከበርም በአስፈላጊ መሣሪያዎች የተደራጀ አለመሆን፣ ቦታው ላይ ግንባታ የሚካሔደው እንደ ቅዳሜና እሑድ፣ ምሽት፣ የበዓል ዕለትና የምርጫ ሰሞን ባሉ አጋጣሚዎች መሆን እንደ ችግር ያነሷቸው ሌሎች ነገሮች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳዳር እንደገለጸው ቦታው ላይ ከሠፈሩ ሰዎች የአዲስ አበባ ኗሪ ስለመሆናቸው የሚገልጽ መታወቂያ ያላቸው ጥቂቶች ናቸው፡፡ ነጋዴዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሹማምንትም በመሬት ወረራው ተሳታፊ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በካሬ ሜትር 400 እና 500 ብር ከፍለው እስከ 300 ካሬ የገዙ በመሆናቸው የገንዘብ ችግር ያለባቸው ሳይሆኑ መሬት የመውረርና በዚህ የማትረፍ ፍላጐት ያላቸው ናቸው፡፡

የአስተዳደሩ የመሬት ልማትና ማኔጅንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይለ እነዚህ በከፍተኛ ሁኔታ የመሬት ወረራ የተካሔደባቸው ቦታዎች (ወረገኑና ቀርሳ ቶምካ) በቀዳሚነት ለልማት ስለተፈለጉ ቅድሚያ ቢሰጣቸውም በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ሕገወጥ ይዞታዎችን የማፈራረሱ ዕርምጃ በስፋት እንደሚቀጥል አስረግጠዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ይህንኑ የአስተዳደሩን ዕርምጃ መደገፍ አለበት ብለዋል፡፡

ወረገኑ እና ቀርሳ ቶምካ ደንብ የማስከበር ሒደቱ ፈተና ገጥሞት እንደነበር ሲገልጹ፣ ‹‹ሕገወጥ ኢኮኖሚ ያፈረጠመው ጡንቻ ለሕግ ማስከበሩ ፈተና ሆኖ ነበር›› ያሉት ከንቲባ ድሪባም የመሬት ወረራን በሚመለከት ምንም ዓይነት ድርድር ስለማይኖር ደንብ ማስከበሩ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ እንደሚቀጥል አስረግጠዋል፡፡          

ውድነህ ዘነበ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በምሕረት አስቻለው እና በጥበበሥላሴ ሥጋቡ

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...