Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በንግድ ምክር ቤቶች የሥልጣን ቅብብሎሽ መለመድ አለበት››

አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

የአገሪቱን የንግድ ኅብረተሰብ የሚወክለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንቅስቃሴ ደካማ ነው የሚለው አስተያየት በተደጋጋሚ የሚነገር ነው፡፡ ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱም ሆነ በየደረጃው ያሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች እያበረከቱ ያለው አስተዋጽኦ ከሚጠበቅባቸው አንፃር ብዙ የሚቀራቸው ስለመሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ሊሠሩ በሚገባቸው ደረጃ ላለመሥራታቸው ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ በተለይ ወደ አመራር ለመምጣት የሚደረጉ ፍትጊያዎች ለንግድ ምክር ቤቶች ድክመት አንድ መገለጫ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ጠንካራ አመራሮች የሌላቸው መሆንም እንደ ችግር ይጠቀሳል፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅም ለችግሩ ሌላው ምክንያት ነው ይባላል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ንግድ ምክር ቤቶች ጠንካራ አመራር እንዳይኖራቸው ጋሬጣ ሆኗል ተብሎ በብዙዎች የሚተችበት ዋናው ጉዳይ አመራር ለመምረጥ የሚደረግ የቡድን ሥራ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አዳዲስ አመራሮች የማይታዩባቸው ተቋማት እየሆኑ የሚለው አስተያየት በግልጽ እየተነገረ ነው፡፡ ወደ አመራር ለመምጣት አባል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች የአባላቶቻቸውን ቁጥር በማሳደግ በድምፅ ብልጫ ተመራጭ ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት፣ የንግድ ምክር ቤቶችን ምርጫ ሁሌም አጨቃጫቂ ሲያደርገው እንደነበርም ይታወቃል፡፡ አሁንም ይህ ችግር ያልተቀረፈና ከወራት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ ላይ ይንፀባረቃል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ ያለው የአደረጃጀት ክፍተት በንግድ ምክር ቤቶች ምርጫ ላይ ተፅዕኖ አለው ስለመባሉ፣ በአጠቃላይ በምርጫና በንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀት ዙሪያ ዳዊት ታዬ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድ ምክር ቤታችሁ ምርጫ ወቅት የሚነሱ ፍትጊያዎች ብዙ ጊዜ ይስተዋላሉ፡፡ ለመመረጥ የሚደረጉ የቡድን ሥራዎች ስለመኖራቸው ይነገራል፡፡ እንዲህ ያለውን ክሰተት ለመቅረፍ ምን አስባችኋል? ንግድ ምክር ቤቶችስ ምን ማድረግ አለባቸው?

አቶ ሰለሞን፡- ይህንን ለማድረግ በተቋሙ የሚሳተፉ አካላት ሁሉ ተቋሙ ሕይወት ያለው እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡ ዝም ብሎ በቲፎዞ የመሰባሰብ ነገር ሳይሆን በተግባር ለንግድ ምክር ቤቱ መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ጊዜው የሙግት አይደለም፡፡ የግል ዘርፉ ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ማለት አለበት፡፡ ለምሳሌ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እልፍ ማለት ካለበት የሚደመጥና ጠንካራ አመራር ሊሰጡ የሚችሉ አመራሮች ሊመረጡ ይገባል፡፡ የሚመረጡት ተመራጮች የሚናገሩት በሌላ አካል የሚደመጥ መሆን አለበት፡፡ እነሱም ሌላውን ማዳመጥ የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ይህንን በራስ መተማመን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጁ መሠረታዊ የሆነ ችግር አለበት፡፡ ሌሎች ክፍተቶችም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ አለበት የሚባለው መሠረታዊ ችግር ምንድነው?

