ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የተለያዩ ቅርንጫፎቹ በመበደር ከ28.2 ሚሊዮን ብር በላይ በማጭበርበር (በመውሰድ) የተጠረጠሩ ሰባት ሠራተኞቹና አምስት ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ታሠሩ፡፡
ከተቋሙ ቅርንጫፎች መሳለሚያ፣ ገርጂ፣ ዓለም ገናና አራዳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ ሐሰተኛ የተሽከርካሪዎች የባለቤትነት መታወቂያዎች (ሊብሬ)፣ ሐሰተኛ ቼኮች፣ ሐሰተኛ ያገባና ያላገባ የምስክር ወረቀቶች፣ በተለያዩ ስሞች የተዘጋጁ ሐሰተኛ የንግድ ፈቃዶችንና ሌሎች ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ 28,270,000 ብር መውሰዳቸውን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ገልጿል፡፡
አብርሃም አበበ፣ ስንታየሁ ታፈሰ፣ ጥበቡ ፀጋዬ፣ ሃና ወልዴ፣ ትዕግስት ደጉ፣ ወይንሸት ሙሉጌታና ቢቂልቱ በየነ የተባሉት ተጠርጣሪዎች፣ የተቋሙ ሠራተኞች ሲሆኑ፣ ሳምሶን ፈረደና ቤተልሔም ደረሰ ደግሞ የተቋሙ ደንበኞች መሆናቸውን መርማሪው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ እስቅያስ አራጋው፣ ፍቅሩ የሺጥላና ተመስገን ወርዶፋ ደግሞ ሐሰተኛ ሰነዶቹን በማዘጋጀት የተጠረጠሩ መሆናቸውንም መርማሪው አክሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከግንቦት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት እየተያዙ ፍርድ ቤት በመቅረብ ላይ መሆናቸውን የገለጸው መርማሪው፣ ለተጨማሪ ምርመራ የ14 ቀናት ጊዜ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የተጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ በመፍቀድ፣ ተጠርጣሪዎቹ የጠየቁትን የዋስትና መብት ጥያቄ አልፎታል፡፡ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