Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መድን ድርጅቶች ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ሰበሰቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች አሻቅበዋል

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2008 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የ5.02 ቢሊዮን ብር ዓረቦን (ፕሪሚየም) ማሰባሰብ ቢችሉም፣ ከፍተኛ የጉዳት ካሳ ጥያቄ እንደቀረበባቸው ተመለከተ፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹን የዘጠኝ ወራት እንቅስቃሴ የሚያሳየው ግርድፍ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በዘጠኝ ወራት ከሰጡት የኢንሹራንስ ሽፋን ያሰባሰቡት ዓረቦን በቀዳሚው ዓመት ካሰባሰቡት ጋር በንፅፅር ሲታይ ብዙም ዕድገት ያልታየበት ነው፡፡

በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ወቅታዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ በዘጠኝ ወራት የተሰባሰበው ዓረቦን ዕድገት ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተሰበሰበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ሽፋን የተገኘ ነው፡፡ ከሕይወት የተገኘው ዓረቦን መጠን 274 ሚሊዮን ብር እንደሆነ መረጃው ያመለክታል፡፡

አነስተኛ ዕድገት ተመዘገበበት የተባለው የዓረቦን መጠን ብቻ ሳይሆን፣ በበጀት ዓመቱ የተጠየቀው የጉዳት ካሳም ከፍተኛ እንደሆነ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የቀረበው የጉዳት ካሳ መጠን ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይህ የጉዳት ካሳ መጠን ግን ሙሉ ለሙሉ ላይከፈል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

በዚህን ያህል ደረጃ የጉዳት ካሳ ጥያቄ ያልቀረበ በመሆኑ ተጣርቶ የሚከፈለውም ቢሆን ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ከተከፈለው የበለጠ ሊከፍሉ እንደሚችሉ አመላካች እንደሆነ ታውቋል፡፡

በዘጠኙ ወራት ሪፖርት መሠረት ከተከማቸው የጉዳት ካሳ ጥያቄ ውስጥ አሁንም ብልጫ የያዘው የሞተር ወይም የተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ክፍያ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት 16ቱ የግልና አንድ የመንግሥት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሀብታቸው አሥር ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለፈው ሙሉ በጀት ዓመት ወቅት ማሰባሰብ የቻሉት የዓረቦን መጠን 5.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ በሙሉ የበጀት ዓመቱም ለጉዳት ካሳ ክፍያ የዋሉት 2.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዓረቦን አሰባሰባቸው ብዙም ዕድገት ሳይመዘገብበት ለካሳ ክፍያው የተጠየቁት መጠን መጨመሩ ግን በኩባንያዎች ዓመታዊ የትርፍ መጠን ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች