Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበምርጫ 97 በተፈጠረ ቀውስ መሬት የወረሩ ሕጋዊ ሆኑ

በምርጫ 97 በተፈጠረ ቀውስ መሬት የወረሩ ሕጋዊ ሆኑ

ቀን:

ግንቦት 1997 ዓ.ም. የተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በፈጠረው ቀውስ በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ በርካታ ይዞታዎች ሕጋዊ ሆኑ፡፡

በገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግና በተለይ በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) መካከል፣ ምርጫውን ተንተርሶ በተፈጠረው አለመረጋጋት በአዲስ አበባ በርካታ መሬቶች ያለ መንግሥት ዕውቅና መያዛቸው ይታወሳል፡፡

እነዚህ ይዞታዎች የተያዙት፣ በተለይ ከ1996 እስከ 1998 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ሲሆን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ቡልቡላና ወረገኑ፣ በየካ ክፍለ ከተማ የቀድሞ 20/21 ቀበሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ሃና ማርያምና ጀሞ ኮንዶሚኒየም ጀርባ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ አንፎ ሜዳን ጨምሮ በርካታ ባዶ ቦታዎች ተወረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸው እንዳስታወቁት፣ በተጠቀሰው ጊዜ መጠነ ሰፊ የመሬት ወረራ ተደርጓል፡፡

በወቅቱ በሕገወጥነት የሰፈረው የሕዝብ ብዛት ከፍተኛ መሆኑና የተገነባው ቤት ቁጥር በርካታ መሆኑ፣ በኅብረተሰቡና በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከግምት በማስገባት፣ አስተዳደሩ ሕጋዊ እንዲሆኑ መወሰኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹5,700 አባላት ያላቸው ማኅበራት የያዟቸው ቦታዎች ዕልባት ሳያገኙ ለዓመታት ተንከባለው እዚህ ደርሰዋል፡፡ እነዚህ ይዞታዎች ከከተማው ፕላን ጋር እያጣጣሙ በሊዝ ሥርዓት እንዲገቡ ተደርጓል፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ የካቢኔያቸውን ውሳኔ አሳውቀዋል፡፡

‹‹ይህ ችግሩን ለመፍታት የተወሰደው ውሳኔ ታሪካዊ ሊባል ይችላል፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ ገልጸው፣ ‹‹ነገር ግን በወቅቱ የማኅበራቱ ኃላፊ ሆነው በሕገወጥ ተግባራት የተሠማሩ ግለሰቦች በዚህ ውሳኔ አይስተናገዱም፤›› በማለት ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ፣ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ከኅዳር 2004 ዓ.ም. በፊት የተፈቀደላቸውን የግንባታ ጊዜ ባልጠበቁ 146 ማኅበራት ላይ የተጣለ ዕግድ አንስቷል፡፡ እነዚህ ማኅበራት 3,600 አባላት አሏቸው፡፡ አባላቱ ከአስተዳደሩ ጋር በገቡት ውል ግንባታቸውን ማካሄድ ባለመቻላቸውና የገነቡትም ከ30 በመቶ የማይበልጥ በመሆኑ ታግዶ ነበር፡፡

ነገር ግን አስተዳደሩ ሲንከባለል የቆየውን ይህን ችግር በድጋሚ በመመልከት የሁለት ዓመት የግንባታ ጊዜ ፈቅዶላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ በአዲስ አበባ ፈር ቀዳጅ የሆነው አያት የመኖሪያ ቤቶች ሥራ ድርጅት ከአስተዳደሩ ጋር በገባው ውል መሠረት ግንባታ ባለማካሄዱ ታግዶ የቆየው ጉዳይ ዕልባት አግኝቷል፡፡

በወቅቱ አያት መኖሪያ ቤት ገንብቶ ለማስረከብ ውል የገባ ቢሆንም፣ ሰርቪስ ቤቶች (ሰርቪስ ኳርተር) እየሠራ ለተጠቃሚዎች ሸጧል በሚል 600 የሚሆኑ ደንበኞች ካርታ እንዳይሰጣቸው ታግዶ ነበር፡፡

ይህ ሲንከባለል የቆየ ጉዳይን አስተዳደሩ በድጋሚ በማጤን ዕግዱ ተነስቶ፣ የይዞታ ስም እንዲዞርላቸውና የተናጠል ካርታም እንዲሰጣቸው ውሳኔ መተላለፉን ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ጉዳዮች ለዓመታት ሲንከባለሉና በባለጉዳዮች መጉላላት የፈጠሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይህንን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ለየት ያለ ዕርምጃ መውሰዱን ከንቲባ ድሪባ አመልክተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...