በልሳነ ምድር ደቡብ ኮሪያ አንድ ትልቅ ሰው ስማቸው ከፍ ብሎ ይነሳል፡፡ ለደቡብ ኮሪያ ሪፐብሊክ የዘመናዊነት ታሪክ ተጠቃሹ ግለሰብ፣ አገሪቱን በዓለም አስገራሚ የታሪክ ዓውድ ውስጥ እንድታልፍ አድርገዋል፡፡ እንደሌሎች በታሪክ ጉልህ ሥፍራ እንደያዙ ግለሰቦች ሁሉ እኒህ ግለሰብ በዚያች አገር ሕዝብ ዘንድ በግራም በቀኝም ስማቸውን የሚያስነሳ የኋላ አከራካሪ ታሪክ ትተው አልፈዋል፡፡ የአመራር ዘይቤያቸውን አንዳንዶች ብልኅነትንና ብልኃትን የተላበሰ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ ሌሎች ግን ሁሉን ጠቅልሎ በመግዛትና በመቆጣጠር ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ያስባሉ፡፡
ሰውዬው ኮሪያዊ ዘርግንዳቸውን አጥበቀው የሚወዱ፣ የብሔራዊነት ስሜታቸው ጫፍ የነካ እየተባሉ ሲጠሩ ቆይተዋል፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለቅኝ ገዥዎች ተንበርካኪ ልብ የነበራቸው ያውም በጃፓን ቅኝ በተያዙ ጊዜ ለጃፓን ጦር ኃይሎች በውትድርና ያገለገሉ እየተባሉም ይተቻሉ፡፡ ነገሩ ከዚህም ሲከፋ ደግሞ ከጃፓን የመጠሪያ ስሞች አንዱን ለራሳቸው መምረጣቸው እንደ ባንዳ ሳያስቆጥራቸውም አልቀረም፡፡
እኚህ መሪ ለኮሚውኒስቶች የቅርብ ሰው እንደሆኑ ሲወራባቸውም ጠንካራ የመንግሥት ሚናን በኢኮኖሚውና በልማት ጉዞ ውስጥ እንዲኖር መፈለጋቸውን በመጥቀስ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን አባባል የሚሽር ገጽታም እንደነበራቸው ይነገርላቸዋል፡፡ በወቅቱ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ የእስያና የአፍሪካ አገሮች ሲያደርጉት ከነበረው ወደ ራስ ወይም ወደ ውስጥ የመመልከትንና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የመተካት አባዜዎችን በተጻረረ መልኩ ገበያ መር ኢኮኖሚ ላይ ያጠነጠነና የወጪ ንግድ ዝንባሌ ያለው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመከተላቸው በዚህ አግባብ የተለየ ገጽታ ይሰጣቸዋል፡፡
እኚህ ሰው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ፓርክ ቹንግ-ሒ ናቸው፡፡ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1961፣ ዓለም የቀዝቃዛው ጦርነትን መቀስቀስ በሥጋት በሚመለከትበት ወቅት በትረ ሥልጣን የጨበጡ የቀድሞ የጦር አዝማች ጄነራል ናቸው፡፡ በሚያወድሷቸውና በሚቃወሟቸው ዘንድ ሳይቀር ቦታ የሚያሰጣቸውን ፕሬዚዳንታዊ ተግባር የፈጸሙ፣ ነፃና ፍትኃዊ ምርጫ ያካሔዱ ተብለው የሚወደሱ ሰው ከመሆንም መንገዳቸውን የገታው ነገር አልነበረም፡፡ እንዲህ የሚንቆለጳጰሱት ሰው ሕገ መንግሥት አሻሽለው ‹‹ዩሺን›› የሚባሉትን ሕግጋት በመትከል ረዘም ላለ ጊዜ በሥልጣን ለመቆየት የሚያስችላቸውን ብልኃትም የቀየሱ ናቸው፡፡
በዚህም በዚያም የሚያነሷቸው ደጋፊዎቻቸውም ሆኑ ተቋዋሚዎቻቸው በአንድ ነገር ይስማማሉ፡፡ በኮሪያ ምድር ከነበሩ ሁሉ የድህነትንና የኋላቀርነትን ሰንሰለት የበጣጠሰ ሰይፍ የመዘዙ የመጀመሪያው መሪ ስለመሆናቸው ማንም አይከራከርም፡፡
እንዲያም ሆኖ በግል ጠባያቸውና በአመራራቸው ዘይቤ የታየው አከራካሪነታቸው ግን ለሦስት ምዕራፍ በዘለቁት የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅዶቻቸውም ላይ ተንፀባርቋል፡፡ በኢኮኖሚ ልማት መስክ የመንግሥት ሚና እንዲኖር ያላቸው እምነትና በሀብት አጠቃቀም ረገድ ጠንካራ ቁጥጥር እንዲኖር መፈለጋቸው አከራካሪ ከሆኑ ተግባራቶቻቸው ውስጥ ይመደባሉ፡፡ መነሻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ዋናው ተፈላጊ ነገር ውጤቱ ነው የሚል ፖሊሲ ያራመዱት ፕሬዚዳንት ፓርክ፣ የግል ኩባንያዎችን በማዋሐድና በማስተዳደር ረገድ የተጫወቱት ሚና ዛሬ ለተፈጠሩት ግዙፍ ኮርፖሬሽኖች (ቺቦልስ) ሕልውና መመሥረት መሠረቱን ጥለዋል፡፡ በቤተሰብ ለሚተዳደሩት እነዚህ ኩባንያዎች ግዙፍ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎች ተጠቃሚ እንደሆኑ በማድረግ በራሳቸውም በአገረ ኮሪያም ላይ ታላቅ የፖለቲካ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ኃላፊነትን ለመሸከም መፍቀዳቸው ከሚነገሩላቸው መካከል አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
የፕሬዚዳንት ፓርክ አስተዳደር የመጀመሪያውንና ጉሮ የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ የተባለውን ግዙፍ የማምረቻ ክልል እ.ኤ.አ. በ1964 ዕውን ለማድረግ በርካታ አንጡራ ሀብት አፍስሷል፡፡ በደቡብ ምሥራቅ አገሪቱ ክፍል ለተንጣለለው የኡልሳን ኢንዱስትሪ ግዛት ምሥረታ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ እንዲሳካ ከአገሪቱ ዓመታዊ ጠቅላላ በጀት ውስጥ እስከ 20 ከመቶውን እስከመመደብ የደረሱ ቆራጥ መሪ እንደነበሩ የሚናገሩት በደቡብ ኮሪያ የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ኮርፖሬሽን ሥር ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቾ ሃይ ያንግ ናቸው፡፡
ከዓመታት በኋላ አሁን ላይ ሲታይ የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ የኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ፣ የፕሬዚዳንት ፓርክ ቁማር ውጤት አስገኝቷል፡፡ ምንም እንኳ እ.ኤ.አ. በ1979 በተቃጣባቸው የግድያ ሴራ በሞት ተለይተው የፖሊሲያቸውን ፍሬ ለመመልከት ባይታደሉም፣ ደቡብ ኮሪያ ግን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ብሔራዊ ገቢዋን በወቅቱ ከነበረበት 79 ዶላር በአሁኑ ወቅት 35 ሺሕ ዶላር በማድረስ በዓለም 11ኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ለመሆን በቅታለች፡፡
ዋና ከተማዋን ሴዑልን አቋርጦ የሚያልፈውን ወንዝ መነሻ በማድረግ ዓለም የደቡብ ኮሪያን የኢኮኖሚ ግስጋሴ፤ የሐን ወንዝ ተዓምር እያለ የሚገልጽላት ኮሪያ፣ በሌላ በኩል ግን የኢኮኖሚዋ ስኬታማ ጉዙ መንስዔ በቀደምቱ ጊዜ ትልልቅ ግን ውጤታማ ኮርፖሬሽኖችን ወይም ቺቦልስ እየተባሉ የሚጠሩትን በጥንቃቄ በመምረጧ ነው የሚሉም አሉ፡፡
ዶ/ር ቾ ሃይ ያንግ የሚገልጹት በሌላ ጎኑ ነው፡፡ የፕሬዚዳንት ፓርክ መንግሥት የተከተለው ግልጽ ፖሊሲ፣ የአገር ውስጥ የአምራችነት አቅምን ለማምጣት በቀላል አምራች ኢንዱስትሪው ላይ የተደረገው ትኩረት እንደ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ያሉትን ዘርፎችን ያቀፈ መሆኑ፣ ኋላም በ1970ዎቹ ውስጥ በከባድ ማሽነሪዎች፣ በብረታ ብረትና በፔትሮኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ያስገኘው ውጤት ነው፡፡
በአንድ ወቅት የመጀመሪያው የኮሪያ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ እየተባለ የቆየው ጉሮ ኢንዱስትሪያል ኮምፕሌክስ፣ በአሁኑ ወቅት ሴዑል ዲጂታል ኮምፕሌክስ (ጂ-ቫሊ) ተብሎ የሚጠራ ግዙፍ ማዕከል ወጥቶታል፡፡ ይህ የኢንዱስትሪ ከተማ ከ9600 በላይ ኩባንያዎችን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች የዘመኑ ቴክኖሎጂ መስኮች ተሠማርተው ወደ ውጭ በመላክ፣ በያመቱ እስከ 2.4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ኩባንያዎች ናቸው፡፡
በአብዛኛው በኢንዱስትሪ ክላስተርና አነስተኛ ወጪ በሚጠይቀው የሰው ጉልበት ላይ በተሠሩ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ መስኮች ላይ ያጠነጠነው የፕሬዚዳንት ፓርክ ፖሊሲ በሁሉም መልኩ ለኮሪያውያን ውጤት አስገኝቷል፡፡ ጥቅም አምጥቷል፡፡ የግማሽ ክፍለ ዘመን ልምድ ያካበተው የኮሪያው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ኮርፖሬሽን እንዲህ ያሉትን ግዙፍ ኢንዱስትሪ ኮምፔክሶች በማስተዳደር ረገድ የጠና ልምድ አካብቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ ከ1040 የኢንዱስትሪ ማዕከሎች ውስጥ 63ቱን ያስተዳድራል፡፡ እነዚህ 63 የኢንዱስትሪ ማዕከሎች በበኩላቸው 49 ሺሕ ኩባንያዎችን በማቀፍ በውስጣቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራሉ፤ የአገሪቱን 40 ከመቶ የኢንዱስትሪ ምርት ያስገኛሉ እንዲሁም የአገሪቱን 41 ከመቶ የወጪ ንግድ ገቢ ያመነጫሉ፡፡ እርግጥ እ.ኤ.አ. እስከ 2015 ድረስ በኮሪያ ምድር 85,789 ኩባንዎች 2.16 ሚሊዮኖችን በመቅጠር በኢንዱስትሪ ማዕከሎች ውስጥ እያተዳደሩ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ ይበልጡን ደግሞ 70.9 ከመቶ የማኑፋክቸሪንግ እሴት የታከለባቸው እንዲሁም 79.7 ከመቶ የኤክስፖርት ምርት የሚያስገኙ የኢንዱስትሪ ከተሞች በኮሪያ ምድር ተንሰራፍተዋል፡፡
በኮሪያ የኢንዱስትሪ ከተሞች ውስጥ የሚስተዋለው ትልቁ ነገር በክላስተር መቀናጀታቸው ነው፡፡ በኮሪያው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ኮርፖሬሽን የሚተዳደሩ አራት ዓይነት የኢንዱስትሪ ማዕከሎች አሉ፡፡ እያንዳንዳቸው እንደየሥራ መስካቸው ትኩረት የሚያደርጉባቸው የተወሰኑ ዘርፎች ላይ ተሠማርተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑን አንደኛው ዓይነት ማዕከል፣ ብሔራዊ የኢንዱስትሪ ማዕከሎችን የሚወክል ሲሆን፣ ለአገሬው ባለሀብቶች የተከለሉ 29 ማዕከሎችን ያጠቃልላል፡፡ ሁለተኛው ዓይነት ጠቅላላ የሚባለው ሲሆን 20 የኢንዱስትሪ ማዕከሎችን፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ዞን ተብለው የተከለሉ 11 እንዲሁም ለግብርናው መስክ የተመደቡ ሦስት ማዕከሎች በዓይነት ተለይተው ተመድበዋል፡፡
