Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ያልተገነቡ ኮንዶሚኒየሞችና ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች

በሳምንቱ መጀመሪያ ቀትር ላይ በተከታታይ የሰማኋቸው ዜናዎች ባልተለመደ ሁኔታ ስሜቴን ቆንጥጠውታል፡፡ ያስበረገጉኝ ዜናዎች ነበሩ ማለት እችላለሁ፡፡

ዜናዎቹ በሁሉም የመገናኛ ብዙኃን የተሠራጩ ስለነበሩ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከአንዱ ጣቢያ ወደሌላው እየቀያየርኩ አዳምጫለሁ፡፡ ድህረ ገጽ እየቀያየርኩ ደጋግሜ ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡

አንደኛው ዜና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መሠረቁን የሚናገረው ነው፡፡ ይህንን ዜና የሰማ ሁሉ የአግራሞቱ መጠን ይለያይ እንጂ አጀብ መሰኘቱ አይቀርም፡፡ አሳዛኝ ዜናም ነበር፡፡

ሁለተኛው ዜና በበኩሉ ጠፉ ተብለው የነበሩ የኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች ያለመጥፋታቸውን፤ ነገር ግን ሳይገነቡ የቀሩ 98 ሕንፃዎች እንዳሉ መረጋገጡን የሚቃኘው ነው፡፡

የዛሬ ጽሑፌም ተሰረቀ ስለተባለው ፈተና ሳይሆን፣ ጠፉ ተብለው ኋላ ግን ያልተገነቡ ሕንፃዎች ስለመኖራቸው በሚገልጸው ዜና ላይ የሚሽከረከር ይሆናል፡፡ የመጠለያ ጉዳይ የሁላችንንም ስሜት የሚይዝ በመሆኑ፣ በተለይም መች ይሆን ቤት የሚኖረኝ ብሎ በተስፋ የሚጠብቅ ዜጋ ሁሉ ስለተገነባው ብቻም ሳይሆን ስላልተገነባውም ሕንፃ የሚወራውን ለመስማት ጆሮ መስጠቱ አይቀርም፡፡

ለኮንዶሚኒየም የተመዘገቡትም ያልተመዘገቡትም ዕጣ የሚወጣው መቼ እንደሆነ በሚጠባበቁበት በዚህ ወቅት፣ ያልተገነቡ 100 ያህል ሕንፃዎች አሉ ሲባል ለምን ማለቱ ግድ ነው፡፡

በግድ እንድንነጋገርበት ያስገድዳል፡፡ ሕንፃ ጠፋ ሲባል ስለመጥፋቱ ብቻ ሳይሆን፤ ባይጠፋ ኑሮ ምናልባት ባለዕድል ልሆን እችል ነበር የሚልም ስሜት ስለሚፈጥር ጉዳዩ ከዚህም በላይ ሊያነጋግረን ይችላል፡፡ ከፍ ብለን ካየነው ደግሞ ሕንፃን የሚያክል ነገር እንዴት ማጥፋት ተቻለ? ሙስናው እዚህ ደረጃ ደረሰ ማለት ነው? ብለን ብዙ የተወያየንበት፣ የየበኩላችንን አስተያየት የሰጠንበት ርዕሥ ሆኗል፡፡

የጠፉ ኮንዶሚኒሞች አሉ ሲባል ሕንፃ በጅምላ መስረቅ ከተጀመረ መጨረሻችን ምንድን ነው? የሚሉና ሌሎች ድርብርብ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ዝም መባሉ ለምን? ሐሰት ከሆነም ወሬው በተናፈሰበት ልክ በፍጥነት መልስ መስጠት ሲገባ ለምን ቸልታ ተመረጠ? በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጠፉ ሕንፃዎች ስለመኖራቸው የሚያመለክት ጥያቄ በቀረበበት ወቅት፣ ለጥያቄው ከመንግሥት እንደራሴው ምላሽ አለመሰጠቱ ሐሜቱ እንዲቀጥል አድርጐታል፡፡ ለማንኛውም ከሰሞኑ ከዚያው ከሕዝብ ተካዮች ምክር ቤት የወጣው መረጃ የጠፋ ኮንደሚኒም አለመኖሩን የሚጠቁም ነው፡፡
ይህ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን የጠፉ ሕንፃዎች እንደሌሉን ለማስተባበል የተሰጠውን ማብራሪያ ተከትሎ የተሰማው ቅጥል ዜና ግን ጠፉ ከተባሉት ሕንፃዎች በላይ አስገራሚ ሆኖብኛል፡፡  

የቋሚ ኮሚቴው የጠፉ ሕንፃዎች ያለመኖራቸውን፤ ነገር ግን በተለያዩ ሳይቶች መገንባት የነበረባቸው ሕንፃዎች ሳይገነቡ ተገኝተዋል በማለት ጠፉ የተባሉት ሕንፃዎች ያልተገነቡ እንጂ የጠፉ አይደሉም ብሎ ለመሞገት ሞክሯል፡፡ ብዙዎቻችን የተረዳነው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በእርግጥም ሕንፃን የሚያህል ነገር ጠፋ መባሉን ለማመን ከባድ ነው፡፡

ስለዚህ ይህንኑ መረጃ ይዘን እንንነጋገር ከተባለም መገንባት ሲኖርባቸው ያልተገነቡ ሕንፃዎች ነበሩ የሚለው ያግባባናል፡፡ ይህም ግን ሊያነጋግር ይችላል፡፡ በሳምንቱ አጋማሽ የከተማው ቱባ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ስለሁኔታው ማብራሪያ ይሰጠን ማለታቸው ጉዳዩን የበለጠ ሳያወሳስበው አልቀረም፡፡ በመንግሥት ውጥን መሠረት እገነባለሁ ብሎ የያዘው ዕቅድ እንዴት ሳይተገበር እንደቀረ ሊብራራ ይገባል ወደሚል መደምደሚያም ይወስደናል፡፡

ሁሉንም ነገር ትተን አሁንም መገንባት ሲኖርባቸው አልተገነቡም የተባሉት ሕንፃዎች ለምን እንዳልተገነቡ እንኳ አጥጋቢ መልስ ያለመሰጠቱ አስገራሚ ነበር፡፡ እስከ ዛሬስ ለምን እንዳልተገነቡ ከዚህ ቀደም ለምን አልተነገረም? የሚለውን ጥያቄም ያስከትላል፡፡ በተለይ እንዲህ ያሉ ግንባታዎች በዕቅድና በጥናት የሚካሄዱ ከመሆናቸው አንፃር የግንባታ ሥራውን በኃላፊነት የሚያስተባብረው መንግሥታዊ ክፍል ጥርት ያለ ሪፖርት ማቅረብ ሲጠበቅበት ይህ ለምን አልተደረገም?

በተደጋጋሚ እንደምንሰማው በአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ለማካሄድ ታቅዶ ይህንን ያህል ተገነባ፣ ይህንን ያህሉ ደግሞ እየተገነባ ነው፡፡ ይህንን ያህሉ ቤቶች ተላለፉ ሲባል እየሰማን ነው፡፡ ይህንን ያህል ሕንፃዎች ግን ሳይገነቡ መቅረታቸውን፤ ሳይነገረን መቅረቱም መንግሥት ያለበትን ችግር የሚያሳብቅ ነው፡፡

ሪፖርት ሲቀርብ ተገነቡ የተባሉትን ብቻ ማቅረብ፤ የተላለፉትን ቤቶች ብቻ ማሳወቅ ተገቢ አይደለም፡፡ ያልተገነቡ ምን ያህል መኖራቸውም ማሳወቁ ግዴታ መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ወይም ሆን ተብሎ መረጃው ተሸሽጓል፡፡ ከዚህ አንፃር ተገነቡ፣ አለቁ፣ ተላለፉ የሚባሉት ቤቶች አሃዛዊ መረጃ የተምታታ ነበር የሚለውን ጥርጣሬ ያጐላዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅርቡ በተካሄደው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቆጠራ ወቅት የተሰባሰበው መረጃ ሳይገነቡ ቀርተዋል የተባሉትን ሕንፃዎች ስለማካተቱ አለማወቃችን ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር የሚያስፈልግ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

ሳይገነቡ ቀሩ የተባሉት ሕንፃዎች ምንም ዓይነት ውል ያልተፈረመባቸውና በፕሮጀክቶቹ ስም ክፍያ ያልተፈጸመባቸው ናቸው መባሉ ግን እፎይታ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሩን በሌላ መንገድ እንመልከተው ከተባለ ደግሞ በተያዘው ዕቅድ መሠረት መገንባት ሲኖርባቸው ያለመገንባታቸው ግን ትልቅ ጥፋት ነው፡፡ ያልተገነቡም በምን ምክንያት እንደሆነ እስካልተገለጸ ድረስ ማለት ነው፡፡ ለግንባታ በተያዘላቸው ቦታ ላይ ሕንፃዎቹ ከሌሉ ሕዝቡ እውነት አለው ጠፍተዋል፡፡ በሌላ በኩል ግንባታዎቹ በዕቅድ ከተያዙ በጀት ተይዞላቸው ነበርና ይህ በጀት ምን ላይ ዋለ? ለሚለው ጥያቄም መልስ ያሻዋል፡፡ መንግሥት ሊሸሸው ከማይችለው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ ለእያንዳንዷ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡  

ዛሬ ሕንፃ ጠፋ አልጠፋ ተገነባ አልተገነባ የሚለው ብዥታ የተፈጠረው መረጃን በአግባቡ ከማቅረብ ድክመት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ መንግሥት ሆይ የጠራ፣ የነጠረ መረጃ አቅርብ፤ ትክክለኛ ሁን፤ ለማለት ያስገድዳል፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት