የሩሲያ መንግሥት በደርግ ዘመን ለኢትዮጵያ ካበደረው አምስት ቢሊዮን ዶላር ብድር ውስጥ እስካሁን ሳይከፈል ወይም ሳይሰረዝ የቀረውን 162 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ለልማት እንዲውል ሲል መወሰኑን የአገሪቱ የሚዲያ ተቋማት አመለከቱ፡፡
የአገሪቱ ሚዲያዎች በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግሩም አባይን በመጥቀስ እንደዘገቡት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ከሩሲያ መንግሥት አቻዎቻቸው ጋር በመሆን በሚያዝያ ወር 2008 ዓ.ም. ቀሪ የኢትዮጵያ ዕዳ በሚሰረዝበት ጉዳይ ላይ ተወያያተዋል፡፡ በዚህ ውይይትም የሩሲያ መንግሥት ‹‹ብድር ለልማት›› በሚል ማዕቀፍ ውስጥ የኢትዮጵያን ዕዳ ለማስተናገድ መፍቀዱን ዘግበዋል፡፡
ይህንኑ ዘገባ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ለሪፖርተር ያረጋገጡ ሲሆን፣ በሚኒስቴሩ በኩልም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ለሩሲያ መንግሥት ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት በዚህ ዕድል ለመጠቀም ከለያቸው ፕሮጀክቶች መካከል የኢንጂነሪንግ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች እንደሚገኙበት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ መንግሥት ኢትዮጵያ ያለባትን ዕዳ እንድትከፍል የቀረጸው ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ያለባትን 162 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ ለሩሲያ መንግሥት በቀጥታ ከመክፈል በዕዳው መጠን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የሩሲያ ኩባንያዎችን እንድታሳትፍ የሚያደርግ ነው፡፡ በመሆኑም የሩሲያ መንግሥት ውሳኔ ዕዳ ስረዛ ሳይሆን በቀረው የኢትዮጵያ ዕዳ ሁለቱም መንግሥታት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
ከፍተኛ የብድር ዕዳ ያለባቸው ድሃ አገሮች ኢንሼቲቭ አማካኝነት በ1999 ዓ.ም. ስድስት ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ተሰርዞለት የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 4.8 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን የሰረዘው የሩሲያ መንግሥት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ከሩሲያ መንግሥት ያገኘው ብድር ለጦርነት የዋለ በመሆኑ የሩሲያ መንግሥት የኢትዮጵያን ዕዳ ሙሉ በሙሉ መሰረዝ አለበት በማለት የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ ለረዥም ዓታት የተከራከሩ ቢሆንም፣ የሩሲያ መንግሥት ግን ይህንን ውሳኔ በማሳለፍ ቋጭቶታል፡፡
የደርግ መንግሥት ተበድሮት የኢትዮጵያ ዕዳ ሆኖ የቀረው ዕዳ ላይ ስረዛ ካካሄዱ አገሮች መካከል ቡልጋሪያ፣ ሊቢያ፣ የቀድሞዋ ዩጐዝላቪያ፣ ጣሊያን፣ ህንድ እና ቼኮዝሎቬኪያ ይገኙበታል፡፡