– ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት መንግሥት የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ተቃውሞን ለማፈን ከመጠቀም እንዲቆጠብ ጠየቁ
ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ እርካታ ተሰምቶኛል አሉ፡፡ አቶ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ተቃዋሚዎችን ለማፈን ኢትዮጵያ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉን ከመጠቀም እንድትቆጠብ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት ጠየቁ፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግንቦት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ዋነኛ አጀንዳ የአንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ እንደሆነ ገልጿል፡፡ መግለጫው ሃሞንድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ጋር እንደተገናኙ የጠቆመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው የሕግ አማካሪ እንደሚያገኙ ማረጋገጫ እንደሰጣቸውም አመልክቷል፡፡
ሃሞንድ በጉብኝታቸው አቶ አንዳርጋቸውን ለመጎብኘት ባይችሉም በጠየቁት ጥያቄ መሠረት የጉብኝቱ አካል የነበሩ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዳይሬክተር መጎብኘታቸውንም መግለጫው ያክላል፡፡ ሃሞንድ፣ ‹‹ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስንገናኝ የአንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ አንስቻለሁ፡፡ ቋሚ የሆነ የኮንሱላር ጉብኝት በመፈቀዱ መሻሻል የታየ ቢሆንም ወደ ፌዴራል ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ለማድረግ ተጨማሪ ዕርምጃዎች እንደሚቀሩ ገልጫለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሃሞንድ በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አያያዝ የተነሳ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መንግሥታት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት እንዳይበላሽ ሥጋት እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡ ይሁንና በዚህ መግለጫ ‹‹ማንም በፍትሕ ሥርዓታችን ጣልቃ እንዳይገባ እንደምንፈልገው ሁሉ እንግሊዝም በሌላ አገር የሕግ ሥርዓት ጣልቃ አትገባም፤›› ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ሃሞንድ ሥጋታቸውን ሲገልጹ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ እንግሊዝ በፍትሕ ሥርዓታችን ጣልቃ እገባለሁ እስካላለች ድረስ በሌላው ጉዳይ መግባባት እንችላለን ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በሃሞንድ የአቋም ለውጥ ዙሪያ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ጌታቸው፣ ‹‹የአቋም ለውጡ የመጣው እውነቱን ከመረዳት ነው፡፡ አክቲቪስት ተብዬዎችና ውሸት በመፈብረክ የሚያሠራጩ አካላትን አቤቱታ እንደ እውነት በመውሰድ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ነበር፡፡ የአሁኑ አስተያየት እውነቱን መረዳታቸውን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡
ተቀማጭነቱን እንግሊዝ ያደረገው ሪፕሪይቭ የተባለ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አንዳርጋቸው እንዲፈቱ አለመጠየቃቸው አግባብነት የሌለው ነው ብሏል፡፡ የቀድሞው የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ ከሰኔ ወር 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ያሉ ሲሆን፣ የተለያዩ አካላት እንዲፈቱ ግፊት ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡
በሌላ በኩል አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አርቲክል 19 እና ሲቪከስን ጨምሮ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ሲቪል ማኅበራት የኢትዮጵያ መንግሥት በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አማካይነት የሰብዓዊ መብት ተከላካዮችን፣ ገለልተኛ የሚዲያ ተቋማትን፣ ሰላማዊ የተቃውሞ ሠልፍ ተሳታፊዎችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን ማፈኑን እንዲያቆም ጠይቀዋል፡፡
ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ በተለይ መንግሥት ከኦሮሚያ የተቃውሞ ሠልፍ ጋር በተያያዘ የወሰደውን ዕርምጃ አውግዘዋል፡፡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ቱፋና አቶ ጉርሜሳ አያና በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ እንደተከሰሱም አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም የነገረ ኢትዮጵያ ኦንላይን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ጌታቸው ሽፈራው፣ የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ አቶ ፍቃዱ ሚርካናና የዲ ብርሃን ጦማሪ አቶ ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ አማካይነት ክስ እንደቀረበባቸው አስታውሰዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ሪፖርቱን እንዳላዩት ተናግረው፣ ‹‹ከተለመደው የኢትዮጵያን ስም የማጠልሸት ተግባራቸው ግን የተለየ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