ምንም እንኳ ለውጭ ኢንቨስተሮች የተመደቡ የኢንዱስትሪ ማዕከሎች ቢኖሩም፣ ኮሪያውያኑ ዋናው ትኩረታቸው የውጭ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንዳልሆነ ዶ/ር ቾ ሃይ ያንግ ይናገራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 1990ዎቹ ድረስ መንግሥት ለውጭ ኢንቨስተሮች የማምረቻ ዞኖችን፣ ነፃ የንግድን የኢኮኖሚ ዞኖችንም እንዳላዘጋጀ ዶ/ር ቾ ሃይ ያንግ አስታውሰዋል፡፡ እስከ ሃቻምና በነበረው ጊዜም በኮሪያ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት የውጭ አምራቾች ቁጥር 3400 ሲሆን፣ አጠቃላይ የምርት መጠናቸውም ከ20 በመቶ በታች እንዲሁም ወደ ውጭ የሚልኩት የፋብሪካ ምርትም ከ20 ከመቶ ያልዘለለ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ኮሪያውያኑ በቀላል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለአምራቾች የተሰጡት ትኩረት እንዲሁም ለተንሰራፋው የሰው ሀብት የሰጡት ቦታ የዕድገታቸው ምሰሶ መሆኑ ይነገራል፡፡ በኮሪያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የጨርቃ ጨርቅ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ጥናትና ልማት ክፍል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሚን ኪዩ ሶንግ እንደሚያምኑት፣ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ኮሪያን በዕቅፉ ደግፎ አሁን ላለችበት አድርሷታል፡፡ ‹‹እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ ጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ የኮሪያን የኢንዱስትሪ ጉዞ አቀጣጥሏል፡፡››
ስለኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሲነሳ አራተኛዋ የኮሪያ ግዙፍ ከተማ ዴጉ ሳትጠቀስ አትታለፍም፡፡ ይህች ከተማ ለኮሪያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ መነሻ እምብርት ሆና ከ1960ዎቹ ጀምሮ አገልግላለች፡፡ በዴጉ እንደ ሱፍ ያሉ ጥሬ ዕቃዎች እንደልብ መገኛ መሆኗ ሲታወቅ፣ ጊዮንግበክ የተባለው ግዛት በተለይ ትክክለኛው የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች መናኸሪያ መሆኑም ይነገርለታል፡፡ በጊዮንግበክ ግዛት፣ የቴክኖሎጂ ፓርክ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቺል-ሴዎክ ዩን እንደሚሉት፣ ግዛቱ ልክ አሁን ኢትዮጵያ እንደምትገኝበት ሁኔታ ተመሳሳይነት አለው፤ በአብዛኛው በተፈጥሮ የጨርቃ ጨርቅ ጥሬ ዕቃዎችና በሰፊ የሰው ኃይል ላይ የተመሠረተ ነውና፡፡