አቶ ሰለሞን፡- መሠረታዊ የሚባለው አንዱ ችግር በጣም ብዙ ቦታ ላይ ዝብርቅርቅ ያለ አደረጃጀት እንዲኖር ማድረጉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ መዘበራረቁ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ሰለሞን፡- ለምሳሌ በጣም ብዙ ዘርፎች አሉ፡፡ እነዚህ ዘርፎች በወረዳ፣ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ መደራጀት ያለባቸው ተብለው የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ በወረዳ ብቻ መደራጀት ያለበት ዘርፍ አለ፡፡ በክልል ብቻ መደራጀት ያለበት አለ፡፡ አሁን ደግሞ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሌላ የዘርፍ አደረጃጀት ደንብ አውጥቷል፡፡ ወደ 52 የሚሆኑ ዘርፎች በቀጥታ ወደ ዘርፍ ማኅበር ነው የሚሄዱት የሚል አዲስ ደንብ አውጥቷል፡፡ እንዲህ ባለው አደረጃጀት ብዙ ክፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡ በማደግ ላይ ባለ ኢኮኖሚ ውስጥ ሚናውን የሚጫወት የግል ዘርፍ ታሳቢ ተደርጐ መሠራት አለበት፡፡ በአንድ ጥላ ሥር እንዲሰባሰቡ የሚደረጉት ዘርፎች ያሉባቸው ችግሮች የተለያዩ ከመሆናቸው አንፃር ችግራቸውን ለመፍታት አያስችልም፡፡ ከዚህ አንፃር የሁሉም ዘርፍ ችግር የተለያየ ነው፡፡ የአንዳንዱ ችግር የግብር ጉዳይ ነው፡፡ የአንዳንዱ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ችግር ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የጥሬ ዕቃ እጥረት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የገበያ ችግር አለብኝ የሚል ነው፡፡

እነዚህን አንድ ላይ አድርገህ ወደ አንድ መፍትሔ የሚያመጣ ዕርምጃ ለመውሰድ በአዋጁ የተቀመጠው አደረጃጀት አይችልም፡፡ በአዋጁ የተቀመጠው የአደረጃጀት ችግር አንዳንድ ጊዜ ውክልና የሌላቸው ንግድ ምክር ቤቶች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 18 የንግድና የዘርፍ ማኅበራት አባላት አሉት ይባላል፡፡ የሚመረጠው ግን 11 ነው፡፡ ከአንዳንዱ ክልል ሦስት አራት ተወካይ ይገባል፡፡ ከአንዳንዱ ደግሞ ምንም ተወካይ የማይገባበት ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? በአገር አቀፍ ደረጃ ድምፅ የሌለው ንግድና ዘርፍ ማኅበራት እንዴት ሆኖ ነው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል የሚሆነው? ውክልና ያስፈልጋል፡፡ ውክልና በራስ መተማመን ነው፡፡ ለምሳሌ ጠንካራ የሚባሉ እንደ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አንዳንድ ጊዜ ውክልና ሳይኖራቸው ይቀራል፡፡ እንዲህ ከሆነ እነሱን እንዴት ነው የምታስተናግደው? የአባላትን ቁጥር በማሳደግና በእነዚህ አባላት ቁጥር ብቻ ድምፅ እየተሰጠ ከሄደ ብዙ አባል አለኝ የሚለው ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ አራትና አምስት የቦርድ አባላትን ያስመርጣል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በቁጥር ላይ ብቻ ተመሥርቶ የሚደረግ ምርጫ ብሔራዊ ምክር ቤቱን የአንድ ዘርፍ ወይም የአንድ ክልል ምክር ቤት ወኪሎች ያስመስለዋል፡፡ ይህም ውክልናውን ይገድበዋል፡፡ አንዳንዶች የአመራር ቦታውን ለማግኘት የማያደርጉት ቅስቀሳ ጠንካራ አመራሮች እንዳይመጡም እንቅፋት ይሆናል፡፡ ቅስቀሳው በአግባቡ ለማገልገል ከሆነ ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ሳይሆን ለመመረጥ የመፈለግ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም እኮ ወደ አመራር ለመምጣት አንዳንዶች በርካታ አባላት አለን እያሉ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ይታያሉ፡፡ በምርጫ ዋዜማ የሚታየው እንዲህ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስተካከል እናንተ ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ ሰለሞን፡- ሕጉ የሚለውን ማለፍ አንችልም፡፡ ሕጉ አንድ ሰው አንድ ድምፅ አለው ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንዱ ጋ መንግሥት እየረዳቸው በጣም ብዙ አባላት ያላቸው አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በራሳቸው ጥረት የሚያደራጁም አሉ፡፡ ብዙ ትኩረት ያልሰጡ ክልሎችም አሉ፡፡ በአንዳንዱ ክልል ደግሞ መንግሥት ራሱ ገብቶ እንዲደራጁ ብዙ ሙከራዎች የሚደረግባቸው አሉ፡፡ መደራጀቱን ራሱ ያለመፈለግ ስሜት የታየባቸውም ይኖራሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን ተቋማት እንደ አንድ የሕዝብ ክንፍ የሚፈልጋቸው ቢሆንም ወደታች ስትሄድ ብዙም ትኩረት የማይሰጥበት ቦታ አለ፡፡ የተመራጩ ጥረት ብቻ የሚታይበት እንዳለ ሁሉ የመንግሥትም ፍላጐትና ለመደራጀቱ የመንግሥት አስተዋጽኦ ያለበት ክልል አለ፡፡ ስለዚህ የመወዳደሪያ ሜዳው እኩል አይደለም፡፡ እንዲሀ ያሉ ጉዳዮች አሉ አለ፡፡ ከዚህ በፊት የሁሉም ውክልና እንዲኖር እንደ ካውንስል ያቋቋምነው፣ ሁሉንም ንግድና ዘርፍ የሚወክል ቦርድ ወይም አመራር እንዲኖር ለማድረግ እንደ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የተሞከረ ነው፡፡ እንደ አየር መንገድ ያሉ ተቋማት እኮ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነ ሚድሮክ፣ ባንኮችና የመሳሰሉት ነጋዴዎች ናቸው፡፡ የእኛ ንግድ ምክር ቤት ግን እንዲህ ያሉ ተቋማት የሌሉበት ነው፡፡ የሚያሳዝን ነው፡፡

ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች የሚያንቀሳቅሱ እንደ ሲሚንቶ ፋብሪካዎችና ትልልቅ ኩባንያዎች የተቋቋሙ ቢሆንም፣ በንግድ ምክር ቤቱ ድምፃቸው የሚሰማበት ውክልና የላቸውም፡፡ መሆን የነበረበት ግን እነሱንም ድምፅ የሚሰያማ አቅም ያለው ተቋም መፍጠር ነው፡፡ ዝም ብሎ በትንንሽ ተቋማት ውክልና ምንም ማድረግ አይችልም፡፡ ለምሳሌ ለአየር መንገድ የሚሆን መፍትሔ ሊመጣ የሚችለው የአየር መንገድ ውክልና ሲኖርበት ነው፡፡ እንደ አየር መንገድ ያለ ትልቅ ተቋምና አንድ ትንሽዬ መደብር ያለው ሰው እኩል ድምፅ ነው ያለው፡፡ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሰው ማነው? ብለህ ነው ማሰብ ያለብህ፡፡ አወካከሉም የተመጣጠነና ሁሉንም ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ጭምር ንግድ ምክር ቤቱ እየደከመ እንጂ እየጠነከረ አይደለም፡፡ በተግባር ከሚሰጠው አገልግሎትና ማበርከት ካለበት አንፃር በጣም ብዙ የሚቀረው ነገር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በምርጫ ዋዜማ ብዙ አባል አለኝ ተብሎ ድምፅ በመውሰድ የሚካሄድ ምርጫ ብዙዎች አመራሮች በተደጋጋሚ እንዲመረጡ እያደረገ፣ አዳዲስ አመራሮች እንዳይመረጡ አድርጓል የሚባለው ጉዳይስ እንዴት ይታያል?

አቶ ሰለሞን፡- እኛ የሥልጣን ክልላችን ውስን ነው፡፡ አሁንም ባለው ተነሳሽነት ሰዎች በተደጋጋሚ እንዳይመጡ ለማድረግ መመርያ እስከማውጣት ደርሰናል፡፡ አመራርነት የአንድ ዘመን ቆይታ እንጂ በንግድ ምክር ቤቱ እስከ ሕይወት ፍፃሜ መቆየት መሆን የለበትም፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች የሥልጣን ቅብብሎሽ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሥልጣን ቅብብሎሹ መለመድ አለበት፡፡ የሠራው ላልሠራው መልቀቅ አለበት፡፡ ምክንያቱም ቻምበር ላይ ብዙ ጊዜህን ትወስዳለህ፡፡ በትክክል ልሥራ ካልክ ጊዜ ሰጥተህ መሥራት አለብህ፡፡ እንዲህም ሆኖ ሥራውን አታዳርስም፡፡ በሌላ በኩል ወደ አመራር የሚመጣ ተመራጭ ጠንካራ መሆን አለበት፡፡

መንግሥትን እንዲህ ነው ብለህ ለመናገር የሚያስችልህም ዕውቀት ያስፈልግሃል፡፡ እርግጥ በአፍሪካም ደረጃ ቢሆን ቻምበሮች ደካማ ናቸው፡፡ አውሮፓ ላይ ደግሞ ትልቅ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ ከድክመት ለመውጣት ጠንካራ አመራሮች ሊመጡ ይገባል፡፡ ነገር ግን በቡድንና በቁጥር ብልጫ መምጣቱ ችግር ሆኗል፡፡ ይህ ተፅዕኖ ግን ቻምበሩን የሚያደራጅ ቢሆን ክፋት የለውም፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ ያሉ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ጽሕፈት ቤት የሌላቸው እኮ አሉ፡፡ ተቋቁመዋል ከማለት ውጪ በተግባር አሉ አይባልም፡፡ የተወሰኑት ቦርድ ቢኖራቸውም አጀንዳ ይዞ ከሚመለከታቸው ጋር የሚነጋገር የለም፡፡ ይኼ በአለበት በቁጥር ላይ ተመርኩዞ ወደ ምርጫ መሄድ በራሱ ችግር ነው፡፡ ቻምበሩን ወደኋላ የሚመልሰው ነው፡፡ ስለዚህ አወካከሉ መስተካከል ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሥር አባል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አሉ፡፡ ለምርጫ ለመቅረብ የውክልና ቀመራቸው የሚሠራው እንዴት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- በጠቅላላው ጉባዔ ላይ 18ቱም ቻምበሮች ቁጥር አላቸው፡፡ 100 ሺሕ አባላት ያሉት አለ፡፡ 20 ሺሕ አባላት ያሉት አለ፡፡ አምስት ሺሕም የሚኖራቸው አሉ፡፡ አምስት አባላት ያሉትም አለ፡፡ አንዳንድ ዘርፎችን ስታይ በቁጥር አነስተኛ ናቸው፡፡ የሚያንቀሳቀሱትን ካፒታል ሲታይ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍሎሪካልቸርን እንመልከት፡፡ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ቢሆንም አወካከሉ ግራ ያጋባል፡፡ ሲሚንቶና ብረት የት ነው የሚገቡት ሲባልም ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡ መንግሥት እኮ ይህንን ማየት አለበት፡፡ በየት በኩል ነው የሚመጡት አንድ የብረት ፋብሪካና የብረት መበየጃ ድርጅት አንድ ላይ መምጣት አለባቸው? ስለዚህ አደረጃጀቱ ሊስተካከል ካልቻለ ውክልና ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ እንዲህ እንዲህ ባለ መንገድ ተደራጅቶ የወጣ ቦታውን ሲይዝ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ግን ጥቂት አባላት ያሉዋቸው ዘርፎች ይዋጣሉ፡፡ ለምሳሌ 500 አባል አለኝ ካለ 50 በመቶውን ወንበር ይወስዳል ማለት ነው፡፡ አምስት አባል ያለው ድምፁን የሚያሰማበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ብንወስድ ወደ 15 ሺሕ አባላት አሉት፡፡ ይህ ቁጥር በአዲስ አበባ ካለው ነጋዴ ጋር ሲመዘን ትንሽ ነው፡፡ ቢሆንም ጠንካራ ከሚባሉ ንግድ ምክር ቤቶች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ ሌሎች ዘርፎች ባላቸው አባላት ቁጥር ከተበለጠ በአመራሩ ውስጥ ውክልና ላይኖረው ነው ማለት ነው፡፡

ወደ ምርጫ ስንመጣ መምረጥ የሚችለው በቁጥር ብልጫ ያለው ነው፡፡ መሆን ያለበት ግን በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ ትልልቅ ተቋማትን የሚወክሉ ጠንካራ የሆኑና የአመራር ብቃት ኖሯቸው አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ፣ የማመቻመች ጉዳይ ሳይሆን ትክክለኛውን መስመር ተከትሎ መሄድ የሚችል ነጋዴ እንዲኖር ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ አካላት መምጣት አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግ መንገዱ አያዋጣም፡፡   

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ ሲታይ የአደረጃጀት ክፍተት በመኖሩ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ብቻ ሳይሆን፣ ለመፍትሔም ያደረጋችሁትስ ጥረት አለ?

አቶ ሰለሞን፡- እንግዲህ እኛ አቅርበናል፡፡ አባላት እንዴት መሆን እንዳለባቸው የሚያሳይ አማራጮች አቅርበናል፡፡ ለምሳሌ ከአሁን በፊት ካውንስል የሚባል ነገር ነበር፡፡ ካውንስል ማለት ከየትኛውም ቻምበር አንድ አንድ ወኪል ይመጣል፡፡ ተወካዩ ፕሬዚዳንቱ ወይም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የካውንስል አሠራር ትክክል ነው ለማለት ሳይሆን፣ በዚህ አሠራር በካውንስሉ የተሰባሰቡት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት ይመርጣሉ፡፡ በዚያ ሲሠራ ነበር፡፡ ይህ አሠራር ግን አሁን አይሠራም፡፡ እሱም ችግር አለበት፡፡ ተስማምቶ የመሥራትና የመቻቻል ሁኔታው አስቸጋሪ ነው፡፡ ለምሳሌ የሆቴል ኢንዱስትሪውንና ቱሪዝምን ተመልከት፡፡ ይህ ዘርፍ እኛ ዘንድ የሚወከልበት መንገድ የለም፡፡ አገልግሎት በሚለው ዘርፍ ውስጥ ነው የሚገባው፡፡ ግን ለኢኮኖሚው ትልቁን ሚና ይጫወታል የተባለው ይህ ዘርፍ ከዚህ ውጪ ነው፡፡ ሌላው ሸራተንና አንድ ትንሽ ምግብ ቤትን አንድ ላይ ታደራጃለህ፣ ይህ ችግር ነው፡፡ ይደራጁ ስትል እንዴት አስማምተህ ልትቀጥል ነው? ስለዚህ ትልልቆቹ በቀጥታ የሚሳተፉበት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ በአነስተኛ ቢዝነሶች የሚወከሉ ከበዙ ችግሩ ይቀጥላል፡፡

በየኢንዱስትሪው ይደራጁና ይምጡ እንደገና በአንድ ጥላ ሥር ተሰባስበው እንዲሠሩ ይደረግ፡፡ ለምሳሌ በአነስተኛ ንግድ ላይ ያሉ ነጋዴዎች ችግራቸው ቢሮክራሲ ነው፡፡ የሁሉም ዘርፍ ችግር አንድ አይደለም፡፡ ምናልባት ለአነስተኛ ነጋዴው ሒሳብ አያያዝን ማሳወቅና ማብቃት ነው፡፡ ችግሩ እዚያ ላይ ያበቃል፡፡ ግን የማኑፋክቸሪንግ (አምራች) ትልልቅ ኩባንያዎች ለምሳሌ ባንኮችን ብንወስድ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ ድምፅ ከሌላቸው የንግድ ምክር ቤቶች ጥንካሬ ይላላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከገለጻዎ እንደተረዳሁትም ሆነ በግልጽ እንደሚታየው ትልልቅ ኩባንያዎችና መሪዎች የንግድ ምክር ቤቶች አባል አይደሉም፡፡ ይኼ ትልቅ ክፍተት ለመሆኑም ጥርጥር የለውም፡፡ እነሱን ወደ ቻምበሩ ለማምጣት ምን መደረግ አለበት? እናንተስ እነሱን ለማምጣት ያላችሁን አቅም ተጠቅማችኋል?

አቶ ሰለሞን፡- ልክ ነህ፡፡ ትልልቅ ተቋማትን የሚወክሉ ተመራጮች የሉም፡፡ አሁን እኮ የአቅም ውስንነት አለብን፡፡ ተቋማቱ ጥሩ ናቸው፡፡ አደረጃጀታቸውና የሰው ኃይላቸው ጥሩ ነው፡፡ ችግር ሆኖ የሚመጣው ግን ለኢኮኖሚው ወሳኝነት ያላቸውን አልፎ አልፎ እነሱን በቢዝነስ አጀንዳችን ላይ እያስጠናን በምክክር መድረኮች ላይ እናነሳለን፡፡ ችግራቸውን ለማወቅ ፈልገን ከማቅረብ የዘለለ ሥራ አልተሠራም፡፡ እነሱም አይመጡም፣ እኛም አልሄድንም፡፡ ስለዚህ መንግሥት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ያስፈልገኛል ማለት አለበት፡፡ ሙስናን ለመዋጋትም ንግድ ምክር ቤቱ ጠቃሚ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡

በእውነት እንዲህ መሞከር ማለት ከአራት አምስት ዓመታት ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ አማካሪዎች ብዙ ነገር ተሠርቷል፡፡ አደረጃጀቱ እንዲህ መሆን አለበት ብለን ሰጥተናል፡፡ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንናገራለን፡፡ አዋጁ ይሻሻል ብለን አማራጮች ሳይቀር አቅርበናል፡፡ አደረጃጀቱ እንዲህ መሆን አለበት ብለን ሁሉ ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋርም ተወያይተናል፡፡ ማጠንከሪያ ዘዴዎቹ እነዚህ ናቸው ብለን አቀርበናል፡፡ ይኼ አደረጃጀት ትክክለኛ መስመሩን ይዞ እስካልሄደ ድረስ ንግድ ምክር ቤቱን ማጠናከር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ለትልልቆቹ የሚፈታው የፖሊሲ ችግር ታች ያለውንም ያግዛል፡፡ የታችኛውንም በክልል ደረጃ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሲስተሙ ጠንካራ የሆነ ነጋዴ ጉቦ ሊሰጥ አይሄድም፡፡ ወደዚያ የሚሄደው ሲስተሙ የላላ ሲሆን ነው፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ከሆነ ይለወጣል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ከሆነ ከመጪው ምርጫ ምን ይጠብቃሉ? ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያወጣው አዲስ የዘርፍ አደረጃጀትስ በዚህ ምርጫ ላይ ይተገበራል?

አቶ ሰለሞን፡- አላውቅም፡፡ ግልጽ አይደለም፡፡ ይኼ ነው ብዬ ለመናገር አልችልም፡፡ አዲስ ነገር ይምጣ አይምጣ መገመት አልችልም፡፡ እንግዲህ ባስቀመጥናቸው መሥፈርቶች መሠረት እናካሂዳለን፡፡ በነገራችን ላይ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት ያላቸው ክልሎች አሉ፡፡ ጠንካራ ያልሆኑም አሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች የመንግሥትን ሥራ እየሠሩ የሚውሉ አሉ፡፡ መንግሥት እኮ ብዙ ባለሙያዎች አሉት፡፡

መንግሥት በዚህ ደረጃ አይደለም የሚፈልገን፡፡ ጠንካራ ሆናችሁ ለመብታችሁ የምትታገሉ ከሆነ እኔን ትደግፉኛላችሁ የሚል ነው፡፡ ሞግተኝ፣ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ግባ፣ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሳተፍ ነው የሚለው፡፡ እኔን እያሞገስከኝ ኑር የሚል አይመስለኝም፡፡ አሁን ምን ይሆናል የሚለውን አላውቅም፡፡ አሁን ግራ ያጋባን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዘርፎች እንዴት ይደራጃሉ ብሎ ያወጣው አዲሱ ደንብ ነው፡፡ እኛ ያለን ደንብ ደግሞ በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ውስጥ የሚገቡት ስድስት ዘርፎች ናቸው፡፡ ዘጠኝ ክልሎች፣ ሁለት ከተሞችና አንድ አገር አቀፍ ዘርፍ ናቸው፡፡ እኛ የምናውቀው ይኼንን ነው፡፡ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደግሞ 52ቱ በአንድ ዘርፍ ይጠቃለላሉ ብሏል፡፡ እኛ ዘንድ ያሉትም ስድስት ዘርፎች በ52ቱ ውስጥ ይጠቃለላሉ ተብሏል፡፡ ይህ ጉዳይ በአዋጅ መዳሰስ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አደረጃጀትን ያወጡት ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተብለው በሚጠሩበት ወቅት ነው፡፡ አሁን ንግዱና ኢንዱስትሪው ተለይቷል፡፡ ስለዚህ በአዲሱ አደረጃጀት ወይስ በቀድሞው የሚለው ያሳስበናል፡፡ አሁን ይህ እንዴት ይሆናል ስንል ቄሱም መጽሐፉም ዝም ሆኗል፡፡ የትኛውን ነው የምንቀበለው? ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባወጣው ደንብ ሁሉም በአንድ ተጠቃሎ በሚቀርብበት ዘርፍ ነው? ወይስ እኛ ውስጥ ያሉትን ስድስቱን ዘርፍ ነው የምንቀበለው? ይህ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን እንግዲህ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር የተሻለ ተቋም እንዲኖረን ማለም ጥሩ ይመስለኛል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...