‹‹ጎል ማስቆጠር ተጫውቶ እንጂ አስፈራርቶ አይቻልም›› ኃይሌ ገብረሥላሴ
ለወትሮው ኦሊምፒክና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመጡ ቁጥር ምርጫን ተከትሎ በፌዴሬሽኑና አትሌቶች መካከል የሚስተዋሉ አለመግባባቶች በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ ግን ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ አነጋጋሪነቱ ጨምሯል፡፡ በቀድሞዎቹ የኦሊምፒክ ባለወርቆች ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ እንዲሁም ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያምና ሌሎችም አትሌቶች አማካይነት ግንቦት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም በተጠራው የአትሌቶች የምክክር መድረክ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑና በአትሌቶች መካከል ያለው ጉዳይ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› ሆኖ ታይቷል፡፡
በወቅታዊው የአትሌቲክስ ሁኔታና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉዳይ ላይ የተጠራው የምክክር መድረክ በበርካታ አጀንዳዎች፣ ማለትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሚከናወነው የሪዮ ኦሊምፒክ የተመረጡ አትሌቶች በሥነ ልቦና፣ በሥልጠና እንዲሁም ባለው መወዛገብና በተለያዩ ጫናዎች ነፃ እንዲሆኑ የጋራ ሐሳብ መያዝ፣ ፌዴሬሽኑ በሙያም ሆነ በአስተዳደራዊ ብቃት ላይ ስላልሆነ አትሌቱን በአግባቡ ማገልገል አልቻለም፡፡ ስለሆነም አሁን ያለው አትሌቱን የመምራት ሒደት ላይ ለባለቤቱ የሚያስረክብበት ሁኔታ መፍጠር ላይ መወያየት፣ የአትሌቶች ማኅበር ከአቋቋመው አካል ይልቅ፣ ለፌዴሬሽኑ ይወግናል የሚሉ መላ ምቶች ስላሉ በማኅበሩ ሕልውና ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፍ፣ ፌዴሬሽኑ በአቅምም ሆነ በገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ስላለ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የጋራ ውሳኔ ማሳለፍ፤ የአትሌቲክሱ ሩጫ ከድሮው ጋር ሲነፃፀር በውጤት ደረጃው እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ሁሉም አትሌት አምኖበትና የጋራ ሐሳብ ይዞ መሄድ የሚሉና ከምክክር መድረኩ በተጨማሪነት የተወሰዱት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
የመድረኩ አስተባባሪ ኃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ ሁሉም አትሌቶች በስፖርቱ ውስጥ ሙያተኛውን የሚያሳትፍ ምንም ዓይነት ቀዳዳ በመጥፋቱ ምክንያትና ይህንኑ ተከትሎ እያሽቆለቆለ የመጣውን አትሌቲክስ ለመታደግ ያለመ መድረክ እንደሆነም ታምኖበታል፡፡
‹‹ጊዜ ደጉ›› በማለት ንግግሩን ያከለው ኃይሌ፣ ‹‹አሁን አሁን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን እያስተዳደሩ የሚገኙ አመራሮች አትሌቶች አዳዲስ ክብረወሰኖችን ለማስመዝገብ ምን ማድርግ እንደሚጠበቅባቸው ሳይቀር የሚነግሩን ናቸው፡፡ ይኼ እናንተን አይመለከትም ስንላቸው ቤቱን ሊያፈራርሱት ነው በሚል ይወነጅለናል፡፡ እኔም ሆንኩ እዚህ የተሰባሰብነው አትሌቲክስ ቤታችን ነው፡፡ ጤነኛ የሆነ ሰው ደግሞ ቤቱን አያፈርስም፣ ይልቁንም ከሚያፈርሱ ኃይሎች ይከላከላል፤›› በማለት ነበር የተናገረው፡፡