በዴጉ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ሙዚየም ለዕይታ የቀረቡ ልዩ ልዩ የዕደ ጥበብ ቁሳቀሶች፣ እንደ ናይለንና ፖሊመር ያሉ ሲንቴቲክ ፋይበር የመሳሰሉ የጨርቃ ጨርቅ አብዮትን ያቀጣጠሉ ምርቶችን በሰፊ የመጠቀምን ዝንባሌ የፈጠረ አካባቢ ስለመሆኑ ይዘክራሉ፡፡ ዶ/ር ሲንግ እንደሚናገሩት፣ ዴጉ ከተማ ሲንቴቲክ ፋይበርን በመጠቀም ቀዳሚዋ ስትሆን፣ የመጠቁ የጨርቃ ጨርቅ ምርምሮችንም ከሌሎቹ የኮሪያ ከተሞች ይልቅ በውስጧ ይዛለች፡፡ እንደ ዶ/ር ዩን ማብራሪያ፣ 1500 ትልልቅ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ይገኛሉ፡፡ እንደ ዱክዉ ኮርፖሬሽን ያሉ የዴጉ ከተማ ኩባንያዎች ከአነስተኛ ደረጃ ዛሬ ላይ ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ሽያጭ የሚያከናውኑ ተቋማት ለመሆን በቅተዋል፡፡
ትክክለኛ ፖሊሲ የሚከተል አገር፣ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ተፈላጊውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ እንደሚችል ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን በየጊዜው በሚለዋወጠው ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ዘላቂ ማድረግ መቻል ፈታኙ እንደሆነም ይስማሙበታል፡፡ በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው አቅጣጫ በቴክኖሎጂና በምርት ሒደት ዘላቂ የቴክኖሎጂ ግስጋሴን በማስጠበቅ ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ ትልቅ ፈተና ሆኖ ተጋርጧል፡፡
ለዚህ ማሳያው የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት አሥር የጥናትና የምርምር ተቋማት በኮሪያ ይገኛሉ፡፡ ሚን ኪዩ ሶንግ ከእነዚህ ውስጥ በዴጉ ከተማ መገኛውን ያደረገውን አንደኛውን ይመራሉ፡፡ እንደ ሶንግ ማብራሪያ ከአሥሩ አምስቱ ተቋማት በዴጉ ከተማና በዙሪያዋ የሚገኙ ናቸው፡፡ እሳቸው የሚመሩት ተቋም ትኩረቱ በጨርቅ አልባሳት ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡
በእንዲህ ያሉ የምርምር ተቋማት የሚታገዘው የኮሪያ ኢንዱስትሪ ጎዳና አንድ ታዳጊ አገር ማለፍ የሚጠበቅባትን ፈተናዎች ሁሉ ተጋፍጧል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ ጀምሮ ከፍተኛ ለውጥ በማሳየት ላይ ለሚገኘው አምራች ኢንዱስትሪ ደጋፊ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች ውለታ ውለውለታል፡፡ ይኸውም በከተሞች አካባቢ ከሚኖሩ አባወራዎች የሚገኘው ገቢ ወደ ገጠርም ሊዳርስ መቻሉ ትልቁን ሥራ ሠርቷል፡፡ ቀልጣፋ ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመጣና የየተሻለ የገቢ ዕድገት እንዲመሠረትም አስችሏል፡፡
ይሁንና በከተማና በገጠር አከባቢዎች ያለው የኢንዱስትሪ ዕድገት፣ የገቢ መጠን ልዩነት መስፋት የፖለቲካ ችግር መቀስቀስ አመጣ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1970 መንግሥት ሲማውል የተባለውንና በማኅበረሰብ ላይ የተመሠረተ ንቅናቄን በአንድ ጊዜ በሁሉም የኮሪያ ጫፍ ማዳረስ ጀመረ፡፡ የሲማውል አንዶንግ ማዕከል ፕሬዚዳንት ሶ ጂን ክዋንግ እንደሚሉት፣ እንደ አፍሪካና ላቲን አሜሪካ አገሮች ሁሉ ኮሪያም በርካታ ያልተሳኩ፣ የታችኛውን ኅብረተሰብ ክፍል ያማከሉ ንቅናቄዎችን ለማድረግ ግድ ሆኖባት ነበር፡፡ ሁሉም ግን በአስከፊ ሁኔታ ሳይሳኩ ቀርተዋል ብለዋል፡፡
