ባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና የተለያዩ ግዙፍ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመገንባት የመሬት ጥያቄ አቅርበው ሲጠባበቁ የቆዩ ኩባንያዎች፣ በሊዝ አዋጅ መስተናገድ አትችሉም መባላቸውን ተቃወሙ፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት የመሬት ጥያቄ አቅርበው፣ መሬት እየተዘጋጀላችሁ ነው ሲባሉ ቆይተው፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት በልዩ ጨረታ ብቻ ነው መስተናገድ የምትችሉት የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ይህንን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ውሳኔ የተቃወሙ ኩባንያዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አቤቱታ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ጥያቄ ካቀረቡ ኩባንያዎች መካከል አርትሜስ ካፒታል በሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ሆቴልና ሆስፒታል ለመገንባት 40 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠው ከሦስት ዓመት በፊት ጥያቄ አቅርቧል፡፡
በሪል ስቴት ልማት የሚታወቀው ኢምፔሪየም በ523 ሚሊዮን ብር ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት 5,000 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል፡፡ የብረታ ብረት ፋብሪካ ባለቤት የሆነው ዋልያ ብረታ ብረት በ505.8 ሚሊዮን ብር ካፒታል፣ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት 5,000 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ታንሚያ ፎር ኦይል ኮንስትራክሽን ኢትዮጵያ በ4.41 ቢሊዮን ብር ካፒታል ሪል ስቴት ለመገንባት 1.5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል፡፡
አይታን ማኑፋክቸሪንግ በ878.5 ሚሊዮን ብር ሆቴልና ሞል ለመገንባት 40,300 ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ታሾ ሆንግሊያንግ በ28 ሚሊዮን ዶላር ሆቴልና ሞል ለመገንባት 12,000 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
ከእነዚህ ኩባንያዎች በተጨማሪ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመገንባት የሚያስችል መሬት በልዩ ሁኔታ እንዲሰጣቸው በርካታ ኩባንያዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በማቅረብም ላይ ይገኛሉ፡፡
አብዛኞቹ ኩባንያዎች የመሬት ዝግጅት እየተካሄደላቸው መሆኑ ሲገለጽላቸው የቆየ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ውሳኔ ተቃውሞ የህንዱ ኩባንያ አርትሜስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ግንቦት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. አቤቱታ አቅርቧል፡፡
ኩባንያው ባቀረበው አቤቱታ እንደገለጸው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገነባው ሆስፒታልና ሆቴል የከተማው አስተዳደር መሬት እንዲያቀርብ ከፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ለከንቲባ ድሪባ ኩማ የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፏል፡፡
በዚህ ደብዳቤ መሠረት፣ ከንቲባ ድሪባ ለፕሮጀክቶቹ የሚሆን መሬት ተዘጋጅቶ ለካቢኔ እንዲቀርብ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ትዕዛዝ ሰጥተው መሬቱ መዘጋጀቱ በደብዳቤ እንደተገለጸለት ኩባንያው አስታውሷል፡፡
ኩባንያው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሰሚት አካባቢ 17,200 ካሬ ሜትር ለሆስፒታል ግንባታ መዘጋጀቱ ተገልጾለት፣ በካቢኔ ይወሰናል ተብሎ በመጠበቅ ላይ እንዳለ ይህን የሚያጥፍ ውሳኔ መወሰኑ አግባብ አለመሆኑ በመግለጽ አቤቱታውን አሰምቷል፡፡
ከአርትሜስ በተጨማሪ፣ ኢምፔሪየም ሪል ስቴት ለምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታ በጻፈው ደብዳቤ፣ ከፍተኛ መጉላላት እየደረሰበት መሆኑን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በጻፈው ደብዳቤ፣ አገራዊ ፋይዳ ያለው 18 ፎቅ ያለው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት በመልሶ ማልማት ቦታዎች እንዲሰጠው መጠየቁን አስታውሷል፡፡
ከንቲባ ድሪባ ኩማ ጥያቄውን በመቀበል ፕሮጀክቱ በኮሚቴ ታይቶ ለውሳኔ እንዲቀርብ መምራታቸውን ገልጾ ነገር ግን አስተዳደሩ በአስቸኳይ ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ መስጠት ሲገባው፣ ይህ ባለመደረጉ ለከፍተኛ እንግልት መዳረጉ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ሕግ ባለበት አገር ሊፈጠር የማይገባው አግባብ ያልሆነ ድርጊት መሆኑን አመልክቷል፡፡
ነገር ግን የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አገራዊ ፋይዳ ላላቸው ፕሮጀክቶች መሬት በምደባ እንደሚሰጥ ይገልጻል፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግ እነዚህ ባለሀብቶች ጥያቄ አቅርበው የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደርም መሬት እንዲዘጋጅላቸው ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ ቆይቶ፣ በመጨረሻ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መስተናገድ ያለባቸው በልዩ ጨረታ እንዲሆን አዟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚስተናገዱት በልዩ ጨረታ ነው፡፡
‹‹ባለሀብቶቹን ጥያቄ አታቅርቡ ማለት አይቻልም፡፡ ስለሆነም ባለሀብቶች መሬት ይሰጠን የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን በአዋጁ መሠረት በምደባ ቦታ ሊሰጣቸው አይችልም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የሊዝ አዋጁ የማያሠሩ ነጥቦች በመኖራቸው ዳግም እንዲሻሻል መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