‹‹ማናችንንም ማንም ሊያስፈራራን አይችልም፡፡ ጎል ማስቆጠር ተጫውቶ እንጂ አስፈራርቶ አይቻልም፤›› በማለት ያከለው ኃይሌ፣ ከምንም ተነስቶ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከሻምበል አበበ ቢቂላ ጀምሮ በየደረጃው ባለፉና በደከሙ አትሌቶች ጥረት መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት አስገንዝቧል፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ሀብት አስመልከቶ አትሌቱ፣ ‹‹በእያንዳንዱ አትሌት ደምና አጥንት የመጣና የተገኘ መሆኑ ግምት ውስጥ መግባት ብቻ ሳይሆን፤ እኔን ጨምሮ አትሌቶች የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ሀብት ኦዲት የማስደረግና የማወቅ መብት አለን፡፡ ይኼው ሊታወቅ ይገባል፤›› ብሏል፡፡ ይኼንኑ የኃይሌን አስተያየት በመደገፉ ሌላው መድረኩን ሲመራ የነበረው ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም በቡኩሉ፣ በእያንዳንዱ አትሌት ላይ እያደረሰ ያለው የመብት ጥሰት በማንም ሳይሆን፣ ‹‹ራሳችን በአትሌቶቹ መብታችንና ግዴታችንን ባለማወቃችን የመጣ ነው፡፡ አሁን በዚህ መድረክ ከተሰባሰብነው ውስጥ ለብሔራዊ ቡድን የተረመጥን ብንኖር ኖሮ አንዳችንም አንገኝም ነበር፡፡ ስለዚህ መብታችንን ማወቅ የሚኖርብን በመመረጥና ባለመመረጥ ሊሆን አይገባም፤›› በማለት በአትሌቶቹ ላይም የሚስተዋለውን ድክመት ተናግሯል፡፡
‹‹እንደዚህ ዓይነት ችግሮችና አለመግባባቶች ድሮም ነበሩ፡፡ የሚገርመው እንዲህ እንዳሁኑ የምንነጋገርበት ቦታ እንኳን እያጣን ጫካ ውስጥ የምንሰባሰብበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን መድረኩን ሳናጣው በራሳችን ቸልተኝነት መብታችንን እየተነጠቅን ነው፡፡ አሁንም አልመሸም ተነጋግረን የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይኖርብናል፡፡ ይህ ካልሆነ ቀደምቶቹ ቀድመን ተጥለናል ቀጥሎ ደግሞ የናንተ ነው፤›› ያሉት ደግሞ የቀድሞው አሠልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ናቸው፡፡
የአትሌቶች ማኅበር ጸሐፊ የማነ ፀጋዬ በበኩሉ ‹‹ውክልናዬ ለአትሌቶች እስከሆነ ድረስ የአትሌቶች መብት ሲጣስ መመልከት ስለሌለብኝ በዚህ መድረክ ለመገኘት ችያለሁ፤›› የምናወራው ስለስፖርት እንጂ ፖለቲካ አይደለም፡፡ ስለሆነም ለመብታችን መታገል የእኛ የአትሌቶቹ ድርሻ እንጂ የሌሎች ሊሆን እንደማይገባም አስረግጦ ተናግሯል፡፡
መጽሐፉ ማንበብ አልያም ሙዚቃ መስማት የሰዎች ፍላጎት (ሆቢ) ሊሆን ይችላል፡፡ አትሌቲክስ ግን የሙያ ቦታ እንጂ እንደምንሰማው ሰዎች ፍላጎት (ሆቢ) ስላላቸው ብቻ ሊመሩት የሚገባ አይደለም፤›› በማለት ያከለው ሌላው የቀድሞ አትሌት ገዛኸኝ አበራ ነው፡፡
ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ አትሌቶች በወቅታዊው የአትሌቲክሱና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ጉዳይ ላይ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተበጀለት አገሪቱ ከፊት ለፊቷ በሚጠብቃት የኦሊምፒክ ተሳትፎ ሳይቀር አደገኛ እንደሚሆን ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም በፌዴሬሽኑና በአትሌቶች መካከል ያለውን ጉዳይ በመከታተል ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር የሚነጋገር ኮሚቴ ተሰይሟል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ኃይሌ ገብረሥላሴ ሲሆን፣ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ የማነ ፀጋዬ፣ ፋንቱ ሜጌሶ፣ አሰፋ መዝገቡና ገዛኸኝ አበራ፣ የቀድሞ አሠልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ በአባልነት ተመርጠዋል፡፡