መንግሥት በወቅቱ በሁሉም ወገን ለገጠሩ ነዋሪ የልማት ፕሮግራሞችን የሚዘረጋበት አቅም አልነበረውን ያሉት ክዋንግ፣ ይህ በመሆኑም አዲስ አሠራር መፍጠርና መንደፍ ግድ ብሎት ስለነበር ማኅበረቦችን በማንቃት ራስ አገዝና ራስ አስቻይ ሥራዎች እንዲጎለብቱ የሕዝቡን መንፈስ በማነቃቃት ዘላቂና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ትንሳዔን የሚያመጣ አካሔድ ማራመድ ጀመሩ፡፡ በመሆኑም መንግሥት ቁጥብ የግንባታ ግብዓቶች ማለትም እንደ ሲሚንቶ፣ አርማታ ብረት ያሉትን በገጠር መንደሮች ለሚኖሩ ኮሪያውያን አዳረሰ፡፡ ምንም እንኳ የተሰራጩት ቁሳቁሶች በቂም ባይሆኑ፣ ነዋሪዎቹ በጋራ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ስምምነት በማድረግ ተከፋፍለው መሥራት ይጀምራሉ፡፡ መንግሥት የሚያቀርባቸው ቁሳቁሶች የነዋሪዎቹን ፍላጎት 30 ከመቶ እንኳ የሚሸፍኑ እንዳልነበሩ ይነገራል፡፡ ይህ መሆኑ ግን ነዋሪዎች በአንድ ተሰባስበው ምን መሥራት እንደሚገባቸው እንዲነጋገሩ አስገደዳቸው፡፡ ይህም ችግሮቻቸው ምን እንደሆኑ መለየትና ለመፍትሔውም አብሮ መሥራትን እንዳስከተለ ክዋንግ አብራርተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ የሴማውል ሕዝባዊ ንቅናቄ የመጀመሪያውን የስኬት ምዕራፍ ጅማሮ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
መንግሥት በምንም ዓይነት ጣልቃ ሳይገባ ነዋሪዎች በራሳቸው መንገድ ተደራጅተውና ተነጋግረው ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት አካሔድ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህ አሠራርና አተገባበሩ ከዓመት በኋላ በመንግሥትና በሰፈር አለቆች እንዲሁም በሰፈር ነዋሪዎች ተገምግሞ ጥሩ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ተጨማሪ ቁሳቁሶች እንዲቀርቡላቸው ይደረግ ነበር፡፡ ጥሩ ለሠሩት ሽልማት የሆነው ይህ አካሔድ ዝቅተኛ አፈጻጸም ላሳዩት ደግሞ ታክስ የሚጥልም ነበር፡፡
በዚህ ሒደት ነበር ተዓምራቶች መከሰት የጀመሩት፡፡ ሶ ጂን ክዋንግ እንደሚሉትም ተቆርጠው የቀሩ መንደሮች የራሳቸውን ነዋይ በማፍሰስ ለሚቀጥለው ዓመት ተጨማሪ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችላቸውን ነገር ሁሉ መሥራት እንዲጀምሩ አስገደዳቸው፡፡ ይህ እየተበራከተ ሲመጣም ድህነት የኮሪያን ጭርንቁስ መንደሮች ለመልቀቅ እየተገደደ መጣ በማለት ኮሪያውያኑ ትርክቱን ያወርዱታል፡፡ ይህ መሆን በጀመረ ጥቂት ዓመታት ውስጥም የኮሪያ ድሃ የገጠር ከተሞች የነበረባቸውን አለመመጣጠን እየቀለበሱ ነጎዱ፡፡
የተዓምራቱ መጪው ጊዜ
መጪው ጊዜ ለኮሪያውያን በጠንካራ መሠረት ላይ የተጣለ መሆኑ ጠያቂ አያሻውም፡፡ ጥናትና ምርምሩ፣ ጨርቃ ጨርቅ ዘርፉ ከቀላል አምራች ኢንዱስትሪ ተነስቶ ዛሬ ላይ ግዙፍነትን መላበሱ ሁሉ ለነገዋ ኮሪያ ጠንካራ መሠረቶች ሆነው የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ኮሪያ በኢንዱስትሪ በሰፊው ስፌት በማምረቱና በመመራመሩ ረገድ የሚቀራት ነገር አለ፡፡ ሌሎች በኮሪያ ተርታ ያሉት አገሮች ስፌትን ይበልጥ ተራቀውበት ከአልበሳት ይልቅ እያመረቱት ይገኛሉ፡፡ ኮሪያም የእንዲህ ያሉትን አገሮች ዱካ የሚከተሉ ኩባንያዎችን አፍርታለች፡፡