በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመገንባት ላይ ለሚኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ ያርፍበታል በተባለው ቦታ ቀድመው ይኖሩ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲነሱና ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወሩ ቢደረግም፣ የካሳ ክፍያ ባለመፈጸሙ ተመልሰው እየሰፈሩ መሆኑ ታወቀ፡፡
ይህ የተገለጸው ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ሲሆን፣ የምክር ቤት አባላት ለነዋሪዎች ለምን ካሳ እንዳልተከፈላቸው ጥያቄ አንስተዋል፡፡
አቶ ጋዋ ጃኔ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ባነሱት ጥያቄ፣ ‹‹በቤኒሻንጉል ክልል የህዳሴው ግድብ በሚገነባበት አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች እንዲነሱ ቢደረግም፣ የሰፈሩበት ቦታ በቂ መሠረተ ልማት ስላልተሟላላቸውና ይከፈላቸዋል ተብሎ ቀድሞ የተነገረው ካሳ ባለማግኘታቸው ወደ ቀድሞ ቦታቸው እየተመለሱ ነው፤›› በማለት የካሳ ክፍያው ለምን እንደዘገየ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄው መልስ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካይደኪ ገዛኸኝ የካሳ ክፍያው መዘግየቱን አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹በቅርቡ ይህ ጉዳይ በቦርዱ ተገምግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ካሳውን እንዲከፍል ስምምነት ተደርሷል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ካሳ ይከፈላቸዋል የተባሉ የአካባቢው ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑና የካሳው አጠቃላይ መጠን አልተገለጸም፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አምስት ዓመት ሲሆነው ተገንብቶ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ የመያዝ አቅም እንደሚኖረውና ውኃው በአጠቃላይ በ603 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው መሠረት ላይ እንደሚተኛም ይጠበቃል፡፡
ግድቡ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት ማምረት የሚያስችል ተደርጎ እየተገነባ ሲሆን፣ አጠቃላይ በጀቱ 80 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስም ይታወቃል፡፡