የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግንቦት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ከፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በፈጣን ችርቻሮ መደብር ባለቤትና ሌሎች ላይ ያቀረበውን ይግባኝ ተመልክቶ የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔን አፀና፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ተከሳሾቹን ከተጠረጠሩበት ወንጀል ነፃ አድርጎ ነበር፡፡
የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2006 ዓ.ም. በፈጣን ችርቻሮ መደብር ባለቤት በአቶ ፍቃዱ ወርቁና በሌሎች ሁለት የአዲስ አበባ አስተዳደር ሠራተኞችና አቶ መላኩ ፈለቀ በተባሉ ግለሰብ ላይ የሙስና ወንጀል ክስ መሥርቶባቸዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክሱን የመሠረተው ሁለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች አቶ ሀብታሙ ዘላለምና አቶ አሀዱ ኤልያስ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም ለሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ፍቃዱ ወርቄ ጥቅም ለማስገኘት በቀድሞ ወረዳ 2 ቀበሌ 12 የቤት ቁጥር 263 የሚታወቀውን ፈጣን መደብር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ማዘጋጀት ሲገባቸው፣ ፈጣን የችርቻሮ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተሰኘ በአቶ ፍቃዱና በልጃቸው በተያዘ ሌላ ድርጅት ስም በማዘጋጀት በአቶ ፈቃዱ አምባዬ የተባሉ ግለሰብ ላይ ጉዳት አድርሰዋል የሚል ነው፡፡
አቶ ፍቃዱ ወርቄና የአሁኑ ተበዳይ አቶ ፍቃዱ አምባዬ ሞዝቮልድ የተባለ ድርጅት የጋራ ባለቤቶች እንደነበሩ፤ በ1989 ዓ.ም. ከመንግሥት ቤቶች ሽያጭ ፒያሳ የሚገኘውን ፈጣን መደብር በሞዝቮልድ ስም እንደገዙና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት አቶ ፍቃዱ አምባዬ ኤርትራዊ በመሆናቸው ለአቶ መላኩ ፈለቀ ለተባሉ ግለሰብ ውክልና ሰጥተው ከአገር መውጣታቸውን የክስ ሠነዱ ያመለክታል፡፡
ክሱ የግል ተበዳይ ከአገር ውጭ በነበሩበት ወቅትም በሞዝቮልድ ስም የተገዛውን ፈጣን መደብር የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በሞዝቮልድ ስም ማድረግ ሲገባቸው፣ አቶ ፍቃዱ ወርቄ ከሁለቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር የቦታና ውል ምዝገባና ማስፈጸሚያ ሠራተኞች ጋር በመሆን የይዞታ ማረጋገጫው ፈጣን የችርቻሮ መደብር በተባለ አቶ ፍቃዱ ወርቄና ልጃቸው ባቋቋሙት ድርጅት ስም እንዲወጣ አድርገዋል በማለትም ያስረዳል፡፡
አቶ መላኩ ፈለቀ የተባሉት ተከሳሽና የግል ተበዳይ በሞዝቮልድ ድርጅት ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እንዲያስተዳድሩላቸው የሕግ ውክልና የሰጧቸው ግለሰብ በበኩላቸው የተሰጣቸውን አደራ ወደ ጐን በመተው የግል ተበዳይን ድርሻ በ1997 ዓ.ም. ለአቶ ፍቃዱ ወርቄና ለልጃቸው በነፃ አስተላልፏል የሚል ክስ ነው ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸው፡፡
የዓቃቤ ሕግን ማስረጃና የተከሳሽ ወገንን የመከላከያ ክርክር ያዳመጠው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና አቶ ፍቃዱ ወርቄ ለራሳቸው ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት እንዲሁም በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በሞዝቮልድ ስም ማዘጋጀት የነበረባቸውን የይዞታ ማረጋገጫ በፈጣን ችርቻሮ መደብር አዘጋጅተዋል ወይስ አላዘጋጁም፣ ይህንን የተዘጋጀ ካርታ ሆን ብለው ያዘጋጁት ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል ወይ የሚለውን በጭብጥነት ይዟል፡፡
ይሁን እንጂ ሁለቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች አቶ ፍቃዱ ወርቄ በጠየቁት መሠረት ካርታ ማዘጋጀታቸውን እንጂ ሕገወጥ የሆነ ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት እንዲሁም በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ አስበው ያደረጉት መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ያስረዳው ነገር የለም ብሏል፡፡ በመሆኑም ሦስተኛ ተከሳሽ አቶ ፍቃዱ ወርቄ በሕግ ተጠያቂ መሆን የሚችሉበት አግባብ የለም ብሏል፡፡ አራተኛ ተከሳሽ የነበሩት አቶ መላኩ ፈለቀም የግል ተበዳዩ ዕዳ ከሀብታቸው በላይ በመናሩ በሞዝቮልድ ድርጅት ውስጥ የግል ተበዳይ ያላቸውን ድርሻ በማስተላለፍ ዕዳቸውን ከፈሉ እንጂ የፈጸሙት እምነት ማጉደል የለም ብሏል፡፡
ይህ ቢሆንም ሁለቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች የይዞታ ማረጋገጫው በፈጣን ችርቻሮ ስም እንዲሆን ሲጠየቅ ውድቅ ማድረግ ሲገባቸው፣ አለማድረጋቸው በግልጽ የሥራ ግዴታን በአግባቡ አለመወጣት በመሆኑ ጥፋቱን በመፈጸሙበት ወቅት ባለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 412(2) መሠረት እንዲከላከሉ ወስኗል፡፡
ይኸው ፍርድ ቤት በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ሁለቱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሠራተኞች በሌሉበት እንዲታይ ያደረገ ቢሆንም፣ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች እንዲከላከሉ የተባሉበት የሕግ አንቀጽ በወንጀለኛ መቀጫ ሕግ ቁጥር 225 (2) እና 216 (1) እና (2) ቀሪ በመደረጉ ክሱም በይርጋ ቀሪ ተደርጓል ሲል ወስኗል፡፡
የፀረ ሙስና ዓቃቤ ሕግ በአቶ ፍቃዱ ወርቁ ላይ የመሠረተው የሠነድ መጭበርበር ክስንም ከፍተኛው ፍርድ ቤት በዚሁ የጥቅምት ወር ውሳኔው ውድቅ አድርጐታል፡፡
ነገር ግን ዓቃቤ ሕግ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔን በመቃወም ይግባኙን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹ይግባኝ የተባለበትን ብይን ለመለወጥ የሚያስችል በቂና አሳማኝ ምክንያት ባለማግኘታችን የሥር ፍርድ ቤት አቶ ፍቃዱ ወርቄን በነፃ ማሰናበቱ ተገቢ ሆኖ ስለተገኘ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 195(2 (ለ) (2) መሠረት አጽንተነዋል፤›› ሲሉ ሦስቱም ዳኞች በሙሉ ድምፅ ወስነዋል፡፡